Monday, 07 May 2018 09:33

የፍቅር ስጦታዬ

Written by  ዳግማዊ፡ እንዳለ(ቃል ኪዳን)
Rate this item
(5 votes)

 -”ግን የትና ከማን ጋር ነው ያየኋት? መቼ ነው ያየኋት? መደናገጧና መርበትበቷ እኔንም አስደነገጠኝ፡፡ ብቻ የሆነ ነገር እንዳወቅሁ ስለተሰማኝ ደስ አለኝ፡፡ በርግጥ ኪሣራው የበዛ ነው፡፡ ብቻ የተወሰነ አካሉን አስቆርጦ ህይወት ያገኘ ሰው የሚሰማው አይነት ደስታ ተሰማኝ፡፡ ዋናው እኮ መኖር መቻሉ ነዉ!-”
    
   የመውደድና የመውደድ ልዩነቱ ምንድን ነው? አንድ ናቸው ብቻ እንዳትሉኝ!  እኔም እንደዛ በማሰቤ ነው ለዚህ ሁሉ ችግር የተዳረግሁት፡፡ በጨዋነቴ ነው ‹ና› እና ‹ሂድ› እየተባልኩ  መቆሚያዬን ያጣሁት፡፡ አንዳንዶች ይወዱልሀል እንጂ አይወዱህም፡፡ ያደንቁልሀል እንጂ አያደንቁህም፡፡ ይሄ ነው እኔን የገጠመኝ፡፡ ‹ምኔን ነው የሚወዱት?› በእርግጥ እንደየ ሴቶቹ፣ ምኞትና ቅዠት ይለያያል፡፡
እሷም እንደ ሌሎቹ ሴቶች ናት!  ትወድልኛለች እንጂ አትወደኝም፡፡ ግና የነዚህን ሴቶች ግብር በወል ስም መውደድ ያስባለው ምንድን ነዉ? እነሱስ እንዴት ወዳጆችና አፍቃሪዎች ተባሉ? ይሄ ነገር እንዴት እስካሁን ሳይገለጥልኝ ቀረ? እንዴት ፍቅር በሌለበት ዓለም ብቸኛ አፍቃሪ ሆኜ ቀረሁ?
ማህሌት ረፋድ ላይ ደውላ ላገኝህ እፈልጋለሁ ካለችኝ ወዲያ ብቻዬን እያወራሁ  ነዉ፡፡ ለነገሩ አብርያት እያለሁ እራሱ የማወራው ብቻዬን እንዳልነበረ፣ በምን እርግጠኛ ልሆን እችላለሁ? ዛሬ የማህሌት የልብ ጓደኛ ተብዬ ደውላ ምስጢር ነግራኛለች፡፡ በዚህም ከማህሌት ጋር የያዝኩት ቀጠሮ፣ ዕጣ እንደሚሸጥበት የዕቁብ ሳምንት አላጓጓኝም፡፡ ብቻ ዕቁቡን አስቀድሜ በላሁም አልበላሁም ዛሬ ሄጄ መጣል አለብኝ፡፡
መሄዴ የማይቀር ነገር ቢሆንም እንኳን ወደ ቀጠሮው መሄድ አለብኝ፡፡ ሁሌም ሽክ እንዳልኩ ቢሆንም እንኳን ዛሬ ቀጠሮዬ ላይ ሽክ ብዬ መገኘት አለብኝ፡፡ በመውደድና በመውደድ መሀል ልዩነት ካለ፣ በመሄድና በመሄድ፤ ሽክ በማለትና ሽክ በማለት መሀል ልዩነት መኖሩ አይቀርም፡፡
አልፎ አልፎ ከቁጥጥሬ ውጪ ከአንደበቴ በሚወጡት ቃላት የሚያጉተመትመው አፌ፤ ግድግዳ ላይ በተሰቀለች የፊት መስታወቴ ከማስረው ከረባቴ ይልቅ ይታየኛል፡፡ በፈጣን አለንጋ ጣቶቼ የሚከናወነው ፍትልትል ከረባት አስተሳሰሬ፣ ለንግግሬ ማጀብያ ዳንስ ይመስላል፡፡ በነገራችን ላይ ‹ጣቶችህ አለንጋ ነው የሚመስሉት› የሁሉም ሴቶች ሙገሳ ነው፡፡ አሁን፣ አሁን ሳስበው ግን ነገርየው ከሙገሳነት ይልቅ ወደ ቅናትነት ያደላ ነው፡፡
ከረፋድ ጀምሮ ብቻዬን እያወራሁ ነው፡፡ ደግሞ መሀል ላይ ዛሬ አንዳች ነገር እንደተገለጠልኝ ትዝ ሲለኝ ፈገግ እላለሁ፡፡ አሁንም ፈገግ አልኩኝ፡፡ የአዳም ልጅ ሁለቴ በእባብ አይነደፍም፡፡ ግን አዳም እራሱ እንዴት ሁለቴ በእባብ ተሸወደ?......አይ! አንደኛው በእባብ ሳይሆን በብርሃን መላእክ ነው፡፡ መፈገጌን አውቆ ነዉ መሰል መስታወት ውስጥ ያለው ምስልም አብሮኝ ፈገግ አለ፡፡ ጠዋት ጠዋት መስታወት ፊት ብዙ ከመቆሜ የተነሳ በመስታወት ውስጥ የማየው ምስል እራሱን የቻለ ሌላ አካል ይመስለኛል፡፡ ፈገግታው የኔ እንዳልሆነ ሁሉ ያስጠላኛል፡፡ ቆይ ከግዢ እንጀራ ለሳሱ ከንፈሮች፣ ትላልቅ ጥርሶች ምን ያደርጉለታል? ፈገግታው ያስጠላል! ደግሞ እኮ መኮሳተር የሚባል አልፈጠረበትም፡፡
በእውነት አልረባም! አልጋ ሲሏቸው አመድ ለሚሉ ሴቶች፣ በአለንጋ ጣቶቼ አልጋ አንጣፊ ሆኜ ልቅር? ቆይ አብሬአቸው የነበሩ ሴቶች ሁሉ እየደወሉ፤ ‹ግርምሽዬ የምትሰራው ቁርስ እንዴት እንደናፈቀኝ፤› ‹ግርምሽዬ እንክብካቤህን እኮ ስወደው!›፤ ‹ግርምሽዬ ምን እንደናፈቀኝ ታውቃለህ? አልጋ ላይ ተኝቼ አሪፍ ቱና ፍርፍር ሰርተህልኝ ከበላሁ በኋላ ድምጽህን ከፍ አድርገህ የሚያሥቅ መጽሐፍ ስታነብልኝ›፤ ‹ግርምሽዬ እንትንህ እንዴት እንደናፈቀኝ......ግርምሽዬ……ግርምሽዬ› እያሉ ሲሟዘዙብኝ እንዴት እኔ እንደማልናፍቃቸው አልተረዳሁም? እውነት አንድ ቀን እንኳን ግርምሽዬ ናፈቅከኝ ብለውኝ እኮ አያውቁም! ለነገሩ የዘመኑ ሰው ወጥ ሠሪዋ ትዝ የምትለው፤ የሆቴሉ ምግብ ከተበላሸ በኋላ ነዉ፡፡
ኡኡኡ ብዬ መስታወቱ ላይ ጮህኩኝ፡፡ አስደነገጥኩት መሰለኝ ባለ ትላልቅ ጥርሱ ምስል መልሶ ጮኸብኝ፡፡ ቆይ ግን ምንድነው እንዲህ ያስጮኸኝ? ይህን ያህል ተበሳጭቻለሁ እንዴ? አንደበቴን ከዳግም ጩኸት ለመግታት ትንፋሼ ቀጥ እስክትል ድረስ ከረባቴን አጥብቄ  አስሬ፣ የቤቴን በር ወርውሬ ዘጋሁት። ግን በሩን እንደዚህ ምን አስወረወረኝ?! ሴቶቹ እንደሆነ እቤት የሉም፡፡
ከታክሲ ወርጄ ማህሌት ወደቀጠረችኝ ካፌ አመራሁ፡፡ ና ባሉኝ ቁጥር እንደዉ መንጦልጦል ነው ሥራዬ! ዛሬ ና የተባልኩት፣ ሂድ ለመባል እንደሆነ አስቀድሜ ሰምቻለሁ፡፡ ስገባ ከካፌው አንዱ ጥግ ተቀምጣ ሌላ ጠረጴዛ ላይ ካሉ ሁለት ጎረምሶች ጋር እያወራች ትሣሣቃለች፡፡ የያዘችው ጠረጴዛ እሷ ከተቀመጠችበት ወንበር ዉጪ ሌላ ወንበር የለውም። መምጣቴንም እረስታዋለች እንዴ? ከዚህ በፊት የራሴን ወንበር ከቤት ይዤ የመምጣት ልምድ የለኝም። ወይስ ብቻዬን ነኝ፣ ኑ አዋሩኝ ለማለት ፈልጋ ነው? ገና ሳታሰናብተኝ ምን እንዲህ አስቸኮላት? ንዴት ቢያሰክረኝም፣ እንደ ምንም ቀጥ ብዬ ሄጄ፣ ጉንጯን ደረቅ መሳም ስምያት፣ ሲያሳስቋት ከነበሩ ጎረምሶች አጠገብ ያለች ወንበር አምጥቼ በግራዋ ተቀመጥኩ። በቀኟ ሆኜማ ማሪኝ አልላትም፡፡ በሷ ገነት አብርያት ልሆን አልሻም፡፡ ሲያዋሯት የነበሩት ሁለቱ ጎረምሶች ወንበሩ ሰው እንዳለ ሳልጠይቃቸው ስለወሰድኩት ይሁን ወይ በድርጊታቸው አፍረዉ አንገታቸውን አቀረቀሩ፡፡
‹‹ቆየህ!›› በቁጣ አፈጠጠችብኝ፡፡ አቋረጥከኝ ማለቷ ነው እንዴ ይህቺ ሴት? ዝም አልኳት፡፡  
‹‹እየጠየቅሁ እኮ ነው›› ይበልጥ ተቆጣች፡፡
‹‹ቆየህ ጥያቄ ነው እንዴ? ጥያቄ ከሆነ አልቆየሁም። እንደውም አምስት ደቂቃ ቀድሜ ነው የመጣሁት።›› ሰዓቴን ተመልክቼ ፈገግ አልኩኝ፡፡ ፈገግታዬ የሷን ቁጣ ለማብረድ የታቀደ ቢሆንም እኔን በራሴ ከመቆጣት ግን አላዳነኝም፡፡ አምስት ደቂቃ ቀድሜ እንደመጣሁ እርግጠኛ ሆኜ ሳለ ሰዓቴን ለማረጋገጥ ለምን ተመለከትሁ? ይሄ፣ ይሄ ነገር እኮ ይሆናል የሚያስንቀኝ!። እሺ እሷስ ብትሆን ቀድሜ መምጣቴን እያየች ምን ቆየህ አስባላት? በርግጥ በፊት፣ በፊት ና ባለችኝ ቁጥር ከቀጠሮዬ ቢያንስ ግማሽ ሰዓት ያህል ቀድሜ ስለምገኝ ይሆናል የቆየሁ የመሰላት፡፡ ግን የራሷ ጉዳይ! ድሮስ መርዶ ለመስማት ተጣድፌ እንድመጣላት ትፈልጋለች እንዴ?
ጠዋት ላይ የማህሌት ጓደኛ ደውላ ‹ማህሌት ጠርታህ፣ አፍንጫህን ላስ ልትልህ ነው› ብላ ነገረችኝ። መጀመርያ አላመንኳትም ነበር፡፡ የሰሞኑን የማህሌት ሁኔታ ሳስብ ግን ደነገጥኩ፡፡ ከድንጋጤዬ ሳልወጣ ደውላ በአስቸኳይ ልታናግረኝ እንደምትፈልግ ነገረችኝ፡፡ ያኔ በመሰናበቴ እርግጠኛ ሆንኩኝ፡፡ የገረመኝ ግን ጓደኝዬው ደውላ ለኔ ለምን እንደነገረችኝ ነው፡፡ አዝናልኝ ይሆን? ካዘነች ደግሞ ለምን እሷኑ እንዳትተወኝ አላሳመነቻትም፡፡ ለነገሩ አሻፈረኝ ብላት ይሆናል፡፡ እምቢ ካለቻት ታድያ ምን ታድርግ? ግን ምክንያቱ እሱ ባይሆንስ? ምናልባት ቅናት ቢሆንስ? አሁን እኮ በሷ ቤት ቀድማ ተናግራ የፍንገላውን ‹ሠርፕራይዝ› ማቀዝቀዟ ይሆናል፡፡ ቆይ ቆይ ሁለቱ ሴቶች ተማክረው ያደረጉት ነገር ቢሆንስ? ፍንገላውን ቀላልና ጊዜ የማይወስድ ለማድረግ አስበው፤ ጓደኝዬው ነገሩን ምስጢር አስመስለሽ ንገሪው የሚል ተልዕኮ ተሰጥቷት ቢሆንስ? ኡኡኡ-- እነዚህ ሴቶች እኮ ሊያሳብዱኝ ነው፡፡
‹‹ምነው ችግር አለ?›› ትልልቅ ዓይኖቿን የጥያቄ ምልክት አደረገቻቸው፡፡
‹‹የምን ችግር?›› በእጆቼ የያዝኩትን ጭንቅላቴን ለቀቅሁኝ፡፡ መቼ ነው ጭንቅላቴን የያዝኩት ደግሞ?
‹‹በእነሱ ተናደህ ነው? እንደዛ ከሆነ እንዳትሳሳት። እንዲሁ ዝም ብለን በተራ ነገር ነው ስንሣሣቅ የነበርነው፡፡ ደግሞ ታውቃለህ እንደዚህ ዓይነት ነገር እንደማይነካካኝ›› የሻይ ብርጭቆዋን በቄንጥ አነሳችና ውስጡ የቀረችውን ጭላጭ ማኪያቶ ተጎነጨች፡፡
ይህቺ ልጅ ግን ለምን በሰላም አታሰናብተኝም? ቆይ የምን ሰበብ አዳኝ መሆን ነው? እዚሁ ጸብ አንስታ እንዳትደርስብኝ ልትለኝ ነው እንዴ የምትፈልገው? አንደኛዋን እንደ ሌሎቹ ለጥቂት ጊዜ ስልኳን ብትዘጋ ወይ ስልኬን አላነሳ ብትል ይሻላት ነበር፡፡ መሸነፍ እንደሌለብኝ ለራሴ ነገርኩት፡፡ እንዲያው ጥሎብን ባገኘንበት እንተኛለን እንጂ ከነቃንማ ነቃን ነዉ! ዘራፍ እኔ ወንዱ!
‹‹ካፌ ውስጥ እኮ ነሽ! ብቻሽን ቢያይሽ ማንኛውም ወንድ ሊያናግርሽ እና ሊተዋወቅሽ ሊሞክር ይችላል። ይሄን እረዳለሁ!›› አልኳት ነገሩን በማቃለል፡፡ ፊቷ ልውጥውጥ አለ፡፡
‹‹ለነገሩ ሥራህን ታዉቀዋለህ፡፡ በየካፌው ምን ስታደርግ እንደምትውል አንተ ነህ የምታውቀው!›› የነገሩን አቅጣጫ ድንገት ቀየረችው፡፡ ደግሞ ከንፈሯን ሳትነክስ ከንፈሯን የነከሰች ሴት ፊት ለማምጣት ሞከረች፡፡
ወንበሩ ላይ ልጥጥ ብዬ ተቀምጬ በትዝብት ተመለከኳት፡፡ ምን አይነት ምላሽ እንደምሰጣት ግራ ገባኝ፡፡ ‹አዎ! ግን አናገርከኝ ብላ እንዳንቺ እንዲህ የምትገለፍጥ ሴት ገጥማኝ አታዉቅም› ልበላት? ይህቺ ሴት በገዛ ፈቃዷ የስንብት ደብዳቤዉን ከማንበቧ በፊት ለዉሻዬ የልደት ድግስ እንድደግስ ትፈልጋለች፡፡ ከዛ ህዝቡ እየተራበ ልትለኝ፤ ሰበብ ልታደርገኝ!፡፡ ዕድልማ አልሰጣትም፡፡ እንውለድም አንውለድም ብትለኝ ዛሬ እሺ ነው የምላት፡፡
‹‹ምነው ዝም አልክ? ሥራህ ትዝ አለህ እንዴ?›› መተንኮስ ጀመረች፡፡
‹‹እንዲሁ ለመናገር ፈልገሽ እንጂ ካፌ እንደማላዘወትር ታውቂያለሽ ብዬ ነዉ?›› ሣቅ ለማለት ሞከርኩ፡፡ ንግግሬን ተከትላ በየትኛው አቅጣጫ እንደምትሄድ፤ ምን አይነት ነገር ይዛ እንደምትመጣ መገመት እየተሳነኝ ነው፡፡ አማራጭ መስሎ የሚሰማኝ ግን ማንኛውንም ጥያቄዋን ከመመለሴ በፊት በደንብ ማሰብ እንዳለብኝ ብቻ ነዉ፡፡
‹‹ሃሃሃ..›› የፌዝ ሣቅ ሳቀች ‹‹መጠጥ ቤትም እኮ ብቻዋን የተቀመጠች ሴት አለች፡፡ እዚህ ጋ ዋናው ነገር ቦታው ወይ የሚሸጠው የፈሳሽ ዓይነት ሳይሆን ብቻዋን የተቀመጠች ሴት መኖሯ ነው፡፡ ያውም መጠጥ ቤት፤ እራሷን፣ ትዳሯን ሁሉ ነገሯን ለመርሳት መለኪያ የጨበጠች ብቸኛ ሴት የምትገኝበት ቦታ? የአዞ እንባ እያነቡ እኔም እንዳንቺው ነኝ አይዞሽ ቢሏት፣ እራሷን አሳልፋ የምትሰጥ ብቻዋን የተቀመጠች ሴት ያለችበት ቦታ ነው……ከዛ እኔ ምስኪኗ ጋር ትመጣና መጠጥ ድሮ እንዳቆምክና አልኮል ያለበት ነገር እንደማትቀምስ፤ ለቁስልህ እንኳን አልኮል እንደማትነካ ትተረተርልኛለህ። ወይኔ ልጅት!››
ድምጿ እየጋለና በዙርያችን ያሉ ካፌተኞችን ትኩረት እየሠረቀ መጣ፡፡ በሀፍረት አንገታችውን አቀርቅረዉ ከዛም አንገቱን ያቀረቀረ ወሬ ሲያወሩ የነበሩት ሁለቱ ጎረምሶች እንኳን ወሬአቸውን አቁመው፤ ፊታቸውን ወደኛ መለሱ፡፡ ድሮስ ይሄን አልነበረ የሚፈልጉት? ግን ምንድነው ሴትየዋ እንደዚህ የሚያንተከትካት?
‹‹እንደዛ አይነት ሰዉ እንዳልሆንኩ ጠንቅቀሽ ታውቂያለሽ፡፡ ደግሞ በፈለግሽኝ ሰዓት ሳታገኚኝ ቀርተሸ ወይ አፌ አልኮል አልኮል ሸቶሽ ያውቃል? አንድ ቀን እንኳን ስልክ ስናወራ ከጀርባ ሙዚቃ ወይ ጫጫታ ሰምተሽ ታውቂያለሽ?›› የሷን ያህል ባይሆንም ድምጼን ሞቅ አደረግሁት፡፡ ማህሌት ተናደደች፡፡ አሞራ - አሞራ እንጂ ዥግራ አልሆንም ስላልኳት ተበሳጨች፡፡ ሳስበው ከኔ ስህተት ከመፈለግ ይልቅ ቀጥታ ወደ ጉዳዩ ገብታ ብታሰናብተኝ ይሻላት እንደነበር ተሰምቷታል፡፡
‹‹አሥሬ ታውቂያለሽ፣ ታውቂያለሽ አትበለኝ። አላውቅህም! እኔማ ሞኝ ነኝ! የማውቅህ መስሎኝ ነበረ!›› ተብሰከሰከች፡፡
አስባው ይሁን ሳታስበው ብቻ ትክክል ናት። አሁን ያለውን ግርማ አታውቀውም፡፡ አሁን ያለው ግርማ በአለንጋ ጣቶቹ ሽንኩርት የሚከትፈው፤ ወጥ የሚያማስለው እና አመድ ሲሉት አልጋ የሚያነጥፈው አይደለም፡፡ አሁን ያለው ግርማ ‹ና› እና ‹ሂድ› የሚሉት አይደለም፡፡ ዛሬ ማህሌት በፍጹም እንድትቀድመኝ አላደርጋትም፡፡
‹‹ቆይ ምንድነው እንደዚህ ያበሳጨሽ? ገብቼ ከማንም ጎረምሳ ጋር ስታወሪና ስገለፍጪ አገኘሁሽ ብዬ አልተናገርኩሽ፡፡ እንደውም ባንቺ ያለኝን እምነት በተግባር ነው ያሳየሁሽ፡፡›› እጆቿን በእጆቼ ጭብጥ አደረግኳቸው፡፡ በህመም ስሜት ፊቷን አጨፈገገችና እጆቿን አስለቅቃኝ፤
‹‹እሱማ ወንድነት ይጠይቃል! ለኔ ግድ ቢኖርህ ኖሮ፤ እውነት ለኔ ፍቅር ቢኖርህ ኖሮማ እንዲህ ዝም አትልም ነበር፡፡ ቢያንስ መኮሳተርና ማኩረፍ ነበረብህ። ቢያንስ ማናቸው ብለህ መጠየቅ ነበረብህ፡፡ አንተ ግን ግድ የለህም፡፡ እንኳን ካፌ ውስጥ አልጋ ውስጥ እንኳን ብታየኝ የሚሰማህም አይመስለኝም!››
‹‹ማሂዬ እውነት ለመናገር እኔ የትም ቦታ ባገኝሽ አምንሻለሁ፡፡ እምነት ያለ ፍቅር እንዴት ይሆናል? ካላመንኩሽ እንዴት አብሬሽ ልሆን ይቻለኛል? ደግሞ ባለፈውም አይቼሽ ምንም ያላልኩሽ ለዛ ነው›› ፊቷ በድንጋጤ አመድ መሰለ፡፡ አንዳች ነገር ለማለት ብላ ተንተባተበች፡፡ የት? ወይ? መቼ? የሚል ጥያቄ ሊሆን እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ፡፡ እጇን ጨብጥ አድርጌ፤
‹‹ማሂዬ እኔ እወድሻለሁ፡፡ እስከማምንሽ ድረስ እወድሻለሁ››
ግን የትና ከማን ጋር ነው ያየኋት? መቼ ነው ያየኋት? መደናገጧና መርበትበቷ እኔንም አስደነገጠኝ። ብቻ የሆነ ነገር እንዳወቅሁ ስለተሰማኝ ደስ አለኝ። በርግጥ ኪሣራው የበዛ ነው፡፡ ብቻ የተወሰነ አካሉን አስቆርጦ ህይወት ያገኘ ሰው የሚሰማው አይነት ደስታ ተሰማኝ፡፡ ዋናው እኮ መኖር መቻሉ ነዉ! ዛሬ በድፍረት መናገር እስክችል ድረስ ሁሉ ነገር ተገለጠልኝ፡፡ እየሱስ ዓይነ ሥውሩን በጭቃ አይኑን እንዳበራው፣ ጓደኛዋ በቆሻሻ ሀሜቷ ዓይኔን አበራችልኝ፡፡ ጌታ ይባርካት!
ድንገት የጨበጥኳቸው የማህሌት እጆች ኮሰኮሱኝ። ምናምንቴአቸው ያበጠ፤ ገላቸው እሳት የሚተፋ ስንት ሰዎች ጨብጠውታል? ስንት ገላን አሙቋል፡፡ ግን እላዬ ላይ እየማገጠች እንዴት ማወቅ ተሳነኝ? ደግሞ አውቃለሁ ማለቴ ይሄን ያህል ያስደነገጣት ምን ያህል ላውቅ የማልችል አድርጋ ብታሰበኝ ነዉ? እጆቿን ለቀቅኋቸዉ፡፡ ካሁን በኋላ ቢያነቅፋት እራሱ ለድጋፍ ልይዛቸው አልፈልግም፡፡
‹‹እሺ በሰላም ነው የፈለግሽኝ?›› ገጽታዬ መለወጡን ተገንዝብያለሁ፡፡ ካሁን በኋላ ማስመሰሉን የምችል አይመስለኝም፡፡
‹‹አዎ በሰላም ነው›› አለችኝ፡፡ የቅድሙ ቁጣዋን ከንፍጥዋ ጋር ተናፍጣዋለች ወይ ወደ ውስጥ ምጋዋለች፡፡ ቆይ ተናፍጣ ነበር እንዴ? ብቻ እንጃ ቁጣዋ ወዴት እንደሄደ፡፡ የእውነት ተንኮል አስባ ባትመጣና ሀሳቧ ባይፈርስባት ኖሮ እንደ እውነተኛ ፍቅረኛ ‹አንተን ለማግኘት ምክንያት ያስፈልጋኛል እንዴ?› ብላ ይሄኔ ነበር ቁጣ መጀመር የነበረባት፡፡
‹‹ድምጽሽ ግን የሆነ ከባድ ነገር ልትነግሪኝ ያሰብሽ ይመስል ነበር›› አልኳት፤ በሚፈታተን አይነት ንግግር፡፡
‹‹አይ ዝም ብዬ…..እንዲሁ ስለከፋኝ ላግኝህ ብዬ ነው!›› ከድንጋጤዋ መረጋጋት የቻለች አትመስልም፡፡ ይህቺ ‹ስለ ከፋኝ ነው› የሴቶች ነገር ማድበስበሻ ናት መሰል፡፡
‹‹ምነው ምን ገጠመሽ?›› የተጨነቀ በመሰለ ድምጽ ግን ባልተጨነቀ ነገረ ሥራ ጠየቅኋት፡፡
‹‹አይ እንዲሁ!›› በረጅሙ ተነፈሰች፡፡
ከዚህ ካፌ ድንገት ተነስታ ብር ብላ ብትሄድ ደስ እንደሚላት ታስታውቃለች፡፡ ያደረግሽውን አውቄአለሁ ማለቴ ምነው ይሄን ያህል አስጨነቃት? ምን አድርጋኝ፤ ምን ክህደት ፈጽማብኝ ቢሆን ነው ይሄን ያህል? የምጨነቅላቸው እናቴ፣ አባቴና አንዲቷ እህቴ በህይወት አሉ፡፡ እኔም በአለንጋ ጣቶቼ ጺሜን እንደ ድሮው እያፍተለተልኩ፤ ቆሜ እየሄድኩ ነዉ፡፡ ምን አድርጋ ይሆን?
ከሌላ ተኝታ እሱን አውቆ ይሆናል ብላ ነው? ማድረጉ ካላስጨነቃት፤ የኔ ማወቅ ምን አስጨነቃት? እንኳን አስነክታ፤ ቆርሳ ሰጥታ ቢሆን እንኳን በአለንጋ ጣቶቼ ጸጉሬን እየነጨሁ ከመሄድ ውጪ ለመጠየቅ ምን መብት አለኝ? አድርጋው ከሆነ በርግጥ ያማል! የኔ ብቻ ስላት የኔ ብቻ አልሆና ከሆነ ያማል! በርግጥ የህመም ስሜት እየተሰማኝ አይደለም፡፡ ግን ምንን ነው የሚያመው? ምንስ ነው መታመም ያለበት? ምኔና ምኗ ነው የኔና የሷ ብቻ ሊሆኑ አልያም ሊታመሙ ቃል የተገባቡት?
‹‹በቃ እንውጣ!›› የጠጣችበትን ልትከፍል ቦርሳዋን መበርበር ጀመረች፡፡
‹‹እንዴ ቆይ ሻይ እንኳን ልጠጣ እንጂ!›› ካፌ ና ብላ ጠርታኝ፣ ሻይ እንኳን ሳልጠጣ ልውጣ እንዴ? እጄን ለማጨብጨብ አዘጋጅቼ፣ አስተናጋጅ ፍለጋ ቤቱን በዓይኔ ዞርኩት፡፡  
‹‹አይሆንም እንውጣ እራሴን አሞኛል›› አሥራ አምስት ብር አውጥታ አስቀምጣ፣ ከመቀመጫዋ ተነሳች፡፡
‹‹እኔም እራሴን አሞኛል፤ ቆይ ቡና ልጠጣና እንወጣለን!›› ጥላኝ ተነስታ፣ ወደ በሩ አመራች፡፡
ተነስቼ ተከተልኳት፡፡ ከካፌው ወጥታ ወደ ግራ የሚወስደውን መንገድ ያዘች፡፡ ዞር ብላ አላየችኝም። መከተሉ አይቀርም ብላ ይሆናል! የካፌው በር ላይ ቆሜ ለአፍታ ተመለከትኳት፡፡ ያ ቄንጠኛ አረማመዷ አብሯት የለም፡፡ ብከተላት ዛሬ መፈንገሉ ይቀር ይሆናል፡፡ ነገ ግን አይቀርልኝም! ነገ ፈንግላኝ ያ ቄንጠኛ አረማመዷን ትራመደዋለች፡፡ ዕድልማ አልሰጣትም፡፡ “ናና ልፈንግልህ” እስክትለኝ አልጠብቃትም፡፡ ደግሞ እያወቅሁ እንዳላወቀ ሆኜ ለምን ስቃይዋን ላብዛው? እኔው እራሴ፣ እራሴን ከሷ ማራቄ የመጨረሻ የፍቅር ስጦታዬ ይሁንልኝ፡፡
ትቻት ወደ ካፌው ተመልሼ ገባሁ፡፡ የተቀመጥንበት ቦታ ሄድኩኝና ማህሌት ተቀምጣበት የነበረው ወንበር ላይ ተቀመጥኩ፡፡ እንዴ ይገባኛል! ውጤቱ ያው ቢሆንም ዛሬ ፈንጋይዋ እሷ ሳትሆን እኔ ነኝ፡፡ ለትእዛዝ  ስፈልጋት የነበረች አስተናጋጅ፤ ገንዘብ ልታነሳ ስትመጣ ነጣ ያለ ማኪያቶ አዘዝኳት። ካፌው ውስጥ የቱ ጋር እንደተሰቀለ በማያስታውቅ ስፒከር፣ የሮኒ ዴቪስ ‹አይ ዎንት ክራይ› የሚል ሙዚቃ ይንቆረቆራል፡፡ እንዴት አልሰማሁትም ነበር ቅድም፡፡
‹‹ዳርሊን አይ ፋውንድ አውት ሎንግ ታይም ኤጎ
ዛት ዩ ዶንት ላቭ ሚ ኖት ኤኒ ሞር
በት አይ ኪፕ ኦን ላቪንግ ዩ ጀስት ዘ ሴም
ኦ አይ ኦ አይ
አይ ዎንት ክራይ!››
ማኪያቶዬን አንስቼ፣ ነብስ ይማር ሮኒ ብዬ ተጎነጨሁ፡፡ ፊቴ በፈገግታ እንደተሞላ ይታወቀኛል። ይሄኔ ያ መስታወት ውስጥ ያለው፣ ባለ ስስ ከንፈርና በቆሎ ጥርስ ሰውዬ ቢያየኝ ኖሮ፣ አብሮኝ ይፈግግ ነበር። እንኳንም በዚህ ሰዓት ፊቱ አልቆምኩ፡፡ አሁን እሱንም ማህሌትንም አልፈልጋቸውም፡፡  

Read 2133 times