Sunday, 29 April 2018 00:00

የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት በዶ/ር ዐቢይ ዘመን

Written by  ብሩህ ዓለምነህ brooha3212@gmail.com
Rate this item
(14 votes)

ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ላለፉት 27 ዓመታት የፖለቲካ ውክልና እንዳይኖረውና በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ እንዳይወጣ ተደፍቆ ኖሯል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የምንመለከተውም፣ የዶ/ር አብይ አህመድን ምርጫ ተከትሎ፣ አንገቱን ከደፋበት ቀና ቀና ማድረግ ስለጀመረው ስለ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማንሰራራት ነው፡፡
ዶ/ር አብይ በይፋ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚ/ር ሆነው በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት መጋቢት 24 ቀን  2010 ዓ.ም ሹመታቸው ከፀደቀላቸው በኋላ ሁለት አበይት ተግባሮችን አከናውነዋል፡፡ የመጀመሪያው፣ ካቢኔያቸውን እንደገና ማዋቀር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአመፅ ስትናወጥ የነበረችውን ሀገር እየዞሩ ማረጋጋት ነው፡፡ በዚህም በሰባት የሀገሪቱ ከተሞች ማለትም በጅግጅጋ፣ በአምቦ፣ በመቀሌ፣ በጎንደር፣ በባህርዳር፣ በአዲስ አበባና በሐዋሳ እየተዘዋወሩ ከህዝቡ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ዶ/ር አብይ በሄዱባቸው ከተሞች ሁሉ ለህዝቡ ያስተላለፉት የጋራ መልዕክት ቢኖር፣ ታሪክንና ወንድማማችነትን እየጠቀሱ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው አወድሰዋል፡፡ በተለይ በባህርዳሩ ስብሰባቸው ላይ ‹‹የታመመውንና የቆሰለውን ኢትዮጵያዊነት›› ማከም እንዳለብን፣ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የዶ/ር አብይ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ከፍ ከፍ ማድረግ የሚጀምረው ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ አይደለም፡፡ ይህ ነገር የሚጀምረው በኦህዴድ ውስጥ ነው፡፡ በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው ኦህዴድ፤ላለፉት ሁለት ዓመታት የኦሮሞና የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን በማስታረቅ የሄደበት አዲስ መንገድ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍን አስገኝቶለታል።
የዶ/ር አብይ የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ስር የሚመዘዘው ግን ከኦህዴድ ብቻ አይደለም፤ ወደ አስተዳደጋቸውና ቤተሰባዊ ሁኔታቸው ይሄዳል። ዶ/ር አብይ ከኦሮሞና ከአማራ ወላጆች የተወለዱ፣ በእስልምና ሃይማኖት አድገው በኋላ ላይ ወደ ክርስትና የገቡ፣ በኦሮሞ ባህል አድገው አማራ ሚስት ያገቡ፣ በአፋን ኦሮሞ አፋቸውን ፈትተው አማርኛና ትግርኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ፣ ኢትዮጵያዊ ዥንጉርጉርነት የሚታይባቸው ሰው ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ከዚህ የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖትና የብሄር ዥንጉርጉርነት ውጭ የሚገልፀው ነገር የለም፡፡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?›› በተባለው መፅሐፋቸው ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እንዲህ በማለት ይገልፁታል፡- ‹‹ኢትዮጵያዊነት ብዙና የተለያዩ ህብረተሰቦች የተዋኻዱበት አካል ክፍል መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከጎሰኝነት በላይና ውጭ የሆነ አጠቃላይ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት የዜጎች ውጥንቅጥ መሬት ባለቤትነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት የደጋው ብርድና የቆላው ሙቀት የሚገናኙበት ኃይል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለሙሴ፣ ለክርስቶስና ለመሐመድ የሚጨሰው ዕጣን በእርገት መጥቆ የሚደባለቅበት እምነት ነው፡፡›› (1985፡ 31)
ዶ/ር አብይ የእንደዚህ ዓይነት ኢትዮጵያዊ ዥጉርጉርነት ጥሩ መገለጫ ናቸው፡፡ ቅይጥ ማንነቴዎች ከተለያዩ ባህሎችና ማንነቶች የሚጋሩት ስነ ልቦና ስላላቸው፣ ልክ እንደ ዘውግ ብሄርተኞች ወደ ውስጥ የታመቀ ማንነት ሳይሆን ወደ ውጭ የተበተነ ማንነት ነው ያላቸው። ይሄም የተበተነ ማንነት መጠጊያውና መጠለያው ይሄኛው ወይም ያኛው ብሄር ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ነው። የኢህአዴግ የብሄር ፖለቲካ ግን ላለፉት 27 ዓመታት ለዚህ ቅይጥ ህዝብ ዕውቅናና ፖለቲካዊ ውክልና በመንፈጉ የተነሳ በሀገሩ ላይ መጠጊያና መጠለያ አጥቷል፡፡
ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት የሚመነጨውም ከዚህ ብትን ማንነትና ዥጉርጉርነት ነው፡፡ ይህ ቅይጥነት ደግሞ ለ100 እና ለ200 ዓመታት የቆየ ሳይሆን ሺ ዓመታትን የተሻገረ ሐቅ ነው፡፡ ለዚህ ነው ዶ/ር አብይም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በሚያወድሰው በፓርላማው ንግግራቸው ላይ ‹‹ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደና የተዋኻደ ነው፤›› ያሉት፡፡ ላለፉት 27 የኢህአዴግ ዓመታት  ውስጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዚህ ፓርላማ ላይ በዚህ ከፍታ ነግሶ አያውቅም። በዚህ የዶ/ር አብይ ንግግራቸው የተነሳም ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ዳግም የማንሰራራት ምልክቶች አሳይቷል፡፡
የኢህአዴግ ፖለቲካ ግን ይሄንን ሐቅ በመካድ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሀገሪቷን በብሄር ሸንሽኖ በሐሳብ ሳይሆን በብሄር ለተደራጁ ኃይሎች ያከፋፈለበት ምክንያት ‹‹በከተሜነት፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በብሄር መቀላቀል የተነሳ ቅይጥ ማንነት ያላቸው ዜጎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው›› በሚል የአስተሳሰብ መነሻ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የሚመጣው ደግሞ ከመሃሉ (ከከተሞች መስተጋብር) በተነጠሉና ጠርዝ ላይ ከሚገኙ ገጠሮች ነው፡፡ ምንም እንኳ አርሶ አደሩ ብሄርተኛ ባይሆንም ከእንደዚህ ዓይነት ከተነጠሉ አካባቢዎች የሚወጣው ልሂቅ ግን የሀገሪቱን ህዝቦች የሚመለከተው ልክ እንደ ራሱ አድርጎ ነው፡፡
ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተካረረ ውዝግብ በገባበት የ1997ቱ ምርጫ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎችን ያስጠነቀቁበት መንገድ ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አቶ መለስ እንዲህ ነበር ያሉት፡- “እኛ የአርሷደር ልጆች ነን፤ በመሆኑም የምናራምደው ፖለቲካ የባላገር ፖለቲካ ነው። ስለዚህ እንደ አመላችን ያዙን” ይህ የአቶ መለስ ንግግር፣ የሀገራችን ፖለቲካ በገጠርና በከተማ ሰዎች፣ ባልተቀየጡ ማንነቶችና በቅይጥ ሰዎች  መካከል የሚደረግ (Center - Periphery) የፖለቲካ ሽኩቻ እንደሆነ ግልፅ ያደረገ ንግግር ነው።
አቶ አንዳርጋቸው ፅጌም የኢህአዴግ አባል በነበሩበት ወቅት በ1985 ዓ.ም ባሳተሙት “የአማራ ህዝብ ከየት ወዴት?” በሚለው መፅሐፋቸው ላይ ቅይጥ ማንነት ያላቸውን ሰዎች “የማንነት ቀውስ ያለባቸው፣ በብሄር ድርጅቶች ውስጥ አስጠቂዎች፣ ለዘብተኞች፣ ግራ የተጋቡና ከብሄር ማንነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን የሚመርጡ ናቸው” በማለት ይኮንኗቸዋል። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያዊ ማንነት በትክክል የሚኖር ማንነት ሳይሆን ግራ የተጋቡ ቅይጥ ማንነቶች የፈጠሩት ምናባዊ ማንነት ነው እንደማለት ነው። አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ቅይጥ ማንነት እንዳለ ቢያምኑም ቁጥሩ ግን አጅግ አነስተኛ በመሆኑ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ ሊወጣ አይችልም የሚል እምነት ነበራቸው።
በዚህ ኢህአዴጋዊ ድምዳሜ ከሄድን፣ ትክክለኛውና በኢትዮጵያ ሊኖር የሚገባው ፖለቲካ ባልተቀየጡ ማንነቶች የሚመራው የብሄር ፖለቲካ ነው ማለት ነው። አቶ አንዳርጋቸው በወቅቱ እንደዛ ያሉት የኢትዮጵያን ህዝብ በኢህአዴግ መነፅር ስላዩት ነው። ከኢህአዴግ ከወጡ በኋላና የኢህአዴግን መነፅር አውልቀው “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭ”የሚለውን መፅሐፍ በ1997 ሲፅፉ ግን አቋማቸው ትክክል እንዳልነበረ አምነዋል። ራሳቸውም የዚህ ቅይጥ ማንነት ተጋሪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ኢህአዴግ ለቅይጥ ማንነቴዎች ትኩረት ባይሰጥም፣ ይህ ህዝብ ያለው ቁጥር ግን በጣም ብዙና አብዛኛውን የሀገሪቱን የተማረ ኃይል ያካተተ ነው፡፡ እናም ኢህአዴግ ለዚህ ሰፊ ህዝብ ዕውቅና ሲነፍግ በተዘዋዋሪ የሀገሪቱ ዋነኛ የሰለጠነ ኃይል ላይ ነበር የፈረደው፡፡
ይሄንን ደግሞ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት አቶ መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን በሰበሰቡበት ወቅት አቶ ሙሉጌታ ጉልማ ከተባሉ መምህር ተነግሯቸው ነበር፣ እንዲህ በማለት፡- ‹‹የብሄርን ነገር እንደ ማታገያ አድርጋችሁ ከሚገባው በላይ ስላጋነናችሁት ሰፊ ቁጥር ያለውን ቅይጥ ህዝብ እንዳታዩ አድርጓችኋል፡፡ ሆኖም ግን ቴክኖክራቱና ቢሮክራቱ ያለው እዚህ ውስጥ ነው፡፡ የብሄር ፖለቲካው እንዳለ ሆኖ፣ ይሄንን ቅይጥ ህዝብ የምታስተናግዱበትን ስርዓት ጎን ለጎን ካልዘረጋችሁና የሀገር ግንባታችሁ ላይ የማታሳትፉት ከሆነ አንድም ይሰደድባችኋል አሊያም በዝምታው ያምፅባችኋል›› ነበር ያሉት፡፡
ሆኖም ግን ኢህአዴግ ይሄንን የምሁራኑን ምክረ ሐሳብ ከመስማት ይልቅ ቅይጥ ማንነቴዎች የፖለቲካ ውክልና ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ሲያደናቅፍ ነው የኖረው፡፡ ኢህአዴግ ቅይጥ ማንነት የፖለቲካ ኃይል ሆኖ እንዳይወጣ ላለፉት 27 ዓመታት፣ ሦስት የማሸማቀቂያ ሥልቶችን ተጠቅሟል፡-
1ኛ - ከተሞችን የብሄርና የነፍጠኛ ከተሞች በማለትና ለሁለት በመክፈል፣ የቅይጥ ማንነት መፈጠሪያና መናኸሪያ የሆኑ አካባቢዎችን “የነፍጠኛ ከተሞች” በማለት ማሸማቀቅ፣
2ኛ - ይህ ህዝብ የፖለቲካ ውክልና ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት ‹‹በአንድነት ስም የተሸፈነ ስውር የአማራ አጀንዳ›› በማለት ማሸማቀቅ፣
3ኛ - ቅይጥ ማንነቴዎች በቀበሌ መታወቂያቸው ላይ ሳይቀር አንዱን ብሄር እንዲመርጡ ማስገደድ።
በእነዚህ ማሸማቀቂያ ስልቶችየተነሳ ላለፉት 27 ዓመታት፣ ይሄ ቅይጥነትና ዥንጉርጉርነት እውቅና ተነፍጎት አንገቱን ደፍቶ የኖረ ቢሆንም፣ የዶ/ር አብይ መመረጥን ተከትሎ ግን ቀና ቀና ማለት ጀምሯል፡፡ ይህ ህዝብ በአብዛኛው ከተሞች አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በብሄርና ሀገራዊ ጥያቄዎች ላይ ማመቻመች (Compromise ማድረግ) የሚችሉ ናቸው። አሁን ኦህዴድ ውስጥ ወደ አመራር የመጣው እንደዚህ ዓይነት ኃይል ነው። ዶ/ር አብይ ላይም የዘውግና ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነቶች ተስማምተውና ተዋህደው እያየን ነው፡፡ እንደ ሀገር የምናስብ ከሆነ፣ ሁሉንም ህዝቦች ሊያስማማና ሊያስታርቅ የሚችለው አማካዩ መንገድ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ነው፡፡

Read 5926 times