Saturday, 21 April 2018 12:12

“አዲሱ የጠ/ሚኒስትር ካቢኔ ከኢህአዴግ አጥር አልወጣም” - ተቃዋሚዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ሰሞኑን ያደረጉት የካቢኔ ሹመት ሙያና ሙያተኞችን ያገናኘ አይደለም ያሉት ተቃዋሚዎች፤ ሹመቱ የሚያሳየው ኢህአዴግ አሁንም ከራሱ አጥር መውጣት እንዳልቻለ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር አብይ ከትናንት በስቲያ ለአዲስም ሆነ ለነባር ሚኒስትሮቻቸው ጠበቅ ያለ የሥራ መመሪያ መስጠታቸው የሚታወቅ ሲሆን ተቃዋሚዎች በበኩላቸው፤ የካቢኔ አደረጃጀቱም ሆነ መመሪያው አዲስ ነገር የለውም ብለዋል፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ተመስገን ዘውዴ በሰጡት አስተያየት፤ ውጤት አልባ ሆነው ህዝብን ለምሬት ሲዳርጉ በነበሩ እንደመብራት ኃይል፣ ውሃ ልማትና ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ተቋማት ላይ ለውጥ እንደሚደረግ ጠብቀው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ከተደረገው የካቢኔ ሽግሽግ አንፃር በነዚህ ዘርፎች ላይ ለውጥ ለማምጣት እንዳልታሰበ ተገንዝቤአለሁ ብለዋል፡፡
እነዚህን በአገልግሎት አሰጣጣቸው የተዳከሙና የህብረተሰቡ የምሬት ምንጭ የሆኑት ተቋማትን በከፊልም ቢሆን ወደ ግል ይዞታነት አሸጋግሮ፣ ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ - አቶ ተመስገን፡፡
የመከላከያ ሚኒስትርና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ግለሰቦችም ከቦታዎቹ ወሳኝነት አንፃር የሚመጥን የትምሀርት ዝግጅትና ልምድ እንደሌላቸው የጠቆሙት አቶ ተመስገን፤ በተመሳሳይ ለግብርና ሚኒስትርነት የተሾሙትም ቦታው ከሚፈልገው የትምህርት ዝግጅት ጋር የተጣጣሙ አይደሉም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ለሆነው ግብርና የሚሾም ሰው፣ ለስራው በቂ እውቀትና ልምድ ያለው ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ ተመስገን፣ ይሄ የፖለቲካ ምደባ እንጂ እውቀትን መሰረት ያደረገ አይደለም ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ፕ/ር አህመድ ዘካሪያም የአቶ ተመስገንን ሃሳብ ይጋራሉ፡፡ በተለይ የግብርና እና እንስሳት ሃብት ሚኒስትርነት ቦታ ላይ የተመደቡት ሚኒስትር ከሙያው ጋር የተገናኙ አይደሉም ብለዋል፡፡ የፖለቲካ ሹመኛ ቢሆኑም እንኳን ለሙያው የቀረቡ ቢሆን፣ በጉዳዩ ላይ ከባለሙያዎች የሚቀርብን ምክርም ሆነ አቅጣጫ አዳምጦ ለመስራት አጋዥ ነው ያሉት ፕ/ር አህመድ፤ ግብርና ከፖለቲካ በላይ የሆነ፣ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው ይላሉ፡፡
የካቢኔ አሿሿም ሁኔታ ሰፊ ሽግግርን የሚጠይቅ ነው ያሉት ምሁሩ፤ ቡድንንና ፓርቲን መሰረት አድርጎ የሚካሄድ የካቢኔ ሽግሽግ፣ የፖለቲካ ሁኔታውን ያሻሽላል የሚል እምነት እንደሌላቸው በመግለፅ፤ ከዚህ አዙሪት የምንወጣበት መንገድ መፈለግ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው ምሁሩ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤ እነዚህ ሽግሽግ የተደረገባቸው የሚኒስትርነት ቦታዎች፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲና የስትራቴጂ እቅድ የሚያወጡ እንደመሆናቸው፣ የሚጠበቀውም የፖለቲካ ሹመት እንጂ ሙያን ማዕከል ያደረገ አይደለም ሲሉ የሁለቱን አስተያየት ሰጪዎች ሃሳብ ይቃወማሉ፡፡
ወሳኙ ነገር፣ የገበያ ተኮሩን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በትክክል ተግባራዊ ማድረግ ነው ያሉት ምሁሩ፤ የሚኒስትር ቦታዎች ላይ ብዙም ለውጥ አይጠበቅም ብለዋል፡፡ “ዋናው የመንግስት ስራ የሚሰራው ከሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ይልቅ በክልሎች ነው” የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ “የሚጠቅመው ክልሎችን ማጠናከሩ ነው” ይላሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነት ለማጠናከር መትጋት ያለባቸው እንደ አየር መንገድ፣ መብራት ኃይል የመሳሰሉትን ተቋማት ነው፤ ለግሉ ዘርፍም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል - ምሁሩ፡፡
በሙስና ጉዳይ አይነኩም የሚባሉትን ደፍሮ በመንካት፣ በተለይ በመንግስት ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ስራ ላይ ያሉትን መፈተሽ ይገባል ያሉት ዶክተሩ፤ ሙስናን ለመዋጋት ሚዲያዎችን ነፃ ማድረግም አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡
ሚዲያዎች በመንግስት ተደግፈው፣ በፋይናንስ ከጠነከሩና ነፃነታቸው ከተጠበቀ፣ ሙስናን በምርመራ ጋዜጠኝነት የማጋለጥ ሚናቸውን ሊወጡ ይችላሉ ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ የንግዱ ማህበረሰብም ተጠናክሮ ሙሰኞችን እንዲያጋልጥ ከተደረገ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
“ገንዘብ አባክነዋል የሚባሉ የመንግሥት ባለስልጣናትን እስከዛሬ ማን ደፍሮ ነካቸው?” ሲሉ የጠየቁት ምሁሩ፤ “በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገ ምርመራ እንኳን ስለመኖሩ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም” ብለዋል፡፡ እነዚህን ቦታዎች እስከ ዛሬ መንግስት ለምን መንካት እንዳቃተው አላውቅም ሲሉም ይጠይቃሉ - ምሁሩ፡፡
አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ኢህአዴግ ከሳጥኑ ወጥቶ ካልተንቀሳቀሰ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሰቡት ለውጥ ውጤት ማምጣቱ አጠያያቂ ነው ብለዋል፡፡
ሀገሪቷን ወደ ብሔራዊ መግባባት እንወስዳለን የሚሉ ከሆነ፣ ተቃዋሚዎችን ባያካትቱ እንኳ ምሁራንን በግብርና ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴርና በመሳሰሉት ተቋማት ውስጥ ቢያካትቱ ጠቃሚ ነበር ያሉት ፖለቲከኛው፤ በሙስና ጉዳይ ምን ያህል ሊሰሩ እንደሚችሉ በሂደት የሚታይ ይሆናል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔያቸውን ሲያቀርቡ “ብሔር” በሚለው ፋንታ የትውልድ ቦታን በመጥቀስ የሰለጠነ ቋንቋ ተጠቅመዋል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ ይህም ምናልባት ኢህአዴግ ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመለወጥ ያቀደውን ወደ መፈፀሙ መቃረቡን አመላካች ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
በሰሞኑ የሚኒስትሮች አሿሿም ኢህአዴግ የህዝቡን ሳይሆን የራሱን ጥያቄ ነው የመለሰው ያሉት ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ የሸዋስ አሰፋ ናቸው። “ይሄም የሚያሳየው አሁንም ኢህአዴግ በሙሉ ልቡ ለለውጥ አለመነሳቱን አመላካች ነው” ብለዋል - አቶ የሸዋስ፡፡  

Read 6249 times