Sunday, 01 April 2018 00:00

‹‹ቻው ቻው ሌኒን››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)


            “በእኔ ግምት፤ ዶ/ር አቢይ በ1977 ዓ.ም በሐገራችን በተከሰተው ድርቅ መነሻነት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከቢቢሲ ቴሌቭዥን ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ፤ ‹‹This is the toughest thing for a fighter to face……›› እንዳሉት፤ አሁን የተመረጡት አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርም ‹‹This is the toughest time for the Chairman of the EPRDF …..›› ማለት የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡”
         
   ‹‹Good Bye Lenin›› የሚል ፊልም አለ፡፡ ይህን ፊልም ወደ አማርኛ ለመመለስ ቢታሰብ፤ ርዕሱ (በለመድነው የጣሊያንኛ ቃል) ‹‹ቻው ቻው ሌኒን›› መባል ይኖርበታል፡፡ በዚህ ፊልም ያለችው ዋና ባለታሪክ የቀድሞ የምሥራቅ ጀርመን ዜጋ ነች፡፡ ይህች ሴት  የልብ በሽታ ገጥሟት ራሷን ስታ ትወድቃለች፡፡ ለወራት ቀልቧን እንደሳተች ቆየች፡፡ ከብዙ ወራት በኋላ ቀልቧ ሲመለስ፤ የበርሊን ግንብ ፈርሷል፡፡ የምሥራቅ ጀርመን ነገርም ታሪክ ሆኗል፡፡ ሻል ሲላት፤ ልጆችዋ ከሆስፒታል አውጥተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው (አፓርትመንታቸው) ሊወስዷት ፈለጉ፡፡ ነገር ግን ዶክተሩ፤ ‹‹አሁን ሌላ አስደንጋጭ ነገር ከገጠማት፤ እንደገና ለችግር ልትዳረግና ህመሟ ሊያገረሽ ይችላል›› በሚል ከሆስፒታል መውጣቷን ተቃወመ፡፡ ልጆችዋም ዶክተሩን ለማግባባት ጥረት አደረጉ፡፡ እናታቸውን ለችግር ሊያጋልጥ የሚችል ሁኔታ እንዳይከሰት ብርቱ ጥንቃቄ ለማድረግ ቃል በመግባት፣ ሐኪሙን አጥብቀው ለመኑት፡፡ በመጨረሻም ጥረታቸው ተሳክቶ እናታቸውን ወደ ቤት ለመውሰድ ቻሉ፡፡
 ልጆችዋ፤ ለምሥራቅ ጀርመን የተለየ ፍቅር የነበራት እናታቸው፤ ሐገሯ ፈርሳ ከምዕራብ ጀርመን ጋር መቀላቀሏን እንዳታውቅ ተጣጣሩ፡፡ እናታቸውን የሚያስደስት የውሸት ዓለም ለመፍጠር የቻሉትን ሁሉ አደረጉ፡፡ የድሮ ነገሮችን ከሚሸጥ አንድ ሱቅ ሄደው እርሷ የምትወዳቸውን ዕቃ በመግዛት ቤቱን የድሮ ቤት አስመሰሉት፡፡ በአጭሩ አዳዲሱን ዕቃ ከቤት አውጥተው የድሮውን ዕቃ መልሰው አስገቡ፡፡ አንድ ጓደኛቸው ከድሮው የምሥራቅ ጀርመን ሪፐብሊክ የሚተላለፍ ዜና አስመስሎ ዕለታዊ ዜና በማቅረብ ተባበራቸው፡፡ ግን አንድ ቀን በስህተት እውነተኛው ዜና የቴሌቭዥን መስኮቱን ሞላው፡፡ እናትየውም የበርሊን ግንብ ሲፈርስ ተመለከተች፡፡ ደነገጠች፡፡
ወዲያው ልጆቹ እናታቸውን ለማረጋጋት ጥረት አደረጉ፡፡ እናም፤ ‹‹በርግጥ የበርሊን ግንብ መፍረሱ ትክክል ነው፡፡ ግን ግንቡን ያፈረሱት፤ በምሥራቅ ጀርመን በጥገኝነት ለመኖር የፈለጉ የምዕራብ ጀርመን ዜጎች ናቸው›› አሏት፡፡ እናት በልጆችዋ ቃል ተረጋጋች። ‹‹በርግጥ ለተወሰኑ የምዕራብ ጀርመን ዜጎች ጥገኝት መስጠት፤ ከአገር ወዳድ የምሥራቅ ጀርመን ዜጎች የሚጠበቅ ተግባር ነው›› በማለት በኩራት ተናገረች። ተጽናናች፡፡ የዚህች ሴት ታሪክ በከተማው ተናፈሰ። ስለዚህ አዲሱን ሁኔታ ለመቀበል የተቸገሩ አንዳንድ ሽማግሌዎች ትንሽ የመንፈስ እርካታ ለማግኘት በማሰብ ወደዚች ሴት መኖሪያ ቤት ይመጡ ጀመር - በድራማው ለመደሰት፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በዚያ ቤት ውስጥ እየተሰባሰቡ የድሮውን ነገር በመተጋገዝ ለማጠናከር ሞከሩ፡፡ ሆኖም፤ ያ አስደሳች ትዝታ በአዕምሮ እንጂ በምድር አልነበረም፡፡ ‹‹ቻው ቻው ሌኒን›› እንዲህ ዓይነት ፊልም ነው፡፡
በዚህ ታሪክ ውስጥ የልጆቹ እና የዜና አቅራቢዎቹ ጥረት እውነታውን መሸፈጥ ነው፡፡ ሽማግሌዎቹ በምርጫ እውነቱን በልቦለድ ቀይረዋል፡፡ የእናትዬው ግን የችግር ነው፡፡ ልጆችዋ ከእውነታው ሊያለያይዋት (ወደው አይደለም) ቢሞክሩም፤ ዞሮ ዞሮ አንድ ቀን ከእውነቱ ጋር መጋፈጧ አልቀረም፡፡ ግን ልጆችዋ በሽንገላ ቃል እውነቱን ደበቋት፡፡ በርግጥ ለዚህች እናት እውነቱን መናገር ጭካኔ ነው፡፡ ይሁንና ከእውነት ተለይታ መኖሯ እውነት ነው፡፡ 
ይህን ታሪክ ያመጣሁት አሁን ያለንበትን ሐገራዊ ሁኔታ የሚገልጽ ነገር ያለው ስለመሰለኝ ነው፡፡ አሁን የምንገኝበትን ሁኔታ በደንብ አልተረዳነውም፡፡ የምንሰራቸው ነገሮች እና የምናቀርባቸው ትንታኔዎች እንደ ሴትዮዋ ልጆች እውነታውን ለመሸፈን የምናደርጋቸው ይመስለኛል፡፡ የተለወጠ ነገር መኖሩን መቀበል አቅቶናል። ‹‹የበርሊን ግንብ መፍረሱን›› መቀበል አልፈልግንም፡፡ ግን አንዳንድ ጊዜ ‹‹እውነተኛው ዜና የቴሌቭዥን መስኮቱን ድንገት ይሸፍነዋል፡፡›› ያኔ የማረጋጊያ ትንታኔ እንሰጣለን፡፡ ሁላችንም በታሪኩ ውስጥ ከተጠቀሱት ገፀ ባህርያት መካከል የአንዱን ባህርይ እየተጫወትን ነው፡፡ እኔ ‹‹እውነተኛውን ዜና›› ለማየት እፈልጋለሁ፡፡ እውነተኛው ዜና ‹‹አይ አንቺ ክምር፤ ያለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል›› የሚል ነው፡፡ ገበሬው ትልቅ ክምር ከምሯል፡፡ ግን አስቀድሞ ከተለያዩ ሰዎች እህል ተበድሮ ስለነበር፤ ‹‹አይ አንቺ ክምር፤ ያለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል›› አለ። ይህ ገበሬ እውነቱን ለመቀበል ደፍሯል፡፡ ያማረውን ክምር እየተመለከተ ራሱን አላታለለም፡፡ መፍትሔው እውነቱን ደፍሮ መመልከት ነው፡፡ ታዲያ አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እንደ ገበሬው እውነቱን ደፍረው ለማየት ይችሉ ይሆን? እኔ በዚህ ጽሑፍ፤ ከኔ የበለጠ የሚያውቁትን እውነት በድፍረት እንዲያዩት እገዛ አደርጋለሁ፡፡
 አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበር
ባለፈው ማክሰኞ ይፋ የተደረገው የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ምርጫ ከገመትኩት በላይ በብዙ ሰዎች ዘንድ ትልቅ ተስፋ አሳድሯል፡፡ ህዝቡ በዶክተር አቢይ አህመድ ላይ ያሳደረው ተስፋ መነሻው ለጊዜው ግልጽ ባይሆንልኝም፤ ምናልባት የሊቀ መንበር ምርጫው የከፋ አደጋ ሊያስከትል ይችላል የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ የተፈራው ሳይደርስ ነገሩ እልባት በማግኘቱ የተፈጠረ ስሜት ይሆን እያልኩ አስባለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር፤ ኢህአዴግንና ሐገሪቱን የገጠማቸው ፈታኝ ችግር በሊቀ መንበር ለውጥ ብቻ ሊቃለል የሚችል አልመሰለኝም። ለውጥ የሚመጣው ኢህአዴግ ደፍሮ መለወጥ ከቻለ ብቻ ነው፡፡
እንደተባለው በኢህአዴግ ምክር ቤት በተካሄደው ውይይት ፍፁም መግባባት የሰፈነበት ሁኔታ ተፈጥሮ ከሆነ፤ አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ዶ/ር አቢይ አህመድ የሚኖራቸው ሚና ለውጥ ያመጣ ይሆናል፡፡ ይህም ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራውም ያሉት ‹‹ወደፊት ይታያል›› ነው፡፡
በአጠቃላይ ግን ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር የሆኑት ኢህአዴግ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ በሚገኝበት ወቅት ነው፡፡ ሥራቸው ከባድ ነው። ለአቶ ኃይለ ማርያም ትብብር የነፈጉ ጓዶቻቸው ለእርሳቸው ድጋፍ ይሰጡ ይሆን? የሚለው ጉዳይም ያሳስበኛል፡፡ በእኔ ግምት፤ ዶ/ር አቢይ በ1977 ዓ.ም በሐገራችን በተከሰተው ድርቅ መነሻነት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከቢቢሲ ቴሌቭዥን ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ፤ ‹‹This is the toughest thing for a fighter to face……›› እንዳሉት፤ አሁን የተመረጡት አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርም ‹‹This is the toughest time for the Chairman of the EPRDF …..›› ማለት የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡ ነገሮችን ፈታኝ የሚያደርጋቸው ሐገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ብቻ አይደሉም፡፡ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችም ወደፊት ፈታኝ ባህርይ እየያዙ የሚሄዱ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ጥናቶች አሉ፡፡  አሁን በሐገራችን ጉዳይ እናትኩር፡፡
ከሰሞኑ የውይይት አጀንዳ ሆኖ የቀረበው ሰነድ የ‹‹ቻው ቻው ሌኒን›› የተባለውን ፊልም መስሎ ታየኝ። ሰነዱ የቀለም አብዮት ጉዳይን አንድ መወያያ ነጥብ አድርጎ ማቅረቡን ከመገናኛ ብዙሃን ዘገባ ተረድቻለሁ። ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም አንድ ያልተገጣጠመ ነገር አለ።  ገዢው ፓርቲ (ሰሞኑን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንደምንሰማው) የገጠመውን ችግር፤ ከውጭ ኃይሎች ጋር አያይዞ አያየውም፡፡ እንዲያ አድርጎ ሲያቀርበው አልታየም፡፡ ገዢው ፓርቲ ራሱን፤ በተለይም ከፍተኛ አመራሩን ተጠያቂ አደረገ እንጂ የውጭ ኃይሎች (የውጭ መንግስታት ወይም ተቃዋሚዎች) የችግሬ ምንጭ ናቸው አላለም፡፡ ነገር ግን የውስጥ ችግራችን ለውጭ ኃይሎች ተጋላጭ ያደርገናል ብሏል፡፡ ትክክል ነው፡፡ ‹‹እውነተኛው ዜና›› ይኸው ነው፡፡ ኢህአዴግ ከውጭ ኃይሎች ጋር የተያያዘ የችግር ትንታኔ ሲያቀርብ አልሰማሁም፡፡ ነገር ግን አሁን የመወያያ ርዕስ ሆኖ የቀረበው የቀለም አብዮት ጉዳይ ነው፡፡
ከቀለም አብዮት ትንታኔ ጋር ተያይዞ በትኩረት መታየት ያለበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው፤ የቀለም አብዮት ኤክስፖርተር የሆኑት የበለፀጉት ሐገራት አሁን ፋታ በማይሰጥ የራሳቸው የውስጥ ጉዳይ የተጠመዱ ናቸው፡፡ የምዕራቡ ዓለም መሪ ተደርጋ የምትታየው ወይም ራሷን የዓለም ፖሊስ አድርጋ ትቆጥር የነበረችው አሜሪካ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች እየወጣች ነው፡፡ መፈክሯም ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› የሚል ነው፡፡ አሜሪካን የሚመሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› የሚል መፈክር ያላቸው፤ ከጎረቤታቸው ሜክሲኮ ጋር ያላቸውን ድንበር በትልቅ አጥር ለማጠር ደፋ ቀና የሚሉ መሪ ናቸው፡፡ በዚህ ወቅት ‹‹የስርዓት ለውጥ›› ጋሪ የሚጎትት የቀለም አብዮት ፈረስ ለመጋለብ የሚፈቅዱ አልመሰለኝም፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ለአፍሪካ (በሎጅክ ለኢትዮጵያ) ደንታ እንደሌላቸው በተደጋጋሚ አሳይተውናል፡፡ በመሆኑም የቀለም አብዮት ትንታኔ፣ ይህን የተለወጠ ነገር ከግምት በማስገባት የሚቀርብ  መሆን ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ፤ ሥራችን በ‹‹ቻው ቻው ሌኒን›› ካየናቸው የውሸት ዜና አቅራቢዎች ጋር ተመሳሳይ ይሆናል፡፡
በእኔ አስተያየት በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ በየትኛውም ሐገር የቀለም አብዮት የማካሄድ ፍላጎት ያላት አይመስለኝም፡፡ በእኔ ‹‹የማህበራዊ ህይወት ሞራ ንባብ›› (ደግሞ ሞራ ገላጭ ሆንኩ) ዋናው ችግር ግዙፍ ሙስና ነው፡፡ የእኛ ችግር ለግዙፍ ሙስና ምቹ የሆኑ አሰራሮች፣ አስተሳሰቦችና ተግባራት ናቸው፡፡ የሐገራችን የሙስና ችግር፤ ጓደኛዬ ዘሪሁን ተሾመ ‹‹የነጠቃ መንግስት›› (State Capture) ሲል በጠራው ደረጃ የገዘፈ ችግር ሆኗል፡፡ ሆኖም እኔ ችግሩን እንደ ዘሪሁን ከቀለም አብዮት ጋር አያይዤ አላየውም፡፡ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ‹‹የነጠቃ መንግስት›› ችግር ከቀለም አብዮት ጋር ተያይዞ አላገኘሁትም፡፡ State Capture (የነጠቃ መንግስት) በዓለም ባንክና በዓለም የገንዘብ ድርጅት የተቀመረ ጽንሰ ሐሳባዊ ቃል ነው፡፡ እነሱ እንደሚሉት፤ ‹‹የነጠቃ መንግስት›› የአደገኛ ሙስና ችግር ነው፡፡ ‹‹የነጠቃ መንግስት›› ችግርን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሐገራችን ወቅታዊ ችግር ጋር አያይዘው በአደባባይ ያነሱት የአአዩ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶ/ር ካሳሁን(?) ነበሩ፡፡ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በ2009 (?) ዓ.ም በሸራተን አዲስ ባካሄደው የውይይት መድረክ፣ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር ካሣሁን፤ ‹‹በኢትዮጵያ የነጠቃ መንግስት ችግር አለ›› የሚል ድምዳሜ ባያነሱም፤ የሐገራችን ችግር ከነጠቃ መንግስት ችግር ጋር የሚያያዝ ከሆነ በጣም አደገኛ ችግር ውስጥ እንወድቃለን ብለው ነበር፡፡
እኔም በዚሁ ውይይት ተሳታፊ የነበሩትን የአቶ ፀደቀ ሀይሌን ቃል ተውሼ፤ ‹‹የስሙኒ መልካም አስተዳደር፤ የሽልንግ ልማት›› በሚል ርዕስ በዚሁ ጋዜጣ በጻፍኩት አንድ ጽሑፍ፤ በወቅቱ ‹‹ቅይድ መንግስት›› በሚል የተረጎምኩት የ‹‹State capture›› ችግር በጣም አሳሳቢ ሆኖ እንደታየኝ ገልጬ ነበር፡፡ የቅይድ ወይም የነጠቃ መንግስት ችግር ከግዙፍ ሙስና ጋር የሚያያዝ ችግር ነው፡፡ ሙስና የሚገንነው መንግስት በቢሮክራሲው ላይ ያለው ቁጥጥር ደካማ ሲሆን ነው። መንግስት የግል ንብረትና የኮንትራት መብቶችን መከላከል ሲያቅተው፤ እንዲሁም በተሟላ ሁኔታ የህግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ ተቋማትን መፍጠር ሲሳነው የሚከሰት ችግር ነው - ሙስና፡፡ መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚገባበት ቀዳዳ ሰፊ ሲሆን እና ባለስልጣናት ሰፊ የመወሰን ስልጣን ሲኖራቸው ሙስና ይበራከታል። ሁሉም መንግስታት የሙስና ችግርን የመከላከል ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም፤ ልማታዊ መንግስት መሆን የሚሻ (በተመረጡ እና የገበያ ጉድለት በሚታይባቸው አካባቢ እየለየ፣ በኢኮኖሚው ጣልቃ ለመግባት የሚሻ መንግስት) ሙስናን ለመዋጋት ከሌሎች መንግስታት በላይ መስራት ይኖርበታል፡፡
ሆኖም ሙስና በመንግስት በኩል ያለውን መሠረታዊ ድክመት የሚያመለክት ጉዳይ ሆኖ ሲቀርብ፤ ትኩረታችንን ከንግድ ተቋማት፣ በየመስኩ ካሉ ከኃያል ልሂቃን ቡድኖችና ግለሰቦች መራቅ የለበትም፡፡ ይልቅስ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት በደንብ መጤን ይኖርበታል፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ግንኙነት ስናጤን፤ ኃያል ልሂቃን ቡድኖች እና ግለሰቦች እንዲሁም የንግድ ተቋማት፤ ለባለስልጣናት ገንዘብ በመስጠት በመንግስት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ማየት እንችላለን፡፡ ከጉቦም አለፍ ብለው፤ የሐገር የመጫወቻ ህግጋት የሆኑ ጉዳዮችን (አዋጆችን፣ ደንቦችን፣ መመሪያዎችን) ባህርያቸውንና ይዘታቸውን በመወሰን ረገድ ያላቸውን ተጽዕኖ ለመመልከት እንችላለን፡፡ ይህም የቅይድ ወይም የነጠቃ መንግስት ችግርን ለመርመር ይረዳናል፡፡
በተለይ በሽግግር ኢኮኖሚዎች ውስጥ ኃያል ልሂቃን ቡድኖችና ግለሰቦች እንዲሁም የንግድ ተቋማት ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይላቸውን በመጠቀም፤ ለራሳቸው የሚጠቅም የህግ ማዕቀፍ በመፍጠርና የፖሊሲ ውሳኔ በማሳለፍ ተጽዕኖ ያደርጋሉ፡፡ አጠቃላይ ኢኮኖሚውንና የህብረተሰቡን ጥቅም በመጉዳት፣ ለራሳቸው ጠቀም ያለ ኪራይ ለማግኘት የሚያስችል ተጽእኖ ለማሳደር የሚችሉበት ዕድል ይኖራል፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ነገሮች መስመር ይለቃሉ ወይም ይዛባሉ፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ‹‹ቅይድ መንግስት›› በሚል የሚጠቅሱት ችግር ሰፊ ሐሳብ የሚያካትትና አጅግ አደገኛ የሆነ ችግር ነው፡፡ በርግጥ፤ በሽግግር ኢኮኖሚዎች ውስጥ ብቻ ሳይሆን በማናቸውም ዘመን እና በትየኛውም ሐገር የሚገኝ የመንግስት ስልጣንን ለመቆጣጠርና በራሳቸው ልጓም ይዘው ለመጋለብ የሚችሉትን መንግስት ለመፍጠር የሚሹ ይኖራሉ፡፡ መንግስትን የጠባብ ቡድናዊ ወይም ግላዊ ፍላጎታቸው መሣሪያ ሊያደርጉ የሚፈልጉ ወገኖች ሁሌም ይኖራሉ። በብዙ ካልተጠነቀቅን፤ እንዲህ ያሉ ኃይሎች የእነሱን መሻት ተከትሎ የሚንቀሳቀስ ቅይድ መንግስት በኢትዮጵያ ለመፍጠር መሞከራቸው የማይቀር ነው። እነዚህ ወገኖች ያላቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ወዘተ ኃይል በመጠቀም ተጽዕኖ ለማሳደር ይሞክራሉ፡፡ እነዚህ ኃያል ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ሰፊ ማህበራዊ ልማትን ሊያደናቅፍ የሚችል ፍላጎት ይዘው ሊንቀሳቀሱ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ የእነሱ ፍላጎት ይሳካ እንጂ የሚሊዮኖችን ዕድል የሚያሰናክል ወይም ሐገር የሚያፈርስ ነገር መያዛቸው ጨርሶ አያሳስባቸውም። ስለዚህ የፈለጉት እንዲፈጸምላቸው ከመጣጣር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሐገር የሚያጠፋ ተግባር ቢሆንም ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም አያመነቱም፡፡ እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ምንጊዜም - የትም ይኖራሉ፡፡
ታዲያ እነዚህን የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ሥልጣን ያላቸው ኃያል ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አደብ እንዲገዙ ማድረግ የሚቻለው፤ እንዲሁም የእነዚህን ቡድኖች ፍላጎት ተረድቶ እንቅስቃሴአቸውን ለመቆጣጠር የሚቻለው፤ ህይወት ያለው፣ ብቁ እና ንቁ የዴሞክራሲ ስርዓት በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለው አማራጭ ሁለት ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች እንዳሻቸው የማድረግ ዕድል ጨርሶ እንዳያገኙ በርን ጥርቅም አድርጎ የሚዘጋ የዴሞክራሲ ስርዓት  መገንባት ወይም ሐገር ሲፈራርስ ቁጭ ብሎ መመልከት ብቻ ነው፡፡
የቀድሞው ጠ/ሚ አቶ መለስ ዜናዊ፤ በዚሁ በሙስና ጉዳይ በተወካዮች ምክር ቤት ሲናገሩ፤ ‹‹ወይ ልማታዊነት ወይ ኪራይ ሰብሳቢነት ያሸንፋል›› ብለው የትግሉን አደገኛነት በግልጽ ነግረውናል፡፡ በዚሁ ጊዜ ‹‹መንግስት አንድ እጁን ታስሮ ነው የሚታገለው፤ በዚህ ትግል ነጻ ሆኖ ትግሉን ማካሄድ የሚችለው ተራው ህዝብ ነው›› ሲሉ መናገራቸውም የሚዘነጋ አይደለም። በዚህ ንግግራቸው ቁልፉ ቃል ‹‹መንግስት አንድ እጁን ታስሮ ነው የሚታገለው›› የሚለው ኃይለ ቃል ነው፡፡ በርግጥ ‹‹መንግስት አንድ እጁን ታስሯል፡፡›› አቶ መለስ ዜናዊ በ2003 (4) አካበቢ የወጣውን አንድ የሊዝ አዋጅ (ደንብ) ማሻሻያ አስመልክተው ሲናገሩ፤ ‹‹የዚህን አዋጅ ደንብ በፍጥነት አጣምመው አቀረቡት፡፡ ይህ አጋጣሚ መርካቶ ከኛ በላይ ብቃት እንዳለው ለመረዳት ያስቻለን ነው›› ማለታቸውም የሚታወስ ነው፡፡ አይ መርካቶ!
ዋናው ነገር አቶ መለስ ከምን ዓይነት ኃይል ጋር ትግል እያደረጉ መሆናቸውን በደንብ ተረድተውታል። በአንጻሩ አቶ ኃይለ ማርያም ችግሩን ቢረዱትም፤ በአቶ መለስ መጠን የችግሩን አደገኛነት የተረዱት አልመሰለኝም፡፡ ሆኖም በፖሊሲ ጥናት ተቋም በቀረበ አንድ የጥናት ሰነድ ላይ ውይይት ሲደረግ የተናገሩት ቃል የችግሩን አደገኛነት ሳይሆን መጠኑን በድንብ እንደተረዱት በግልጽ ያመለክታል፡፡ በዚሁ ውይይት፤ ‹‹እያንዳንዳችሁ ከዚህ ስትወጡ ኔትወርካችሁን መከላከል ውስጥ ትገባላችሁ፡፡ የሐገሬ ልጅ፣ አብሮ አደጌ፣ የፓርቲዬ አባል እያላችሁ ወንጀለኞችን መከላከል ውስጥ ትገባላችሁ፡፡ ……የግል እስር ቤት ተፈጥሯል፡፡ … ሚኒስትሮችን የሚያዝ ደላላ ተፈጥሯል›› ሲሉ ሰምተናል። ሁኔታው ተስፋ አስቆርጧቸው ‹‹….ከመካከላችን ኮርያ ደጋግሞ ያልሄደው ሰው አይገኝም፡፡ ታዲያ ለውጥ ማምጣት የቸገረን ለምንድነው?›› እያሉ መናገራቸውንም እናስታውሳለን፡፡
በዚህ ንግግራቸው አቶ ኃይለ ማርያም ሙስናን ለመታገል ፍፁም ቁርጠኛ መሆናቸውን መረዳት እንችላለን፡፡ ነገር ግን አሁን ሥልጣን የለቀቁት አቶ ኃይለ ማርያም፤ የፀረ-ሙስና ዘመቻ በይፋ መጀመራቸውን በገለፁ አንድ ሣምንት እንኳን ባልሞላ ጊዜ ሐገሪቱ በሁከት መታመስ ጀመረች፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የተነሳው የአቶ ኃይለ ማርያም መንግስት፤ በህዝብ አመጽ ያሰበውን ነገር መፈጸም ተስኖት ሐገሪቱ ‹‹ማርያም …ማርያም›› በሚያሰኝ ምጥ ለሦስት ዓመታት ስትንገላታ ቆየች፡፡ በእኔ እምነት አቶ ኃይለ ማርያም የፀረ ሙስና ዘመቻቸውን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከለላ ሊፈፀሙት ይገባ ነበር፡፡ ዘመቻው አደገኛ ዘመቻ ነበር፡፡ ህዝብ እና መንግስት ‹‹ተበደልኩ›› …. ‹‹አዎ ተበድለሃል›› እየተባባሉ ሲጋጩ ከረሙ፡፡ በመጨረሻም አቶ ኃይለ ማርያም ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡  
‹‹ቅይድ መንግስት ወይም ነጠቃ መንግስት›› በሚል የሚጠራው የግዙፍ የሙስና ችግሮች፤ ተራ አስተዳደራዊ ሙስናዎች አይደሉም፡፡ አስተዳደራዊ ሙስና በነጻ የህግ አውጪ አካል ተመርምረው፤ በትክክለኛው ሂደት አልፈው በወጡ ህጎችና ደንቦች ውስጥ የሚገኝን ቀዳዳ በመጠቀም ኪራይ ለመሰብሰብ የሚደረግ ሙከራ ነው። ‹‹ቅይድ መንግስት ወይም ነጠቃ መንግስት›› በሚል የሚገለጸው ሙስና ግን፤ የህጉን ቀዳዳ ለመጠቀም የመሞከር ተራ እንቅስቃሴ ሳይሆን፤ ራሱን የህጉን ይዘት ለራሱ እንዲጠቅም ሆኖ እንዲደነገግ ለማድረግ የሚሞክር የሙሰኝነት አንቅስቃሴ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ህግን ወይም አዋጅን በተጽዕኖና በገንዘብ የመግዛት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመንግስት የግዢ ሂደት የሚፈጸም አደገኛ ሙስና ነው፡፡
ሙስና በተለምዶ ‹‹የግል ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የመንግስት ስልጣንን ያለ አግባብ የመጠቀም እንቅስቃሴ›› በሚል ይተረጎማል፡፡ ግዙፍ ሙስና የሚባለው ግን መሠረታዊ የጨዋታ ህጉን ይዘት (የአዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን) ለመወሰን በማሰብ፤ ግለሰቦችና ቡድኖች በመንግስት ባለሥልጣናት ላይ የሚያደርሱት ተጽዕኖ ነው፡፡ ይህ ነው፤ ‹‹ቅይድ መንግስት ወይም ነጠቃ መንግስት›› ማለት፡፡ በመሆኑም፤ በግዙፍ ሙስና ሂደት የግል ተቋማትና የተለያዩ ልሂቃን፤ የፖሊሲ ውሳኔዎች የእነሱን የተለየ ጥቅም እንዲያስከብሩ ሆነው እንዲቀረጽ የሚያደርጉበት ሂደት ነው፡፡ በዚህም ህጋዊው አሰራር እንዲጣመምና የመንግስት አሰራር ግልጽ እንዳይሆን ያደርጋሉ፡፡ ቁልፍ የሆኑ የመንግስት ተቋማትን ‹‹መንጠቅ›› የሚችሉበት ዕድል ያገኛሉ፡፡ ተራ ሙስና ግለሰቦች ለአንድ የንግድ ሥራ  ከመንግስት ጋር በቀጥታ በተገናኙ ጊዜ የሚፈጠር እንጂ የጨዋታ ህግን የሚወስን እንቅስቃሴ አይደለም፡፡
የተለያዩ የነጠቃ መንግስት ሙስናዎች አሉ፡፡ የህግ አውጪውን የመንጠቅ (legislative capture) እርምጃ አለ፡፡ የፓርላማውን ወይም የፕሬዚዳንቱን ወይም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወይም ካቢኔውን ውሳኔ ለመግዛት የሚደረግ እንቅስቃሴ አለ፡፡ የብሔራዊ ባንክ ነጠቃ (capture of the Central Bank) አለ፡፡ ይህ የፋይናንስ ብልሹ አጠቃቀምን የሚመለከት ነጠቃ ነው፡፡ የህግ ነጠቃ (legal capture) አለ፡፡ የህግ ነጠቃ የሚባለው የፍርድ ቤት የዳኝነት ውሳኔን የመግዛት እንቅስቃሴ ነው፡፡ እንዲሁም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ  (non-transparent political party financing)  የሚታይ ነጠቃ አለ፡፡ ይህ የተለያየ ኃይል ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በምርጫ ዘመቻ ለሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያውሉትን ገንዘብ የሚመለከት የነጠቃ ዓይነት ነው። አሁን በሐገራችን የሚታየው ችግር ጓደኛዬ እንዳለው፤ ‹‹የነጠቃ መንግስት›› ችግር ነው፡፡
ታዲያ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ይህን ችግር ካልተጋፈጡ ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ይህን ችግር እጋፈጣለሁ ካሉ፣ ከገነገነ ኃይል ጋር ይላተማሉ። የትኛውን ይመርጣሉ? ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ ‹‹ወይ ኪራይ ሰብሳቢነት ወይ ልማታዊነት ያሸንፋል›› ብለው የሚነሱ ከሆነ፤ ህዝቡ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል፡፡ ህዝቡ እስከ ዛሬ ያደረገው ትግል ለገዢው ፓርቲ ግልጽ መልእክት አስተላልፏል፡፡ ሆኖም ትግሉ የማይደረመስ የሌቦች ዋሻ ሆኖ መቆየቱንም መረዳት ይኖርበታል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት፤ የመንግስት ሥራ ቀጥ ብሎ በመቆሙ ብቻ ሳይሆን ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፤ ዘረፋ ተጧጡፎ የሚካሄድበት ዕድል በመፈጠሩም ተጎድተናል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለአስር ዓመታት በፀረ ሙስና እና ሥነ ምግባር ኮሚሽን መሳቢያ፤ እንዲሁም ባለፉት ሁለት-ሦስት ዓመታት ደግሞ በጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽ/ቤት ሳጥን ተቆልፎ የተቀመጠው፣ የባለስልጣናትን የሐብት መጠን የሚያሳየው ሰነድ፣ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ በማዘዝ ትግሉን መጀመር አለባቸው፡፡ ‹‹ቻው ቻው ሌኒን›› ይበቃል፡፡
በተረፈ፤ በዚህ ትንታኔ ‹‹የሐገራችን ችግር የነጠቃ መንግስት ችግር ነው›› ስል፤ ጉዳዩን ፍንትው አድርገው ሊያሳዩ የሚችሉ እና ህዝቡ በደንብ የሚያውቃቸውን ማስረጃዎች መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ሆኖም አሁን ከዚህ በላይ ለመሄድ የጋዜጣው ገጽ አይፈቅድም፡፡ ለጊዜው በቅርቡ ፓርላማው ለሚሰይመው ለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን መልካም የስራ ዘመን በመመኘት ልሰናበት፡፡ 

Read 818 times