Sunday, 29 April 2018 00:00

በሙስና ወንጀል ተከሰው በቀጠሮ ላይ የሚገኙ ከ150 በላይ ተከሳሾች ለጠ/ሚ አቤቱታ አቀረቡ

Written by 
Rate this item
(5 votes)


             “የበላይ ባለስልጣናት በፈፀሙት ወንጀል እኛ ዋጋ እየከፈልን ነው”
            
      ባለፈው ሐምሌ ወር በተካሄደው የፀረ ሙስና ዘመቻና በተለያዩ ጊዜያት በልዩ ልዩ የሙስና ወንጀሎች ተከሰው ጉዳያቸው በፍ/ቤት እየታየ የሚገኘው 152 ተከሳሾች፤ ፍትህ ይሰጠን የሚል አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀረቡ፡፡
ጉዳያቸው በፍ/ቤት ቀጠሮ ላይ የሚገኘው እነዚህ የሙስና ወንጀል ተከሳሾች፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እንዲቀርብላቸው የላኩት የ152 እስረኞችን ፊርማ ያካተተ የአቤቱታ፤ ደብዳቤ ሲሆን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲደርስ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ለፍትህ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተመርቶላቸዋል፡፡
ተከሳሾቹ፤ በዚህ አቤቱታቸው ላይ እንደገለፁት፤ የሙስና ወንጀል ሳንፈፅም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የታሰርን ሰዎች በመሆናችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ፍትህ እንድናገኝ ሊያደርጉን ይገባል ብለዋል፡፡ “ትልልቆቹና ዋንኞቹ አሳዎች በሰሩት ሙስና እኛ ዋጋ ከፋይ ልንሆን አይገባም” ያሉት እነዚሁ ተከሳሾች፤ “አብዛኛዎችን የራሳችን የሆነ ምንም ነገር የሌለን በኪራይ ቤት የምንኖርና በወንጀል ሥራ ውስጥ ተሳትፎ ያላደረግን ሰዎች ነን” ብለዋል፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ዘመቻው የፖለቲካ መሆኑን ጠቁመው፤ ያለበቂ ማስረጃ ክስ ቀርቦባቸው ያለአግባብ እየተሰቃዩ መሆኑን በአቤቱታቸው ላይ ገልፀዋል፡፡ ፍርድ ቤቶች ያለ ተፅዕኖ በነፃነት ፍትህ እየሰጡን አይደለም ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ “ያለ ስራችን እጅግ አሳፋሪና ሞራላችንን የሚነካ ሙሰኞች የሚል ስም ተሰጥቶን በእስር እየተሰቃየን እንገኛለን፡፡ ስለዚህም ፍ/ቤቱ ነፃ ሆኖ የሚገባንን ፍትህ ይሰጠን ዘንድ እንጠይቃለን” ብለዋል፡፡
እነዚሁ አቤቱታ አቅራቢዎች በአቤቱታቸው ላይ እንደገለፁት፤ “አቃቤ ህግ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ አወጣሁ በሚላቸውና ትክክለኛውን የፍትህ ሂደት ባልጠበቁ የተለያዩ ማስረጃዎች ማቅረብ ሰበብ የማይገባንን ዋጋ እየከፈልን በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆኑን ለአቤቱታችን አፋጣኝ ምላሽ ይሰጡን ዘንድ እንጠይቃለን” ሲሉ ተማፅነዋል፡፡

Read 5891 times