Sunday, 01 April 2018 00:00

“ከሁነኛ ሰው ነው የሰማሁት…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

“እናማ… ‘ችግር’ የዚች አገር መለያ ከሆነ የሰነበተና የከረመ ቢሆንም የዘንድሮው ግን
ከምንጠብቀው በላይም እየሆነብን ነው፡፡ የምር ሳቃችን ሙልጭ ተደርጎ ሊሄድ ጫፍ ላይ
የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ፈገግታ ከታየብንም ወይ የለበጣ፣ ወይ የምሬት እየሆነ ነው፡፡--”
        ኤፍሬም እንዳለ


   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ስለሆነ ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከተው በላይ እኛ አዋቂ የሆንንበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ለምሳሌ…ስለሆነ ሰው እያወራን ይሆናል፡፡ እናላችሁ… “ኑሮ የከበደው ነው የሚመስለው፡፡ አንድ ቀን ፊቱ ትንሽ እንኳን ፈካ ብሎ አይቼው አላውቅም፣” ምናምን ይባላል፡፡ ከመሀል ግን ከሰውየው በላይ ስለ አሱ የሚያውቅ ሰው ይኖራል፡፡
“ኑሮ ከበደው! ደግሞ አጅሬው ነው ኑሮ የሚከብደው? ፊቱን የሚያጨማድደው ሲያስመስል ነው፡፡”
“አንተ ደግሞ የሌለ ነገር አታውራ፡፡ ቤት እንኳን የለውም፤ እስካሁን እኮ በቀበሌ ቤት ነው የሚኖረው፡፡”
“እኔ ስነግራችሁ… ሰውየው ቅልጥ ያለ ሀብታም ነው፡፡ እንደውም ባንክ እንኳን ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ቀብሯል ነው የሚባለው፡፡” ሰውየው እኮ እንኳን ያን ያህል ብር ሊኖረው፣ ሦስት ሚሊዮን የሚባል ቁጥር መኖሩን ያወቀው፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ ሦስት ሚሊዮን አልፏል ምናምን ሲባል የሰማ ጊዜ ነው፡፡
“እንደውም እኮ መሥሪያ ቤቱ ስልጣን ሊሰጠው ነው ይባላል፡፡ አጅሬው እኮ በዋሻ ውስጥ ነው ሳይታይ የሚሄደው፡፡” (እንኳን ስልጣን ሊያገኝ---)
አናላችሁ..ይሄ በእለት ኑሯችን ላይ ያለው እኔ የምናገረውን ስሙ አይነት ነገር በቦተሊካውም፣ በምኑም በምናምኑም እየገባ፣ ግራ የተጋባንበት ዘመን ላይ ነን። አሀ…ማንን እንመን? ማንን እንጠራጠር? ማንን “ይቺ እንኳን ሁለተኛዋን ድራፍት ጨልጠህ፣ ሦስተኛውን ስታጋምስ የፈጠርካት ፊክሺን ነች፣” እንበል!
ሁላችንም የምናወራውን ነገር ከታማኝ ምንጭ እንዳገኘነው ነው የምናስመስለው፡፡ ወሬያችን ያለ ምንም ጥያቄ እንዲታመን እንፈልጋለን፡፡ አሀ…ማንስ ቢሆን ‘ከታማኝ ምንጭ’ ያገኘነውን መረጃ የመጠራጠር ምን መብት አለው!
“ስማ ሰዎቹ እኮ ጥሩ አይደሉም አሉ፡፡”
“ምን ሆኑ?”
“ምን ያልሆኑት ነገር አለ፣ ብቻ ነገርዬው አላማረኝም።” ከዛማ… አለ አይደል… በአንቀጽና በምእራፍ የተከፋፈለ የሦስት ዓመት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የሚወጣው ታሪክ ይነገራችኋል፡፡
“ግን ይሄን ሁሉ አንተ ከየት ሰማኸው?”
“ሁነኛ ከሆነ ሰው ነው የሰማሁት፡፡”
በነገራችን ላይ…‘ሁነኛ ሰው’ ማለት ‘የውስጥ አዋቂ’ ማለት ነው፡፡
እና አሁን አንዱ ችግራችን፤በሚፈሰው መረጃ መሃል እህሉንና ገለባውን መለየቱ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡ አንዳንዱ እውነት ሊሆን የሚችል አለ፣ ለእውነት የተጠጋ አለ፣ ከእውነት በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮች የራቀ አለ፤ ደግሞም ሙሉ ለሙሉ የፈጠራ ችሎታ የፈሰሰበት አለ፡፡
ታዲያላችሁ…ችግራችን አንዱን ከአንዱ መለየት ነው። ዘንድሮ ሁሉንም ወሬዎቻችንን የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ስለ ችግር፣ ስለ ተስፋ ማጣት፣ ስለ ግራ መጋባት መሆናቸው ነው፡፡ ያለንበት ሁኔታ አነኚህ ሁሉ ነገሮች በእጅጉ የሰፈሩበት ነውና፡፡
እናማ… ‘ችግር’ የዚች አገር መለያ ከሆነ የሰነበተና የከረመ ቢሆንም የዘንድሮው ግን ከምንጠብቀው በላይም እየሆነብን ነው፡፡ የምር ሳቃችን ሙልጭ ተደርጎ ሊሄድ ጫፍ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ፈገግታ ከታየብንም ወይ የለበጣ፣ ወይ የምሬት እየሆነ ነው፡፡ የቤት ወጪውን ተሸክማችሁ ቤት ስትገቡ ደግሞ ሌላው ዙር ይገጥማችኋል፤ ምኑን ከምኑ እንደምታብቃቃው ግራ የገባት ባለቤት…
“ስማ አንድ ፈረሱላ በርበሬ ስንት እንደሆነ ታውቃለህ? ኮረሪማ ኪሎው ስንት መቶ ብር እንደገባ ታውቃለህ?” ስትላችሁ፣ በቃ ሉሲፈር ምናምነኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሩን አሰልፎ የዘመተባችሁ ነው የሚመስላችሁ፡፡ እሷስ ምን ታድርግ! ሆድ እንደሁ… “ችግሩን በማየት ለሰባት ወር፣ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ምግብ ባገኝ ይበቃኛል፣” አይል ነገር!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ሌላ ጊዜ እኮ እነዚህ  ለምግብነት የምንፈልጋቸው ነገሮች ዋጋ ተወደደ ሲባል ለማብቃቃት እንሞክር ነበር፡፡ “በቃ ሽንኩርቱንም ቀነስ ማድረግ ነው፡፡ ቲማቲሙ አምስት ኪሎ መሆኑ ቀርቶ አራት ይበቃል፣ ዘይትም ቢሆን ሁለቷን ሊትር ለወር ማብቃቃት ነው፣” ምናምን እየተባለ ነገሮችን ለማስተካከል ይሞከር ነበር፡፡ አሁን ግን የሸመታ ነገር በጣም አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ በመቶ ብር ይሞላ የነበረ ከረጢት ቀርቶ ትንሿ ፌስታልም በመቶ ብር መሙላት እያቃታት ነው፡፡ እናማ… የሁሉም ነገር ዋጋ በየቀኑ በሚያስደነግጥ ፍጥነት እየጨመረ…መጪዎቹ ወራት ምን ይዘውልን እንደሚመጡ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
እናላችሁ…ሁሉም ነገር አናት በአናት ሲሆንባችሁ “እስቲ ከሁሉም ነገር ለሁለት ሦስት ሰዓት ራቅ ልበልና የደም ዝውውሬን ላስተካክል፣” ብላችሁ፣አለ አይደል… “አሥር ዓመት ብቀመጥ የሚያውቀኝ ሰው አይመጣብኝም፣” የምትሉበት አካባቢ ሄዳችሁ አንዱ ቤት ትሰየማላችሁ፡፡ ሁለተኛውን ድራፍት ሦስቴ እንደተጎነጫችሁ…ማን ቢመጣ ጥሩ ነው፣ ያኔ የተቀወጠው ምርጫ ጊዜ ቁጥር አንድ ሌኒን ምናምን ነገር ሆኖ ሰፈራችሁን ሲያምሰው የነበረው ሰው፡፡ እንደለፈለፈ በዛው ሲጠፋ “የሆነ ክልል ምናምን ተሹሞ ሄዶ ይሆናል፣» ተብሎ እንደተወራ ትዝ ይላችኋል፡፡
“አንተ ሰውዬ፣ አሁንም እዚሀ አገር አለህ እንዴ!…የሚገርም ነው፣” ይላል፡፡ ያኔ እኮ እንደ ሌኒን ያደረገው ሰሞን…
“አብረሀቸው የምትውላቸው ሰዎችን አልወደድኳቸውም፡፡”
“በጊዜህ ብትጠቀምበት ይሻልሀል፤ ከፈለግህ እኔ አገናኝሀለሁ…” ምናምን እያለ ሲነዘንዛችሁ ነበር።  እናማ…ከስንት ዘመን በኋለ ሰላምታውን “አሁንም እዚህ አገር አለህ?” ብሎ ሲጀምር ምን ሊሰማችሁ እንደሚችል አስቡት፡፡
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን…ለበርካታ ጊዜ ሳታዩት የቆያችሁት ሰው፤ “አሁንም እዚህ አገር አለህ!”  ብሎ ወሬ የሚጀመርው እንዴት ነው!… የምር…“እዚህ መኖር አልነበረብኝም እንዴ!” ምናምን ትላላችሁ፡፡ በዛ ቢበቃ ጥሩ ነው፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ዓረፍተ ነገር “የሚገርም ነው!” የሚል ነው፡፡ መቶ ሚሊዮን ምናምን ህዝብ በሚኖርበት አገር፤ የእናንተ መኖር ምኑ ነው የሚገርመው!
እናላችሁ…የደም ዝውውራችሁ መስተካከሉ ቀርቶ ይብስበታል፡፡ እድሜ ለአገር በቀሉ ሌኒን! ንዴታችሁን ዋጥ አድርጋችሁ ትሰሙታላችሁ፡፡
“አንተ ነህ እንጂ የጠፋኸው…” ምናምን ትላላችሁ…አንዱ ፊደል እንደ አስር ኪሎ እየከበዳችሁ፡፡
“አኔማ አለሁ…ምን እሆናለሁ ብለህ ነው…” ይልና የድምጹን ቃና ወደ ሀዘን ይለውጠዋል፡፡ ፊቱ የሰሞኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ይመስላል፡፡
“እዚህ አገር ነው እንዴ ያለኸው?” ትሉታላችሁ፣ በተራችሁ፡፡
“አይ ምን አገር አለና! ምን አገር አለና!” አሀ..ሰውየው ቀይ ካርድ ተሰጥቶታል ማለት ነው፡፡ በተለይ ከቤንች ወደ ዋና አሰላለፍ ልገባ ነው ሲሉ ጭራሽ ቀይ ካርድ የሚያገኙ ሌኒኖች ብሶታቸውን ሲያሰሙ…ለሆነ የሼክስፒር ትራጄዲ ቃለ ተውኔት የሚያጠኑ ነው የሚመስለው፡፡
“ትንሽ ሰዓት እንኳን ራሴን ሪቻርጅ ሳላደርግ ሰውየው ሊጀምረኝ ነው!” ትላላችሁ በሆዳችሁ፡፡
“ቤተሰብህ እንዴት ነው…ሁሉም ደህና ናቸው?” ትሉታላችሁ፡፡
“አይ ደህንነት..አዚህ አገር እንዴት ደህና መሆን ይቻላል…” ሌኒን ‘አምስተኛ ረድፈኛ’ ሆነ እንዴ! (ቂ…ቂ…ቂ…) እናላችሁ…እንደዛ ሲላችሁ የምድሩንም፣ የሰማዩንም እያነሳችሁ በሆዳችሁ ትረግሙታላችሁ፡፡ የሸሸሁትን ሆረር እዚህ ድረስ ያመጣብኛል!
“አንተስ እንዴት ነህ?” ይላችሁና አያይዞ ምን ቢል ጥሩ ነው… “ሳይህ የተመቸህ ትመስላለህ፡፡”
በነገራችን ላይ… ይቺ “የተመቸህ ትመስላለህ…” የሚሏት አንድ መቶ አንድ ትርጉም ሊኖራት ይችላል፡፡ “ሰው ሁሉ አሮጌ ሳንቃ መወልወያ ጨርቅ መስሎ አንተ እንዴት ነው እንዲህ ያማረብህ?” አይነት ነገር ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ልክ ሌላው አሮጌ የሳንቃ መወልወያ ለመምሰሉ ተጠያቂው እናንተ የሆናችሁ ያህል፡፡
እናማ…ዘንድሮ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው። ሰውየው በብሶት ወሬ ያጥለቀልቃችኋል …የራሳችሁ ብሶት የሌላችሁ ይመስል፡፡ እናላችሁ… ከሰላምታ ያልፍና ስለ ሰዎች፣ ስለ ድርጅቶች ስለ ምናምኖች ዜና ፋይል አይነት ነገር ይደረድርላችኋል፡፡ ስለ አንዳቸውም አንዲት ደግ ቃል አይወጣውም፡፡ ይህንንም መኮነን ነው፣ ያንንም መኮነን ነው፡፡ ሁሉንም የሚነግራችሁ ታዲያ “ከሁነኛ ሰው የሰማሁት…” እያለ ነው፡፡ ስለ አገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታም…አለ አይደል… ልክ በሆነ ፕሬዚዲየም፣ ፖሊት ቢሮ፣ አስቸኳይ ስብሰባ ምናምን ያስወሰነ ይመስል…የመጨረሻውን ውሳኔ ይነግራችኋል፡፡ “እመነኝ፤ይቺ አገር አልቆታል፣” ይላችኋል፡፡ በሆዳችሁ “ኸረ የሚጨርስ ነገር ይጨርስህ!” ትሉና ሸሽታችሁት የመጣችሁት የመኖሪያና የመሥሪያ አካባቢ ይናፍቃችኋል፡ ልክ ነዋ… የሆረር፣ የሆረር እዛ አይደለም ለእናንተ፣ ለሌላም የሚበቃ ይገኛላ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 783 times