Saturday, 05 May 2018 00:00

ጠ/ሚኒስትሩ ከካርቱም ወደ ባሌ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

 · ዛሬ በባሌ ሮቤ ስቴዲየም ንግግር ያደርጋሉ፤ ህዝብ ያወያያሉ
 · ኢትዮጵያ በሱዳን ወደብ ባለድርሻ እንድትሆን ስምምነት ተፈረመ
 · በሱዳን ታስረው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይፈታሉ ተባለ


    በሱዳን የሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ኢትዮጵያ በሱዳን ወደብ ባለድርሻ እንድትሆን ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፣ ከፕሬዚዳንት አልበሽር ጋር በጋራ የመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል። በሌላ በኩል በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞች እንዲፈቱ የጠየቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አፋጣኝ አዎንታዊ መልስ አግኝተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት አልበሽር ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ታሳሪዎች እንደሚፈቱ ለጠ/ሚኒስትሩ ማረጋገጫ ሰጥተዋቸዋል - ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፡፡
ዶ/ር አብይ ለጅቡቲ ያቀረቡትን የወደብ ድርሻ ጥያቄ፣ ለሱዳንም ያቀረቡ ሲሆን የሱዳን መንግስትም ጥያቄውን ተቀብሎ፣ ኢትዮጵያ በሱዳን ወደብ ድርሻ እንዲኖራት መስማማቱ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ በወደቡ ላይ ምን ያህል ድርሻ ይኖራታል የሚለው ዝርዝር ጉዳይ ወደፊት በሚደረጉ ተጨማሪ ስምምነቶች የሚፈፀም ይሆናል ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ አዳዲስ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ተገኝተዋል ብለዋል፡፡
“ሱዳን እና ኢትዮጵያ የተፈራረሙት የወደብ ድርሻ ስምምነት፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የገዥና ሻጭ አይነት ሳይሆን በጋራ አልምቶ፣ በጋራ የማስተዳደር እድልን የሚፈጥር ነው” ብለዋል - አቶ መለስ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው፤ ሱዳን ወደቧን ለኢትዮጵያ ለማጋራት በመፍቀዷ፣ የወደብ ልማቱና በጋራ የማስተዳደር ስራው በአፋጣኝ ይጀመራል ብለዋል፡፡ የሁለቱ ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ በጋራ ድንበራቸው አካባቢ ነፃ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር መስማማታቸውም ተጠቁሟል፡፡
በትላንትናው ዕለት ከሱዳን የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬ ወደ ኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በማቅናት፣ በሮቤ ስታዲየም ለህዝብ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን 800 ከሚደርሱ የህዝብ ተወካዮች ጋር ይወያያሉ ተብሏል፡፡
በጠ/ሚኒስትርነት በተሾሙ ማግስት ወደ ሶማሌ ክልል የተጓዙት ዶ/ር ዐቢይ፤ እያንዳንዷን ቀን ትርፋማ ለማድረግ እየተጉ ይገኛሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙም ዛሬ 33ኛ ቀንናቸውን ይዘዋል፡፡ የመጀመርያ የውጭ አገር ጉብኝታቸውን በጅቡቲ ያደረጉት ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራትና ወደቡን በጋራ ለመጠቀም ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ጅቡቲም በቴሌኮም መስክ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንድታደርግ ጋብዘዋል፡፡ የወደብ ድርሻ ጥያቄያቸውም በጅቡቲ በኩል በመርህ ደረጃ ተቀባይነት ማግኘቱ ተገልጿል፡፡

Read 4778 times