Monday, 07 May 2018 08:46

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተባብሷል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

· በየዕለቱ በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ብቻ ከአንድ ሺ በላይ ዜጎች በቱሪስት ቪዛ ይወጣሉ
· ከኩዌት፣ ከአረብ ኢምሬትስ ጋር የስራ ስምሪት ስምምነት አልተፈረመም፡፡
· ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ጋር የተፈረመው ስምምነት፣ በተወካዮች ምክር ቤት አልፀደቀም
· ከኳታርና ጆርዳን ጋር የተፈረመው ስምምነትም ተግባራዊ መሆን አልጀመረም
         
    ከጥቅምት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተጥሎ የነበረው የውጪ አገር የስራ ስምሪት እግድ መነሳቱ ይፋ ከተደረገ ጊዜ ጀምሮ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በከፍተኛ መጠን መጨመሩንና በየዕለቱም በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ብቻ ከአንድ ሺ በላይ ዜጎች፣ በቱሪስት ቪዛ ከአገር እየወጡ ነው ተባለ፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ፤ በህጋዊነት ስም ወደ ውጪ በሚሄዱ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት አስመልክቶ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፤ አንዳንድ ህገ ወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች፣ ኢትዮጵያ የተፈራረመቻቸው ሰምምነቶች ተግባራዊ መደረግ ሳይጀምሩ እንደተጀመሩ አስመስለው፣ ዜጎችን በማጭበርበር በቱሪስት ቪዛ ወደ ውጭ አገር እየላኩ ይገኛሉ፡፡
የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ዓለማየሁ፤ በየዕለቱ በቱሪስት ቪዛ በቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ብቻ ከአንድ ሺ አንድ መቶ በላይ ዜጎች ከአገር እየወጡ ነው ብለዋል፡፡
“ተጓዦቹ የሚይዙት ቪዛ ለጉብኝት ብቻ የሚያገለግልና እንደየአገራቱ የአሰራር መመሪያ መሰረት ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወራት ብቻ የሚያገለግል ቢሆንም ዜጎች “ለሥራ ስምሪት ቪዛውን ይዘው ከአገር በመውጣት ህገ ወጦች እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ” ያሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ “በተለይም የአረብ አገራት የስራ ስምሪት ጉዞ ተጀመረ የሚል መረጃ በየሚዲያው ከተሰራጨ በኋላ፣ ሁኔታው እጅግ ተባብሶ ቀጥሏል” ብለዋል፡፡
ዕድሜያቸው ገና 18 ዓመት ያልሞላቸው ልጆች ሁሉ በህገ ወጦች ተደልለውና ተገፋፍተው ወደተለያዩ የአረብ አገራት በህገ ወጥ መንገድ እየተላኩ መሆኑንም ምክትል ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምሪያ፤ ዕድሜያቸው 18 ዓመት ላልሞላቸው ልጆች ፓስፖርት የሚሰጠው በምን አግባብ ነው በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም፤ ሲመልሱ፤ “አንድ ዜጋ ፓስፖርት ለማውጣት የሚጠየቀው የመጀመሪውና ብቸኛው መረጃ ህጋዊ የቀበሌ የመታወቂያ ወረቀት ነው፡፡ በመታወቂያው ላይ የተገለፀውን የዕድሜ መረጃ ብቻ በመጠቀም ለጠየቀው ሰው ፓስፖርቱን እንሰጣለን፡፡ መታወቂያው ላይ የሰፈረው ዕድሜ ትክክለኛ መሆኑንና አለመሆኑን ልናረጋግጥ የምንችልበት ምንም ዓይነት መንገድ የለንም” ብለዋል፡፡ “አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው ከአቅማችን በላይ ሲሆንና ለማመን በጣም ስንቸገር መታወቂያውን ለሰጠው አካል መታወቂያውን ከደብዳቤ ጋር እንልክና ማጣሪያ አድርጋችሁ ምላሽ ስጡን እንላለን፡፡ ግን እስከ አሁን ድረስ አንድም መስተዳድር ምላሽ አልሰጠንም” ያሉት ኃላፊው፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በዋና መምሪያው በኩል የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገው እንደነበር የገለፁት አቶ መንግስቱ፤ ሁኔታው ለሙስናና ለሌሎች ብልሹ አሰራሮች የሚያጋልጥ በመሆኑ እንዲቀር መደረጉንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ችግሩ ሊፈታ የሚችለው ብሔራዊ የመታወቂያ ወረቀት ለዜጎች እንዲሰጥ ሲደረግ መሆኑንም አቶ መንግስቱ አክለው ገልፀዋል፡፡
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የውጪ አገር ስራ ስምሪት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ አበራ፤ ዜጎች በህጋዊ መንገድ በውጪ አገር ለመስራት ዕድሜያቸው ቢያንስ 18 ዓመት የሆነ፣ የትምህርት ደረጃቸው ቢያንስ ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቁ፣ በሚሄዱበት አገር ለስራ የሚያግዛቸው በቂ ክህሎት ያላቸውና ስልጠና የወሰዱ፣ እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫ የያዙ መሆን ይኖርባቸዋል” ብለዋል፡፡ እነዚህ ተጓዦችም በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ልዩ መታወቂያ እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ ከዚህ ውጪ የሚደረገው ጉዞ ህገ ወጥና ዜጎችን ለተለያዩ ችግሮች የሚያጋልጥ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ዜጎችን ለውጭ አገር ስራ ስምሪት የሚመለምሉ ኤጀንሲዎች ህጋዊ እውቅና ያላቸውና ስራውን ለመስራት የሚያስችላቸውን መስፈርቶች ያሟሉ መሆን ያለባቸው ሲሆን ዜጎችን ለስራ በሚመለምሉባቸው ክልሎች ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ከፍተው የሚሰሩ ሊሆንም ይገባል ብለዋል አቶ ብርሃኑ፡፡
ኢትዮጵያ የዜጎችን በውጪ አገር የመስራት መብት ከማስከበር አኳያ ከኳታርና ጆርዳን መንግስታት ጋር የተፈራረመቻቸው ህጋዊ የውጪ አገር የሥራ ስምሪት ስምምነቶች ማፅደቋን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከሳኡዲ አረቢያ መንግስትም ጋር የተፈረመው ስምምነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ ከኩዌት ሊባኖስና የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋር ገና በድርድር ላይ እንደሚገኙም አቶ ብርሃኑ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
“አንዳንድ ህገ ወጥ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች፣ እነዚህን ገና ተግባራዊ መሆን ያልጀመሩና ሥራ ላይ ያልዋሉ ስምምነቶችን ተግባራዊ እንደሆኑ በማስመሰል፣ ዜጎችን በማጭበርበር በቱሪስት ቪዛ እየላኩ መሆኑን ደርሰንበታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ “ዜጎች ከእነዚህ አደገኛና ህገ ወጥ አዘዋዋሪች ሊጠነቀቁ ይገባል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ህጋዊ በሚመስል ህገ ወጥ መንገድ የሚደረገው ጉዞ፤ በረሃዎችንና ውቂያኖሶችን አቋርጦ ከመሄድ ያልተለየና የዜጎችን ህይወት እጅግ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑንም የሥራ ኃላፊዎቹ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡

Read 3229 times