Sunday, 29 April 2018 00:00

“ዛሬም አሰብ አሰብ እንላለን”

Written by  በያዕቆብ ኃ/ማሪያም (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

    ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፡-
የአድህሮትና የክፍፍል ኃይሎች በአንድ ጎራ፣ የነፃነትና የአንድነት ኃይሎች በሌላው ጎራ ሰቅዞ በያዛቸው ትግል ውስጥ ሆነው በሚፋለሙበት በዚህ ተስፋ ሰጪ ወቅት፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን ማንሳት፣ዋናውን የተጀመረውን በጎ እንቅስቃሴ ማዘናጋት እንዳይሆን የሚሰጉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም የአሰብ ባለቤትነት ጥያቄ፣ የአገር ህልውናና ልማት ጥያቄ አንዱ አካል እንደመሆኑ መጠን፣ ዛሬ ከተከሰተው ብዙ ተስፋ ከጫረውም የዴሞክራሲና የአንድነት እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ፣ ገና ከጠዋቱ መነሳት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ የአሰብ ጥያቄ ግዙፍነትን ተረድተው፣ አዲሶቹ የኢትዮጵያ መሪዎች፣ ከቀዳሚ አጀንዳዎቻቸው ውስጥ እንዲያካትቱ በአክብሮት ለማሳሰብም ነው፡፡ ዛሬ የተነሱት የኢትዮጵያ መሪዎች፤ የኢትዮጵያን ጥቅሞችና መብቶች የሚያስከብሩ መሪዎች ናቸው የሚል ፍንጭ ስለአየን ጉዳዩን እንድናነሳ ቀሰቀሰን፡፡
ኤርትራ ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ተገንጥላ፣ የኢትዮጵያ ሉዐላዊ ግዛት የነበረችው አሰብን ስትይዝ፣ አሰብ በታሪክ፣ በሕግና በስነ መንግስት እሳቤ የኤርትራ አካል እንዳልነበረች ለማስረዳት፣ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልማሱት ስር አልነበረም፡፡ በወቅቱ የአሰብን የኢትዮጵያ ግዛት መሆን ማስረዳት፣ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ አልነበረም። በተቃራኒው ደግሞ በጊዜው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና አቶ በረከት ስምዖን ከመንገዳቸው ወጥተው፡- “አሰብ የኤርትራ ግዛት ነች፤ ኢትዮጵያ በአሰብ ላይ ምንም መብት የላትም” ሲሉ መስክረዋል፡፡ ይኸ ስም ማጥፋት ሳይሆን በሰነድ ሊረጋገጥ የሚችል ጉዳይ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል የተደረገው አላስፈላጊና ትርጉም የለሽ ጦርነት፣ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት እንደሚደመደም ግምት ተወስዶ ስለነበር፣ ጦርነቱ አልቆ ወደ ድርድር በሚኬድበት ጊዜ ለኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ግብዓት የሚሆኑ በሕግና በታሪክ የተደገፉ ሃሳቦችን ምሁራን በተለያዩ ሚዲያዎች አቅርበው ነበር፡፡ ጦርነቱ እንደተጠበቀው በኢትዮጵያ አሸናፊነት ሲደመደም፣ ኢህአዴግ ከመነሻው ኤርትራን ለማስገንጠል በብዙ የደከሙት የኢትዮጵያ ጠላት የአልጄርያው ፕሬዚዳንት ቡተፍሊካን አስታራቂ እንዲሆኑ ጠየቀ፡፡ ቡተፍሊካም አቶ ኢሳያስና አቶ መለስን አጨባብጠው፣ውዝግቡን ዓለም ሁሉ እምነቱን ወደጣለበት ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International Court of Justice) በመውሰድ ፈንታ በገንዘብ በተገዙ ግለሰቦች እንዲዳኝ፣ የድምበር ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ጉዳዩ ወደዚያ ተመራ፡፡
በታሪክ በሕግና በሥነ መንግሥት የተካኑ ኢትዮጵያውያን፣ ግልጋሎታቸውን በነፃ እንደሚለግሱ ቢረጋገጥም፣ ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊና ወቅታዊ ግንኙነት ምንም እውቀት የሌላቸው ዳኞች፣ በዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ተቀጥረው፣ ጉዳዩ ወደ እነዚህ ዳኞች ችሎት ተመራ፡፡
በክርክሩ ወቅት ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች አንድም ጊዜ፣ አሰብን በክርክራቸው አላነሱትም፤ ይልቅስ እጅግ በጣም አስገራሚ የሚሆነው ውሳኔው ጣልያኖች በታላቁ መሪ በእምዬ ምኒልክ ላይ በግድ በተጫኑ፣ ጣልያን በኢትዮጵያ ላይ ጦር በማዝመትዋ፣ በተባበሩት መንግስታት፣ ኢትዮጵያም በአዋጅ በሰረዙዋቸው ውሎች ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡ እነዚሁ ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች፣ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ፣ በውሳኔ ቁ. 289 (IV) የኢትዮጵያ ተገቢና ሕጋዊ የባህር በር ባለቤትነት መብትን ቢያረጋግጥም፣ ጠበቆቹ ከቁብ ሳይቆጥሩት ታለፈ፡፡
እዚህ ላይ አንድ አስገራሚ ምናልባትም በአገር ክህደት ወንጀል የሚያስጠይቅ በደል መጠቀስ አለበት፡፡ የድንበር ኮሚሽኑ ዳኞች የቀረበላቸውን ማስረጃዎች ተንተርሰው፣ ጾረና የኢትዮጵያ ግዛት መሆንዋን ውሳኔ በሚሰጡበት ጊዜ በኢትዮ መንግስት ትዕዛዝ፣ ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች፣ “የለም ተሳስታችኋል፣ ጾረና የኤርትራ ግዛት ነው” በሚል በመከራከራቸው፣ዳኞቹ ምርጫ በማጣት፣ ጾረናን ወደ ኤርትራ አካለሉት፡፡
በተጨማሪም ማንኛውም መንግስት ወይም አገር፣ ከሻዕቢያና ከኢሕአዴግ በስተቀር ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነበረች ያለ የለም፤ ሻዕቢያ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነበረች ካለ፣ የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት መቀበል ነበረበት፡፡ ዛሬ የልማዳዊ ሕግ (Customary law) አካል የሆነው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ በካይሮ ስብሰባው፣ በውሳኔ ቁ. AHG/Res. 61(1) ያሳለፈው የሕግ መርህ፤ “አንድ በቀኝ ግዛትነት የተገዛ አገር ነጻ በሚወጣበት ጊዜ፣ ቅኝ ግዛት በነበረበት ወቅት የነበረውን ድንበር ማክበር ይኖርበታል” በማለት ደንግጓል፡፡ ይህ መርህ፤” በያዝከው እርጋ” የሚል ድንጋጌ ነው፡፡ ኤርትራ “ነፃ” በወጣችበት ጊዜ አሰብ ራስ ገዝ የኢትዮጵያ አካል ስለነበረች፣ አሰብ በኢትዮጵያ እጅ መቅረት ነበረባት፡፡ ኢትዮጵያን የወከሉ ጠበቆች፤ ይህንን መርህና ሌሎችንም ኢትዮጵያን የሚደግፉ የህግ መርሆች ሳያነሱ ኮሚሽኑ ውሳኔውን ሰጠ፡፡ በዚህም ውሳኔ ባድመንና ጾረናን እንዲሁም ሌሎችንም ለኤርትራ ሰጥቶ፣ በእግር መንገድ ርቀት ሁለት ወደቦች የነበራት ኢትዮጵያ፣ የባህር በር ተዘግቶባት፣ ከቀይ ባህር አካባቢም ተገልላ፣ ቀይ ባህርም የአረብ ሃይቅ ሆነ።
የድምበር ኮሚሽኑ በወረቀት ላይ የሚካለል ስራ ከሰራ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በስምምነቱ መሠረት፣ ኮሚሽኑ መሬት እረግጦ፣ በወሰኖቹ ላይ ችካል መትከል ነበረበት፤ ሆኖም አቶ ኢሳያስ በኤርትራ ተሰማርቶ የነበረውን የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ጦር በማባረራቸው፣ የድምበር ኮሚሽኑ ከስምምነቱ ውጭ፣ “ወሰኑን በአየር አካልዬ የማስመሰል ችካል ተክዬአለሁ (Virtual demarcation አድርጌአለሁ) ብሎ አካባቢውን ጥሎ እብስ አለ፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ የኢትዮጵያና የኤርትራ የማካለል ውልን የሚጥስ በመሆኑ፣ ወሰኑ ተካልሏል ማለት አይቻልም፡፡ ኤርትራ ግን መካለሉ ተጠናቅቋል በሚል ኢትዮጵያ የያዘችው ግዛቶችዋን በተለይም ባድመን እንድታስረክባት ለዓለሙ ህብረተሰብ አቤቱታ ስታሰማ ቆይታለች፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፡-
በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ያመዘነ አገራዊ ጉዳይ ማሰብ አዳጋች ነው፤ ስለሆነም አዲስ ተስፋ እንድንሰንቅ ያደረገን የኢትዮጵያ መንግስት አመራር፣ ከኤርትራ ጋር ሁሉን አቀፍ ድርድር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ድርድሩ ባለፈው እንደነበረው በብልጠትና በመሸወድ የተጀነጀነ ሳይሆን ጠቃሚነቱን አጉልቶ በማሳየት መከናወን አለበት፡፡ ምናልባትም ኤርትራን ሊያማልሉ የሚችሉ ነገሮች ማመልከትም ያስፈልጋል፡፡ አንድ ነገር ግን ግልጽ መሆን አለበት፡፡ የድርድሩ አልፋና ኦሜጋ አሰብን ወደ ኢትዮጵያ ማጠፍ መሆን አለበት፡፡ ይህም ውሳኔ ውልፊት የማይባልበት የመጨረሻ አቋም መሆን ይኖርበታል፡፡ ግልጽ ለመሆን ያህል የአሰብ ወደብን በነፃ መጠቀም ማለትም እንዳልሆነ ልብ ማለት ይገባል፡፡ ይህም ሲባል አሁን መገለጽ የማይገባቸው፣ የኢትዮጵያ የአሰብ ባለቤትነትን ሊያስረግጡ የሚችሉ እርምጃዎችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
ክቡርነትዎ፡- ለዚህ ጉዳይ ፍጹም የሆነ ትኩረት እንደሚሰጡት ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡
ለአዲሱ አመራር መልካም የሥራ ዘመን እመኛለሁ!!


Read 2715 times