Sunday, 29 April 2018 00:00

ዶ/ር ዐቢይ - ሕዝብን ያከበሩ መሪ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(14 votes)


መኖር ካሉትማ ትርጉሙ …
ተስፋ ሲኖር ነው ሀቁ፤
ወደፊት ብለው ሲተልሙ …
መሰላል ሲያዩ ከሩቁ፣ (ገጣሚ መቅደስ ጀንበሩ)
       
    አሁን ጭጋግ የለበሰ ሰማይ … ሀዘን ያረበበት ፊት ….ጨለማ የጋረደው ልብ የለም፡፡ ብዙ ነገሮች ሰክነዋል፡፡ አድማሳቱም የነገን ፊት በተስፋ ወልውለው፣ በምድረበዳው መንገድ፣ በበረሀው ጽጌረዳ አስቀምጠዋል፡፡ ዛሬ ከትናንት ይሻላል፤ ደም ያጠቀሰው ዘንባባ፣ በፍቅር ቃል እየታጠበ፣ ቁጣ ያሰከረው አደባባዩ፣ ወደ ምህረትና ይቅርታ መዝሙር እየተመለሰ፣ ለጥፋት የተሳሉ ሰይፎች ወደ ሰገባቸው እየተከተቱ ነው፡፡
በትልቁ መጽሐፍ የተወራላቸውን የካሌብና ኢያሱን ያህል ጥምረትና እምነት የነበራቸው አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በመከራ ቀን መጋረጃውን ገልጠው ከወጡ በኋላ ብዙ ነገር ተቀይሯል፡፡ በፍርሀት የተቀሰፉ ልቦች በማፅናኛ ቃል በርትተዋል፡፡ ህዝብ ያለ ጠመንጃ ጀግና የሚሆንበትን ሀገር ፈጥረዋል፡፡ ህዝብ የሚከበርበትን ሃሳብ አምጥተዋል፡፡ “ህዝብ ሆይ፤ አለቃ ነህ!” ብለው ዘምረዋል፡፡ ዣን ዣክ ሩሶ እንዳለው፡- “The People are sovereign, not the king” እውነትም ህዝብ ሉአላዊ እንደሆነ አሳይተውናል፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ በትግልና ምጥ መካከል ሾልኮ ከእሳት ያመለጠው ትንታግ አደባባዩን ሞልቶታል፡፡
ይህንን ለዓመታት የተጎነጎነ እሾህ፣ ለጥፋት የተቆፈረ ጉድጓድ፣ በዘረኝነት የተበጣጠሰ አንድነት መቀየር እጅግ ከባድና ጊዜ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህን የህዝብን አለኝታነት የሚሻ፣ ብልሃትና ስልት በተሞላ ሁኔታ ለማቃናት ዋጋ የሚጠይቀውን ሥራ ለመስራት፣ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ከፈተናው ጋር ተፋጥጠው ጉዞ ጀምረዋል፡፡
ቀደም ሲል አቶ ለማ መገርሳ እንደ ምንም ነገር ችላ ተብሎ የኖረውን “ኢትዮጵያዊነት” የሚል ሃሳብና ቃል፣ በፍቅር ነክረው፣ ጆሮዋችንን ካሟሹት በኋላ፣ ዶ/ር ዐቢይ ተቀብለው እንደ መዝሙር በየአደባባዩ እያቀነቀኑትና በየሰው ልብ ውስጥ እያተሙት ሳምንታትን አስቆጥረናል፡፡
ይሁንና በዚህ አዲስ ምዕራፍ ጅማሬ፣ በዚህ የተስፋ ቀናት ደጅ ላይ ሆነንም በጠ/ሚኒስትሩ ላይ የሚሰነዘሩ ወቀሳዎች ብቅ ብቅ ያሉ ይመስላል። ሰውየው ግን በፍቅር፣ በይቅርታና በአንድነት ሃሳቦች የተቃኙ መሳጭ ንግግሮችን በማድረግ፣ ህዝቡን ወደ አንድነት ለማምጣት ያለ እረፍት እየተጉ ነው። ታዲያ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ አሳማኝ መረጃ ባይኖራቸውም፣ አንዳንድ ወገኖች ጠ/ሚኒስትሩ እንደተመረጡ ወደተለያዩ ክልሎች ሄደው፣ ህዝብን ማወያየታቸውንና ንግግር ማድረጋቸውን አልወደዱትም፡፡ “ዶክተሩ ወደ ስራ መግባት ሲገባቸው ጊዜያቸውን በወሬ አባክነዋል” የሚል የወሬ ማዕበል አስነስተዋል፡፡ ምናልባት እነዚህ ወገኖች፣ ለሥነ አመራሩ ሳይንስ እጅግ ባይተዋር ሳይሆኑ አልቀሩም፡፡ አንዱ የብርቱ መሪ ሥራ፣ ህዝብን ማነጋገርና ማሳተፍ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሰውየው ደግሞ ይህንን ሳይንስ በሚገባ የተማሩና የተካኑበት ሲሆኑ ጽንሰ ሀሳቡንና ትግበራውንም አሳምረው የሚያውቁ ናቸው፡፡ ህዝብ ብዙ ጊዜ ስሜቱን ይናገራል፤ መሪ ግን በጥበብ ልጓም ሃሳቦችን ገርቶ ወደ ራዕዩ ይጓዛል፡፡
የኛ ሀገር ጉዳይ ደግሞ ከዚህም ያለፈ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ ግጭቶች የቆሰለው ህዝብ ልብ ገና አልጠገገም፡፡ ከዚያ ቁስል ጋር “አብረን እንስራ፣ አብረን እናልማ!” ማለት በቁስሉ ላይ እንጨት ከመስደድ አይተናነስም፡፡ ስለዚህም ዶ/ር ዐቢይ እያንዳንዱ ክልል፣ በተለይም ቁጣ፣ ቂምና ጥርጣሬ ያጎበጣቸውን ወገኖች ጠጋ ብለው ማድመጥ ነበረባቸው፡፡ ያንን ነበር ሲያደርጉ የሰነበቱትም፡፡  
ሌሎች ወገኖችም አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ ህዝቡን ማነጋገር ሳይሆን፣ ማሞገስ አይገባም ባይ ናቸው። የነዚህ ሰዎች ምክንያት “ሁሉንም ወገን ማስደሰት አይቻልም” የሚል ነው፡፡ ይህም ሃሳብ በራሱ ተገቢና ትክክለኛ አይደለም፡፡ አንድ የቤተሰብ ኃላፊ ቤተሰቡን ሁሉ በእኩል ዐይን የማየት፣ ሁሉንም እንደየ ጠባዩ፣ አቅሙ፣ ችሎታው የማስተዳደርና የመምራት ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ፣ የሀገር መሪም ተመሳሳይ አያያዝ ይጠበቅበታል፡፡
የአንድ ቤተሰብ አባላት፣ የተለያዩ ጠባዮች፣ ልዩ ልዩ ችሎታዎች ይኖራቸዋል፡፡ አንዱ ታጋሽ፣ ሌላው ቁጡ፣ ሌላው ኃይለኛና ችኩል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና አባት እነዚህን ልጆቹን እንደየ ጠባያቸው ማሳደርና ማግባባት መቻል አለበት፡፡ እንደየ ችሎታቸውና ተሰጥዖዋቸው ማድነቅና ማበረታታት ግድ ይለዋል። አንዱን “የኔ ጎበዝ!” ብሎ አድንቆ፣ ሌላውን “ሰነፍ!” ማለት የለበትም። ሁሉም የየራሳቸው በጎ ጎን ስለሚኖራቸው፣ ያንን በጎ ጎን እየመዘዘ ቢያሞካሻቸው፣ ልጆቹን ከማበረታታት ውጭ የሚፈጥርባቸው አደጋ አይኖርም፡፡ “አንተ ወርቅ ነህ፣አንተም ወርቅ ነህ” ቢላቸው፣ የትኛውም ወገን አይከስርም፡፡ ይልቅስ ቤቱ በፍቅርና በጥሩ መንፈስ ይሞላል፡፡
የሀገርም ጽንሰ ሀሳብ ብዙ የራቀ አይደለም፡፡ በአንድ አስተዳደር በአንድ ባንዲራ የሚተዳደር፣ በአንድ መሶብ የሚቆረስለት፣ ክፉና ደግ ሲመጣ፣ በአንድ ሁሉን የሚቀበል ህዝብ፤ አንድ ቤተሰብ ማለት ነው፡፡
ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤እርሳቸው የኦሮሞ ብቻ አይደሉም፣ የአማራ፣ ትግራዋይ፣ የአፋር፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የሌሎችም መሪ ናቸው፡፡ ስለዚህ ለምን ሁሉም ዘንድ ሄደው ንግግር ያደርጋሉ የሚለው ትችት፣ ትክክል አልነበረም ባይ ነኝ፡፡ ከዚያ በሻገር “ለምን ቀድሞ እነ እንቶኔ ጋ ሄደ?” የሚሉ ድምፀት ያላቸው ሹክሹክታዎችም ተሰምተዋል፡፡ እነዚህ ለምን ኖሩ አይባልም? .. በየትኛውም አገር፣በየትኛውም ህዝብ ውስጥ በሳል አእምሮዎች ብቻ ሳይሆን ጨቅላዎችም ይኖራሉና በቸልታ እናልፈዋለን፡፡ ግን ዶክተር ዐቢይ ትክክል የሆኑበትን ምክንያት ለማየት ብዙ ማሰብ፣ ሩቅ መፈተሽ አያስፈልግም፡፡ በመጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ መሄድ ነበረባቸው፡፡ ምክንያቱም በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ ድንበር ግጭቶች ሳቢያ ምን ያህል ዜጎች ለሞት እንደተዳረጉና ስንት መቶ ሺዎችም ከቀዬአቸው እንደተፈናቀሉ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡   በሚዲያ እንደተመለከትነውም “ኦሮሞ ተመረጠ” ሲባል ስጋት ገብቷቸው እንደነበረ የክልሉ ተወላጆች ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በነበራቸው ውይይት በግልፅ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ዐቢይ እርቅ ለማውረድና ይህንን ዓይነቱን ስጋት በእንጭጩ ለማጥፋት ወደ ክልሉ መሄዳቸው በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው እንጂ ፈጽሞ የሚያስተቻቸው አይደለም፡፡ ብልህና ጥንቁቅ መሆናቸውንም የሚያሳይ ነው፡፡ ውሎ ማደር የሌለበት፣አንገብጋቢ የህዝብ ጉዳይ ነበርና፡፡  
ብቻ ዶ/ር ዐቢይ የተቀጣጠለውን እሳት ወይም ተዳፍኖ ያደረውን ፍም ማንም ተንኮለኛ እንዳይቆሰቁሰው ውሃ ከልሰውበት መጥተዋል፡፡ በዚህ በጎ ተግባራቸውም ብዙዎቻችን አድንቀናቸዋል፡፡
ሁለተኛው ጉዟቸው እዚሁ ቅርባችን ኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ ነበር፡፡ አምቦ ከተማን የመረጡበትንም ምክንያት ሲገልጹም፤ አምቦ በተለያዩ ጊዜያት አመፅ የሚነሳባት፣ በዚያም ምክንያት ብዙ ወጣቶችዋን በሞት ያጣችና በቁጣ የምትንተጋተግ ከተማ ናት። ምናልባትም ከትግል በስተቀር የትኛውንም የፍቅር ድምፅ ላለመስማት ጆሮዋን የዘጋች ሳትሆን አትቀርም ብለን ልንገምት እንችላለን፡፡ “አምቦ” ሲባል አንዳች የተለየ የኃይል ቀለም አላትና!
አዲሱ ጠ/ሚኒስትራችን ግን ኃይል ጠመንጃ ሳይሆን “ፍቅርና ይቅርታ ነው!” ብለው ያምናሉ፤ ይሄንኑም ይሰብካሉ፡፡ ልባቸው ወደ ማህተመ ጋንዲ፣ ወደ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ወደ ሌዎ ቶልስቶይ ያጋድላል፡፡ እናም አምቦ ከተማ ሄደው በብዙ ሺህ ለሚቆጠር ህዝብ በኦሮሚፋ ቋንቋ ንግግር አደረጉ። እሳቱ ላይ ዝናቡን አወረዱት፡፡ እሾህ በተነሰነሰበት ከተማ፣ ዘንባባቸውን እረጩት፡፡ የሞቱን መስቀል ነቅለው፣ የህይወት ፅጌሬዳ ተከሉ፡፡
ህዝቡ በገዛ ቋንቋው የራሱንና የሀገሩን ጉዳይ ሲሰማ ደስ አለው፡፡ እዚህም ፍቅር ሰበኩ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን አቀነቀኑ፡፡ ባልንጀሮቻችን ሲተረጉሙልን፤ አንገታችንን ነቅንቀን ተደነቅን፡፡ አምላካችን የሚያሳርፍ፣ በጥላቻ የደደረ ልባችንን በፍቅር የሚነክር መሪ ሰጠን ብለን ተደሰትን፡፡ እኔና የቅርብ ወዳጆቼ ማለትም የሥነ ፅሑፍ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የጥበብ ሰዎች ጥሩ ስሜት ተሰማን፡፡ ተረጋጋን፡፡
ቀጥሎ በናፍቆት የጠበቅነው ጉብኝታቸው የመቀሌው ነበር፡፡ የመቀሌው ስብሰባ ቀጣይ መሆኑም ትክክልና ተገቢ ነበር፡፡ እዚህም ተወላጆቹ ራሳቸው ባወደሱላቸው የትግርኛ ቋንቋ ብቃታቸው የአገሩን ህዝብ አደነቁ፤ የተለየ ባህልና ታሪኩንም አሞካሹለት፡፡ ሰውየው የትግራይ ህዝብ ፍቅርና ህይወትን ለዓመታት ኖረው፣ በአካል ያዩት መሆኑን አስመሰከሩ፡፡ ህዝቡም ደስ አለው፡፡ ንግግራቸውን በማያቋርጥ ጭብጨባም አጀበላቸው፡፡ እኒህ ሰው ስልጣኑን በያዙ ጊዜ፣ ቀጣዩ ዕጣችን ምን ይሆናል? የሚል ጥርጣሬ ለተፈጠረባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም፣ የደህንነት ስሜትን ለማረጋገጥ የቻሉ ይመስላል፡፡ ከሚመሩት ህዝብ ጋርም በቅድሚያ መተዋወቅ ትክክለኛ የመሪ አካሄድ እንጂ የሚያስተች አይደለም፡፡
እኛም ወገኖቻችን ደስ ሲላቸውና አንድነታችንን የሚያጠናክርልን መሪ በማግኘታችን ፈነደቅን። ነገሮችን በቀና ማየት የተሳናቸውና እንደ ህፃን ልጅ፣ ስጋዊ ቅንዓት የተሰማቸው ጥቂቶች ኩርፊያ ቃጣቸው፤ ግን ውሎ አላደረም፡፡ ሁሉም በፍቅራቸው የያዘውን ጣለ፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ክልላዊነት ሲጠብቅ በጎ እንዳልሆነ፣ በሳቅ አጣፍጠው፣ በፈገግታ ፈትፍተው አጎረሱ፡፡ ለረጅም ዓመታት ከመሪዎች ዘለፋና ቁጣ፣ የማይፈታ ገፅታና ገፊ ግንባር የታየባቸው ቴሌቪዥኖች፤ ህዝብን በሚያከብሩ መሪ፣ ጋባዥና ጣፋጭ ቃላት ፈነጠዙ፡፡ የምንፈራውንና የምንጠላውን ቴሌቪዥናችንን ወደድነው፡፡ “ለሁሉም ጊዜ አለው…” ብለንም ተደመምን፡፡  
በመቀሌ የአዳራሽ ውይይት ከተነሱት ጥያቄዎች አንዱ የብዙዎችን ልብ አሳዘነ፡፡ የወልቃይቱ ጉዳይ! … ምክንያቱም ያንን ጉዳይ ራሳቸው ከመመለስ ይልቅ ወደ ህዝቡና ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት የመሳሰሉት ተቋማት ቢመሩት ጥሩ ነበር ብለን ተቆጨን፡፡ ትግራይ ላይ “ሞተር፣ ወርቅ” ያሉት ነገር ያስኮረፋቸውም ነበሩ፡፡ እኔ በበኩሌ፤ ይህንን ኩርፊያ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ “ኢትዮጵያዊ ወርቅ ነው!” በሚለው ከተስማማን ትግራይም ኢትዮጵያዊ ናትና፣ ወርቅ መባሉ አያስቆጣም፤ቢያስደስት እንጂ፡፡ ስለዚህ ዶ/ር ዐቢይ ትክክል ነበሩ፡፡
ብዙዎች ቀዳዳ አግኝተው ሊሾልኩበት ያመቻቹት ቀዳዳ ሆኖ የሰነበተው የመቀሌው ስብሰባ ክፍተት፣ ለአንዳንዶቻችን ፀፀት፣ ለሌሎች ደግሞ ነገር ማራገቢያ ስለነበር፣ የባህርዳሩንና የጎንደሩን ስብሰባ ያበላሽባቸው ይሆን ስንል ያማጥን አልጠፋንም፡፡ ምጣችን ለማንም አይደለም፣ ለሀገራችን ስለታየው ተስፋና ስለሚያጓጓው የምኞት አድማስ ናፍቆት እንጂ!
ቀኑ ሲደርስ በተለይ ባህር ማዶ ያሉ ሃሳባቸውና ህልማቸው የማይገባኝ፣ በፊትም ገብቶኝ የማያውቅ ሰዎች፤ ህዝቡ እንዲያምፅ ሁሉ በማህበራዊ ሚዲያው ጎተጎቱ፡፡ “ኢትዮጵያዊነትን ከመቃብር አውጥተውልናል” ብሎ የእነ ለማን ቡድን የሚያደንቀው ወገን ደግሞ ነገሩን ያስተካክሉታል በሚል ቀና ሃሳብና ምኞት፣ “አይዟችሁ!” አለ፡፡
ዶ/ር ዐቢይ በፍቅር ተለውሰው፣ በፍቅር የበሰሉ ድንቅ ሰው ናቸው፡፡ በሁሉም አቅጣጫ የተቀመሙ፣ ጣፋጭና ስልጡን! ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ የተባሉ የማህበራዊ ሚዲያ ብርቱ ፀሐፊ ተደስተው፤ “አንተን የወለደች ማህፀን ብሩክ ትሁን!” ሲሉ ስሜታቸውን በገነነ ሁኔታ ገለፁ፡፡ በርግጥም ሰውየው ጎንደር ሄደው ያቀረቡትን ንግግር፣ አንድ ደራሲና ጋዜጠኛ ጓደኛዬ በአድናቆት አነበበልኝ፡፡ ቋንቋቸውና ገለፃቸው የብዙ ገጣሚያንን፣ የዘይቤ ልዕቀት ያስንቃል፡፡ በዚያ ላይ በፍቅር የተሞላው ድምፀታቸው፣. የማንንም ጀግናና ጨካኝ ልብ ያንበረክካል፡፡ እውነትም የተቆጡ ሁሉ የፍቅራቸውን ድልድይ መሻገር አልቻሉም። ተመልሰው በአድናቆት ዘመሩላቸው፤ እኛም መዝሙሩን አስተጋባን! … ደጋግመን ዘለፋና ፍረጃ በጠገብንባቸው አደባባዮች፣ “ህዝቡ ቢቆነጥጠኝ እንጂ” ብሎ ራስን የህዝብ ልጅ አድርጎ፣ ህዝብ እጅ ላይ መውደቅ ያለ ምንም ጥርጥር ያገሬን ሰው ያሸንፈዋል፡፡
ታዋቂውና ዘመን አይሽሬው ፖለቲከኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፣ ስለ ዶ/ር ዐቢይ ንግግር እንዲህ ብለዋል፡- “ዶ/ር ዐቢይ በተለያዩ ስፍራዎች ያደረጋቸውን ንግግሮች በጥሞና አዳምጫለሁ፣ በተለይም ከሀብታሞች ጋር አንድም ቦታ ሀሳቡ ሲደናገር ወይም ሲዛነፍ አልሰማሁም፣ በዚህም የእውቀቱን ስፋት፣ የአእምሮውን ምጥቀት፣ የኅሊናውን ጽዳት፣ የወኔውን ብርታት፣ የዓላማውን ጥራት፣ የዘዴውን ሥልጡንነት በጣም እጅጉን አደንቃለሁ። ለእኔ ኢትዮጵያ የሰውም ሆነ የአእምሮ ችግር ኖሯት አያውቅም የሚለውን እምነቴን አረጋግጦልኛል፤”
በርግጥም ዶ/ር አብይ በዕውቀትም በፍቅርም የላቁ ሆነው ሁሉንም አሸንፈዋል፡፡ ስለዚህ አብረናቸው እንቆማለን እያልን እንዘምራለን፣ አድማሳት ከእኛ ጋር ያስተጋባሉ፡፡ ኢያሱና ካሌብ የከንዐንን ፅኑዐን እንዳልፈሩ ሁሉ፣ እኛም “እንደ እንጀራ ይሆኑናልና ኑ እንውጣ” እንላለን! ሀገራችን በፍቅርና በመከባበር ማርና ወተት ታፈስልን ዘንድ እነሆ ቀኑ ደርሷል። ግና ደግሞ ትዕግስት ያሻናል፡፡ ሮም በአንድ ሌሊት አልተገነባችምና!! 

Read 6883 times