Sunday, 29 April 2018 00:00

የ21ኛው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ራሽያ በ21 ሁኔታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

በ21ኛው ዓለም ዋንጫ በ8 ምድቦች በተደለደሉት 32 ብሔራዊ ቡድኖች መካከል 48 ጨዋታዎች  እንደሚደረጉ ይታወቃል፡፡
በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) እና ብሄራዊ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ  ቢያንስ   15 ግጥሚያዎችን  በቀጥታ በየስታድዬሞቹ  ተገኝቼ መከታተል እንደምችል አስታውቀውኛል።  በስፖርት አድማስ በቀጥታ ከስፍራው ሽፋን የሚያገኙትና ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው 15 የምድብ ጨዋታዎች በራሽያ 9 የተለያዩ ከተሞች በሚገኙ 10 ስታድዬሞች የሚስተናገዱ ናቸው፡፡ 21ኛው የዓለም ዋንጫ 47 ቀናት የሚቀሩት ሲሆን @ ከዚህ በታች  የቀረቡት  የአዘጋጇን ራሽያ፤ አስተናጋጅ ከተሞች እና ስታድዬሞቹን የሚያስተዋውቁ 21 ሁኔታዎች ናቸው፡፡
**************
1. የዓለም ዋንጫውን በ12 ስታድዬሞች የሚያስተናግዱት 11 የራሽያ ከተሞች ሲሆኑ እነሱም የመክፈቻ እና የዋንጫ ጨዋታዎች የሚካሄዱባትን ሞስኮን ጨምሮ፤ ሴንት ፒተርስበርግ፤ ኤካተሪንበርግ፤ ካዛን፤ ሳማራ፤ ቮልጎጋርድ፤ ኒዛኒ ኖቮግሮድ፤ ሳርናሳክ፤ ሮስቶቭ ኦን ዶን፤ ካሊንኢንግራድና ሶቺ ናቸው፡፡ በእነዚህ 11 ከተሞች ከ25 ሚሊዮን በላይ ራሽያውያን ይኖራሉ፡፡
**************
2. የዓለም ዋንጫው 12 ስታድዬሞች በድምሩ ከ550ሺ በላይ ተመልካቾችን ያስተናግዳሉ፡፡ ከምድብ ጨዋታው እስከ ዋንጫው ድረስ 12ቱ ስታድዬሞች 65 ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ሲሆን በአማካይ የሚይዙት የተመልካች ብዛት 45ሺ ይሆናል፡፡በተመልካች ብዛት ቀዳሚው 81ሺ የሚያስተናግደው ሉዝሂንኪ ስታድዬም ሲሆን  የመጨረሻው ደግሞ 35 212 ተመልካች የሚይዘው የካሊኒንግራድ ስታድዬም ነው፡፡ 12ቱም  ከዓለም ዋንጫ በኋላ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሰጡ የታቀደ ሲሆን 3 ስታድዬሞች በውድድሩ ማግስት የሚያስተናግዱትን  የተመልካች ብዛት ከ45ሺ ወደ 30ሺ ይቀንሳሉ፡፡
**************
3. 96 የስልጠና የልምምድ ማዕከሎች በአዲስ መልክ የተገነቡ ሲሆን ከዓለም ዋንጫው በኋላ ለ16ሺ ታዳጊዎች አገልግሎት እንዲሰጡ የታሰቡ ናቸው፡፡
**************
4. በአጠቃላይ ዓለም ዋጫው ከ100ሺ በላይ የስራ እድሎችን ፈጥሯል፡፡ በተለይ በ10 ስታድዬሞች ግንባታ እና እድሳት 13ሺ የራሽያ ዜጎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
**************
5. ሉዝንሂኪ  ስታድዬም የመክፈቻና የዋንጫ ጨዋታዎችን ጨምሮ 7 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን በሞስኮ ከተማ የሚገኝ ነው። በ2013 እኤአ ላይ 81ሺ ተመልካች እንዲያተስናግድ ተደርጎ ታድሷል፡፡ ሌላው በሞስኮ ከተማ የሚገኘው ስታድዬም የራሽያ ፕሪሚዬር ሊግ ተሳታፊ የሆነው የስፓርታክ ሞስኮ ክለብ ሜዳ ሲሆን 4 የምድብ ጨዋታዎችና 1 የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ እንደሚካሄድበት ይጠበቃል፡፡
**************
6. በግንባታው ከ10 ዓመታት በላይ የወሰደው የሴንትፒተርስበርግ ከተማው ስታድዬም 1 የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ እና 6 የምድብ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ሴንትፒተርስበርግ የታዋቂው የራሽያ ክለብ ዜኒት ፒተርስበርግ መገኛ  ከተማ ስትሆን በ1703 እኤአ ላይ በራሽያው ንጉስ ታላቁ ፒተር የተመሰረተችና የንጉሳዊ ስርዓቱ መዲና የነበረች ናት፡፡ በሶቪዬት ህብረት ዘመን ይህች ከተማ ሌኒግራድ ተብላ ትጠራ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የራሽያ ባህላዊ እና ኪነጥበብ መዲና ናት፡፡
**************
7. በካዛን ከተማ የሚገኘው ስታድዬም በ2013 እኤአ ላይ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን በዓለም የዩኒቨርስቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል የመክፈቻ እና የመዝጊያ ውድድሮችን አስተናግዷል፡፡ ስታድዬም 1 የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ እና 4 የምድብ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል፡፡ ከሞስኮ በስተምስራቅ 700 ኪሜ ርቆ የሚገኘው ይህ ስታድዬም በ2015 የዓለም አኩዋቲክ ሻምፒዮናን በ2017 ደግሞ የፊፋን ኮንፌደሬሽን ካፕን አስተናግዷል፡፡
**************
8. በሶቺ ከተማ የክረምት ኦሎምፒክ መክፈቻ እና መዝጊያ ስነስርዓቶችን በልዩ መስተንግዶ በማከናወን የተደነቀው ፊቸት ስታድዬም ይገኛል፡፡ ዓለም ዋንጫውን እንዲያስተናግድ ወደ የእግር ኳስ ሜዳ የተቀየረ ሲሆን 1 የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ እና 5 የምድብ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል፡፡ የሶቺ ከተማ በባህርዳርቻ ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ ጥቁር ባህር የሚያወስናት እና ከግዙፉ ካውከስ ተራራ ግርጌ የተመሰረተች ናት፡፡
**************
9. በኒሂዚኒ ኖቮጎሮድ የሚገኘው ስታድዬም ለዓለም ዋንጫው አዲስ የተገነባ ነው፡፡ 45 ሺ ተመልካች የሚይዝ ሲሆን 1 የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ እና 5 የምድብ ጨዋታዎችን ያስተናግዳል፡፡ ኒሂዚኒ ኖቮጎሮድ ከሞስኮ በስተምስራቅ በ400 ኪሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ከተማ ሲሆን ሁለቱ የራሽያ ታላላቅ ወንዞች ቮልጋ እና ኦኮ የሚገኙበት እና ከራሽያ ከተሞች በህዝብ ብዛት 5ኛ ደረጃ ላይ የሚጠቀስ  ነው፡፡
**************
10. በካሊኒንግራድ የሚገኘው ስታድዬም ከሁሉም ስታድዬሞች ግንባታው ዘግይቶ ያለቀ አዲስ ስታድዬም ነው፡፡ 35ሺ ተመልካች የሚይዘው ይህ ስታድዬም 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን በከተማው እምብርት ላይ በሚገኝ ደሴት ላይ የተገነባ ነው፡፡
**************
11. በቮልጎጋርድ የሚገኘው ስታድዬም 45ሺ ተመልካች የሚይዝ ሲሆን የተገነባው በ2ኛው የዓለም ጦርነት የጦርነት አውድማ በሆነ ስፍራ ላይ ነው። 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግደው ይህ ስታድዬም የሚገኝበት የቮልጎጋርድ ከተማ በቀድሞ ስሙ ስታሊንግራድ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ ‹‹ዘ ማዘርላንድ ኮልስ›› ተብሎ የሚጠራው የዓለማችን ግዙፍ ሃውልት ይገኝበታል፡፡
**************
12. ታዋቂው የራሽያ ወንዝ ቮልጋ የሚዋሰነው የሮስቶቭ ስታድዬም 45ሺ ተመልካች የሚያስተናግድ ሲሆን በዓለም ዋንጫው አንድ የጥሎ ማለፍ ጨዋታና 4 የምድብ ጨዋታዎች ይካሄዱበታል፡፡  1 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርበት የሮስቶቭ ኦን ዶን ከተማ የራሽያ የትራንስፖርት መናሐርያ  ሲሆን ከዩክሬን ጋር በሚያዋስነው ድንበር አቅራቢያ ይገኛል፡፡
**************
13. 35ሺ ተመልካች የሚይዘው የኢካተሪናበርግ ስታድዬም በ1950 እኤአ ላይ የተገነባ እና ለዓለም ዋንጫ በልዩ እድሳት የተዘጋጀ ሲሆን 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ይሆናል፡፡ ኢካተሪናበርግ ራሽያን ከአውሮፓ እና ከኤሽያ ጋር በሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎች እና አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የተመሰረተች ከተማ ናት፡፡
**************
14. ሳማራ ከተማ ውስጥ የሚገኘው ስታድዬም 1 የጥሎ ማለፍ፤ 1 የሩብ ፍፃሜና 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ነው፡፡ በቮልጋ ወንዝ ላይ የተመሰረተው ይህ ከተማ ከሞስኮ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 850 ኪሜ ላይ የሚገኝ ሲሆን የራሽያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀስበት ነው፡፡
**************
15. የሳርናሳክ ከተማ ከሞስኮ በደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ 500 ኪሜ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዓለም ዋንጫው 4 የምድብ ጨዋታዎችን የሚያስተናግድው ስታድዬም እና አዲስ የተገነባ ነው፡፡
**************
16. ዛቢቫካ ይህ የተኩላ ዝርያ የዓለም ዋንጫ የገድ ምልክት የሆነ እንስሳ ነው፡፡ የሰራችው ኤካተሪና ቦችሮቫ የተባለች የስነህንፃ ዲዛይን ተማሪ ስትሆን በድረገፅ የተካሄደ ምርጫን አሸንፋበታለች፡፡
**************
17. የዓለም ዋንጫውን እንግዶች ለማስተናበር የሚሰማሩት በጎ ፍቃደኞች በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ናቸው፡፡ 16 የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰሩ ማዕከሎች የተገነቡ ሲሆን በዓለም ዋንጫው እንግዶች የሚሆኑ ከ1 ሚሊዮን በላይ ስፖርት አፍቃሪዎችን ለማስተናገድ የሚሰማሩት ከ25ሺ በላይ በጎ ፈቃደኞች ናቸው፡፡
**************
18. ለዓለም ዋንጫው 26 የትራንስፖርት መሰረተልማቶች ተገንብተዋል፡፡  11 የአየር ማረፊያ ጣቢያዎች አዲስና በእድሳት ተገንብተዋል፡፡ አዳዲስ የአየር ማረፊያዎች በሴንትፒተርስበርግ ፤ በኒዚሂ ኖቭጎሮድ፤ በሳናራ፤ ሳርሳንካ እና ሞስኮ ከተሞች ተሰርተዋል፡፡ በሮስቶቭ ኦን አዲስ የአየር ማረፊያ ጣቢያ ሙለሙሉ ተሰርቷል፡፡
**************
19. 3 አዳዲስ የሜትሮ ባቡር ጣቢያዎች፤ 12 አውራ ጎዳናዎች እና ማሰለጫ መንገዶች ተዘርግተዋል፡፡ በአዲስ መልክ የተገነቡ እና ሙሉ እድሳት የተደረገላቸው 13 ሆስፒታሎች፤ 29 የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት፤ 27 አዳዲስ ሆቴሎች፤ 12 የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ ጣቢያዎች ተሰርተዋል፡፡
**************
20. 800 ሄክታር የህዝብ መናፈሻዎች እና ፓርኮች ተዘጋጅተዋል፡፡

Read 3236 times