Sunday, 29 April 2018 00:00

ክብርና ሞገሱን የተቀማው፤ የአድዋው ...

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ በኢጣሊያ በተሰነዘረባት ጥቃት የግዛት አንድነቷን ለመጠበቅና ነጻነቷን ለማስከበር ሶስት ጦርነቶች ለመዋጋት ተገድዳለች፡፡
ከአውሮፓ አገሮች ሁሉ ግዛትን በቅኝ በማስፋፋት ተግባር ወደ ኋላ የቀሩት ጣሊያኖች፤ እንደ አባ ማሲያስና ጁሴፔ ሰፖቶ ያሉትን ሰዎች  ‹‹በወንጌላዊነት›› ሽፋን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የስለላ ሥራ እንዲሠሩ አደረጉ። ከአሰብና ከራሂታ ሡልጣኖች፣ ሩቢኒቶ በተባለ ኩባንያ ስም ሰባት ኪሎ ሜትር መሬት ገዙ፡፡ ኩባንያው መሬቱን ለኢጣሊያ መንግሥት ባስተለለፈ ጊዜ ሰንደቃላማቸውን ለመትከል፣ ወታደር ለማስፈር ቻሉ። የአሰብ የባሕር በር በኢጣሊያ  በቅኝ ተያዘ፡፡
በእንግሊዞች አደራዳሪነት (የሒዊት ስምምነት) ኢትዮጵያ በደርቡሾች የተከበቡትን ግብጾች  ተዋግታ ነጻ አወጣች፡፡ እንግሊዞች ስምምነቱንና  የገቡትን ቃል  አጥፈው፣ ኢትዮጵያዊያን ደም የተቃቡበትን መሬት ምጽዋን በ1876  በጣሊያኖች እንዲያዝ አደረጉ፡፡ መስፋፋታቸው ከአሰብ ምጽዋ ቢደርስም፣ ጣሊያኖች በዚህ አልቆሙም፡፡ ወደ ደጋው አገር ዘልቀው ሰሐጢ ላይ መሸጉ፡፡
ራስ አሉላ ከከሰላ ጦርነት እንደተመለሱ፣ ለጄኔራል ካርሎ ዢኒ ጦሩን እንዲያነሳ፣ የንግድ እንቅስቃሴው በጊንዳ በኩል እንዲሆን ደብዳቤ ጻፉለት፤ መልሱ “አንለቅም አይሆንም” የሚል ሆነ፡፡ ራስ አሉላ አልፈው ዶጋሊ ላይ ከምጽዋ እንዳይገናኝ አድርገው ሲቆርጡት ከምሽጉ ወጥቶ ለመዋጋት ተገደደ፡፡ የጦሩ አዝማች፣ አምስት መቶ ነጭ ወታደሮችና ሶስት መቶ ያገር ተወላጆች (ባንዳዎች) ተገደሉ፡፡ ድሉ ለራስ አሉላና ለሠራዊታቸው ሆነ። በዚህ ጦርነት ሁለት ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸው አይዘነጋም፡፡
ይህ ድል ኢትዮጵያዊያንን ከሌላ ጥቃት አልታደጋቸውም፡፡ ሽንፈቱ ጣሊያኖችን ወደ ኋላ እንዲመለሱ ወይም ባሉበት እንዲቆሙ አላደረጋቸውም፡፡
አጼ ዮሐንስ ጣሊያኖችን ለመውጋት እየተዘጋጁ እያለ ጎንደር በደርቡሾች መቀጠሉን ስለሰሙ  ወደ ኋላ ተመለሱ፤ በዚያውም ወደ መተማ ዘመቱ። የንጉሡ በጦርነቱ ላይ መሞት፣ የአገር ያለጠባቂ፣ ያለተከላካይ  መቅረት ለጣሊያኖች ምቹ ጊዜ ሆነ። በጊንዳ በኩል ወደ አሥመራ፣ በላይት በኩል ወደ  ከረን ዘለቁ፡፡ ከአጼ ምኒልክ ጋር ባደረጉት የውጫሌ ውል በአንቀጽ  3፣ ይህን በወረራ የያዙትን መሬት እንደ ባለ መብት ተቆጥረው፣ ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር የሚካለሉበት መሬት አደረጉት፡፡
ጣሊያኖች ድርድር የሚገቡት፣ ውል የሚፈርሙት፣ ለጊዜው ሌላውን ለማዘናጋት እንጂ ለዘለቄታው ባለመሆኑ በውጫሌ ውል ላይ ድንበር ተደርገው የተቀመጡትን ቦታዎች ጥሰው አሁንም በቦታ መያዙ ገፉ፡፡ ኳአቲትና ሰናፌ ላይ ከራስ መንገሻ ጦር ጋር ተዋግተው አሸነፉ፡፡ ሁኔታው ያላማራቸው ራስ መንገሻ፤ ዮሐንስ በመኳንንቱ ምክር ወደ ራስ ወሌ ግዛት እንዲያፈገፍጉ ሲደረግ፣ የቀረው ጦር መስከረም 29ቀን 1888 ደብረ ኃይል ላይ ከጣሊያኖች ጋር ገጠመ፡፡ አሁንም  ጣሊያኖች አሸነፉ፡፡ የልብ ልብ ስለተሰማቸው አዴግራትንና መቀሌን ከያዙ በኋላ አምባላጌ ላይ መሸጉ፡፡
አጼ ምኒልክ ባንድ ወገን ለጦርነት እየተዘጋጁ፤ በሌላ ወገን ከጣሊያን የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል በከብት አንድአንድ ብር ግብር ጥለው፤ ለዋስትና የተያዘው የሐረር ጉምሩክ እንዲለቀቅ አደረጉ። የክተት አዋጅ አስነግረው ጥቅምት 2ቀን 1888 ከአዲስ አበባ ለዘመቻ ተነሱ፡፡
በራስ ሚካኤል፣ በራስ መኮንን፣ በራስ መንገሻ፣ በራስ ወሌና በሌሎችም የሚመራው የኢትዮጵያ ሠራዊት አምባላጌ ላይ የመሸገውን የጄኔራል ቶሌዜን ጦር እንዲወጋ ምኒልክ አዘዙ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምሽጉ ከመሰበሩ በላይ አዝማቹም በጦርነቱ ላይ ተገደለ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ድል አደረጉ፡፡
የመቀሌውን የጣሊያኖች ምሽግ ማስለቀቅ ከአምባላጌው በላይ የከበደ ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ እቴጌ ጣይቱ  ባመጡት መላ፣ ምሽግ ውስጥ የሚገኙ ጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን ውኃ ምንጩን በመያዝ፣ በውኃ ጥም እንዲቀጡ አደረጉ። አዛዡ ጄኔራል ጋሊያኖ፣ በእርቅ ምሽጉን ለቅቆ ወጣ። እዚህ ላይ አስገራሚው ነገር አጼ ምኒልክ መልሶ እንደሚወጋቸው እያወቁ፣ ከእነሙሉ ትጥቁ እንዲሔድ መፍቀዳቸውና  ለዕቃ መጓጓዣ የሚሆን የጭነት እንስሳት መስጠታቸው ነው፡፡
የአድዋ ጦርነት የካቲት 23ቀን 1888 ንጋት ላይ ተጀመረ፡፡ በመነኩሲቶ በራስ መኮንንና በፊታውራሪ ገበየሁ ግንባር የጠላትን ጦር መጫን በመረዳት፣ የአልበርቶኒን ጦር መውጋት ተያዘ፡፡ ራስ መኮንን ቢቆስሉም፣ ፊታወራሪ ገበየሁ ቢሞቱም፣ የእነራስ መንገሻ ጦር የጦሩን አዛዥ ጄኔራል አልበርቶኒን ማረከው፡፡ የንጉሥ ሚካኤል የራስ ወሌ ጦር እየሸሸ እየተዋጋ የነበረውን የጄኔራል አርሞንዴን ጦር በመውጋትና ጄኔራሉን በመግደል አሸናፊነቱን አጠናከረ፡፡ በሌሎችም የውጊያ ግንባሮች የነበረው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡
አጼ ምኒልክ  ብትንትኑን የወጣውን የጣሊያንን ጦር እያባረረ፣ እየማረከ፣ ግዳይ እየጣለ ያለውን ሠራዊታቸውን ተከትለው ሲሄዱ፣ እትጌ ጣይቱ ጦራቸውን አሰልፈው ከመዋጋታቸውም  በላይ፣ ለደከመው ውኃና ምግብ በመስጠት፣ ‹‹ጦሩ ሲወዛወዝ››፣ ንጉሥህን ጥለህ ወዴት ትመለሳለህ? በማለት በማደፋፈር ጦርነቱ እንዲጋጋል አደረጉ፡፡
በአራት ጄኔራል የተመራው የጣሊያን ጦር አንዱን በምርኮ፣ ሁለቱን በሞት እያጣ፣ ባለበት ጊዜ ነገሩ በቅጡ ሳይለይ፣ የጣሊያን ጦር ዋና አዛዥ ጄኔራል በራቲዬሪ፣ ጄኔራል ኤሊኖን አስከትሎ  በአዲ ቀይህ በኩል በመሸሽ ነፍሱን ለማትረፍ ቻለ። የኢትዮጵያ ሠራዊት እስከ ለሊቱ አምስት ሰአት ድረስ እያሰደደ ምርኮውን ሰበሰበ። ያለ መሪ የቀረው የጣሊያን ጦርም  በያቅጣጫው ሸሸ፡፡ ድል ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያዊያን ሆነ -ታሪካዊው የአድዋ ድል!
ዛሬ ግጥም የሚደረደርለት፣ ዜማ የሚንቆረቆርለት፣ ዩኒቨርሲቲ የሚቋቋምለትና በየአጋጣሚው የኢትዮጵያ የአፍሪካና የጥቁር ሕዝብ ኩራት መሆኑ የሚነገርለት የአድዋ ድል ግን እጣው ከዶጋሊ የተለየ አልሆነም፡፡
ህዳር 14ቀን 1927 ኢጣሊያ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ገብታ ወለወል ላይ 250 የባንዳ ጦር አስፍራ ሰንደቅ አላማዋን ሰቀለች፤ የኢትዮጵያ ግዛት ተደፈረ። ጥቅምት 23፣ 24 እና 25 በየቀኑ ሃያ አይሮፕላን በማሰማራት፣ የደጃዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማያትን ምሽግ በቦምብ ደበደበች፡፡ እሳቸውና በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን አጡ፡፡ መንግሥት ችግሩን በዲፕሎማቲክ መንገድ ለመወጣት ያደረገው ጥረት በጣሊያን ፈቃደኝነት ጉድለት ሳይሳካ ቀረ፡፡
ጣሊያን መስከረም 21 ቀን 1928 በኢትዮጵያ ላይ በይፋ ጦርነት አውጃ፣ ከሸንበቆ እስከ ዛላንበሳ ያለውን አካባቢ በእግረኛ በታንክና ባይሮፕላን ደበደበች፡፡ ንጉሡ  በነጋው የክተት አዋጅ አወጁ፡፡ በነደጃዝማች ገብረ ሕይወት መሸሻ፣ በእነደጃአማች አባይ ካሣ የሚመራው የአካበቢው ጦር  የጠላትን ግሥገሴ መግታት አልቻለም፡፡ በተከታታይ አዴግራት፣ አድዋና መቀሌ ተያዙ፡፡ አድዋ ላይ በ1888 ጦርነት ለሞቱ ዘመዶቻቸው ያዘጋጁትን ሐውልት ተከሉ፡፡
ሕዳር 27ቀን 1928 ተንቤን ላይ በተከፈተው ጦርነት፤ በራስ ሙሉጌታ የተመራው የኢትዮጵያ ጦር፣ ከአራት ቀን ተጋድሎ በኋላ አሸነፈ፡፡ 60 መኮንኖች፣ 605 ነጮች ሲገድል ከእሱ ስምንት ሺ ሰው አለቀበት፡፡
በሽሬ ግንባር የዘመተው  በራስ እምሩ የሚመራው የጎጃምና የጎንደር ጦር ከፍተኛ ውጊያ ያደረገ ሲሆን ‹‹አድዋ ሊደገም ነው እንዴ›› የሚል ስጋት ከማሳደሩ በላይ ሞሶሎኒ ጀነራል ቦዶሊዮን ሽሮ፣ ግራዚያኒን ለመሾም እንዲያሰብ አድረጎታል፡፡ ጣሊያኖች የመርዝ ጋዝ መርጨት የጀመሩት በዚህ ግንባር ሲሆን እጅግ የተጎዳውም እሱ ነው፡፡ ራስ ከነበራቸው 25000 ጦር፣ የተረፋቸው 300 እንደነበር ይጠቀሳል፡፡
የመጨረሻው የመከላከል ጦርነት የተካሔደው መጋቢት 23 ቀን 1928 ማይጨው ላይ ነው፡፡ የራስ ሙሉጌታ ከጦር ሚኒስትርነት መሻርና የራስ ካሣ መሾም አንድ ችግር ነበር፡፡ የዘመቻው መሪ ራሳቸው ንጉሡ ናቸው፡፡ እስከ 11 ሰዓት ድረስ እንደ አንድ ወታደር መዋጋታቸውን የወለጋው ገበሬ፣ መቶ አለቃ ባዬ ወልደ ሥላሴ ባንድ ወቅት መስክረዋል፡፡
‹‹እኛ አበሾች ተማምለናል፤ ድል እናደርጋለን ካልሆነም እንሞታለን›› ብለው ቆርጠው የተነሱት ኢትዮጵያዊያን፤ እንደ ቃላቸው ሁሉ መራራ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ አምስት ያህል ምሽጎች አስለቅቀው በብረቱ እያጠቁ እያለ፣ ጠላት ተዳክሞ ‹‹አሁን የሚተኩሰው የቆሰለ ሠራዊታችን  ብቻ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ ሁላችንም እንሞታለን››  እያለ እየወተወተ እያለ፤ አድዋ ሊደገም ነው ተብሎ ሲጠበቅ እያለ ኢትዮጵያዊያን እጃቸው ሊገባ  የቀረበውን ድል የተነጠቁት፣ ከጠላት ወገን ተሰልፈው፣ የራሳቸውን ወገን ይወጉ በነበሩ ራያዎች መሆኑን “የአበሻ ጀብዱ” ጸሐፊ አዶልፍ ፓርለስክ ገልጧል፡፡
በጭንቅ በመከራ ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት ንጉሥ፣ በጉዳዩ ላይ ምክር ተደርጎበት በስደት ወደ እንግሊዝ አገር ሔዱ፡፡ መሔዳቸውን የማይቀበሉ ወገኖች፤ አገር ውስጥ የሚችሉትን አድርገው ሲያቅታቸው እንደ ቴዎድሮስ እራሳቸውን ቢገሉ ጥሩ ነበር ይላሉ፡፡ እኔ ደግሞ መሄዳቸው በጄ እንጂ ብዙ ያቄሙባቸው ስለነበሩ አንዱ እጃቸውን ይዞ ለጠላት ያስረክባቸው ነበር እላለሁ፡፡
የዛሬ ሳምንት ሰባ  ሰባተኛው የነጻነት ቀን ይከበራል፡፡ አርበኞች በዱር በገደሉ ተሰማርተው  መላዋን ኢትዮጵያን የጦር ሜዳ አድርገው የፈጸሙትን  ተጋድሎ፣ ሕዝብና አገር የተቀበለውን ፍዳ፣ ባንዳ የሕዝቡን መከራ በማብዛት የተጫወተውን ሚና መዘርዘሩ ብቻ ሳይሆን ማሰቡም ይከብዳል፡፡
በየጦርነቱ ግንባር ተሰልፈው ከተዋደቁት በብዙ መቶ ሺህ ከሚቆጠሩት አርበኞች ሌላ በየመንደሩ፣ በየጎጡ፣ በየገበያ ቦታው፣ በየአድባራቱ እናቶችና አባቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በዚህ ጦርነት አገር 850 ሺህ የሚደርሱ ዜጎችዋን አጥታለች፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቤተ ክርስቲያኖች ተቃጥለዋል፡፡ አገር በብዙ አይነት ተላላፊ በሽታ ይሁነኝ ተብሎ እንደትጠቃ ተደርጓል። ሚያዚያ 27 የነጻነት ቀን፣ ይህ ሁሉ የመከራ ጎርፍ እንዲገታ፣ እንደያበቃ ያደረገ ቀን ነው፡፡
በየአደባባዩ መመኪያ አድርገን ዛሬ  የምንጠቅሰው የአድዋ ድል፣ እንዳይሞት በማድረግ ነፍስ የዘራበትና የነፍስ አባቱ የሆነው  ሚያዝያ 27 የነጻነትና የድል ቀን  ነው፡፡ ለምን ይህ ቀን የሚገባውን ክብርና ሞገስ አጣ?
መልሱ፤ ሚያዝያ 27 የኢትዮጵያ ሕዝብ የድልና የነጻነት ቀን ከፍ ከፍ ተደርጎ ሲከበር፣ ከድሉ ጋር ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ኃይለ ሥላሴ አብረው ከፍ ከፍ ይላሉ፤ ይከበራሉ፡፡ እሳቸውን የሚጠሉ ደግሞ ንጉሡን እንበቀልበታለን ብለው የመረጡት መንገድ እሳቸው የተሳተፉበቸውን የኢትዮጵያ ታሪክ ሁነቶች ሁሉ ዝቅ ዝቅ በማድረግ ስለሆነ፣ ማድነቁ የበቀል ጥርሳቸውን ስለሚሰብረው ነው፡፡ እውነቱ ግን ሚያዝያ 27 የነፃነትና የድል ቀን መሆኑ ነው፡፡ የዛሬ ሳምንት 77ኛው የነፃነት ቀን ይከበራል፡፡

Read 1422 times