Sunday, 22 April 2018 00:00

“ፋታ የምትፈልገው ኢትዮጵያ ናት!”

Written by  ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
Rate this item
(4 votes)

  በጃንሆይ ዘመነ መንግስት ልጅ እንዳልካቸው መኮንን “ፋታ ስጡኝ” እያሉ ቢጮኹም፥ ሰሚ አጥተው “አቶ ጥድፊያ” ኢትዮጵያን ላለፉት ዓመታት መከራ አሳልፎ እንደሰጣት እናውቃለን። ከታሪክ ጠባሳ ካልተማርን ታሪክ ራሱን ይደግማል። ለዶ/ር አብይ አህመድ ፋታ መስጠት የሚያስፈልገው ለእርሳቸው ስልጣን ማራዘሚያ አይደለም። ፋታ የምትፈልገው ኢትዮጵያ ናት። አሁንም ዶ/ር አብይን የሚያዋክቡ ወገኖቻችን፤ ዓይናቸውን ከእሳቸው ላይ አንስተው፣ እናት ሀገር የምትባለው ኢትዮጵያ ያለችበትን ምጥ ማየት ቢችሉ መልካም ነው። ጊዜው አዲሲቷ ኢትዮጵያ ለመወለድ ጫፍ ላይ ያለችበት ወቅት ይሆን? በማለት የአዋላጅነት ሚና  እንድንጫወት፣ ሁላችንም መጣር የሚገባን  ወቅት ነው። ከጥንቃቄ አንጉደል።
ዶ/ር አብይ የሕዝብን ድምፅ አድምጠው፥ ይህንንም የሕዝብ ድምፅ ገንዘብ በማድረግ ከሌሎች ጋር ተቀናጅተው በሕዝብ ትግል እየተደገፉ እዚህ ደርሰዋል። በዚህም ምክንያት መላውን ሕዝብ ያስደመመና ከተዐምር የማያንስ ጉዳይ የሆነውን ኢትዮጵያዊነትን ሞሽረውና ሸልመው ሲያበቁ፥ኢትዮጵያና ህዝቧን በብርሃን አፍክተዋቸዋል። ለውስጥም ሆነ ለውጭ ተፎካካሪዎች፣ ተስፋ በሰነቀ ንግግራቸው፣ የፍቅር ጥሪ አድርገዋል፡፡ አሁን እርቅና መግባባት በምድራችን ዕውቅና ያገኘበት ወቅት ነው። ሙያ በልብ ነው የሚለውን መርህ ያነገቡ የሚመስሉትን እኚህን የኢትዮጵያ ልጅ፣ ማስተዋልን በተፋታ መልኩ ጥላሸት እየቀቡ መሞገት አሁን ጊዜው ነውን? “ሰሚ ያጣ ሕዝብ” በሚል ርዕስ የዛሬ ሁለት ዓመት ለንባብ ካበቃሁት ፅሁፍ ልጥቀስ፦
“--ከእንግዲህ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የለም። ማንም ላይታመን፥ ሕዝቡ ራሱን ብቻ ሊያምን ተነስቷል። ስልጣን የሕዝብ ነው እያሉ በስሙ የሚነግዱ፣ ከእንግዲህ በቃችሁ ተብለዋል። ስልጣን የሕዝብ መሆኑን የሚናገር ሳይሆን በሕዝቡ ለመመራት ራሱን የሕዝቡ ተከታይ የሚያደርግ ብቻ ይፈለጋል። ከትልቅ ትዕግስት በሁዋላ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሕዝቡ የተነሳው፥ መንግስት ስልጣኑን የሚያስረዝምበትን መላ ለማፈላለግ፥ ወይም ተቃዋሚ ስልጣን እንዲወርስ ለማመቻቸት ሳይሆን መሪዎቻችን የሕዝቡን ድምፅ እንዲሰሙና ስልጣንን ለባለቤቱ (ሕዝብ) ማስረከቢያውን መንገድ እንዲፈጥሩ ነው። ፈሪሃ ፈጣሪ ያለው ይህ ሕዝብ፣ አምላክ እንዳለለት ይታወቅለት።--”
ከዶ/ር አብይ የቁርጠኝነት ቃል በመነሳት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰሚ አግኝቼ ይሆን? እያለ የተነገረውን በተግባር ለማየት በተጠንቀቅ በሚጠብቅበት በዚህ ወቅት፥ አፍራሽ የሆነ ነገር መናገርና ማደናገር ለማን ይጠቅማል? ይልቁንስ እነዚህ ትዕግስት የጎደላቸው ወገኖቻችን፣ የትግላቸው ስልት ጊዜውን እንዲመጥን በማደስና ከሕዝብ የልብ ትርታ ጋር በማጣጣም፣ለኢትዮጵያ ፋታ ቢሰጡ አይበጅምን? የሩስያው ፕሬዚዳንት ጎርቫቾቭና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሬገን፤ “እመን ግን አረጋግጥ” እያሉ ነው ታሪክ የሰሩት። ይህንን መርህ በመጠቀም ትግሉን በቀና መንፈስ አጠናክሮ፣ገንቢ በሆነ አካሄድ መንቀሳቀስ ማስተዋል ነው። ለሁላችንም ልቦና ይስጠን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
(ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡)

Read 5015 times