Saturday, 21 April 2018 11:17

በ38ኛው የለንደን ማራቶን ላይ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

  • 116 ሺ ሜትር የጎዳና መለያ ሪባን ይዘረጋል፡፡
  • 45 አምቡላንሶች ይሰማራሉ፡፡
  • 671 ውሃ መጠጫ ጣቢያዎች ይቆማሉ፡፡
  • 650 ሺ የፕላስቲክ ውሃዎች ይቀርባሉ፡፡
  • የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ ባለቤቶች ለዓለም ሪከርድ ይሮጣሉ
  • በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ 55ሺ ዶላር በአጠቃላይ 313ሺ ዶላር ተዘጋጅቷል፡፡
  • የተመልካች ብዛት ከ750ሺ በላይ ይሆናል
  • ለፈጣን ሰዓት እና ለሪከርድ ቦነስ 850ሺ ዶላር በአጠቃላይ ቀርቧል፡፡
 
• ለዓለም የማራቶን ሪከርድ125ሺ ዶላር ለለንደን ማራቶን ሪከርድ 25ሺ ዶላር ይታሰባል፡፡

     38ኛው የለንደን ማራቶን በለንደን ከተማ ሲካሄድ 386 ሺ ስፖርተኞች ለመሮጥ ያመለከቱ ሲሆን 54,685 ለተሳትፏቸው ማረጋገጫ እንዳገኙ ታውቋል። በዋናው የአትሌቶች ውድድር የዓለም ማራቶን ሪከርድ በሁለቱም ፆታዎች ሊሻሻል እንደሚችል ተጠብቋል። የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድን በሁለቱም ፆታዎች የያዙት ጥሩነሽ ዲባባና ቀነኒሳ በቀለ የዓለም ማራቶን ሪከርድን የመስበር እቅድ እንዳላቸው ከውድድሩ በፊት በሰጧቸው መግለጫዎች አመልክተዋል፡፡
የለንደን ከተማ አየር ሁኔታ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛው የሙቀት መጠን እንዲኖር መነገሩ ሪከርድ የሚሻሻልበትን ዕድል እንደሚያጠበው እየተገለፀ ነው፡፡ የሙቀቱ መጠን ከ16 እስከ 19 ዲግሪ ሴንትግሬድ ቢሆን ይመረጣል ተብሏል፡፡ የኬንያዋ ማሪ ኪታኒ የአየሩ ሙቀት በውድድሯ ላይ ምንም ተፅእኖ እንደማይፈጥር ነው የተናገረችው፡፡
ይሁንና የለንደን ማራቶን አዘጋጆች ለቢቢሲ በሰጡት አስተያየት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ የአየሩ ሙቀት ከ22 እስከ 24 ዲግሪ ሴንትግሬድ ሊሆን ይችላል የሚል ትንበያ በመሰማቱ ነው፡፡ ይህ መጠን ለሪከርድ አስቸጋሪ እንደሚሆን የአትሌቲክስ ባለሙያዎች እየተናገሩ ናቸው፡፡ በውድድሩ ታሪክ ለሁለት ጊዜያት በ1996 እና በ2007 እኤአ ከፍተኛ የአየር ሙቀት አጋጥሞ ነበር፡፡
በተያያዘ የለንደን ማራቶን አዘጋጆች “ጊነስ ዋርልድ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ” ጋር በመተባበር 49 የተለያዩ የሪከርድ ሙከራዎች እንደሚደረግ ያስታወቀ ሲሆን፤ በ38 የለንደን ማራቶኖች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለበጎ አድራጎት የሚውል ገንዘብ ተገልጿል፡፡
በወንዶች ምድብ ቀነኒሳ በቀለ ከኬንያው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ጋር ከባድ ፉክክር እንደሚገባ ሲጠበቅ፤ በሴቶች ምድብ ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ ትንቅንቋ ከሌላዋ ኬንያዊት ማሪ ኪታኒ ጋር ይሆናል፡፡  በሁለቱም ፆታዎች ዋናው ፉክክር በኬንያ እና በኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች መካከል እንደሆነ ቢገለፅም በወንዶች ኤርትራውያን፤ በሴቶች የእንግሊዝ ፤ የአሜሪካ እና የጃፓን ማራቶኒስቶች ተቀናቃኞች እንደሚሆኑም ተወስቷል፡፡ በለንደን ማራቶን ታሪክ በሁለቱም ፆታዎች 23 አሸናፊዎች (13 በወንድ 10 በሴት) በማስመዝገብ ኬንያ ቀዳሚ ስትሆን በ11 አሸናፊዎች (6 በወንድ 5 በሴት) እንግሊዝ ትከተላለች፡፡ በለንደን ማራቶን ኢትዮጵያውያን ያሸነፉት በሁለቱም ፆታዎች ስድስት ጊዜ ነው፡፡ በወንዶች በ2003 እ.ኤ.አ ገዛኸኝ አበራ እንዲሁም በ2010 እና በ2013 ፀጋዬ ከበደ አሸንፏል። በሴቶች ደግሞ በ2001 እ.ኤ.አ ደራርቱ ቱሉ በ2010 እ.ኤ.አ አሰለፈች መርጊያ እና በ2015 እ.ኤ.አ ትእግስት ቱፋ አሸናፊዎች ነበሩ፡፡  
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ዘንድሮ  የለንደን ማራቶንን ለሶስተኛ ጊዜ የሚሮጥ ይሆናል፡፡ በ2016 እኤአ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሮጥ 3ኛ ደረጃን እንዲሁም ባለፈው ዓመት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡  ጉዮ አዶላና ቶላ ሹራ  ለንደን ማራቶንን የሚሮጡ ሌሎቹ የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች ሲሆኑ ባለፈው ዓመት ያሸነፈው ዳንኤል ዋንጂሩ፤ የዓለም የማራቶንንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት እየሰራ የሚገኘው ኤሊውድ ኪፕቾጌ፤ ስታንሊ ቢዎት፤ አቤል ኪሪዊ፤ ላውረንስ ቼሮኖና ቤዳን ካሮኪ ኬንያን የሚወክሉ ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡  እንግሊዛዊው የረጅም ርቀት አትሌት ሞ ፋራህ የመጀመርያ ማራቶኑን የሚሳተፍም ይሆናል፡፡
በለንደን ማራቶን የኢትዮጵያው ቀነኒሳ በቀለ ከኬንያው ኤሊውድ ኪፕቾጌ መተናነነቃቸው ከሞ ፋራህ የመጀመርያ ተሳትፎ የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ከትራክ ወደ ጎዳና ከወጣ በኋላ በ10 ማራቶኖች ሮጦ 9 ጊዜ አሸንፏል፡፡ የለንደን ማራቶን ሪከርድን በ2016 እ.ኤ.አ ሲያሸንፍ በ2፡03፡05 በሆነ ጊዜ የቦታውን ሪከርድ ማስመዝገቡ የሚታወቅ ሲሆን በናይኪ Breaking2 ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት ፕሮጀክት 2፡00፡25 በሆነ ጊዜ የዓለም ሪከርድ ባይሆንም ልዩ ክብረ ወሰን ማሳካቱ ይታወሳል፡፡ በ2015 እና በ2016 እኤአ ላይ የለንደን ማራቶንን ያሸነፈ ሲሆን ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ ለማሸነፍ ማነጣጠሩን አስታውቋል፡፡ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በሚሰራበት ፕሮጀክት እየተጋ በመሆኑ በዓለም አትሌቲክስ ባለሙያዎች ሪከርድ መስበር እንደሚችል በተደጋጋሚ እየተመሰከረለት ቆይቷል። ይህን አስመልክቶ ከውድድሩ በፊት ሲናገር ‹‹እቅዴ በጣም ውበት ያለው ውድድር ለማድረግ ነው።  የዓለም ማራቶን ሪከርድን የምሰብርበትን ሁኔታ ከወዲሁ ልወስን አልችልም›› ብሏል፡፡
ከዓለም ማራቶን ሪከርድ ቀጥሎ ምርጥ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ቀነኒሳ በቀለ በ2016 እኤአ በበርሊን ማራቶን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው 2:03:03 የሆነ ጊዜ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ ሆኖ መመዝገቡ የሚታወቅ ነው፡፡ ቀነኒሳ ወደ ማራቶን ከገባ በኋላ ማሸነፍ የቻለው በ2014 ፓሪስ  ላይ በበርሊን በ2016 እኤአ ለ2 ጊዜ ብቻ ነው ነው፡፡ በሶስት ማራቶኖች አቋርጦ ሲወጣ በሌሎቹ ደግሞ ማሸነፍ አልቻለም፡፡ ቀነኒሳ በማራቶን ውጤታማ ለመሆን የተሟላ ወሳኝ ጤንነት መሆኑን ከለንደን ማራቶን በፊት በሰጠው መግለጫ ሲያመለክት‹‹ ጤና በዋነኝነት አስፈላጊ ነው። ፓሪስ እና በርሊን ላይ ሳሸንፍ ሙሉ ጤነኛ ነበርኩ። በሌሎች ማራቶኖች ግን ጉዳቶች ነበሩብኝ፡፡ 100 በመቶ የተሟላ ብቃት ላይ አልነበርኩም፡፡ ማራቶንንን ከጉዳት ጋር መሮጥ ፈታኝ ነው›› ሲል ተናግሯል፡፡
በሌላ በኩል የመጀመሪያ ማራቶን ውድድሩን የሚያደርገው ሞ ፋራህ ብቸኛ ተስፋ ያደረገው በ1985 እ.ኤ.አ ላይ  ስቲቭጆንስ 2፡07፡13 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው የብሪቲሽ የማራቶን ሪከርድ ለማሻሻል ነው፡፡
የኬንያው ማራቶኒስት ዴኒስ ኪሜቶ በ2014 እኤአ በበርሊን ማራቶን በ2 ሰዓት ከ02 ደቂቃዎች ከ57 ሴኮንዶች የዓለም ማራቶን ሪከርድን ማስመዝገቡ የሚታወቅ ነው፡፡
በሴቶች ምድብ ጥሩነሽ ዲባባ በለንደን ማራቶን ለ3ኛ ጊዜ መካፈሏ ሲሆን ማሬ ዲባባ፤ ትግስት ቱፋና ታደለች በቀለ ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ሴት ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡ ኬንያዊቷ የ36 ዓመት ማራቶኒስት ማሪ ኪታኒና የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችው የባህሬኗ ሮዝ ቼሊሞ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ሲሆን፤ ቪቪያን ቼሮይት፤ ግላዲስ ቼሮኖና ብሪግድ ኮሴጊም ይወዳደራሉ፡፡
የለንደን ማራቶን የውድድር ዲያሬክተር ሁግ ብራሸር ማሪ ኪታኒና ጥሩነሽ ዲባባ  በ2017 እኤአ ላይ በተመሳሳይ ቦታ የነበራቸውን ፉክክር ጠብቀዋል። የዓለም ማራቶን ሪከርድ በሴቶች የመሰበሩን እድል ሰፊ የሚያደርገው የሁለቱ ፉክክር መሆኑን የተናገሩት ከወራት በፊት ነበር፡፡ ለ3 ጊዜያት በለንደን ማራቶን ያሸነፈችው ማሪ ኪታኒ የማራቶን ሪከርዱን ለማሻሻል ብዙ ዓመታን እንደሰራች ተናግራ፤ ዘንድሮ በወንድ አሯሯጮች በመታገዝ የመስበር እቅድ አለኝ ብላለች። በሴቶች ምድብ ያለፉትን 15 ዓመታት ሳይበር የዓለም ማራቶን ሪከርድ እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ  2፡15.25 በሆነ ጊዜ በለንደን ማራቶን ያስመዘገበችው ነው።
አምና ኬንያዊቷ ማሪ ኬይታኒ የለንደን ማራቶንን ስታሸንፍ ርቀቱን የጨረሰችበት 2፡17፡01 በሴቶች አሯሯጭነት አዲስ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፤ ፓውላ ራድክሊፍ በ2005 እኤአ ላይ በሴቶች አሯሯጭነት ያስመዘገበችውን 2፡17፡42 በአርባ አንድ ሰከንዶች በማሻሻሏ ነው፡፡
ከ15 ዓመታት በፊት በለንደን ማራቶን ፓውላ ራድክሊፍ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ስታስመዘግብ አዘጋጆቹ ልዩ እቅድ ነበራቸው፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ወንዶችና ሴት አትሌቶች ሳይቀላቀሉ ለየብቻ ነው የሮጡት፡፡ በሴቶቹ ውድድር ላይ ለምርጦቹ ማራቶኒስቶች ሰባት ወንድ አሯሯጮች ተመድበዋል። ሁሉም ኬንያውያን ነበሩ፡፡ ከዚያ ውድድር በኋላ ግን የለንደን ማራቶን አዘጋጆች ቀጣዮቹን 14 የለንደን ማራቶኖች እንዲካሄድ ያደረጉት በሴት አሯሯጮች ነበር፡፡ ይህም የራድክሊፍ ሪከርድ ሳይሰበር ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡
ዘንድሮ ግን የውድድሩ ዲያሬክተር ሂውጅ ባሸር የሴቶች ሩጫው በወንዶች አሯሯጭነት እንዲካሄድ ወስነዋል፡፡ ዋና ትኩረቱም የዓለም ማራቶን ሪከርድ በሴቶች ይመዘገባል በሚል ግምት ነው፡፡ ለሪከርዱ ከፍተኛ ግምት ያላቸው የኬንያዋ ማሪ ኪታኒ እና የኢትዮጵያዋ ጥሩነሽ ዲባባ ከውድድሩ በፊት በሰጡት መግለጫ የወንድ አሯሯጮች ሚናን ብዙ አላደነቁም፡፡
የተሟላ ዝግጅት ማድረጓን የተናገረችው ጥሩነሽ‹‹ የውድድሩ አዘጋጆች ብቁ አሯሯጮች ሊመድቡ ይችላሉ፡፡ ዋናው አስፈላጊ ነገር በምርጥ ብቃት ላይ መገኘቴ ነው፡፡›› ብላለች፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ ባለፈው ዓመት በለንደን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃ ስታገኝ ያስመዘገበችው  2:17:56 የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ውድድር በኋላ ወደ ለንደን ተመልሳ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ ያገኘች ሲሆን፤ ከዚያም በማችስተር የ10 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ አሸንፋ የቺካጎ ማራቶንንም በአንደኝነት ጨርሳለች፡፡ ከዚያም ለሁለት ወራት ሙሉ እረፍት ከወሰደች በኋላ በከፍተኛ ትኩረት ልምምዷን ስትሰራ ቆይታለች፡፡  ስለ ዓለም የማራቶን ሪከርድ የመሰበር እድል ተጠይቃ ‹‹የዓለም የማራቶን ሪከርድ ለመስበር ብዙ ወሳኝ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡  የአየር ሁኔታው፤ የአሯሯጮቹ ብቃት፤ አጠቃላይ የሩጫው ሂደት እና ሌላውም ሁሉ፡፡ ሁሉም ነገር ምቹ ከሆነ ለሪከርድ መሮጤ አይቀርም›› ብላለች፡፡ ማሪ ኪታኒ በበኩሏ ‹‹2 ሰዓት ከ15 ደቂቃዎች የተለየ ብቃት ነው፡፡ ቀላል አይደለም፡፡ እየተጠበቅን ያለነው የታላቋን ሯጭ ፈለግ እንድንከተል  ነው፡፡ ›› ስትል ተናግራለች፡፡

Read 4006 times