ቱኒዚያ የዓለም የፕሬስ ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ ከትላንት በስቲያ የዩኔስኮ ዋና ሃላፊ አይሪና ቦኰቫን ተቀብላ ያስተናገደች ሲሆን ይሄም ሃላፊው ህዝባዊ አብዮቶች በተጠነሰሱባቸው ሥፍራዎች ለአራት ቀናት የሚያደርጉት ጉብኝት አካል ነው ተብሏል፡፡
መቀመጫውን ፓሪስ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ቡድን፤ አዲሱን የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ እና በስልጣን ላይ ያሉትን የግብፅ ወታደራዊ መሪዎች ጨምሮ ስድስት አዳዲስ የፕሬስ ነፃነት “አፋኞችን” ይፋ አድርጓል፡፡
የአገሪቱን ሚዲያ እግር ከወርች ጠፍረውት የነበሩት የቀድሞ የቱኒዚያ አምባገነን መሪ ቤን አሊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በርካታ አዳዲስ ህትመቶች፣ ኦንላይን የዜና ድረገፆችና የቴሌቪዥንና የሬድዮ ጣቢያዎች እንዳቆጠቆጡ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡