Sunday, 29 April 2018 00:00

የጠ/ሚኒስትሩ ሥልጣን በህገ መንግስት ይገደባል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(25 votes)

 የአገሪቱ መሪዎች  የስልጣን ዘመን በህገ መንግስት የተገደበ እንዲሆን እንሰራለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ  አህመድ፤ ከዚህ በኋላ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ከሁለት ዙር በላይ በሥልጣን ላይ አይቆይም ብለዋል፡፡    
ከትናንት በስቲያ ከደቡብ ክልል የህዝብ ተወካዮች ጋር በሃዋሳ ሚሊኒየም አዳራሽ ውይይት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “በሀገሪቱ ያለው የዲሞክራሲያዊ ስርአት እየጎለበተ እንዲሄድ፣ የሃገር መሪዎች የስልጣን ዘመን በህገ መንግስቱ ጭምር የተገደበ እንዲሆን እንሰራለን” ብለዋል፡፡  
በውይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች የተሰነዘሩ ሲሆን አንድ አዛውንት፤ “ብሔርተኝነትን ያጥፉልን፣ የሃገር አንድነትን ይፍጠሩ” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩን አሳስበዋል፡፡ “ትልቅ ህዝቦች ነን፤ ነገር ግን ወደየጓዳችን እየገባን አንነስ” ብለዋል ዶ/ር ዐቢይ፡፡
በክልሉ ከተንሰራፋው የሙስና አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር ተያይዞም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄና አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ ከተለመደው ‹ሙስና› የሚል የኢህአዴግ አጠራር ይልቅ ‹ሌብነት› ብለው መጥራት የሚደፍሩት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ “ሌብነት ለጊዜው የሚጠቅም ቢመስልም በመጨረሻ ተቀባዩንም ሰጪውንም ይጥለዋል” ብለዋል። “ሌብነት ክፉ ሥራ ነው፤ ቤተሰብ ያፈርሳል፡፡ ሌብነት ካለ ዲሞክራሲ አያስፈልግም፤ ማፈን ነው፤ ሌብነት ካለ ፍትህ በገንዘብ ነው የሚገዛው…” ሲሉ ሌብነት በበዛበት አገር የሚፈጠረውን ሥርዓት አሳይተዋል - በንግግራቸው፡፡    
ለቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተደረገውን ይፋዊ የክብር አሸኛኘት አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በሰጡት ምላሽ፤ “ለአቶ ኃ/ማርያም የተሰጣቸው እውቅና ዓላማው፤ ስልጣንን የሞትና የሽረት ጉዳይ አድርገው ለተቸገሩ ባለስልጣናት እናንተም ስልጣን በሰላም ብትለቁ ይሄው ክብር ነው የሚጠብቃችሁ ብሎ ለማስተማር ነው” ብለዋል፡፡
“አንዳንዶች በእሳቸው ጊዜ ሰው ሞቶብን እንዴት ይሸለማሉ” የሚል ቅሬታ እንዳላቸው የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤”በተፈጠረው ነገር እንደ ፓርቲም እንደ መንግስትም ይቅርታ ጠይቀናል፤ አሁንም እንጠይቃለን፤በግጭቱ ለተጎዱት ወገኖች ማድረግ የሚገባንንና አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
“አቶ ኃይለማርያም እንኳንስ ሰው ሊገድሉ፣ ሰው በሚሞትበት ጊዜ አብረው ቁጭ ብለው የሚያለቀሱ እጅግ ሩህሩሀ ሰው ናቸው” ሲሉም ብዙዎች የማያውቁትን የአቶ ኃ/ማርያም ገፅታ አሳይተዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ውስጥ ነገስታት የሉም፤ህዝብን የሚያገለግሉ፣ በህዝብ የተመረጡ፣ ሌብነትን የሚጠየፉ፣ከሥልጣን ወርደው ከህዝብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ መሪዎች ነው መሆን ያለባቸው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤”እያደገች ያለች አገር ስለሆነች ጥቂት ሰዎች ለረዥም ዘመን ሥልጣን ላይ ሊቀመጡ አይችሉም፤ከአሁን በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሁለት ዙር በላይ ስልጣን ላይ አይቆይም፤ ህገ መንግስቱን የማሻሻል ሥራዎች ይሰራል” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስቲያ በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስቴዲየም ከ30 ሺ የማያንሱ ከተማዋና አጎራባች አካባቢዎች የመጡ ሰዎች ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን የሲዳማ የሃገር ሽማግሌዎችም በልዩ የምርቃት ሥነሥርዓት ተቀብለዋቸዋል፡፡

Read 9193 times