Print this page
Monday, 07 May 2018 09:46

የላይቤሪያ የቀድሞ መሪ በተሸለሙት 5 ሚ. ዶላር የሴቶች ማዕከል ሊያቋቁሙ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   የሞ ኢብራሂም ሽልማትን ያገኙ የመጀመሪያዋ ሴት ናቸው

   የሞ ኢብራሂም ተቋምን የአፍሪካ የአመራር ልህቀት ሽልማት በማግኘት የመጀመሪያዋ ሴት የሆኑት የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፤ ባለፈው ሳምንት ከተቋሙ በሽልማት መልክ ያገኙትን 5 ሚሊዮን ዶላር የአገራቸውን ሴቶች የማብቃት አላማ ያለው ማዕከል ለማቋቋም እንደሚያውሉት አስታውቀዋል፡፡
ለሁለት ተከታታይ የስልጣን ዘመናት አገራቸውን የመሩትና ከወራት በፊት ስልጣናቸውን ያስረከቡት የኖቤል የሰላም ተሸላሚዋ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፤ አገሪቱን ለአመታት ከዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት እንድታገግም ለማድረግ በተጫወቱት ቁልፍ ሚናና በአመራር ብቃታቸው ለዘንድሮው የሞ ኢብራሂም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን የዘገበው ሲኤንኤን፤ ባገኙት የሽልማት ገንዘብ በስማቸው የተሰየመ የሴቶችና የልማት ማዕከል እንደሚያቋቁሙ መናገራቸውን አመልክቷል፡፡
“የአገሬ ሴቶች የለውጥ ሃዋርያ፣ የሰላም ጠባቂና የእድገት ቀያሾች እንዲሆኑ ለማገዝ ራሱን የቻለ ማዕከል የማቋቋምና ሴቶችን የማብቃት ስራዬን አጠናክሬ እቀጥላለሁ” ሲሉ የቀድሞዋ መሪ የ79 አመቷ ሰርሊፍ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል። በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ፣ አገራቸውን በተጨባጭ ያሳደጉ፣ ህጉ የሚፈቅድላቸውን የስልጣን ገደብ አክብረው በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ያስረከቡ አፍሪካውያን መሪዎችን የሚሸልመው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፤ እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ በነበሩት አመታት ሽልማት ሳይሰጥ መቆየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም የሆነው መስፈርቱን የሚያሟላ አፍሪካዊ መሪ ሊያገኝ ባለመቻሉ እንደነበር ጠቁሟል፡፡
በሱዳናዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጸጋ ሞ ኢብራሂም እ.ኤ.አ በ2006 የተቋቋመው የሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን፤ ከመሪዎች በተጨማሪም የአፍሪካ አገራትን የመልካም አስተዳደር ሁኔታ 88 ያህል መስፈርቶችን በመጠቀም እየገመገመ ደረጃቸውን በየአመቱ ይፋ እንደሚያደርግም አመልክቷል፡፡

Read 1409 times
Administrator

Latest from Administrator