Monday, 07 May 2018 09:15

ኦ! ጎግ ማጎግ

Written by  ቤተማርያም ተሾመ betishk@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

      (ወዮ ለሩሲያ! እግዚኦ ለፑቲን)
             
    (የሃገር እንደ ሃገር  የመቀጠል ጥያቄ ከታጠቃቸው ሃገር አቋራጭ ሚሳኤሎች የመወንጨፍ እርቀት እና ከሚሸክፏቸው፡ የኒውክሊየር አረሮች አውዳሚነት ጋር መሳ ለመሳ ተዛማጅ ሆኗል፤  እንደ ሃገር ለመቀጠል በኒውክሊየር መርሃ-ግብር እራስን መቻል ግድ ሆኗል)
ፖለቲካው አብዷል፡፡ መደማመጥ እርቋል፤ እዚህም እዚያም  በውሃ ቀጠነ ሰበብ ተግ! ተግ!  የሚሉ ጦርነቶች የየዕለት ህይወታችን አካል ሆነዋል። እልቂትና ጦርነት ማስደንገጣቸው እየቀነሰ ነው፤ በሰላም አድረው የነበሩ ሃገራት ከካርታ ላይ ተደምስሰው ፍርስራሽ ሆነው ጠፍተው የማደር ዜና በጣም እየተደጋገመ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ስልጡኑ ሰው፤ ከባድ የነገ ፍርሃት ውስጥ ወድቋል፡፡ የጠዋትዋን ጀንበር ስለማየቱ እርግጠኛ አይደለም፡፡ አርቆ ማቀድ ትቶ፣ ሮኬት አርቆ ስለመተኮስ ሲያውጠነጥን ያድራል፡፡ አዳሩን የሶሪያን አሊያም የሊቢያን ፅዋ ላለመጠጣቱ ማንም፣ ምንም፣ ማረጋገጫ አይሰጠውም፤ የቀን ውሎውና ሁኔታው እንደ ነውጠኛውና ድንቡሽቡሹ ኪም ጆንግ፤ አሊያም እንደ ፑቲን ስሜት የሚቀያየር ሆኗል (ክፋቱ ደግሞ እንደ ሀገሩ በረዶ የቀዘቀዘውን የፑቲንን ገፅታ መረዳት መክበዱ)፡፡
“ስልጡኑ” ሰው፣ አብሮ የመኖርን፣ ችግርን ተነጋግሮ የመፍታትን ነባር ጥበብ ፈፅሞ የረሳው ይመስላል፡፡ ከክብ ጠረጴዛ ውይይት ይልቅ  ክብ ቦንቦችን ከአየር ላይ እያዘነበ፣ ሃሳቡን መግለፅ ፋሽን አድርጎታል፡፡
የሃገር እንደ ሃገር  የመቀጠል ጥያቄ ከታጠቃቸው ሃገር አቋራጭ ሚሳኤሎች፣ የመወንጨፍ እርቀትና ከሚሸክፏቸው የኒውክሊየር  አረሮች አውዳሚነት ጋር መሳ ለመሳ ተዛማጅ ሆኗል፡፡ እንደ ሃገር ለመቀጠል በኒውክሊየር መርሃ ግብር እራስን መቻል ግድ ሆኗል፡፡ ቅጥ ያጣው የሃገራት መርህ አልባ ግንኙነት፣ የምድርን መፃኢ እድል በሳይንሳዊ መልኩ መተንበይ የማይታሰብና ከባድ  አድርጎታል፡፡ የሃገራ እድልና የጉዞ አቅጣጫ  በባለ ኒውክሊየር ጎረቤታቸው መዳፍ ውስጥ ወድቋል፡፡
የዘመናት የሰው ዘር “መቼ ምን ይሆናል?” የጥያቄ አዙሪትና ፍርሃት፣ ዙሩን እያጠበበ፣ አፍንጫው ስር ደርሷል፡፡ መጻኢ እድል ፈንታው፣ በወፈፌና ስሜታዊ ሃያላን መዳፍ ውሰጥ ወድቋል፡፡ “ለምን ጮክ ብለህ አወራኸኝ!”፣ “ለምን ባልንጀራዬን ገላመጥክብኝ!” በሚሉ አይነት ተልካሻ ምክንያቶች ሳቢያ በሚቀሰቀሱ አምባ ጓሮዎች ሰበብ፣ በየሚዲያው በመፎከር፤ ኒውክሌየር ማቀባበል፤ ጠብደል  ቦምብ መወራወር፣ የየእለት ተግባራት ሆነዋል፡፡ ይህ ግራ ክስተት ግራ ያጋባው የሰው ዘር፣ ቀድሞ “ኮንስፓይሬሲ” እያለ ያጣጣለውን የቅዱስ መጽሐፍ ትንቢቶች፣ እንደ አማራጭ እንዲያስብና እንዲከልስ አስገድዶታል፡፡
በእነዚህም መካከል ከዘመናት በፊት በነብዪ ህዝቅኤል የተተነበየው የታላቁና አይቀሬው የጎግ ማጎግ ጦርነት ዋናው ሲሆን ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳትና የድንገቴ የሃገራት መቧደን  ተነስተው “የነብዩ ትንቢት እየያዘለት ነው” የሚሉ የነገረ ፍጻሜ ምሁራን፤ ስለ አይቀሬው የጎግ ማንጎግ ጦርነትና ስለ ዋናው ተዋናይ ጎግ ማንነትና ወቅታዊ አድራሻ  መላ  እየመቱ ነው፡፡
ጎግ ማነው? ማጎግስ?    
የሰው ልጅ ሆይ፤ በጎግ ላይ እና በማጎግ ምድር ላይ በሞሳህ እና ቶቤል ዋነኛ አለቃ ላይ አቅናባት ትንቢትም ተናገርበት፤
ህዝ 38፤2
ይህ ጥቅስ ጎግ ስለተባለ የወረራ መሪ እና ማጎግ ስለተባለ ግዛቱ ያወራል፡፡ መፅሐፉን ስንመረምር ጎግ ከያፊት ልጆች አንዱ እንደሆነ እና በምድር በስተሰሜን እንደሰፈረ ብዙ ድርሳናት ያትታሉ፡፡ ጎግ የሮሽ ምድር ንጉስ እንዲሁም ሞሳህና ቶቤል የተባሉ በእስያ ያሉ ቦታዎች ገዢ እንደሆነም እናነባለን፡፡ ተያይዘውም የተደረጉ ጥናቶችና የስነቃል መረጃዎች፤ ጎግ የዛሬዋ ሩሲያ እንደሆነች ያስረዳሉ፡፡
በህዝቅኤል የተጠቀሱት የሮሽ ምድር የዛሬዋ  ሩሲያ፤ ቶቤል (ቱቢል) የአሁንዋ ቱብሊሰክ እንዲሁም  ሞሳህ (ማሴክ) መዲናቸው ሞስኮ የተጠሩበት ጥንታዊ ስማቸው መሆኑን የስነቃልን ምንጮችን ጠቅሰው  ያስረዳሉ፡፡ ይህ ታላቅ መሪ (ጎግ) ሚጢጢዋን እስራኤል የመውረር እቅዱን የሚከውነው  በዛው መፅሃፍ በግልፅ በስም ከተጠቀሱ ግብረ አበሮቹ ጋር ሲሆን የእነዚህን ሀገራት ወቅታዊ ሁኔታ ስንመለከትም፣ በቅርብ ጊዜ ሊቋቋም የዳዳውን የሩሲያ ፓን ኢስላሚክ ህብረት ምስረታ አይቀሬነት ያስረግጣል ይላሉ፤ ምሁራን፡፡
ወቅታዊ ሁኔታው ምን ያሳየናል?
የጎግ ማጎግ ጦርነት ከፍ ብሎ አለምን የወረረው የክህደት ሃሳብ (ኮሚኒዝም) ቀፍቃፊና ጠንሳሽ  በሆነችው ሩሲያና ግብረ አበሮቿ፤ የመንፈሳዊ ሃሳቦች መናገሻ በሆነችው ሚጢጢዋ እስራኤል መካከል የሚደረግ የምድር ሁሉ ጦርነቶች ማሳረጊያ ነው፡፡ ይህ ጦርነት የመላእክት ክንፍ የሚያፏጭበት፣ እሳትና መብረቅ የሚንጎዳጎድበት መንፈሳዊ ጦርነት አይደለም። በአይናችን በብረቱ እያየን የሚከወን ምናልባትም ኒውክሊየርን ያካተተ ድብልቅልቅ ያለ ጦርነት እንጂ፡፡
የዚህን ጦርነት አይቀሬነት የሚያመላክቱ ሶሺዮ-ፖለቲካል ክስተቶች በግልፅ መታየት ጀምረዋል። የወቅቱን የሩሲያ የኢኮኖሚ ሁኔታና ክፉኛ የተጠናወታትን የነዳጅ ሱስ በመታዘብ (ያው ነዳጅ ካለ ደግሞ እሳት አለ)፤ ከመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት በተለይም ከጥንቷ ባቢሎን ከዛሬዋ ኢራን ጋር የጀመሩት ከአይን የዘለለ ፍቅር፣ እንደ ውቃቢ ደርሶ የተጠናወታት (ያገረሸባት) የተሰሚነት (የማን አለብኝነት) ዛር (በነገራችን ላይ የመንግስታቸውም ስያሜ ዛር ይሰኛል) ማስተዋል በቂ ነው፡፡
በባለፈው የምረጡኝ ቅስቀሳው፤ ያ ቁጥብና በዝምታው የምናውቀው ፑቲን፤ በነውጠኛ ምስሎችና  ቪዲዮ ታጅቦ “ቡራ ከረዩ፤ ያዙኝ ልቀቁኝ፤ እያንዳንድሽ ወየውልሽ፤ የእኛ ሚሳኤልና የኒውክሊየር አረር የማይደርስበት አንድም ስምጥ አንድም ስርጥ የለም፤ ነብር አየኝ በሉ” አይነት ዛቻው፣ በጤናው ነው ትላላችሁ? (ነው ዛሩ እያስጓራው)፡፡
ጎግ ከአይን ጥቅሻና ከማሽኮርመም በዘለለ ከወደፊት ግብረ-አበሮቹ ጋር እውር አይነት ፍቅሩን እያጧጧፈ ነው፡፡ ዘመናት የተሻገረና በፑሽኪን ሳቢያ በደም የተቋጠረ የሀገሬና ሩሲያ ፍቅርም አሳሰበኝ፡፡
ያም ሆነ ይህ የፑቲኗ ሀገር  የሮሽ ምድሯ ሩሲያ፤ ከነዳጅ አጣጭ (ውሃ አጣጭ ከሚለው የተወሰደ) የመካከለኛው ምስራቅና ከሰሜን አፍሪቃ ግብረ አበሮችዋ ጋር የምድራችንን ስትራቴጂካዊ ቦታ ሚጢጢዋን እስራኤልን በመውረር የነዳጅና የሃያልነት ጥማቸውን ለማርካት  ይተምማሉ፡፡ “ደባዬ! እፓሲቫ!፤ ካራሾ!” ምናምን ብለው ፎክረው (የፉከራ ቃላት አይደሉም ዝም ብለው፣ የማውቃቸው የሩሲያ ቃላት ናቸው) ከዘመናት በፊት ወደተቆረጠው ታላቅ ጦርነት ዘልለው ይገባሉ ይለናል፤ ነብዩ ኢዩኢል፣ በ38ኛ ምዕራፉ፡፡ እና ምን አገባን፤ እዛው በጠበላቸው እንዳትሉ። ጦሱ የሁሉም ነው፤ ውጊያው የኒውክሌር ነዋ! መቼ በዚህ ያልፍልናል፡፡ ጎግን አጅበው “በል በል ዘራፍ  ዘራፍ” ከሚሉት ሃገራት ስም ዝርዝር ውስጥ ከእነ ሊቢያ፣ ቱርክና ኢራን ጋር፣ የእናት ሃገራችን ስምም ተካትቷል፡፡ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን (የፑቲንም ይደፈን!)፡፡ እናም የኢትዮ ሩሲያን ስር የሰደደ ጥብቅ ግንኙነት መለስ ብዬ ቃኘሁት፤ በህብረተሰባዊነት ርእዮተ አለም ፍልስፍና ተጭኖ በቀይ ባንዲራ ተጀቡኖ ገብቶ ያመሰንን ቀይ ሽብርን የከሰተ፣ ቀይ ስህተት አስታወስኩ (ወላጆቼ ሲያወሩ ሰማሁ)፡፡ በቅርቡ  ተሰናባቹ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝትን እግር ለእግር ተከትሎ (እንደ ሃይሌ እና ፖል ቴርጋት) ድንገት ዘው ያለው የሰርጌይ ላቭሮቭ ጉብኝት፤ አንዳች ነገር ጫረብኝ። ለማንኛውም ይሄንን ትንታኔ ተከትሎ፣ ሃገራችን ከሩሲያ ጋር የምታደርጋቸውን ቀጣይ ግንኙነቶች መከለስ ሳይኖርባት አይቀርም፡፡ ሰላም ያቆየን!

Read 3214 times