Monday, 07 May 2018 09:25

ደበበ --- ለእኛ የተጻፈ ደብዳቤ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(2 votes)

 ደበበ ከዚህ ዓለም ከተለየ ዘንድሮ 18 ዓመት ሞላው፡፡ ባለፈው ሣምንት እርሱን የሚዘክር ዝግጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የባህል ማዕከል ተከናውኖ ነበር፡፡ ደበበ መምህራችን ነበር፡፡ ደበበ ለእኛ የተጻፈ ደብዳቤ ነበር፡፡ ይህ ደብዳቤ ሲነበብ፡-
 ለምን ሞተ ቢሉ ንገሩ ለሁሉ፤
ሳትደብቁ ከቶ፣
ከዘመን ተኳርፎ፤
ከዘመን ተጣልቶ፤ የሚል ነው፡፡
ደበበ ለምን ሞተ?
ደበበ ለምን ለምን ለምን ሞተ?
 እርግጥ ደበበ እንጂ መቼ ሞተ፤ አበበ እንጂ መቼ ሞተ የሚል ሐሳብ ለመቀበልም አልፈራም፡፡ መሞቱ የአዕምሮ ነው፡፡ ማበቡ መደበቡ የስሜት ነው፡፡ ህላዌው የዘይቤ ነው - የፍካሬ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ የአዕምሮ እና የስሜት ገመድ ጉተታ አያስፈልግም፡፡ በሁለቱም የትርጓሜ ጎዳና መሄድ ይቻላል፡፡ እንዲያውም የደበበ ህይወት በአንዱ ጎዳና ብቻ ሊገለጽ አይገባም፡፡ ግን አሁን በሁለቱም ጎዳና መሄድ አልፈልግም፡፡ ለጊዜው አንዱን ብቻ አያለሁ፡፡ ማበቡን መደበቡን ሳይሆን ሞቱን እዘክራለሁ፡፡ የስሜትን ሳይሆን የአዕምሮን ትርጉም በመከተል ጥቂት እናገራለሁ፡፡ ደበበ ለምን ሞተ? የሚለውን ጉዳይ አነሳለሁ፡፡
ለምን ሞተ ቢሉ ንገሩ ለሁሉ፤
ሳትደብቁ ከቶ፣
ከዘመን ተኳርፎ፤
ከዘመን ተጣልቶ፡፡
 እነኚህ የጠቀስኳቸው ስንኞች የደበበን አንድ ወሳኝ የህይወት ምዕራፍ በደንብ የሚገልጹ ስንኞች ናቸው፡፡ ደበበ መምህሬ ነበር፡፡ ያገኘሁት በዩኒቨርስቲ የመጨረሻ ዓመት ነበር፡፡ የመመረቂያ ጽሑፌን ስሰራ አማካሪዬ ነበር፡፡ ስለዚህ ደበበን በቅርብ የማውቀው በህይወቱ የመጨረሻ ምዕራፍ አካባቢ ነው፡፡ ደበበ ለእኔ እና ለእኛ የተጻፈ ደብዳቤ ነው፡፡
 ደበበ በአንድ የጥናት ሥራው ዮሐንስ አድማሱን ጠቅሶ፤ ዮፍታሔ ንጉሴን ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› በሚል እንደጠቀሰው ይገልጻል፡፡ እናም ‹‹ይህ ቃል ለራሱ ለዮሐንስ ህይወት የተገባ መግለጫ ነው›› ይላል፡፡ እኔም ደበበን ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› እለዋለሁ፡፡ ደበበ ‹‹ለምን ሞተ›› የሚለውን ግጥም ሲገጥም ማንን እያሰበ እንደሆነ አላውቅም፡፡ ሆኖም ይህ ግጥም ለራሱ ህይወት የተገባ መግለጫ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ ይህ በእርሱ የመቃብር ድንጋይ ላይ ሊሰፍር የሚገባው ግጥም ነው፡፡ በዚህ ለእኛ በተጻፈው ደብዳቤ ውስጥ ኪናዊ ግዝት አለ። ‹‹ለምን ሞተ ቢሏችሁ፤ አንዳች ሳትደብቁ ለሁሉ ተናገሩ፤ እኔ ከዘመን ተኳርፌ፤ ከዘመን ተጣልቼ መሞቴን መስክሩ›› የሚል መሰለኝ፡፡ ግን ደበበን ከዘመን ያኳረፈው ምንድነው? ከዘመን ያጣላው ምንድን ነው? የደበበ ጸብ ከሰው አይደለም፡፡ ከዘመን ነው፡፡ 
 ፀቡ በፖየቲክስ እና በፖለቲክስ ሊመነዘር ይችላል። ያ ዘመነ-መንሱት፤ ያ ዘመነ- ፈተና፤ ሁሌም ከሰው ጋር ጸንተው ሊኖሩ የሚገባቸውን ሦስት ነገሮች -ፍቅር - እምነት - ተስፋ - ነፍጎታል፡፡ ስለዚህ ከዘመን ተኳርፏል፡፡ ጀርመኖች Zeitgeist (ቸዚስት) የሚሉት ነገር አለ፡፡ የዘመኑ መንፈስ ሲሉ ነው፡፡ ቸዚስት የአንድ ዘመን እና ቦታ አጠቃላይ እምነት፣ መሪ ሐሳብ እና መንፈስ (the general beliefs, ideas, and spirit of a time and place ማለት ነው፡፡ እንግሊዚኛ ይህን የጀርመን ቃል ተውሶ ወስዷል። ጥምር ቃል ነው፡፡ ጊዜ እና መንፈስ የሚሉ ሁለት ቃላት ተጣምረው የሰሩት አንድ ቃል ነው።  ቸዚስት በሌላ አገላለጽ የአንድ ዘመን አጠቃላይ ምሁራዊ፣ ሥነ ምግባራዊ እና ባህላዊ ድባብ (ከባቢ) (the general intellectual, moral, and cultural climate of an era) ማለት ነው፡፡
 ምሁራን፤ ‹‹እያንዳንዱ ዘመን፤ ከሌሎች ክፍለ ዘመናት የሚለየው፤ የራሱ የሆነ ልዩ መንፈስ፣ ተፈጥሮ ወይም ድባብ አለው›› የሚል እና ዕድሜ ጠገብ የሆነ እምነት አላቸው፡፡ የተወሰኑ ፀሐፍት እና ከያኒያን የዘመን መንፈስ ዘመኑ ተጠቃሎ እስኪያልፍ ድረስ አይታወቅም ይላሉ፡፡ ጥቂቶች የዘመንን መንፈስ በውል ሊለዩት እና ሊገልፁት የሚችሉት የተወሰኑ ከያኒያን እና ፈላስፎች ብቻ ናቸው የሚል እምነት አላቸው፡፡
በበኩሌ፤ ፀሐፌ ተውኔቱ ገጣሚው፣ ተመራማሪው ደበበ የዘመኑን እንዲህ ያለ ብቃት እንዳለው አምናለሁ፡፡ እኔ ከደበበ ጋር የተዋወቅኩት በሆነ ልዩ ባህርይው የሚታወቅ አንድ የዘመን ምዕራፍ ተዘግቶ፤ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ይከፈት በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ የመወለድ ምጥ ወይም የሞት ጣዕር በነገሰበት እና የዘመን መንፈስ እንደኔ ላለው ተራ ሰው ሁሉ ጎልቶ ይታይ በነበረበት የሐገራችን ወይም የዓለማችን የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡
ደበበ አፍላ የወጣትነት ዘመኑን ያሳለፈው ሐገራችን የሰላ የመደብ ትግል ታካሂድ በነበረበት ዘመን ነው፡፡ የደበበን ፖይቲክስ እና ፖሊቲክስ የተመለከተ ሰው፤ ደበበ ከ1980ዎቹ የመጀመሪያ ግድም ከታየው ሁኔታ ጋር ሊኳረፍ እንደሚችል ለመረዳት አይቸገርም፡፡
ደበበ የተወለደው 1942 ዓ.ም ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተማር የጀመረው በ1966 ዓ.ም ነው፡፡ ፖየቲክሱ በ19 ዓመት ዕድሜው መገለጥ ጀምሯል፡፡ የመደብ ትግል በጋለበት ዘመን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር ነበር፡፡ የደበበ የመደብ አሰላለፍ ከጭቁኖች ጋር ነበር፡፡ የደበበን ፖለቲክስ ከፖየቲክሱ መረዳት ቀላል ነው፡፡ ደበበ ለጭቁኖች መብት የቆመ ምሁር እና ከያኒ ነው።  ደበበ ማርክሲዝምን በደንብ የታጠቀ ምሁር እና ከያኒ ነው፡፡ ደበበ አርብ ወደ ጥናት ክፍሉ ሲገባ ደበበ ነበር፡፡ ነገር ግን ሰኞ ከክፍሉ ሲወጣ የጠነቀቀ ኮሚኒስት ሆኖ ነበር የሚሉት ነበሩ፡፡ ትጋቱን እና የርዕዮተ ዓለማዊ ሰልፉን የሚያደንቁ እና የሚገልፁ ሰዎች፡፡
የደበበ ፖየቲክስ በፖለቲክሱ የተቃኘ ይመስለኛል፡፡ ደበበ ሶሻሊዝምን በጸና ርዕዮተ-አለማዊ መሠረት እና እምነት የተቀበለ ነበር፡፡ የሚያውቀውን የሚያደርግ፤ የሚያደርገውንም በደንብ የሚያውቅ ከያኒ ነበር፡፡ መደባዊ ትግሉን የተቀላቀለው በዕውቀት ነው፡፡ ሆኖም የደበበ ስሱ የሆነ ስሜት የኢትዮጵያ አብዮትን መጥፎ ገጽታ ለመቀበል የሚችል አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ምናልባት ከ1970ዎቹ መጨረሻ ግድም ጀምሮ ማርክስ ከደበበ ቤት ሳይወጣ አልቀረም፡፡ ሆኖም ካርል ከእርሱ ጋር እንደቆየ አገምታለሁ፡፡
በዚያው አካባቢ የጎርባቾቭ ግላስኖስት እና ፔሬስትሮካ መጣ፡፡ የሶሻሊዝም ካምፕ ተናደ። የበርሊን ግንብ ፈረሰ፡፡ ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ፊት ለፊት የቆመው የሌኒን ሐውልት ተገነደሰ፡፡ መናኸርያ ግድም በጥናት ክፍሉ ቁጭ ብሎ የዘመኑን መንፈስ ይመረምር የነበረው ደበበ፤ የሌኒን ሐውልት ሲገነደስ ይሰማው ነበር፡፡ ዓለም ለሁለት ጣዖታት አልገዛም ብላ ከካፒታሊስቱ አይዲዮሎጂ ጣዖት እግር ሥር ወደቀች፡፡ የአራት ኪሎ ቤተ መንግስት የነበረው የአይዲዮሎጂ ታቦትም ወደቀ፡፡
የአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ለሁለት ጣዖት አልገዛም ያለችውን ዓለም፤ ‹‹በቅይጥ ኢኮኖሚ›› ሊሸነግላት ሞከረ፡፡ እንዲህ ያለ ርዕዮተ ዓለም ይዞ የመጣው የዘመን መንፈስ ከደበበ ፖለቲክስ እና ፖየቲክስ ጋር የሚስማማ አልበረም፡፡ የእምነቱ ሐውልት ከበርሊን ግንብ ጋር ድንገት ሲፈርስ ተመለከተ፡፡ ደበበ እምነቱን ከቀማው ዘመን ጋር ተኳረፈ፡፡ ህይወትን በበጎ መንፈስ የማየት ብርቱ ዝንባሌ ያለው ከያኒው ደበበ፤ የርዕዮተ ዓለም መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራኒዮ ወጣ፡፡
ደበበ ሐገሩን በጣም ይወዳል፡፡ የዘመኑ መንፈስ በፍቅር የሚወዳትን ሐገሩን ይተነኳኩሳት ጀመረ፡፡ ወቅቱ የኢትዮጵያ እንደ ሐገር የመቆም ዕድል አጠራጣሪ ሆኖ የታየበት ዘመን ነበር፡፡ የብሔር አሰላለፍ የነበራቸው በርካታ የነጻ አውጪ ቡድኖች በኩፍርፊያ እና በቁጣ የሚናገሩበት ዘመን ነበር፡፡ ሰዎች የብሔር ማንነታቸውን ማውጠንጠን የጀመሩበት ዘመን ነበር፡፡ ይህ ወቅት፤ የደበበን የሐገር ፍቅር ስሜት የሚያራክሱ ክስተቶች የተበራከቱበት ጊዜ ነበር፡፡
ኤርሚያስ ሁሴን ‹‹እሣት እና ውሃ›› (2009) በሚል ርዕስ ስለ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ለጻፈው መጽሐፍ መግቢያ ጽፌ ነበር፡፡ በዚህ መግቢያ ላይ ደበበን አንስቼ ነበር፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ወደ ደበበ ሰይፉ ቤት በሄድንበት አጋጣሚ የፀጋዬ ነገር ተነሳ፡፡ በወቅቱ ይታተሙ ከነበሩት መጽሔቶች (ጋዜጦች) በአንዱ የወጣው ዘገባ የወቅቱ የከተማ ወሬ ነበረ፡፡ አንድ የኦሮሞ ብሔር ድርጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ልደት አዳራሽ ለማካሄድ ባሰበው አንድ ጉባዔ ጸጋዬ ገብረ መድኅን እንደሚገኝ የሚያውጅ ዜና ነበር፡፡ ጸጋዬ ብቻ አይደለም። ጥላሁን ገሠሠም በዚሁ ጉባዔ እንደሚሳተፍ የሚያትት መሰለኝ፡፡
በውቅቱ በብሔር በተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባዔ መገኘት አሳፋሪ እና አስደንጋጭ ስሜት የሚፈጥርባቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ እኔም ከእነሱ አንዱ ነኝ፡፡ ጸጋዬን በብሔር በተደራጀ ፓርቲ መድረክ መገኘቱን መቀበል አስቸጋሪ ነበር፡፡ ደበበ ቤት ከጓደኞቼ ጋር በሄድን ጊዜ ይህንኑ ጉዳይ እየተነጋገርንበት ነበር፡፡ ይህን ለደበበ ነገርነው። ነገርነው ቀላል ቃል ነው፡፡ አረዳነው ማለቱ ይበልጥ ለእውነቱ ይቀርባል፡፡ ደበበ በሰማው ዜና ደነገጠ፡፡ ደነገጠ አይደለም በጣም አዘነ ማለቱ ይሻላል፡፡ የመጀመሪያ ምላሹ ዝምታ ነበር፡፡ ረጅም ዝምታ፡፡ የተቀመጥነው ከንባብ ክፍሉ ወይም ቤተ መጻሕፍቱ ነበር፡፡ ደበበ የሚያጨሰውን ሲጋራ በጣቱ መሐል እንደያዘ በዝምታ ተዋጠ፡፡ ሁላችንም በዝምታው ዋጠን፡፡ የመጻፊያ ጠረጴዛውን እንደተደገፈ፤ አንገቱን እንዳቀረቀረ፤ የያዛት ሲጋራ ከግማሽ በላይ አመድ ሆነች፡፡ የሲጋራው አመድ ርዝመት የስሜቱን ጉዳት የሚለካ ሜትር ሆኖ ታየኝ፡፡ የሲጋራው ጭስ የፍታት ማዕጠንት ሆኖ፤ አመዱ በእምነት የለመለመ ተስፋው አመድ ሲሆን የሚያሳዩ ዘይቤዎች ሆኑ፡፡ ደበበ እና ሲጋራው እየነደዱ አመድ መሆን ቀጠሉ፡፡ እሣቱ በፍጥነት ወደ እጁ ጣቶች ሲጠጋ አየሁ፡፡ የሲጋራው እሣት ጣቱን ሲያቃጥለው፤ ከተጫነው የሐዘን ስሜት ለመውጣት እንደወሰነ ሁሉ፤ ድንገት ከመደበኛ የአነጋገር ድምጹ ላቅ ባለ የገነነ ድምጽ፤ ‹‹እንዴ! እኔ ኢትዮጵያን የት አውቃታለሁ›› በሚል ቃል፣ የዝምታውን መቃብር ገልብጦ ነፍስ ዘራ፡፡ ይህ ቃል በውስጡ አውጥቶ አውርዶ፣ በወገ ነፍስ አምሶ ያብሰለሰለው ሐሳብ የመጨረሻ ዐ.ነገር ነበር፡፡ በዝምታ በርሃ ከሄደበት ስደት ሲመለስ የተናገረው የማጠቃለያ ቃል ነበር፡፡ የብቻ - የዝምታ - የቅሬታ - ሙግቱ እና የአቤቱታው ማመልከቻ ነበር፡፡ ደበበ በቁጣ እና በሐዘን ስሜቶች መሐል እንደተንጠለጠለ የሚከተለውን አስከተለ፡፡
‹‹እንዴ እኔ ኢትዮጵያን የት አውቃታለሁ? ጸጋዬ አይደለም እንዴ ‹አንቺ እማማ ኢትዮጵያ- አይ አንቺ እናት ዓለም› እያለ ልባችንን በፍቅር ዕዳ የያዘው፡፡ እኔ ኢትዮጵያን የት አውቃታለሁ?›› አለ፡፡ ሁላችንም ደነገጥን፡፡ ለወትሮው ለደበበ ለምንነግረው ነገር ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ ይህን ያህል ስሜት እንደሚፈጥርብት አስቀድመን ብናውቅ ኖሮ የምንነገረው አይመስለኝም፡፡ የስሜት ጫናውን የሚያቀል እንጂ ተጨማሪ ሸክም የሚሆን ነገር መውሰድ አንሻም ነበር፡፡ እርሱም ለተማሪ ከሚነገረው በላይ ነፍስን የሚያሳድፍ ነገር ሊነግረን እንደማይፈልግ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲጠነቀቅ እናውቃለን፡፡ የጸጋዬ ዜና በፈጠረው ያልተገመተ የሐዘን ስሜት በተፈጠረ ምድረ በዳ ስንንገላታ፤ ዘወትር እንደሚያደርገው ፈውስ የሚሆን ሌላ አስተያየት አከለ፡፡
 ‹‹በጣም ርግጠኛ ነኝ፡፡ ጸጋዬ በዚህ ጉባዔ ለመገኘት የወሰነው፤ ግብዣውን የተቀበለው ሊመክራቸው ሊገስጻቸው ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ›› በማለት በፍጥነት ከወደቀበት ተነሳ፡፡ እኛም ያን ቆሻሻ ስሜት እያራገፍን አብረን ተነሳን፡፡ የእኛንም ሆነ የቤቱን ድባብ በአዲስ ብርህት ቀለም ቀብቶ አደማመቀው፡፡ ‹‹….ሲጠሩት ሊገኝ ይችላል፡፡ እምቢ ሊል አይችልም፡፡ ግን ጸጋዬ በዚህ ጉባዔ የሚገኘው ሊመክራቸው ነው›› እያለ፤ የደበበን ሥጋ የለበሰ ሌላ ሰው ሆኖ ያጽናን ጀመረ፡፡
 ደበበ ቀና አለ፡፡ እንደገና የተናገረውን ደገመው። ‹‹እኔ በጣም እርግጠኛ ነኝ፤ ፀጋዬ ወደዚህ ስበሰባ ሄዶ ከሆነ፤ የሄደው ሊመክራቸው መሆን አለበት›› በማለት፤ እኛ ዓሣዎቹን ወደ ውሃው መለሰን። የሁላችንንም ሸክም አውርዶ እረፍት ሰጠን፡፡ ደበበ የሀገሩን ፍቅር የሚያራክሱበት እንዲህ ያሉ ክስተቶች የተበራከቱበት ዘመን፣ ሰላም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ስለዚህ ከዘመኑ ጋር ተኳረፈ፡፡
 ደበበ ሰውን በርኅራኄ ስሜት የሚያስተናግድ፤ ዓይኑም የነገሮችን በጎ ገጽታ አጉልቶ ለማየት የሚሞከር ሰው ነው፡፡ እንዲያ የሚወዳት ሐገሩ ተጨንቃ ነበር፡፡ እናም የወገኑን የወደፊት ህይወት አጠራጣሪ አድርጎ ከሚያሳያው ዘመን ጋር በፍቅር ሊያድር አይችልም፡፡ ያ ዘመን ተስፋ ማድረግን ከለከለው፡፡ ስለዚህ እምነት፣ ፍቅሩንና ተስፋው ከነጠቀው ዘመን ጋር ተኳረፈ፡፡ በእምነት፣ በፍቅርና በተስፋ እጦት ተሰቃየ፣ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፡፡ በመቃብሩ ድንጋይ ሊሰፍሩ የሚገባቸው ስንኞች የሚከተሉት ናቸው፤
ለምን ሞተ ቢሉ ንገሩ ለሁሉ፤
ሳትደብቁ ከቶ፣
ከዘመን ተኳርፎ፤
ከዘመን ተጣልቶ፤

Read 1641 times