Print this page
Monday, 07 May 2018 09:19

በ‹ንክ ዙፋን› ንጉሥ

Written by  ፈለቀ አበበ arthabesha@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

   (‹‹ስብሐት ለአብ - ሪ ሚክስ››)
               
     (ስብሐት ለአብ  ገ/እግዚአብሔር
 ሚያዚያ 27 ቀን 1928 -የካቲት 12 ቀን 2004)

ዝክረ ስብሐት ለአብ
‹‹በየንታ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆርበት›› ከልጅነት እድሜያችን ጀምሮ፤ እርሱ ጠጁን፡ የደግ አንደበቱ በሚያስተጋባበት ጉሮሮ፤ እኛ ወጉን፡ ለማወቅ በጉጉት በጦዘ ጆሮ እያንቆረቆርን ባሳለፍናቸው ዓመታት፤ የጠፋውን ጥንታዊ የዓለም ስልጣኔ አንቅተው ለሰው ዘር ያቀበሉ ናቸው ከሚላቸው The world’s oldest ciVilizations, remoulded by the Romans ከሮማዊያን ድንቃ ድንቅ ታሪኮች መካከል በተለይ ደጋግሞ ባወጋልንና ‹‹እብድ ቤተሰብ›› እንደነበሩ፤ ሆኖም ግን እብደታቸው ለየት ማለቱን እያንቆለጳጰሰ በነገረን በሮማዊያን ገዢዎች ታሪክ እንዘክረዋለን፡፡ በየመሀሉም ከእርሱው ጣፋጭ ወግ ይኸውም በወተት ጥርስ የንባብ አቅማችን መቆርጠም/ልንደርስበት ያልተቻለንን እየቆነጠርን እናክልበታለን፡፡ (ድንገት ትውስታው ደብዝዞ ከገደፍንም ለ‹አፉ› እንቆማለን፡፡) ጋሽ ስብሐትን ልዩ የሚያደርገውም ይኸው ነውና፤ ዛሬ እንኳን በሰከንድ ክፍልፋይ ማንኛውንም ተፈላጊ መረጃ ለማግኘት በሚቻልበት የቴክኖሎጂ ዘመን፤አንዳንዶቹ እርሱ የነገረን ታሪኮች ተፈልገው መገኘት ያለመቻላቸው ጉዳይ ሲታይ፤ የኔታ ስብሀት ምን ያክል አብላጫ የእድሜ ዘመኑን በመጻሕፍት ገጾች ውስጥ ተከትቶ መኖሩን አመላካች ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል አንድ እንደ እርሱ ያለ አዛውንት ሲያልፍ፤ አንድ ትልቅ ቤተ መዘክር እንደተቃጠለ ይቆጠራል መባሉ፡፡ ነፍስ ይማር የኔታ! እያልን፤ ወደዚህች ምድር የመጣባትን የዛሬዋን ቀን ለማሰብ (ከሞቱ - በልደቱ) እነሆ ...
‹ንክ ዙፋኑ›
የ‹‹እብዶቹ›› ነገሥታት ስርወ መንግሥት (Julio-Claudian dynasty) ከክ.ል.በ 27 ጀምሮ እስከ 68 ዓ.ም ድረስ ለ94 ዓመታት የዘለቀ ነበር፡፡ በዚህም ረዥም ዘመን ከአውጉስተስ ቄሳር እስከ ንጉሥ ኔሮ አምስት ንጉሠ ነገሥታት በ ‹ንክ ዙፋኑ› ላይ ተቀምጠውበታል። የሥርወ መንግሥቱ መጠሪያ Julio-Claudian dynasty የተሰኘው ከጁሊ ሲዛራዊያን Julii Caesares እና ከክላውዲያዊያን Claudii Nerones የተመዘዙ ዝርያዎች ጥምረት የፈጠረው ስልጣን ስለነበረ ነው። ነገሥታቱ ከሰውነት ይልቅ ራሳቸውን ወደ መመለክ ደረጃ ሲነዱትና ፈላጭ ቆራጭነታቸውም ከዚሁ ሲመነጭ፤ ፍጻሜያቸውም የዚያው ውጤት ሲሆን እናስተውላለን፡፡ በሕዝቡና ነገሥታቱ መካከል የነበረው የማያቋርጥ የገዢና ተገዢ ምስልም በጉልህ ይነበባል፡፡ የነገሥታቱ ታሪክ በአለም ዙሪያ በልዩ ልዩ ድርሰቶች፣ ተውኔቶችና የምስል ወ ድምጽ...ወዘተ. ተሰርተው ከፍተኛ ዝናን የተቀዳጁትም በዚሁ ተዝቆ በማያልቀው ዘርፈ ብዙ የታሪክ እሴታቸው የተነሳ ነው። ምንም እንኳ እዚህ የምናነብበው እጅግ ብዙ ከሆነው ድርሳናቸው አንጻር ከቶም ቁጥር ባይገባም . . .
ኦውጉስተስ ቄሳር
አያቱ ዝነኛ ወታደር ነበረ፡፡ እርሱ ደግሞ በቀድሞው ንጉሠ ነገሥት በጁሊየስ ቄሳር እጅ አደገ፡፡ አሳዳጊው በሚያምናቸው ቅርብ ወዳጆቹ ሲገደል፤ በ36 አመት እድሜው ዙፋኑን ወረሰና የጁሊዮ ክላውዲያን ስርወ መንግስት መስራችና ቀዳማይ ንጉሠ ነገሥት ሆነ። አውጉስተስ ወደ ዙፋን ከመጣ በኋላ ያለ ማቋረጥ ስሙን በማሳመር የተጠመደ ይመስላል፡፡ በመጀመሪያ ኦክታቪየስ የነበረውን Gaius Octavius Thurinus የልደት ስሙን በቄሳር የማደጎ ልጅነቱ አሳብቦ ወደ Gaius Julius Caesar Octavianus ቀየረ፡፡ አመታት ቆይቶ Gaius Julius Caesar Divi Filius የመለኮት ውላጅ የሚል ቀጠለበት፡፡ አሁንም አመታት አዝግሞ ደግሞ Imperator Caesar Divi Filius ገናናው ቄሳር -  የአምላክ ልጅ ብሎ ራሱን ሰየመ፡፡ አሁንም እንደገና ሰነባበተና አውጉስተስ - ‹‹ጽንፍ የለህ›› እሚል ቆለለበት Imperator Caesar Divi Filius Augustus.
አሁን እንግዲህ የስም ነገር ተቀባብቶ አብቅቷል፤ የሚቀረው መግዛት ብቻ ነው - ምናልባት ይህን  ባለበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም፤ በቅኝ ግዛታቸው ‹‹በይሁዳ ቤተልሄም ንጉሥ ተወለደ!›› የሚባል ዜና የሚሰማው። በዚያን ጊዜ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ንጉሡ ሄሮድስ እንዲያ ክው ብሎ ከደነገጠ፡ የንጉሠ ነገሥቱን ድንጋጤ አባዝቶ ማስላት ይቻላል፡፡ እናም ለ27 አመታት ተደላድሎ ከተቀመጠበት እልፍኙ ሆኖ ባስተላለፈው ቀጭን ትእዛዝ፤ ተወልዷል የተባለው  የአይሁድ ንጉሥ ዳናው ስለጠፋ፤ ለሁለት አመት ያህል ሌት ተቀን በዚያ ዙፋን ላይ ሆኖ ‹‹በታላቅ ብልሀት›› ተብሰልስሎ የደረሰበትን መላ ሄሮድስ እንደምን እንደፈጸመውም ተጽፎልናል፡፡ በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። አዎን! ሕጻኑን ንጉሥ ማግኘት ካልተቻለ በእርሱ እድሜ ያሉ የግዛቱን ነዋሪዎች ጨቅላ ሕጻናት ሁሉ መግደል፡፡ በቃ! (‹‹እንትኑን ለማጥፋት ቤቱን የማቃጠል!›› አይነት ድንቅ መላ!) ያኔ ግን ኢየሱስ ከእናቱ ድንግል ማርያምና ከእጮኛዋ ዮሴፍ ጋር በግብጽ ምድር ነበረ፡፡ ፉርሽ!
አውጉስተስ ቄሳርም ልክ እንደ አሳዳጊው ጁሊየስ ቄሳር በሚያምነው የቅርቡ ሰው እጅ ከመሞት አልቀረለትም፡፡ በ75 አመት እድሜው ታምሞ ሲሞት፣ ለህመሙ/ሞቱ ምክንያት ተደርጋ ‹‹መርዝ ሰጥታ ገደለችው›› ተብላ በሀሜት የተብጠለጠለችው የእርሱው ሚስት ሊቪያ Livia ነበረች፡፡እነሆ አውጉስተስ የራማ ሕጻናት እሪታ፣ የእናቶቻቸው ዋይታ በሩቁ ባለው ዙፋኑ እልፍኝ ውስጥ እየጮኸበት 12 አመታትን ቆይቶ ባጠቃላይ (ከክ.ል.በ 27 እስከ 14 ዓ.ም) 40 አመታት ገዝቶ ዙፋኑን ለጢባርየስ ትቶ አለፈ፡፡
ጢባርየስ ቄሳር
ወደ ዙፋኑ ሲመጣ እድሜው 56 ደርሶ ነበር። ከዚያም ለ23 አመታት፣ በንጉሠ ነገሥትነት ቆይቶ (ከ14-37 ዓ.ም) በ78 አመት እድሜው አዛውንቱ ከማለፉ በፊትም በአቅም ማነስ ራሱን ከፖሊቲካ ለማራቅ የተገደደ ይመስላል፡፡ ለመሞት አንድ አመት ሲቀረውም በወራሹ በካሊጉላ አማካኝነት ከእልፍኙ ተገልሏል፡፡
ጢባሪየስ እንደ ሌሎቹ ነገሥታት እንደ አምላክ ለመመለክ አይፈልግም ነበር፡፡ በስሙ ቤተ መቅደስ እንዲሰራለት ሲጠይቁትም አልፈቀደም፤ ይልቅስ በስሙ አንዲት ከተማ ይሰየም ዘንድ ፈቅዶ ዛሬም ድረስ በዘመናዊቷ እስራኤል ምድር የምትገኝ ከገሊላ ወንዝ ማዶ ያለች ከተማን ሄሮድስ አንቲፓ Tiberias ጢባሪየስ ብሎ በስሙ ሰይሞለታል፡፡
የጢባርየስ የንግሥና ዘመን ኢየሱስ በምድር የተመላለሰበትና እርሱም ከሮማ ሆኖ እሚያስተላልፈውን ትእዛዝ በጲላጦስ አማካይነት ሲያስፈጽም የነበረበት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ታዲያ በመጨረሻም ከሞቱ አራት አመት በፊት ኢየሱስ ተሰቅሎ፣ በሦስት ቀን ውስጥ ትንሣኤ ማድረጉንም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
አሁን ከጋሽ ስብሀት ወጎች አንዱን እንምዘዝ . . .
(አዛውንቱ ሊሞቱ እያጣጣሩ ባለሞሎቻቸውን መቀበሪያ ስፍራ ፍለጋ በየሀገሩ ይልካሉ፡፡ ፈረንሳይ ይህን ያህል ሊሬ አሉን፡፡ ውድ ነው! ሌላ ቦታ ፈልጉ ይላሉ፡፡ እንግሊዝ ይህን ያህል ፓውንድ አሉን፡፡ ይቅር! ደሞ ከማንም ሴት ነገሥታት ጎን ለመቀበር! በመጨረሻም በቃ እዚያው እስራኤል ኢየሱስ ተቀብሮ የነበረበት ስፍራ አካባቢ ጠይቁ፡፡ ጠይቀው ተመልሰው መጡ፡፡ከእስካሁኖቹ ከፍ ያለ ዋጋ ነበር፡፡ ይህን ያህል ዲናር/ሼክል አሉ ሲሏቸው አዛውንቱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው... ‹‹በጣም ተወደደ! እንዴ...! ለሦስት ቀን!!!››)
እሚበላ ቁራሽ እሚለብሰው እራፊ ተነፍጎት፣ እርጅናውን በጉስቁልና የኖረው ጢባርየስ ቄሳርም እንዲሁ ዙፋኑን ፈቅዶ በተወለት በልጅ ልጁ በካሊጉላ መርዝ ተሰጥቶት መሞቱ ይነገራል፡፡
ካሊጉላ
ሦስተኛው የስርወ መንግሥቱ ንጉሥ በእድሜው ገና 26 አመት ብቻ ነበረ፡፡ ስብሀት እንደነገረን፤ እርሱ ከሌሎቹ በተለየ የአምላክነት ስሜቱ ከፍ ያለ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ገና ከሕፃንነት እድሜያቸው ጀምሮ አንጋፋዎቹ የቤተ መንግሥት ባለሟሎች ዝቅ እያሉ ስለሚሰግዱላቸው ሰው መሆናቸውን ስለሚዘነጉት ነበር፡፡ ይህን ሀሳብ የሚያስረዳ ንባብ አጋጥሞኝ ያውቃል - The untouched key ለምሳሌ ፒካሶ በልጅነቱ ስፔይን ውስጥ ሲኖር በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲደርስና እናቱ እጁን ይዛው ስትሮጥ፣ ቤቶችና ህንጻዎች ሲፈራርሱ . . .ወዘተ. እያየ ስላደገ በአዋቂነት እድሜው የሰራቸው ስእሎቹ የተዘበራረቁ Distorted ሆኑ፡፡ የልጅነት እድሜ ዘመን ስንቅ Childhood turauma ለጉልምስና፣ ለአዋቂነት እድሜ ዘመን የሚያቀባብለው ነገር ይላል - መጽሐፉ፡፡ እናም ካሊጉላ ገና ከዙፋኑ ያነሳቸው አዛውንት ተመልሰው እንዳይመጡ ሲል በግዞት ሳሉ ምግብ እንዳይሰጣቸውም ከልክሎ ነበር። ምግብ ከተሰጣቸውማ ሙቀትና ጉልበት ያገኙና ወደ ዙፋኑ ይመለሳሉ፡፡ ህእ! በዚህም መሰረት ካሊጉላ የገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ በአማካሪነት የሚሰባሰቡትን የቤተ መንግሥቱን ክቡራን ሽማግሌዎች ‹‹አንቺ›› ብሎ እየጠራና ሸበቶ ጢማቸውን እየጎተተ ፈሱን ያንዛርጥባቸው ነበር፡፡ስብሀት አንድ የካሊጉላን ወግ ይነግረናል . . .
(ካሊጉላ ጨረቃን ለመሳም ተራራ ለተራራ ሲሮጥ አምሽቶ ወደ እልፍኙ ሲደርስ፤ መጻጉዕ አጎቱ ክላውዲየስን አገኘው፡፡ ‹‹ከጨረቃ ጋር ስሳሳም አየኸኝ?!›› አለውና ምላሹ ዘግየት ሲል እጁን ወደ ሻምላው ዘረጋ። ምስኪን አጎቱ ቀስ ያለው ሞቱን ላለማፋጠን ነበር። አይቻለሁም ውሸታም አሰኝቶ አንገት ሊያስቀላ ይችላል፤ አላየሁምም እንዴት አባክ እኔ ጨረቃን ስስም አላየህም! ያው ነው ሁለቱም ምላሽ ያስገድላል፡፡ እናስ ክላውዲየስ ምን ብሎ አመለጠ...‹‹አማልእክት ሆይ፤ አማልእክት ከአማልእክት ጋር ሲሳሳሙ ማየት የሚችሉ አማልእክቶች ብቻ ናቸው!›› እ...አለቀ፡፡)
እነሆ ካሊጉላም ሦስት አመት ከአስር ወራት (37 - 41 ዓ.ም) ብቻ ገዝቶ፤ ‹‹ከእንግዲህ የናንተን ቀፋፊ አይኖች ማየት ስላስጠላኝ ወደ አሌክሳንድሪያ ግብጽ ምድር ሄጄ ለመኖር ጓዜን ሸክፌያለሁ›› ባለበት ማግስት፤ እርሱም፤ ሲያላግጥባቸው በነበሩት በቅርብ ባለሟሎቹ እጅ በተቀነባበረ ሴራ ተገድሎ፤ በሁሉም ዘንድ የሚናቀውና በፍጹም ለንግሥና ይበቃል ተብሎ የማይጠበቀውና አጎቱ ክላውዲየስ በዙፋኑ ተቀመጠ።
ክላውዲየስ
ስብሀት፤ ይህን ሲያወጋን የነገሥታቱን ሁሉ ጠቢብ የመሆን ያበደ ምኞትና ይኸውም በክላውዲየስም ላይ ስር ሰድዶ እንደነበር አጽንዖት እንሰጥ ዘንድ ያሳስበናል። ችግሩ ጥበቡን ለህዝብ ለማቅረብ ወጪውን መሸፈን አለመቻሉ ነበር፡፡ እናም እዚያች ንክ ዙፋን ላይ ቁጭ ብሎ በጥሞና አስቦ አስቦ አውጥቶ አውርዶ ሲያበቃ ‹‹ድንቅ›› መላ አገኘ፡፡
(ንጉሥ ክላውዲየስ ባገሩ የተዛመተውን የተቅማጥ በሽታ ሰበብ አድርጎ፣ ብዙ የሸክላ ፖፖዎችን አሰርቶ በርካሽ ዋጋ አደለ፡፡ በማግስቱ የቤተ መንግሥት ወታደሮች በየቤቱ ሄደው ፖፖውን አስደፍተው ሕዝቡ ያላስተዋለውን ያያሉ- ያሳያሉ። መሀል እምብርቱ ላይ የቄሳሩ አርማ አለበት፡፡ ሀ! እኮ ይኼ እንዴት እንዴት ያለ ንቀት ነው ለመሆኑ! በተከበረው የንጉሠ ነገሥቱ አርማ ላይ እንትን ....እ?! በሉ እኮ አሁኑኑ መቀጮዋን ከነ ወለዷ እና ምናምኗ ሁላ ቶሎ ቁጭ! በዚህ መልኩ ብዙ ገንዘብ በማሰባሰብ የጥበብ ስራውን የሚያቀርብበት በጀት አጠራቀመ፡፡ እናም በመጨረሻ ምናለ፤ ከነገረ ቀደም እኔ የነገስኩት ለዚሁ ‹የጥበብ ስራዬን ለማሳየት› ስል ብቻ ነበረ፡፡)
ክላውዲየስ ለ13 አመታት (41 - 54 ዓ.ም) ገዝቶ እርሱም በገዛ ሚስቱ ተገደለ፡፡
ኒሮ
ንጉስ ኒሮን የሚገልፀው የቅርብ ጊዜ ዚቀኛው ተዋናይ ሙታ ባሩካ የሰራው The Dictator ፊልም ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ መሪው በሩጫ መም ላይ እየተወዳደረ ፍጻሜው ላይ ሲደርስ ሽጉጡን ላጥ አድርጎ ተወዳዳሪዎቹን አነባብሮ ይጥልና እጆቹን በድል ወደ ላይ ዘርግቶ ክሩን በጥሶ ይገባል፡፡ በቃ እንዲህ ያለ ነበር ኒሮ፡፡ ለስፖርታዊ ውድድሮች እና ለኪነ ጥበብ የነበረው ምኞት እጅግ ከፍተኛ ነበር። በዚህም ‹‹ጠቢበኝነቱን›› ተጠቅሞ እዚያችው ንክ ዙፋን ላይ ቁጭ ብሎ አውጠነጠነና የቀድሞ አጎቱን የአውጉስተስን መላ ተጠቅሞ በሮም ያሉ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ከተማዋን አቃጠለ፡፡ ከዚያም ደግሞ ለቃጠሎው ራሳቸውን ክርስቲያኖቹን ከስሶ፤ በተቃጠለው ስፍራ ላይ ያለመውን ወርቃማው እልፍኝ የተባለ ግዙፍ ህንጻ አቆመበት፡፡
ስብሐት አንድ ባለሟሉን ጨምሮ ያወጋናል፤ ፔትሮኒየስ ይባላል ሰውየው፡፡
(ሕዝቡ በጣም ስለሚወደው እንደ ፔትሮኒየስ ይለብስም ነበር፡፡ ኔሮ አንድ ወንጀለኛ አደባባይ ላይ አቁሞ ሕዝቡ ግደለው! ብሎ ሲጮህ ካባውን ይደርብለታል፡፡ ምስኪን ሰው ሕዝቡ ፊት አቁሞ ደግሞ ‹‹እባክህን ማረው!›› ብለው ሲማፀኑት ሻምላውን ላጥ አድርጎ አንገቱን ይቀነጥስና ለፔትሮኒየስ ‹‹አየኸው ጥበበኛነቴን !›› ይለዋል፡፡
ፔትሮኒየስ ከታችኛው ማህበረሰብ ካገባት ሚስቱ ጋር የሞቀ ውሃ ገንዳ ውስጥ ገብተው የመዳፋቸውን ስር በስለት ቆርጠው፣ ቀስስስ እያሉ እየሞቱና በዙሪያቸው የሚጋበዙት ክቡራን እንግዶች ነክብር እየተሰናበቷቸው ከሄዱ በኋላ አረፉ፡፡ ለኒሮ መልእክቱ ከአጭር ማስታወሻ ጋ ሲደርሰው ‹‹እንዴት እኔን ሳያስፈቅድ ይሞታል! ብሎ ተበሳጨና በጠቢብነቱ ዙፋኑ ላይ ቁጭ ብሎ አሰላሰለና አንዲት ብልቃጥ አስመጥቶ፣ ቀኑን ሙሉ ሲያምጥ ውሎ አንዲት ጠብታ እንባ ጠብ አድርጎ፣ በሙዚየም ውስጥ እንዲቀመጥ አስደረገ። ከዚህ በኋላ የፔትሮኒየስን አጭር መልእክት ከፍቶ አነበበ፡፡ እንዲህም ይል ነበር . . .‹‹ያንተን ጠቢበኝነት ማየት ሰልችቶኝ ሞቻለሁ!!!››)
ኔሮም ለአስራ ሦስት አመታት ገዝቶ (ከ54 - 68 ዓ.ም) ምናልባትም ‹ንክ ዙፋኑ› ላይ ቁጭ ብሎ ሲያስብ የመጀመሪያው በሰው እጅ ያልተገደለ ንጉሥ በመሆን ጠቢበኝነቱን ለማሳየትም ይሆናል ራሱን ገደለ። የጁሊዮ ክላውዲያን ስርወ መንግስትም በዚያው አከተመ፡፡
ጁሊየስ ቄሳር -  እንደ ‹‹ምርቃት››
ከእነርሱ አስቀድሞ ስለነበረው ንጉሠ ነገሥት ስብሐት ዘወትር የሚያደንቅለት ሕዝቡን ለጦርነት የሚያነሳሳበትን ‹‹እብድ›› የሆነች የቅስቀሳ አቀራረቡን ነበር፡፡ እንዲህ ነበር እሚላቸው ይላል . . .‹‹ጠላት መጥቶብሀል፤ ሴት ልጅህን፤ እህትህን፣ ሚስትህን፣ እናትህን ‹እነሆ በረከት› ይልልሀል! የራስህ ጉዳይ!›› በቃ። ሮማዊ ሁሉ ደሙ ይንተከተካል፤ ሴት ልጅ ባይኖረው እህት ባይኖረው ሚስት ባይኖረው ቢያንስ እናት አለዋ፤ ዜጋው በሙሉ፡፡ ታዲያ ይህን የመሰለ ንጉሠ ነገሥትም እንደ አብዛኛዎቹ ተተኪዎቹ ነገሥታት በቅርብ ወዳጆቹ ነበር የተገደለው፡፡ ስብሀት ስለ ትርጉም ሲነግርህ፤ ይውልህ ሁለት ግስ፤ ለምሳሌ trust in GOD but lock your car እሚለውን በደረቁ ‹‹እግዚአብሔርን እመን መኪናህን ቆልፍ›› ከማለት ይልቅ ‹‹አላህን እመን ግመልህን እሰር›› ብትለው ሀሪፍ አይደል? . . . እግረ መንገድ፤ ጁሊየስ ቄሳርን ተውኔት ሼክስፒር በአማርኛ የጻፈውን ያህል ነቢይ መኮንን እንደተረጎመው እና የቋንቋውን ውበት ለማስታወስ ያህል - ‹‹ፊቸሪንግ›› - ነመ...
ጁሊየስ ቄሳር ከተገደለ በኋላ ሕዝብ ወደ አንቶኒየስ ዘንድ እየተንጋጋ ጨፍጭፎ ሊገድለው ይመጣል፤ በወሬ አፍዝዞ ይመልሳቸዋል፤ ብሩተስ ነው ይላቸዋል፤ ወደ ብሩተስ ቤት እየደነፉ ይሄዳሉ፤ በንግግር ያደነዝዛቸዋል፤ ካሺየስ ነው ይላቸዋል፤ ካሺየስ ጋር ይሄዳል ሕዝብ ገጀራውን እያወናጨፈ፤ ካሺየስም አሁንም በቃላት ይደልልና ይልካቸዋል . . . እናም ካሺየስ በድብቅ ያደረጉት ግድያ በአደባባይ እየፋመ እውነቱ ሊወጣ መሆኑን ሲያስተውል እንዲህ ይላል፡- ... ‹‹ኦ! ሴራ ሆይ! የእንጦሮጦስ ጭለማ እንኳን አንቺን ሊደብቅ አይቻለውም!››
‹‹ተውኔቱ ከተለመደው አፃፃፍ በተለየ ከዋና ገጸ ባህርይው ሞት ነው የጀመረው›› ይል ነበር ስብሐት ለአብ  . . . በጡዘት - Climax.
ንጉሡ ባለሟሎቹ ዙሪያውን ከብበው በስለት በየተራ ሲሸቀሽቁት፣ አንድ ባንድ እየተዟዟረ አይቶ አይቶ ሲያበቃ፤ ከሁሉም ለይቶ ለአንድ የቅርብ ወዳጁ ብቻ የሚላት ንግግሩ አሳዛኝ ናት፤ ዛሬም ድረስ በአለም ዙሪያ፤ የወዳጅን፡ በተለይ የቅርብ ሰውን መክዳትን ለማመልከት ዘወትር የሚናገሯት አባባልም ሆና ቀርታለች፡፡ Et tu, Brute. ጁሊየስ ቄሳር፤ ወዳጆቹ እየተፈራረቁ ሲወጉት በዝምታ ሲያስተውላቸው ቆይቶ፤ በዚያ በደም አበላ መዘፈቅ በያዘበት ቅጽበት ፤ ልክ የኔ ሰው ነው እሚለው ብሩተስ ሲወጋው ግን፤ በትዝብት ትክ ብሎ እያየው። በመጨረሻዋ የእስትንፋሱ ህቅታ  You too, Brutus? ይለዋል . . .  ‹‹አንተም ፤ ብሩተስ?!››

Read 1892 times