Saturday, 05 May 2018 00:00

የዶ/ር ወልደመስቀልና የሻምበል ምሩፅ ሃውልቶች ነገ ይመረቃሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

   • የመታሰቢያ ውድድሮችን እናዘጋጃለን
             - ልጆቻቸው
           • ‹‹ለጀግና አትሌቶች አደባባይ ያስፈልጋል፡፡›› - ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ
           • የማሞ ወልዴንስ ማን ያሰራዋል? ልጁ
              ሳሙኤል ጥሪ ያቀርባል

     ለዋና አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ እና ለአትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ማስታወሻ የተሰሩት ሁለት ሃውልቶች ነገ የሚመረቁ ሲሆን፤ በነገው እለት ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚከናወን ስነስርዓት ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በላከው መግለጫ ሃውልቶቹን  ቤተሰቦቻቸው፤ የኢፌዲሪ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በጋራ እንዳሰሯቸው ገልፆ፤ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ውስጥ የነበራቸው ጉልህ ድርሻና ታሪክ ለመዘከር መሆኑንም አመልክቷል፡፡ ሀውልቶቹን ለማሰራት  በአጠቃላይ እስከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው “የሐውልት መሰራት ጥቅሙን በአግባቡ መለየት ያስፈልጋል፡፡  የሚሰራው ሃውልት ማንን ይጠቅማል? ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው፡፡ እንጅ የሞተው ሰውማ አንዴ አልፏል፡፡ ለጀግና ሃውልት መሰራቱ ለወገኑ፣ ለህዝቡ ነው የሚጠቅመው፡፡ በየትኛውም የሙያ መስክ  ተምሳሌት የሚሆኑት በህይወት ዘመናቸው ለአገራቸው ተግተው የሰሩና ያለፉ፤ ጀግንነታቸውን የሚያወርሱ ናቸው። የሚረከባቸው ትውልድ ከእነሱ ተምሮ፤ አገሩን ወዶ ለአገሩ ሰርቶ እንዲያልፍ ይነሳሳል፡፡››  የዶ/ር ወልደ መስቀልና የሻምበል ምሩፅ ሃውልቶችን ለማሰራት በተደረገው እንቅስቃሴ አንዳንድ ሰው በቁማቸው ብትረዷቸው አይሻልም ነበር ቢሉም እኛ ግን በቁማቸው ተረድተው ላይሆን ይችላል፤ ከሞቱ በኋላ  ግን ሌላው የሚረዳበትን መንገድ ማበጀት አለብን በሚል አስተሳሰብ ተግባራዊ ለማድረግ ችለናል ነው ያለው ሻለቃ ኃይሌ፡፡
በርግጥ የኢትዮጵያ ስፖርት በተለይ አትሌቲክስ ታላላቅ ታሪኮችን ለኢትዮጵያ፤  ለአፍሪካና ለዓለምም ያስመዘገቡ ብዙ ጀግኖችን አፍርቷል፡፡ ይሁንና ለእነዚህ ጀግኖች መታሰቢያ የሚሆኑ ሃውልቶች፤ አደባባዮች፤ የስፖርት መሰረተልማቶች እና ማዕከሎች ተሟልተው ተሰርተዋል ለማለትም ያስቸግራል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመላው ኢትዮጵያ ትልልቅ ስታድዬሞች የተገነቡ ቢሆንም በስፖርት ጀግኖች የመሰየማቸው ነገር ሳይስተዋል ቀርቶ ብዙዎቹ በሚገኙበት መዲና የሚጠሩ ሆነዋል፡፡  በስፖርት እና ሌሎች የመሰረተልማት ግንባታዎችም ስያሜዎችን ለጀግኖች መታሰቢያ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ብዙም የሚያበረታታ አይደለም፡፡ በታላላቅ ጀግና አትሌቶችና ስፖርተኞች ከተሰየሙ ስታድዬሞች መካከከል በአዲስ አበባና በአዳማ የሚገኙ ሁለት ስታድዬሞች በአበበ ቢቂላ ስም፤ በአሰላ የሚገኘው ጥሩነሽ ዲባባ ዘመናዊ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል፤ በአዲስ አበባ የኃይሌ ገብረስላሴ ጎዳና…. ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህ ባሻገር ግን የታላላቅ የኢትዮጵያ ስፖርት ጀግኖች የሆኑት  ቋሚ  መታሰቢያዎች በተለይ ሃውልቶች መገኛቸው የመቃብር ስፍራዎች ናቸው፡፡  የታላላቅ ጀግና አትሌቶችና ስፖርተኞች ሃውልቶች  ከመቃብር ስፍራ ይልቅ በአደባባዮች ፤ በስታድዬም መግቢያ ደጃፎች፤ በህዝብ መሰብሰቢያ ስፍራዎች፤ በስፖርት ማዕከሎችና መሰረተልማቶች ቅጥር ግቢ ቢተከሉ ይመረጣል፡፡
‹‹እከሌ ሃውልት ተሰራለት ቢባል ለራሱ ምንም አይደለም፡፡ ለህዝቡ ግን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ለቀደምት የስፖርት  ጀግኖች ሃውልት መሰራቱ አዳዲስ ጀግኖችን ለመፍጠር የሚጠቅም ነው፡፡ ለታሪክ ጀግኖቻችን ቋሚ መታሰቢያዎችን በምናቆምበት አቅጣጫ በሁሉም ባለድርሻ አካላት መታሰብ አለበት፡፡ ለዚህም የማቀርበው ሃሳብ የጀግና አትሌቶችና ስፖርተኞች አደባባይ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ ይህ አይነት የታሪክ ቋሚ መታሰቢያ የሆነ አደባባይ ሊፈቀድ ይገባል፡፡ በአደባባዩ ላይ  ጀግና አትሌቶችና ስፖርተኞችን በቋሚነት የሚዘክሩ ሃውልቶችን በአንድ አካባቢ አሰባስቦ ለማቆም በማቀድ ብንሰራ እመርጣለሁ፡፡ ምናልባት አደባባዩ ላይ የሚሰሩ ሃውልቶች የጀግና አትሌቶችና ስፖርተኞችን የአሯሯጥ፤ የአጨራረስ ሁኔታ እና የተለየ ስብዕና የሚገልፁ፤ ታላላቅ የስፖርት ታሪኮቻቸውንና ጀግንነቶቻቸውን የሚያንፀባርቁ ቢሆኑ መስህብነታቸው ይጎላል።›› በማለት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ስለሚያደርጓቸው ጥረቶች የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ  ተናግሯል፡፡
እንደሻለቃ ኃይሌ እምነት የጀግና አትሌቶችና ስፖርተኞች አደባባይ መገንባት ለአገር ባለውለታ ለሆኑ ሁሉ ክብር የሚሰጥበት፤ በሌሎች መስክ ያሉ ጀግኖችንም ለማበረታታት፤ ለመጭው ትውልድ መነሳሳትን ለመፍጠር፣ እንዲሁም የከተማዋን ገፅታ ለማሳመር የሚቻልበት ይሆናል፡፡ ሻለቃ ኃይሌ ለሚያቀርበው ለዚህ ልዩ እቅድ ምሳሌዎችን ይኖራሉ፡፡ እሱ የጠቀሰው ምሳሌ በፊንላንድ አገር በእነምሩፅ ይፍጠር ዘመን ለነበሩት ምርጥ የረጅም ርቀት አትሌቶች እነ ፓቮ ኑርሚና ሌሎችም ተመሳሳይ አደባባዮች ተሰይሞላቸው ቋሚ መታሰቢያዎች እንደቆሙላቸው ነው፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ራሽያ ዋና ከተማ ተመሳሳይ አደባባዮች አሉ፡፡ በሞስኮ ከሚገኙ በታዋቂ አደባባይ ከሚገኙ የህዝብ መናፈሻዎች አንዱ ምንም እንኳን የስፖርት ጀግኖች ባይሆኑም ለጠፈር ተመራማሪ ሳይንቲስቶች፤ ተጓዦችና መንኮራኩራቸው በግዙፍ ሃውልቶች እና ቅርፆች መሰራቱንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሻለቃ ኃይሌ ለስፖርት አድማ እንደገለፀው እንዲህ አይነቱን ቋሚ መታሰቢያ ለቀደምት የስፖርት ጀግኖች የመመስረት እቅድ ሊሰራ የሚችል ቢሆንም ፈታኞቹ ሁኔታዎች ቦታ ለማግኘት እና ለማስፈቀድ፤ ባለድርሻ አካላትን አስተባብሮ ግንባታውን ለማስጀመር የሚታለፍባቸው ሂደቶች ከልክ በላይ ግዜ የሚፈጁ መሆናቸው ነው፡፡ እንግዲህ የጀግኖቹ አትሌቶችና ስፖርተኞች የአበበ ቢቂላ፣ የምሩፅ ይፍጥር፣ የዶ/ር ወልደመስቀል ….ሌሎችም በየመካነመቃብሮቹ ተወስነው መቅረታቸውን የጀግና አትሌቶችና ስፖርተኞች አደባባይ መመስረቱ ሊቀይረው ይችላል። ‹‹የአደባባዩ መቋቋም በሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶችን ያነቃቃል፡፡ ሌሎች አዳዲስ ጀግኖች ይፈጥራል ይህ ዋና ግቡ ነው። ከዚያም ባሻገር ለአገር ባለውለታዎች እንዲህ በገዘፈ ሁኔታ ክብር ሲሰጥ፤ በየትኛውም የሙያ መስክ ለሚሰሩ ፤ ለሌሎችም አርኣያና ተምሳሌት ለሚሆኑ ግለሰቦች ብርታትም ይሆናል፡፡ ታሪክ ሰርቶ የማለፍ ጉጉት ይኖራል፡፡›› በማለት ሻለቃ ኃይሌ የልዩ እቅዱን ተግባራዊነትና ውጤቱን እንደሚናፍቅ አስገንዝቧል፡፡
ልጆቻቸው ያዕቆብና ቢኒያም ምን ይላሉ?
ልጃቸው ያዕቆብ ወልደመስቀል ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት ለሐውልቱ መሰራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያደረጉትን አስተዋፅኦ ከልቡ እንደሚያመሰግን ገልፆ በተለይ የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ከፍተኛ አመራሮች ፕሬዝዳንቱ ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ የፅህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ቢልልኝ መቆያ፤ የአትሌቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ስለሺ ስህንና ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ  እንዲሁም የቀድሞ የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ አለባቸው ንጉሴ ከጎኔ መቆማቸውን በአድናቆት አመሰግናለሁ ብሏል፡፡ በተለይ ደግሞ ዶክተር ከዘራቸውን ይዘው፤ ወንበር ላይ ተቀምጠው ሰዓታቸውን እየያዙ ሲያሰልጠኑ የነበራቸውን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ፎቶ አፈላልጎ ለሰጠው የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ገብረእግዚአብሄር ልባዊ ምስጋናውን ያቀረበው ያዕቆብ ሃውልቱ ተሰርቶ እስኪያልቅ ከጎኑ በመሆን ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ በመግለፅ ነው፡፡ ያዕቆብ ወልደ መስቀል አባቱን በቋሚ መታሰቢያ ለመዘከር ያለውን እቅድ ለስፖርት አድማስ ሲገልፅ በቀጣይ ዓመታት በስማቸው መታሰቢያ የአትሌቲክስ ውድድር ለማዘጋጀት አቅዶ ዝግጅቱን መጨረሱን ጠቁሞ የህይወት ዘመን ታሪካቸውን፤ የአሰልጣኝነት ስራቸውንና ሌሎች ከአትሌቲክስ ጋር የሚገናኙ ቅርሶቹን በመፅሃፍ እንደሚያሳትምም አስታውቋል፡፡
በአትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የሃውልት ስራ ከፍተኛውን ጥረት ያደረገው ልጁ ቢኒያም ምሩፅ ሲሆን ለሐውልቱ የሚሆነውን ፎቶ በመምረጥ፤ ስፖንሰሮችን በማፈላለግ እንዲሁም ስራው ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ለስድስት ወራት መንቀሳቀሱን ለስፖርት አድማስ ተናግሯል፡፡ ሃውልቱ በነገው እለት ሲመረቅ የህይወት ታሪኩንና የሩጫ ዘመኑን የሚያወሳ ልዩ መፅሄት አዘጋጅቻለሁ የሚለው ቢኒያም በቅርብ ጊዜ ደግሞ የመታሰቢያ ውድድር ለማዘጋጀት እቅድ እንዳለው አመልክቷል፡፡ አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ህይወቱ ካለፈበት ጊዜ አንስቶ ወደ አገሩ በክብር እንዲመለስ እና የቀብር ስነስርዓቱ በአግባቡ እንዲፈፀም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አትሌቶችና ሌሎች የስፖርት ባለድርሻ አካላት  ለሰጡት ድጋፍ ቢኒያም ምሩፅ ምስጋናውን ይገልፃል፡፡ ሃውልቱን ለሁለት ወጣት አርቲስቶች እድሉን በመስጠት ማሰራቱን ለስፖርት አድማስ የገለፀው ቢኒያም፤ ለአትሌቶች ቋሚ መታሰቢያዎች በአገሪቱ እንዲኖሩ ከፈርቀዳጆቹ ከእነአበበ ቢቂላ አንስቶ ብዙ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ በመጥቀስ ወደፊት ለሁሉም የሚሆን አደባባይ ቢሰየም እና ክብርና ደረጃውን ጠብቆ ቢተገበር ደስተኛ ነኝ ብሏል።
ዶክተር ወልደመስቀል  
ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ በ69 ዓመታቸው ግንቦት 8 2008 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ይተወቃል፡፡ በተለይ በረጅም ርቀት አሰልጣኝነታቸው ጉልህ ለውጥ በማምጣት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ዕውቅና ሊያገኙበት የቻሉበትን ስራ ማከናወን የቻሉ ታላቅ ባለሙያ ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን እያሰለጠኑ በተሳተፉባቸው አምስት ኦሎምፒኮች ላይ 28 ሜዳሊያዎችን  (13 ወርቅ 5የብር እና 10 የነሐስ ሜዳሊያዎችን) በድምሩ አስገኝተዋል፡፡ ከ8 በላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ በመስራትም ተሳክቶላቸዋል፡፡ በአትሌቲክሱ ዓለም ለአሰልጣኞች የሚሸለመውን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝነት ሽልማትን በ2006 ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓመቱ ምርጥ አሰልጣኝ የተባሉ ሲሆን በ2011 እኤአ የአፍሪካ ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው በሞሮኮ ማራካሽ የተሸለሙ እና በ2015 ደግሞ የበጎ ሰው ሽልማትን በስፖርት ዘርፍ አሸናፊም ነበሩ፡፡
ማርሽ ቀያሪው
ጀግና አትሌት፤ ፈርቀዳጅ ኦሎምፒያን፤ ማርሽ ቀያሪው በሚሉ ልዩ ስሞቹ የሚታወሰው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በ72 ዓመቱ ያረፈው ከዓመት በፊት ታህሳስ 23  ነበር፡፡ በወጣትነቱ ከጋሪ ነጂነት ጀምሮ፤ በተለያዩ ፋብሪካዎች ተቀጥሮ የሰራው ምሩፅ በሩጫ ዘመኑ ከ410 በላይ ውድድሮች ተሳትፎ በ271 ውድድሮች አሸንፏል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ መድረክ በድምሩ 7 የወርቅ ሜዳልያዎች ለኢትዮጵያ ያበረከተ ሲሆን፤  በተለይ በሁለት ኦሎምፒኮች በመሳተፍ 2 የወርቅ እና 1 የነሐስ የኦሎምፒክ ሜዳልያዎች ተጎናፅፏል፡፡ በ1972 እኤአ በሙኒክ ኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም በ1980 እኤአ በሞስኮ ኦሎምፒክ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ያስመዘገባቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡  ምሩፅ ውድድር ሲያቆም ከአትሌቲክስ አልራቀም፡፡ ጀግና ጀግናን ያፈራል፡፡ እንደሱ የኦሎምፒክ ጀግኖችን፤ እነቀነኒሳ በቀለን፤ እነሚሊዮን ወልዴንና ገዛኸኝ አበራን በማሰልጠን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በ2008 እኤአ ላይ ቤጂንግ አስተናግዳ በነበረው 29ኛው ኦሎምፒያድ የኢትዮጵያን ባንዲራ በማነገብ ሲሰለፍ ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ በ10ሺና በ5ሺ ሜትር የድርብ ወርቅ ሜዳልያዎች አሸናፊ በመሆን የምሩፅን ክብረወሰን በተጋሩባቸው ድሎች ኮርቷል፡፡
የማሞንስ ማን ያሰራዋል? ልጁ ሳሚ ጥሪ ያቀርባል…
በነገራችን ላይ ለዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ እና ለአትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የተሰሩ ሃውልቶች ነገ በስላሴ ቤተክርስትያን መመረቃቸውን ተከትሎ መነሳት ያለበት ተያያዥ ጉዳይ አለ፡፡ ይሄውም  ጎተራ አካባቢ በሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር ስላረፉት  የኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ አትሌቶች አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ ሃውለቶች በተመለከተ ነው። ከ12 ዓመታት በፊት ለሁለቱ አትሌቶች በዚሁ መካነ መቃብር ተሰርተው ጎን ለጎን የተተከሉት ሁለት ሃውለቶች በሚያሳዝን ሁኔታ  መፈራረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡  የሻምበል አበበ ቢቂላ ቤተሰቦች እና ሌሎች ድጋፍ ሰጭዎች ከ4 ዓመት በፊት የታላቁ የማራቶን ጀግና ሐውልት እንደገና ተሰርቶ በስፍራው እንዲተከል አድርገዋል፡፡ ይሁንና  አጠገቡ ለነበረው የማሞ ወልዴ ሃውልት ግን ይህ ማድረግ አልተቻለም፡፡  የማሞን ሀውልት ከፈረሰ በኋላ ደግሞ ለማሰራት ግንባርቀደሙን ጥረት  ያደረጉት ክቡር አቤሴሎም ይህደጎ ነበሩ፡፡ እሳቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ግን ተመሳሳይ ጥረት ያደረገ የለም ከማሞ ወልዴ የበኩር ልጅ ሳሙኤል በቀር፡፡
የማሞ ወልዴ የበኩር ልጅ ሳሙኤል ማሞ ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው በዮሴፍ ቤተክርስትያን ከአበበ ቢቂላ ጎን የሚገኘው የአባቱ  መቃብር ህጋዊ መረጋገጫ ባለው ቦታ ላይ የሚገኝ ነው። የአባቱን ሃውልት መልሶ ለማቆም ጥረት ማድረግ የጀመረው በፈረሰበት ማግስት መሆኑን የሚጠቀስው ሳሙኤል፤ በቦታው ይገባኛል ከአበበ ቢቂላ ቤተሰቦች ጋር ክርክሮች መፈጠራቸው ብዙ ነገሮች ማጓተቱን በቁጭት ነው የሚናገረው፡፡ ከተከበሩ የአትሌቲክስ ስፖርት የቅርብ ደጋፊ እና አጋር አቤሰሎም ይህደጎ ጥረት በኋላ ግን በማሞ ሐውልት መልሶ መቆም ዙርያ ሳሙኤል ብቻውን እልህ አስጨራሽ ትግል ሲያደርግ ቢቆይም ሊሳካለት አልቻለም፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ጉዳዩን በመግለፅ ድጋፍ የሚሰጠው አካል ማፈላለጉን፤ ባለፈው 1 ዓመት እንኳን በፋና ኤፍኤም ስፖርት ዞንና በጄቲቪ ጆሲ ኢንዘሃውስ ሾው በመቅረብ መናገሩንም ለስፖርት አድማስ ገልጿል፡፡
‹‹የተከበሩ አቤሰሎም ይህደጎ በቀስተደመና የስፖንጅ ፋብሪካ የስራ እድል ሰጥተውኝ በወርሃዊ ደሞዝ የምተዳደር ነኝ፡፡ ስለዚህም በግሌ ሐውልቱንየማሰራበት አቅም የለኝም፡፡ ማሞ የእኔ አባት ሆነ እንጅ ጀግነነቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ነው፡፡ ስለዚህም ሃውልቱን እንድናሰራ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ ሃላፊነቱም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ፤ እንዲሁም የስፖርቱ ተቋማት ናቸው፡፡ ፍላጎቱ ካለ በግለሰብ ደረጃም ሊሰራ ይችላል፡፡ ስለዚህም ጀግኖችን ማክበር አለብን፡፡›› በማለት ሳሙኤል ማሞ ወልዴ ለስፖርት አድማስ የማጠቃለያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ  ይህን በተመለከተ ከስፖርት አድማስ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ “የማሞን ሐውልት ለማሰራት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከርን  ነበር፡፡ ሀውልቱ በቆመበት መካነ መቃብር ያስተዋልናቸው አንዳንድ ችግሮችአሉ፡፡ ልክ የምሩፅ ልጅ ቢኒያም እንዳደረገው ባለድርሻ አካላት ከማሞ ወልዴ ቤተሰቦች ጋር ተባብረው ሃውልቱን መልሰው የሚያቆሙበት ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት ማድረጋችን የሚቀጥል ነው፡፡›› ብሏል፡፡
ሻምበል ማሞ ወልዴ
ማሞ ወልዴ ከ16 ዓመታት በፊት ግንቦት 16 ላይ በ69 ዓመት እድሜው ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ የሚታወስ ነው፡፡   የኢትዮጵያ ወታደር ኦሎምፒያንና ጀግና ሯጭ
በሚል ርእስ  በቀጣይ ሳምንታት የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ የሚዘከር ይሆናል፡፡
ለሻምበል ማሞ ወልዴ ክብር መካነ መቃብሩ በሚገኝበት ዮሴፍ ቤተክርስትያንና ከዚያም በኋላ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተሰቀለው የኦሎምፒክ ቦርድ መታሰቢያ ያደረጉለት የረጅም ጊዜ የአትሌቲክስ አፍቃሪ ክቡ አቤሰለም ይህደጎ ነበሩ፡፡  ከኢትዮጵያ ውጭ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ በሚደነቅበት ስፔን በ2002 እኤአ ላይ ልዩ መታሰቢያ እንደቆመለት መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ በ1963 እኤአ ላይ በስፔኗ ኤልጎባር ከተማ በሚካሄደው የሁዋን ሙጉዌራዛ አገር አቋራጭ የተሳተፈ የመጀመርያው አፍሪካዊ ነበር። በዚሁ የአገር አቋራጭ ላይ ለአራት ጊዜያት በ1963፤ 1964፤ 1967 እና 1968 እኤአ ላይ ማሸነፍም ችሏል፡፡ ይህን ደማ ታሪኩን በማክበርም በስፔን የባስክ ግዛ በምትገኘው ኤልጎባ የተባለች ከተማ ኢስታላሲኒዮስ ስፖርትስ ማንቴስታ በተባለ ማዕከል በአልሙኒዬም ላይ የተሰራ እና 1.80 ሜትር የሚረዝም ልዩ ሃልት በ1930ዎቹ ገናና ሯጭ ከነበረው ስፓንያዱ ሁዋን ሙጉዌራዛ ጎን ቆሞለታል፡፡
አበበ እና ማሞ የክቡር ዘበኛ ወታደሮች ከሆኑበት ጊዜ አንስቶ የሚተዋወቁ ሲሆን በሩጫ ዘመናቸውም የማይነጣጠሉ የቅርብ ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ አብረው ይሰለጥናሉ፡፡ አብረው ይወዳደራሉ፤ ርስባራሳቸው ይከባበራሉ ይደጋገፋሉ፡፡ ማሞ አትሌቲክሱን ከአበበ ቢቂላ ቀድሞ ቢጀምርም ስኬታማ ሆኖ በጀግንነት የወጣው እሱን ተምሳሌት አድርጎ ነው፡፡ አበበ ሮጦ ውጤታማ መሆን ያስተማረኝ ጀግናዬ ብሎ በአንድ ወቅት አድንቆታል፡፡

Read 3768 times