Sunday, 01 April 2018 00:00

ዶ/ር አብይ አህመድ - ከልጅነት እስከ ጠ/ሚኒስትርነት በጨረፍታ

Written by  በታምራት መርጊያ
Rate this item
(3 votes)

 የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ በአንዳንዶች የድርጅቱ (ኦሕዴድ)፥ አዲሱ የተሐድሶና የለውጥ አመራር ተብሎ የሚጠራውና በሌሎች ደግሞ “ቲም ለማ” (Team Lemma) ከሚባለው ቡድን ውስጥ ከጓዳቸው ከአቶ ለማ መገርሳ ጋር የድርጅቱ ቁልፍና አብይ ሰው ተደርገው፣ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱትን ዶክተር አብይ አሕመድ አሊን  ሊቀ መንበሩ አድርጎ መረጠ። በርግጥ በርካቶች የጠበቁትና የገመቱት፥ ኦህዴድ የቀድሞው ሊቀ መንበር፥ የአሁኑን ምክትል ሊቀ መንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ድርጅቱን በመምራት ሐላፊነታቸው ቀጥለው፣ በቀጣይ ለሚደረገው የጠቅላይ ሚኒስትርነት ምርጫ እጩ አድርጎ ያቀርባቸዋል የሚል ነበር።
የሆነው ሆኖ አቶ ለማ መገርሳ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ባለመሆናቸው ምክንያት፥ ከእርሳቸው ይልቅ፥ ዶክተሩ  ለሐገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ምርጫ እጩ ሆነው ለመቅረብ የሚያስችላቸው ተጨባጭ የሆነ ህጋዊና ፖለቲካዊ መሰረቶች እንዳላቸው ታሳቢ በማድረግ፣ ድርጅቱ የአመራር ሽግሽግ በማካሔድ ከወዲሁ ሁኔታዎችን አመቻቸላቸው። የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት፣ የሕዝብ አስተያየትና ፐብሊሲቲ ዘርፍ ሐላፊ አቶ ካሳሁን ጎፌ፥ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከዶክተር አብይ የኦህዴድ ሊቀመንበርነት ሹመት በኋላ፥ ለአሜሪካ ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል በሰጡት ቃለመጠይቅ እንደተናገሩት፦ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ይህን የአመራር ማስተካከያ ያደረገው አቶ ለማ መገርሳ ሐላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያት አለመሆኑን አስረግጠው በመግለጽ፥ ድርጅቱ በቀጣይ በተሻለ መልኩ ክልላዊና ሐገራዊ ሐላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ መሆኑን አስረዱ። ይሄን ተከትሎም፣ ዶክተር አብይ አህመድ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት መታጨታቸው፣ በብዙዎች ዘንድ እንዲታሰቡ በር ከፋች ሆነ። አቶ ካሳሁን አያይዘውም፤ አቶ ለማ መገርሳ  የዚህ የአመራር ማስተካከያ ዋና ቀያሽና ተዋናይ (Designer) መሆናቸውን አስታውቀው እንደነበርም ይታወሳል። አቶ ካሳሁን ጊዜው ሲደርስ ይታወቃል ቢሉም፥ ኦህዴድ ዶክተር አብይን ለሐገሪቱ ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ አድርጎ ያቀርባቸዋል የሚለው ግምት በብዙዎች ዘንድ ሚዛን የደፋ ሆነ። በዚህ ረገድም ኦህዴድ የስልት ለውጥ (Tactical shift) ማድረጉን ለመመልከት ተችሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም፥ ኦሕዴድ በአንፃራዊነት ከሚመሩት ክልል አልፎ፣ በሐገር አቀፍ ደረጃ በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ተሰሚነት ካገኙት አቶ ለማ መገርሳ ይልቅ ምክትላቸው የሆኑትን ዶክተር አብይ አህመድን በሊቀ መንበርነት የሾመበት አብይ ፖለቲካዊ ምክንያት ግልፅ ነበር ለማለት ይቻላል። ይኸውም ዶክተር አብይ አህመድ የፓርላማ አባል በመሆናቸው የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩ አድርጎ ለማቅረብ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በዚህም መነሻ የዶክተር አብይ አህመድ በኦሕዴድ ሊቀመንበርነት መመረጥ፣ ድርጅቱ አቶ ለማን በእጩነት በማቅረብ ምናልባትም በኢህአዴግ ምክር ቤት ከህጋዊነት ጋር በተያያዘ እጩው ውድቅ እንዳይሆንበት በማሰብ አስቀድሞ የፖለቲካ ስህተት ላለመፍጠር እንደሆነ በብዙዎች ተጠቁሟል፡፡ ይህም የሚያሳየው ድርጅቱ የኢህአዴግ ሊቀመንበርነትና የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታዎች በድርጅቱ  እንዲያዝ አጥብቆ መሻቱን ነው። እናም ከዚህ ጊዜ አንስቶ ዶክተር አብይ ለቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በእጩነት እንደሚቀርቡና ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ከፍተኛ እድልም እንዳላቸው ግምቶች በስፋት ይናኙ ያዙ። እነሆ የብዙዎች ግምት እውን ሆኖ፥ የኦህዴድም ጥብቅ መሻት መሬት ይዞ፣ ዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በቁ።
ዶ/ር አብይ አህመድ  ማናቸው?
በ1976 በኦሮሚያ ክልል በምትገኘው በጅማ ዞኗ አጋሮ ከተማ፤ የእስልምና ሐይማኖት ተከታይ ከሆኑት የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ አርሶ አደር  አባታቸውና፥ የአማራ ብሔር ተወላጅና የክርስትና እምነት ተከታይ ከሆኑት እናታቸው የተወለዱት ዶክተር አብይ፤የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ናቸው። ዶክተር አብይ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በ2001 አዲስ አበባ ከሚገኘው የማይክሮ ሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ አገኙ። በ2005 ከደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፤ ማሺን ዳይናሚክስ በተሰኘ የሙያ መስክ፣ የድህረ ምረቃ አድቫንስድ ዲኘሎማ ማግኘታቸውን የግል ማህደራቸው ያመለክታል።
በመቀጠልም አዲስ አበባ የሚገኘው የአመራር ጥበብ ማሰልጠኛ ተቋም፤በእንግሊዝ ለንደን ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ ጋራ በጥምረት በሚሰጡት Transformational Leadership and Change with Merit የትምህርት ዘርፍ፣ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ተከታትለው፣ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት ዶ/ር አብይ አሕመድ፥በ2013 ደግሞ አሽላንድ ሊድስታር ከተባለ ዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን (management of Business Administration) በMBA በመከታተል ሌላ የሁለተኛ ዲግሪ ማግኘት ችለዋል። በመጨረሻም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከInstitute for Peace and Security Studies የዶክትሬት ድግሪያቸውን  አግኝተዋል፡፡
ዶ/ር አብይ የሥራና የፖለቲካ  ህይወታቸውን የጀመሩት ገና በለጋ እድሜያቸው ነበር፤ በ1990 ዓ.ም። ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል፤በውትድርና ኢህአዴግን በመቀላቀል ነበር የጀመሩት። በ1991 የደርግን ውድቀት ተከትሎ፣በምዕራብ ወለጋ በነበረው አሰፋ ብርጌድ ውስጥ መደበኛ የውትድርና ስልጠና ወሰዱ። በ1995 ደግሞ የሩዋንዳን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ለማስቆም በተባበሩት መንግስታት አማካኝነት በተቋቋመው የሰላም አስከባሪ ግብረ ኃይል፤ ኢትዮጵያ ከላከችው ጦር ጋር ሆነው፣ለሰላም ማስከበር ተልእኮ ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ ዘመቱ። ከዚያ መልስ  ከ1998-2000 በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ የወታደራዊ ደህንነት ቡድን መሪ በመሆን የኤርትራን ጦር አጠቃላይ ይዘትና አሰላለፍ እያጠኑና ለኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ከስር ከስር መረጃ በመስጠት ሐገራቸውን አገልግለዋል። እስከ 2010 ድረስ በጦር ሰራዊት ቤት በነበራቸው ስኬታማ የውትድርና  ቆይታቸውም፣ የሌተናል ኮሎኔልነት ማዕረግ ለማግኘት ችለዋል።
በሲቪል ህይወታቸው ደግሞ በ2007 በኢትዮጵያ መንግሥት ይሁንታ፣ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲን (ኢንሳ) እራሳቸው ወጥነው በማቋቋም፥የተቋሙ መስራችና ዳይሬክተርም በመሆን አገልግለዋል። በዚሁ ወቅት ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ሐላፊነታቸው ጎን ለጎንም ከኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ጋር ግንኙነት ያላቸው መንግስታዊ ተቋማት፡- እንደ ኢትዮ- ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመሳሰሉ ተቋማት ውስጥ የቦርድ አባል በመሆን  ያገለግሉ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። በ2014 ደግሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከልን በማቋቋም፣ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል። በ2010  የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት  ኤጀንሲ ሐላፊነታቻውን የለቀቁት ዶ/ር አብይ፥ በዚያው ዓመት የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አባል በመሆን የፖለቲካ ተሳትፏቸውን አሀዱ ብለው ጀመሩ። በኦህዴድ ውስጥም ከ2010 – 2012 የድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን፣ የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት አባል ነበሩ፡፡
በዚሁ ዓመት በተካሄደው ሐገራዊ ምርጫ፤ዶ/ር አብይ በተወለዱባት አጋሮ ወረዳ፣ ኦህዴድን ወክለው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ተወዳድረው ተመርጠዋል። እንደዚሁም በ2015 ለሁለተኛ ጊዜ፣ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት ተወዳድረው በድጋሚ ለመመረጥ ችለዋል። በ2016 የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል መሆን የቻሉት ዶ/ር አብይ፥ በዚሁ ጊዜ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ሆነው ተሾሙ። ይሁን እንጂ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣በሚኒስትርነት ሐላፊነታቸው ብዙም ሳይቆዩ፥ በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ሰበብ፣ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ኦህዴድ/ኢህአዴግ፤ የአመራር ለውጥ በማድረግ፣ ዶ/ር አብይ አሕመድን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የድርጅቱ ፅ/ቤት ሐላፊ አድርጎ ሾማቸው።
አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ትግርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው የሚናገሩት ዶ/ር አብይ አሕመድ፥ እነሆ አሁን ደግሞ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል። የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት መንበርን ከነገ ወዲያ ሰኞ፣በተወካዮች ምክር ቤት እንደሚረከቡ  ይጠበቃል።
 ዶ/ር አብይ አሕመድ ያላቸውን የብሔርና የሐይማኖት መሰረት እንዲሁም የፖለቲካ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ብሎም ያላቸው የሰብዕና ደረጃ፥ በጠቅላይ ሚኒስትርነት የስራ ዘመናቸው፥ በቀውስ ውስጥ የምትገኘውን አገራችንን ከገባችበት የፖለቲካ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ የቀውስ አዙሪት በማውጣት፥ አረጋግተው፣ ወደቀደመ ሰላሟ እንድትመለስ እንደሚያደርጓት  ብዙዎች ገምተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ብስለትና ብልሐት ባለው አመራር፣ ሐገሪቱን የማስተዳደር እጅግ ከባድ ፈተና ከፊታቸው መጋረጡ አያጠያይቅም። ይህንን ፈተናም በብቃት ይወጡት ዘንድ ያላቸው የሰብእና መሰረት እንደሚያግዛቸው፣ ዶ/ር አብይን  በቅርበት የሚያውቋቸው ይመሰክራሉ፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ የሆኑት ዶክተር አብይ አህመድ፤በጠቅላይ ሚኒስትርነት ዘመናቸው መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማቸው ልባዊ ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡   በሐገራችን የፖለቲካ ሰማይ ላይም የሰላም አየር እንደሚነፍስበት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡  
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ሰላሙንም ያብዛልን!!
(ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ ውስጥ የተጠቀሱት ዓመተ ምህረቶች በሙሉ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ናቸው፡፡)  

Read 1798 times