Print this page
Sunday, 22 April 2018 00:00

ሥልጣን ዘለዓለማዊ ቢሆን ኖሮ አንተ ጋ አይደርስም ነበር

Written by 
Rate this item
(12 votes)

 በአንድ አገር በአንዲት መንደር ውስጥ ብቻውን የሚኖር አንድ ሰዓሊ ነበር፡፡
በመንደሩ ውስጥ አንድ ሐይቅ አለ፡፡ ሐይቁ ሰዓሊው ከሚኖርበት ቤት ጥቂት ራቅ ይላል፡፡
ያ ሰዓሊ ታላላቅ የተባሉ ስዕሎችን ይሰራና ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይልካል፡፡ በዚህም ታላቅ ስምና ዝናን ያተርፋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የእሱ መንደር ሰው ስለሱ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። እሱ ከማንም አይገጥምም፡፡ ቤቱ ስቱዲዮው ነው፡፡ ከቤቱ ከወጣ ወደ ሐይቁ ሄዶ ቁጭ ብሎ ተፈጥሮን ሲያደንቅ ይውላል፡፡
በዚህ ዓይነት ህይወቱን ሲገፋ ኖሮ፣ አንድ ቀን ታመመ፡፡ ብዙ ማቅቆ ማቅቆ ሞተ፡፡
የዓለም የዜና ማሰራጫ አውታሮች በጠቅላላ የሚያወሩት ስለዚያ ታላቅ ሰዓሊ ሆነ፡፡ የማታ ማታ የመንደሩ ሰው፤ የአገሩ ታላቅ ሰዓሊ መሆኑንና በዓለም ላይ ስመ ጥር ሰው መሆኑን አወቀ፡፡ ስለዚህ በስሙ አንድ ማስታወሻ ማቆም ያስፈልገናል ተባለና መመካከር ጀመሩ፡፡
አንደኛው - ይህ ታላቅ ሰዓሊ ጠባዩ ምን መሳይ ነበረ? በትክክል ገፅታውን ያስተዋለ ሰው አለ?
ሁለተኛው - አመለካከቱስ? ፍልስፍናውስ? ትምህርቱስ ምንድን ነበር?
ሦስተኛው - ይሄንን ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም ማንም አናግሮት የሚያውቅ ሰው የለም፡፡ ስዕሉን እንኳን ዓይተንለት አናውቅም፡፡ ስለዚህ ማንን ጠይቀን መረጃ እናግኝ?
አንደኛው - ማንንም ልንጠይቅ አንችልም፡፡ የሚሻለው ሁልጊዜ ይሄድበት የነበረውን ሐይቅ ሄደን መጠየቅ ነው፡፡
ሁሉም ወደ ሐይቁ ሄዱ፡፡ ከዚያም፤
“ሐይቅ ሆይ! ታላቁ ሰዓሊያችን አርፏል፡፡ እኛ አንድ መታሰቢያ ልናቆምለት አስበናል፡፡ ሆኖም መልኩን እንኳን በቅጡ ማስታወስ የሚችል ሰው ጠፋ፡፡ ስለዚህ ያ ሰዓሊ ምን መሳይ እንደነበር እንድትነግረን ነው ወደ አንተ የመጣነው!”
ሐይቁዉም፤
“አመጣጣችሁ መልካም ነው፡፡ ሆኖም ብዙ የምረዳችሁ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እናንተ፤ ሰውን በህይወቱ እያለ ከማክበር ይልቅ ሲሞት ክብር የምትሰጡ ሰዎች ናችሁ፡፡ እኔም ብሆን በመጣ ቁጥር ዐይን ዐይኑን ሳይ ነው የከረምኩት፡፡ ስለዚህ ዐይኑ ብርሃን እንዳለው ብቻ ነው የማውቀው፡፡”
*   *   *
ብርሃናማ ሰዎቻችንን ለማወቅ የውጪ ሰው እስኪነግረን አንጠብቅ፡፡ እኛው ብርሃናማ ሰዎቻችንን እንወቅ፡፡ ከየትኛውም ጠባብነት፣ ከየትኛውም ትምክህተኝነት እንለያይ፡፡ የምስራቅንና ምዕራብ ጀርመንን ይከፍል የነበረው “ታላቁ” ግምብ፤ ዛሬም ጀርመናውያን አዕምሮ ውስጥ አለ ይባላል፡፡ ግምብን በአካል ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አገርን የሚያድነው፤ አንድያውን ከአዕምሮ መሰረዝ ነው! ምናልባትም ሥር ነቀል ለውጥ (Radical Transformation) የሚመጣው አላስፈላጊ ጉዳዮችን ከናካቴው ከዕሳቤ በመገላገል ነው! አለበለዚያ “እንደቀንድ - አውጣ ሰንኮፈን፣ እንጭጭ ህሊና ያወጡ” እንዳለው ሎሬት ፀጋዬ፤ በየጊዜው እንጭጭ ህሊና መቀፍቀፍ ይሆናል ዕጣ-ፈንታችን፡፡ ይህን ልብ እንበል፡፡
ሌላው ጉዳያችን፤ ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር (viva la difference!) የሚለውን ከልብ መቀበል ነው፡፡ ሆኖም ልዩነት ያለ ጥንቃቄና ያለ ዕውቀት ኪሳራ ነው፡፡ አምላክ አንድ ያደረጋቸውን መለያየት አይቻልም እንደሚባል ሁሉ፤ የለያያቸውንም ማዋሃድ አይቻልም፤ ማለትም ያስኬዳል፡፡ በሁለቱም አባባሎች ውስጥ የኃይል እርምጃ (Coercive measure) እንዳይኖር መጠንቀቅ ነው ዋናው፡፡ የጠረጴዛ ውይይት የሚፈታውን ችግር ጦር ሰብቆ፣ ዘገር ነቅንቆ ካልሆነ፣ አይሆንም ማለት ከግብዝነት የማይተናነስ ጀብደኝነት ነው፡፡ በአንፃሩ በምንም ዓይነት ዘይትና ውሃ መሆኑ የታወቀን ነገር፣ በንግግር ካልፈታሁ ማለት፤
“Poet! Don’t go far a word
When what you all need is a sword
Bile, not the veil, in the war field!”
(“አንት ባለቅኔ ሆይ!
እጦር ሜዳ ገብቶ ጎራዴ ለሚሻው
መፍትሔው ወኔ ነው፣ ቅኔ አይደለም ቋንቋው!
ሀሞትህ ነው እንጂ የሙሽራ ልብስህ
ከባሩድ መካከል፣ ከቶም አያድንህ!”
… እንደማለት ነው፡፡ ሁሉም ነገር አግባብ ባለው ቦታና ሰዓት መደረግ አለበት፡፡ የሹመትና ሥልጣን ሽግግር፤ የለውጥ ዝግጁነትን የሚያስከትል ከሆነ ብቻ ነው፤ ለውጥ የሚገኘው፤ ስለሆነም አመለካከትን መለወጥ ላይ መሰራት አለበት!
ገጣሚው፡-
“በቀን ሦስት ጊዜ እንበላለን ብለን
አንዱም ባንዴ አቃተን!”
እንዳለው እንዳይሆንብን፤ በምግብ ራስን ለመቻል መትጋት ተቀዳሚ መሆን አለበት፡፡ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራልንም መቼም ቢሆን አንዘንጋ!
ሥልጣን የሁልጊዜ ይዞታ አይደለም፡፡ ርስተ - ጉልትም አይደለም፡፡ ወሳኙ ነገር ከህዝብ ጋር እየመከሩ፣ ዘለቄታው ምን ይሁን? የሚረከበንን እንዴት እንምረጥ? እንዴት እንቅረፅ? እኔ እንዴት እዘልቃለሁ ሳይሆን አገር እንዴት ትዘልቃለች? ከትላንት የተሻለች ኢትዮጵያን እንዴት እናምጣት? ማለት ያባት ነው! ምንጣፉን ከእግራችን ሥር የሚጎትቱ ባላንጦች እንዳሉ አንርሳ! ማደግ የሚቻለው የዕድገት ግብአቶችን በትክክል፣ በትክክለኛው ቦታ፣ በትክክለኛው ሰዓት በመጠቀም ነው፡፡ የዚህ ሁሉ መጎናፀፊያው፤ ዕውቀትንና መረጃን መሰረት በማድረግ፣ ዘላቂነትን፤ ረዥም ዕድሜን፤ ከዘለዓለማዊነት ባለማምታታት ነው፡፡
(Not mistaking longevity for eternity)
ዋና ጉዳይ፤ “ሥልጣን ዘለዓለማዊ ቢሆን ኖሮ አንተ ጋ አይደርስም ነበር!” የሚለው የአረቦች ተረት ትርጉም የሚኖረው እዚህ ላይ ነው! ልብና ልቦና ይስጠን!

Read 5524 times
Administrator

Latest from Administrator