Monday, 23 April 2018 00:00

“በርካታ ሙዚየሞችን መገንባት አለብን”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

• የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ፋውንዴሽን ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደርሰናል
  • ቅርሶችን ከውጭ አገራት የማስመለስ ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል
  • እንግሊዞች የመቅደላ አምባ ሙዚየም ግንባታን ማገዝ አለባቸው

    የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ  በዓል “መስዋዕትነት ለብሔራዊ ኩራት” በሚል መሪ ቃል ከሚያዝያ 2-8 ቀን 2010 ዓ.ም በጎንደር፣ ደብረታቦርና መቅደላ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ ባለፈው ሰኞም በአዲስ አበባ ጌትፋም ሆቴል የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ በደመቀ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን በዝግጅቱ ላይም የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም፣ ፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ፣ ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ፣ ፕ/ር ማሞ ሙጨ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሣው እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አርቲስቶችና የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡
ከአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ በዓል ዝግጅት ምን ውጤት ተገኘ? በክብረ በዓሉ ላይ የተመሰረተው ጊዜያዊ የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ዓላማ ምንድን ነው? ሳይገነባ ከ10 ዓመት በላይ የቆየው የመቅደላ አምባ ሙዚየም ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? አደጋ የተጋረጠባቸውን ላሊበላና ጣና ሐይቅን ማነው የሚታደጋቸው?---የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከባህልና ቱሪዝም  ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማሪያም ጋር በእነዚህና ሌሎች የቱሪዝም ዘርፍ ጉዳዮች ተከታዩን ቃለ ምልልስ  አድርጋለች፡፡

   የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ በዓል፣ ለሳምንት ገደማ ከጎንደር እስከ አዲስ አበባ፣ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡ ከዚህ ክብረ በዓል ምን ውጤት ተገኘ?
ይህ ዝክረ በዓል ትልቅና ታሪካዊ ነው ብሎ በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል፡፡ በዚህ የአፄ ቴዎድሮስ 150ኛ ዓመት ዝክረ በዓል ላይ ብዙ ዝግጅቶች ተከናውነዋል። ከአጼው የትውልድ ቦታ ራሳቸውን በክብር እስከ ሰዉበት መቅደላ ድረስ ታሪካዊ አሻራቸውን ያኖሩባቸው ቦታዎች ተጎብኝተዋል፡፡ የመዝጊያ ሥነ ስርዓቱም በአዲስ አበባ ጌትፋም ሆቴል በደመቀ ሁኔታ ተከናውኗል። እንግዲህ ምን ውጤት ተገኘ ለተባለው፣ አፄው በዘመናቸው ከሰነቋቸው ራዕዮች የአሁኑ ትውልድ ምን መማር ይችላል፣ የእርሳቸው ትሩፋቶች ምንድን ናቸው፣ አገርን ከማልማት፣ ከማዘመንና አንድ ከማድረግ አኳያ ህልማቸው ምን ነበር ወዘተ--የሚሉትን ለመፈተሽ ያስቻለ ሁነት ነበር ማለት ይቻላል። ከአፄው ስኬት ብቻ ሳይሆን ከውድቀታቸውም፣ ከውጭም ከውስጥም ከገጠሟቸው ፈተናዎች ምን እንማራለን? የህልማቸው ጫፍ ላይ እንዳይደርሱ ፈተና የሆነባቸው ምን ነበር? የሚሉትን እንድናይ፣ የአሁኑ ትውልድም ትምህርት እንዲቀስም ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ሌላው ደግሞ በየቀኑ በንጉሱ ህይወት ላይ የሚያጠነጥኑ፣ ጥልቅ ምርምር የተደረገባቸው የጥናት ጽሁፎች በትላልቅ የአገር ውስጥና የውጭ ምሁራን እየቀረቡ፣ ስንማርና ዕውቀታችንን ስናሰፋ ነው የቆየነው፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ አምባም ሆነ በአዲስ አበባ፤ በውጭ የሚገኙና እየተመለሱ ያሉ ቅርሶቻችንን፣ የልዑል አለማየሁን ፎቶግራፍ፣ የአፄውን የክብርና የንግስና ጌጣጌጦች እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያደረጉባቸው ደብዳቤዎችን ያካተተ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ ለእይታ ቀርቦ ነበር፡፡ ከዚህም ብዙ እውቀት መቅሰም ተችሏል፡፡ ጋዜጠኞች የአፄው ዱካዎች ያረፉባቸው ታሪካዊ መዳረሻዎችን ጎብኝተው በየሚዲያዎቻቸው በማስተላለፍ፣ ለማህበረሰቡ ትልቅ መነቃቃትና ግንዛቤ ፈጥረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ እንግዲህ የዚህ ዝክረ በዓል ትሩፋቶች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል እነዚህን ታሪክ የተሰራባቸውን ቦታዎች በሚገባ አልምተን፣ እንዴት የቱሪስት መዳረሻ ማድረግ እንደምንችል አቅጣጫ ያሳየና ትልቅ ትምህርት የተወሰደበት ነው፡፡ ጠቅለል ስናደርገው፤ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ያለን እውቀት ሰፍቷል፤ የምንወስደውን ትምህርት ለይተን ከቱሪዝም ጋር አቀናጅተን ምን መጠቀም እንችላለን የሚለውን ተገንዝበናል፣ የአፄ ቴዎድሮስ ፋውንዴሽን እንዲቋቋም ሀሳብ ቀርቦ፣ በደብረ ታቦር ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደርሰናል። መቅደላ ላይ ደግሞ ሙዚየም ለማቋቋም ተስማምተናል፡፡
በዚህ ዝክረ በዓል ላይ ከኢትዮጵያ ተዘርፈው በእንግሊዝ ሙዚየሞች የሚገኙ ቅርሶችን የማስመለስ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ይመስላል---  
እውነት ነው፣ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል። እንደሚታወቀው አፄው መጨረሻ ላይ ራሳቸውን ሲሰዉ፣ እንግሊዞች ልጃቸውን ወስደዋል፤ ሽሩባቸውን ከራሳቸው ላይ ገፍፈው ወስደዋል፣ ልብሶቻቸውን ሳይቀር ቆራርጠው ተቀራምተውታል፡፡ በግምጃ ቤታቸው ያጠራቀሟቸው የአገራችን የእጅ ጥበብ ውጤት የሆኑ በርካታ አይነት ቅርሶችንም (የፅሁፍ፣ ጌጣጌጦች፣ አልባሳት፣ ታቦታት፣ ዘውዶችና ሌሎች በርካታ ሀብቶች) ዘርፈዋል፡፡ ከ200 በላይ በሚሆኑ በቅሎዎችና ከ20 በላይ በሆኑ ዝሆኖች ጭነው ነው የወሰዱት፡፡
እንደውም በእንግሊዝ አገር ያሉ ቅርሶቻችን እስከ 2 ቢሊዮን ፓውንድ እንደሚያወጡ ይነገራል….
እውነት ነው፤ ከዚያም በላይ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የተዘረፉትን ቅርሶች አይነትና መጠን ስንመለከት፤ አፄ ቴዎድሮስ በዚያ ቦታ ላይ ቤተ መፅሐፍትና ሙዚየም የማቋቋም ሀሳብ ነበራቸው ለማለት ያስችላል፡፡ ይህን የሚያመላክት ጥልቅና አሳማኝ ጥናትም ዛሬ በዚሁ መድረክ ላይ ሲቀርብ ተመልክተሻል፡፡ ምክንያቱም እሳቸው ከውጭ ማለትም ከአውሮፓና ሌሎች አገራት ጋር በፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ ስለ ቤተ-መፃሕፍትና ስለ ሙዚየም ጥሩ ግንዛቤ ነበራቸው።  መቅደላ ላይ በብዛት የነበሩት ቅርሶችም ከመላ አገሪቱ የሰበሰቧቸው ነበሩ፡፡ የቅርሶቹ በአንድ ቦታ ላይ መገኘት፣ ለዘራፊዎቹ ምቹ ሁኔታን  ፈጥሮላቸዋል፡፡
እነዚህ ከአገራችን የተዘረፉ ሀብቶችን በማስመለስ ረገድ በህግና በዲፕሎማሲ ምን ስራዎች መሰራት አለባቸው፣ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት እነማን ናቸው፣ ምሁሩ አርቲስቱ፣ ሚዲያው፣ ባህልና ቱሪዝም፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት--ምን ምን የቤት ስራዎች ይውሰዱ፣ ምን አይነት ስልቶችስ ይቀየሱ --- የሚሉ በርካታ ምክረ ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃም ከፍተኛ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ ባሻገር ጠንካራ ቅርስ አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ለማቋቋም ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ተመስርቷል፡፡ ስለዚህ እጅግ የተዋጣለት፣ ብዙ ውጤት የተገኘበት ሁነት ነው፡፡ ይህን ኢንሺየቲቭ የወሰደውን ጎንደር ዩኒቨርሲቲንና በዚህ ክብረ በዓል ላይ አሻራቸውን ያሳረፉ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጽ/ቤቶችን እንዲሁም ተሳታፊ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን ለማመስገን እወዳለሁ፡፡
የእንግሊዝ መንግሥት ቅርሶቻችንን በረጅም ጊዜ ውሰት ለኢትዮጵያ ለመስጠት ጥያቄ ቢያቀርብም  የኢትዮጵያ መንግሥት “ሰው ንብረቱን ይወስዳል እንጂ አይዋስም” በሚል ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ተነግሯል፡፡ “ብልጥ ልጅ የያዘውን ይዞ ያለቅሳል” እንዲሉ፣ቅርሶቹን በውሰት ተቀብሎ ሙሉ ለሙሉ ለማስመለስ ጥረት ማድረግ አይሻልም ነበር?
በነገራችን ላይ የእንግሊዝ መንግሥት አቀረበ የተባለው ጥያቄ  በቀጥታ ለእኛ አልቀረበልንም። ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም ሆነ ለሌላ የትኛውም የመንግሥት አካል “ቅርሱን ለረጅም ጊዜ ተውሳችሁ ውሰዱ” የሚል ጥያቄ በቃልም በፅሁፍም አልመጣልንም፡፡ እኛም የሰማነው “ዘ ጋርዲያን” ከተባለ ጋዜጣና ከሌሎች የእንግሊዝ ሚዲያዎች  ነው፡፡ እኛን የጠየቀንም ያማከረንም የለም፡፡ የእንግሊዝ መንግስት ከምን ተነስቶ ሀሳቡን እንዳነሳው የምናውቀው ነገር ስለሌለ መልስ ለመስጠት፣ ለመቀበልም ሆነ ሌሎች አማራጮችን ለማየት አልተንቀሳቀስንም፡፡ እርግጥ እኛ እንደ መንግስት ሀብታችን ይመለስልን የሚል ጥያቄ አቅርበናል፡፡ በ2007 ዓ.ም ይህ ጥያቄ በርዕሰ ብሔሩ ፊርማ ተልኳል፡፡ ግን መልስ አልሰጡም፤ እኛም በተለያየ መንገድ ጥያቄ ማቅረባችንን ቀጥለናል፡፡
እርስዎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን መምራት ከጀመሩ በኋላ ተሳክቶልኛል ብለው የሚጠቅሱት ሥራ ወይም ፕሮጀክት ካለ ቢነግሩኝ?
ገና እኮ ነው! ይሄ አልቋል፣ አሳክቸዋለሁ ልልሽ አልችልም፡፡ ነገር ግን በዚህም በዚያም የሚታየው ጅምር ሁሉ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ስኬት ሂደት ነው፡፡ ለምሳሌ ዛሬ እኛ የምናመቻቸው፣ የምንቀይሰው ነገር እውን የሚሆነው፣ ከኛ ቀጥሎ በሚመጡት መሪዎች ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ሂደት ነው የምልሽ። ተስፋ ሰጪ ነገሮች እየሰራን ነው፤ ያንን ነዳጅ ጨምረን ፍጥነታችንን አሳድገን ወደፊት መሄድ ነው፡፡ አገራችን የረጅም ጊዜ ታሪክ፣ ስልጣኔና ቅርስ ባለቤት እንደመሆኗ፣ ይህችን ትልቅ አገር አጉልቶ ታሪኳን፣ ስልጣኔዋንና ቅርሷን ለማሳየት በርካታ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ አመለካከትን መቀየር፣ ቅርስንና ሀብትን ወደ ብሔራዊ ጠቀሜታ መለወጥ ያስፈልጋል፡፡
እርስዎ ከተሾሙ በኋላ ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ ይህ ደግሞ በዋናነት እርስዎ የሚመሩትን የቱሪዝም ዘርፍ የሚጎዳ ነው፡፡ በአገሪቱ ላይ ተፈጥሮ የነበረው የሰላም መታወክና አለመረጋጋት በቱሪዝም ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምን ያህል ነው?
ቱሪዝም እንደሚታወቀው በመጀመሪያ ደረጃ የሚፈልገው ሰላምና መረጋጋትን ነው፡፡ ይሄ ግልፅ ነው። አንድ ቱሪስት ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር ለመዘዋወር መጀመሪያ የሚጠይቀውና የሚያጠናው የሚሄድበትን አገር ደህንነት፣ ሰላምና መረጋጋት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር እኛም አገር ተፅዕኖ ማሳረፉ የሚካድ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ አንዳንድ አገሮች የሚያወጧቸው የጉዞ መረጃዎች የተጋነኑ መሆናቸው፣ ዘርፉ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡
ሆኖም እነ እስራኤልን ብትመልከቺ፣ በየቀኑ ቦንብ እየፈነዳ ውሎ የሚያድርበት አገር ነው። ግብፅና ሌሎችም አገራት እንደዛው ናቸው፡፡ በዓለም ላይ ሙሉ በሙሉ ወይም መቶ ፐርሰንት መረጋጋት አለ ማለት አይቻልም፡፡ ግን እስራኤልም ሆነ ሌላው አገር ቱሪስት እንደ ጉድ ይጎርፋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ትንሽ ኮሽ ሲል የሚጋነን ነገር  አለው፡፡ የሆነ ሆኖ የአገሪቱን ገፅታ ለመመለስ በተደረጉ የተለያዩ ጥረቶች፣የቱሪስት ፍሰት የተፈራውን ያህል አልቀነሰም ማለት ይቻላል፡፡
በአሁኑ ወቅት እመጣለሁ ብሎ ጉዞ የሰረዘ ቱሪስት የለም፡፡ ሰሜን ተራሮች ብትሄጂ ቱሪስት በብዛት አለ። ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎችም ላይ እንዲሁ፡፡ ነገር ግን አሁንም ጠንክረን መስራት ይኖርብናል፡፡ ከዚህም በኋላ የቱሪስቶች መምጣትና መቅረት፣ በምንሰራው ሥራ የሚወሰን ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተለያዩ ስራዎች እየሰራን ነው፡፡ አሁን አገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው፡፡ ለየትኛውም ቱሪስት የስጋት ምንጭ የሆነ ነገር የለም፤ግን አሁንም ከዚህ በተሻለ መስራት አለብን፡፡
በላሊበላና በጣና ሀይቅ ላይ ትልቅ አደጋ መጋረጡ ቢታወቅም፣ እነዚህን ቅርሶች ለመታደግ መንግሥት በተለይም እርስዎ የሚመሩት መሥሪያ ቤት ዳተኝነት አሳይቷል የሚል ወቀሳ ይሰነዘራል፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?
ምንም ዳተኝነት የለም፤ ማድረግ ያለብንን ሁሉ እያደረግን ነው፡፡ አገራችን የበርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች ባለቤት እንደ መሆኗ፣ ቅርሶቿ ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ይሄ በየትኛውም ዓለም ያለ ነገር ነው፡፡ ሁሉም ነገር ዘላለማዊ አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ ላሊበላን ያየን እንደሆነ፣ ረጅም እድሜ ያለው ጥንታዊ፣ከአንድ አለት የተፈለፈለ፣ አለቱም በቀላሉ የሚፈረካከስና ውስብስብ አርክቴክቸራል አሻራ ያረፈበት ትልቅ የአብያተ ክርስቲያናት ቅርስ ነው፡፡ እንግዲህ ቅርሱ ከእድሜውም ባሻገር በዝናብና በፀሐይ የተለያዩ ጉዳቶች ደርሶበታል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት የተደረጉ የጥገና ስራዎች ለምሳሌ፡- ጥላው (ሼዱ) ተፅዕኖ አሳድሮበታል የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ፡፡
እርስዎ  ቦታው ድረስ ሄደው ችግሩን  አይተውታል?
ኦው… በጣም ብዙ ጊዜ! በነገራችን ላይ እዚህ መስሪያ ቤት እንደተመደብኩ መጀመሪያ የሄድኩትም ላሊበላ ነው፡፡ ከስጋቱ አኳያ አንድ አጥኚ ቡድን አቋቁመን፣ ጥናት አካሂዶ ውጤቱን ሰጥቶናል፡፡ የጥናቱ ውጤት የሚያሳየውም ችግሩ አስጊ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ችግሩን ለመቅረፍ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በርካታ ሥራዎችን እየሰሩ ነው፡፡  
ለምሳሌ ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ---?
አንደኛ ከዩኔስኮና ይህንን ሼድ ከሰራው ኩባንያ ጋር ተገናኝተን በመነጋገር፣ባለፉት ሶስት አራት ቀናት አንድ ቡድን መጥቶ ላሊበላን እያየው ይገኛል፡፡ አሁን ነገ (ሰኞ ነው ቃለ ምልልሱ የተደረገው) ከእኛ ጋር ስብሰባ አላቸው። እነዚህ ባለሙያዎች ችግሩ በትክክል ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ይነግሩናል፡፡ የባለሙያዎች ቡድኑ ከጣሊያንና ከዩኔስኮ የተውጣጡ ናቸው። እነሱ የሚሉትን እንሰማለን፡፡ የእኛ ባለሙያዎችም ያጠኑት አለ። እነሱም እይታቸውን ይገልፁልናል፡፡ ዞሮ ዞሮ እኛ ሪስክ አንወስድም፤ትንሽም ቢሆን የሚያሰጋን ነገር ካለው እንደ መንግስት ሼዱ እንዲነሳ ነው የምንፈልገው።
ላሊበላን ለመታደግ ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡ ይሄን ገንዘብ ከየት ለማግኘት ነው ያቀዳችሁት?
እንዳልሺው እጅግ ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ምን ያህል ነው ለሚለው የተለያየ ግምት አለ፤ ግን ገና ዝርዝሩ አልተሰራም፡፡ ዞሮ ዞሮ በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ወይም በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አቅምና በጀት የሚሰራ አይደለም፡፡ ሀገራዊ ንቅናቄ ተፈጥሮ፣ ሀብት መሰብሰብ አለበት። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጋር ተነጋግረናል። በተለይ ከምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ጋር ረጅም ውይይት አድርገን፣ ጥናቱን ያቀረብንላቸው ሲሆን አንድ አገራዊ ኮሚቴ እንደሚቋቋምና የላሊበላ ጉዳይ ብሔራዊ አጀንዳ እንደሚሆን ተወስኗል፡፡ በተለይ ከቱሪዝም ዘርፉ ጥቅም የሚያገኙ አካላት በሙሉ፡- ቤተ ክህነት፣ ቱር ኦፕሬተሮች፣ አየር መንገድና ሆቴሎች እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲረባረቡና የበኩላቸውን እንዲወጡ፣ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታትም ተባብረው የሚያስፈልገውን ሀብት በማሰባሰብ ስጋቱ እንዲቀረፍ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰናል። በቅርቡ ይህንን ብሔራዊ አጀንዳ አድርገን ለህዝቡ እናስተዋውቃለን፡፡
የጣናም ጉዳይ ከላሊበላ በባሰ መልኩ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ እንደሚታወቀው ዩኒቨርሲቲዎቻችን ምርምር እያካሄዱ ነው፡፡ እንዴት አድርገን መጤውን አረም እናስወግዳለን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስና በእውቀት ላይ የተመሰረተ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው፡፡
የውጭ አገራት የወሰዱብንን በርካታ ቅርሶች ለማስመለስ እየጣርን ነው፡፡ ነገር ግን  አፄ ቴዎድሮስ ከተወለዱበት እስከ ተሰዉበት ባሉት ታሪካዊ ቦታዎች ላይ የሚገኙት ቅርሶች ሙዚየም የላቸውም፡፡ አጼው በነገሱባት የዳናሞራዋ ደራስጌ ማርያም እጅግ ውድ ታሪካዊ ቅርሶች አልባሌ ቦታ ላይ ነው የሚገኙት፡፡ እዚህ ያሉት ቅርሶች በአግባቡ የሚቀመጡበት ሳያገኙ  ከውጭ የሚመጡትን የት ልናደርጋቸው ነው---?
እርግጥ ነው እስካሁን ብዙ ሙዚየም አልገነባንም። በርካታ ሙዚየሞች ያስፈልጉናል፡፡ እጅግ በርካታ ልናሳየው የምንችለው ሀብት አለ፡፡ ስለዚህ ሙዚየሞች በብዛት መገንባት አለባቸው። ሙዚየም የሚገነባው ደግሞ በመንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሙዚየም መገንባት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ኤትኖግራፊክ ሙዚየም አለው፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ መንግሥት ሙዚየሞችን መገንባት አለባቸው። የክልልም የፌደራልም ተቋማት ሙዚየም መገንባት ይገባቸዋል፡፡
ሆኖም  የውጭዎቹ ቅርሶች ይመለሱልን እንጂ የምናስቀምጥበት አናጣም፡፡ በነገራችን ላይ በየቦታው የተጀማመሩ የሙዚየም ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የመቅደላ አምባ ሙዚየም በሀሳብ ደረጃ ቀርቧል፤ ያንን ተረባርቦ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ እንግሊዞችም እንደ ካሣ፣ ይህን ግንባታ ማገዝ አለባቸው፡፡ በግንባታ ብቻም ሳይሆን ባለሙያን በማሰልጠን ሊያግዙን ይገባል። እንግሊዞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የእኛን ቅርሶች ወስደው ሲጠቀሙ የነበሩም ሆነ እየተጠቀሙ ያሉ አገራት ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ እኛም ትኩረት ሰጥተን በጀት መድበን፣ ከህዝቡም አሰባስበን፣ በርካታ ሙዚየሞችን መገንባት አለብን፡፡ ይህ እንዳልኩት የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡  

Read 2622 times