Saturday, 28 April 2018 10:05

የሰሜን ኮርያ ግዙፉ የኒውክሌር ሙከራ ጣቢያ በከፋ ሁኔታ መጎዳቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በሰሜን ኮርያ እጅግ ግዙፉ እንደሆነ የሚነገርለትና ላለፉት 12  አመታት በአገልግሎት ላይ የቆየው የኒውክሌር ሙከራ ጣቢያ፤ አብዛኛው ክፍል በተደጋጋሚ ፍንዳታዎች በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ መደርመሱና አገልግሎት የማይሰጥበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተዘግቧል፡፡
ከአቅሙ በላይ በሆነ መልኩ ተደጋጋሚና በርካታ የኒውክሌር ሙከራ ፍንዳታዎችን ያስተናገደው ግዙፉ የሰሜን ኮርያ የሙከራ ጣቢያ፣ በከፋ ሁኔታ የተጎዳ ሲሆን ምናልባትም ቀጣይ ሙከራዎች ከተደረጉበት የኒውክሌር ጨረሮችን ሊያሾልክና አደጋ ሊያደርስ እንደሚችል አረጋግጠናል ሲሉ ቻይናውያን ተመራማሪዎች ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረጉት የጥናት ሪፖርት ማስታወቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ፑንጌሪ በተባለው የአገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ ተራራማ ስፍራ ላይ የሚገኘው ግዙፉ የኒውክሌር ሙከራ ጣቢያ፣ ፕሬዚዳንት ኪም ጁንግ ኡን እ.ኤ.አ ከ2006 ወዲህ ያደረጓቸውን ስድስት የኒውክሌር ሙከራዎች በሙሉ ማስተናገዱን ያስታወሰው ዘገባው፤ የቻይና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችም ጣቢያው በመደርመሱ ሳቢያ ከአሁን በኋላ አገልግሎት ላይሰጥ እንደሚችል አረጋግጠናል ማለታቸውን አመልክቷል፡፡
የኒውክሌር ሙከራ ጣቢያው በሃይለኛ ፍንዳታዎችና በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጦች በመመታቱ ክፉኛ መጎዳቱን የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች በጥናት ማረጋገጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ይህንን ግዙፍ የኒውክሌር ሙከራ ጣቢያ እንደሚዘጉ፣ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችንና የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራዎችን እንደሚያስቆሙ ከሰሞኑ ማስታወቃቸውንም አስታውሷል፡፡

Read 1444 times