Saturday, 12 May 2018 11:40

ፕ/ር አብይ ፎርድ (ከ1927-2010 ዓ.ም)

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

አስክሬናቸው ረቡዕ ጠዋት አዲስ አበባ ይደርሳል
    
    ታዋቂው የጋዜጠኝነት እና የፊልም ጥበብ ምሁሩ ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ በ83 ዓመታቸው ህክምናቸውን ሲከታተሉ በቆዩበት አሜሪካን ሃገር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን አስክሬናቸው ረቡዕ ጠዋት አዲስ አበባ ደርሶ የቀብር ስነ ስርዓታቸውም የቤተሰባቸው መካነ መቃብር በሚገኝበት ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ይፈፀማል ተብሏል፡፡
የአፄ ኃይለ ሥላሴን የ25ኛ ዓመት የዘውድ በዓል ለማክበር ከካሪቢያን መጥተው እዚሁ ኢትዮጵያ ኑሮአቸውን ከመሰረቱት የፎርድ ቤተሰቦች እ.ኤ.አ መጋቢት 5 ቀን 1935 አዲስ አበባ ውስጥ የተወለዱት ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እናታቸው ሚስ ፎርድ ባሰሩትና ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው “ሚስ ፎርድ የአፀደ ህፃናትና የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት” የተማሩ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሊሴ ገ/ማሪያም ተከታትለዋል። አብይ ፎርድ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአሜሪካ በፓኔ ውድስ ጁኒየር ኮሌጅ በአንደኛ ደረጃ ስርአተ ትምህርት” የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አብይ ፎርድ፤ በአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በ“ፊልም ጥናት” ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል፡፡ በፊልምና ተያያዥ የትምህርት መስኮች ለ33 ዓመታት በመምህርነት ከአገለገሉ በኋላ ከዝነኛው ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም ለረጅም ዓመታት በኮሚኒኬሽን ዲፓርትመንት የጋዜጠኝነት እና የፊልም አሰራር ስነ ጥበብ ትምህርት አስተምረዋል፡፡ ከ26 በላይ ዶክመንተሪ ፊልሞችም ሰርተዋል - ፕሮፌሰሩ፡፡
ከፊልም እና ጋዜጠኝነት አስተማሪነታቸው ባሻገር በአሜሪካ አየር ኃይል ኤሮ አክቲቪቲ በፓይለትነት አገልግለዋል፡፡
የዘርፈ ብዙ ሙያዎች ባለቤት የነበሩት ፕሮፌሰሩ፤ ከሙዚቃ መሳሪዎች ጊታር፣ ሳክስፎንና ፒያኖ አሳምረው በመጫወት ይታወቃሉ፡፡ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ጣልያንኛ ቋንቋዎች አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር፡፡
ለረጅም ጊዜ ከኖሩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ድህረ ምረቃ (የሁለተኛ ዲግሪ) ትምህርት መርሃ ግብር እንዲጀመር አስተዋፅኦ ከማበርከታቸው በተጨማሪ የትምህርት ክፍሉ ዲን በመሆንም አገልግለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የፊልም ጥናት ትምህርት ክፍል ለመክፈት ጥናት ያደረገው ግብረ ኃይል አማካሪም ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ አፍቃሪ የነበሩት የፕሮፌሰሩ ወላጆች እዚሁ ኖረው፣ ህይወታቸው ሲያልፍም፣ እዚሁ ነው ያረፉት፡፡ ልጆቻቸውን ለመጠየቅ ወደ አሜሪካ ባቀኑበት አጋጣሚ ህይወታቸው ቢያልፍም አስክሬናቸው ወደዚህ መጥቶ ቀብራቸው አዲስ አበባ ተፈፅሟል፡፡ በተመሳሳይ ወንድማቸው ዮሴፍ ኃይለሥላሴ ፎርድ በአሜሪካ ህይወታቸው ቢያልፍም ቀብራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈፅሟል፡፡
ከፕሮፌሰር አብይ ፎርድ ጋር የቀረበ ወዳጅነት የነበራቸው የኢኮኖሚክስ ምሁሩ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ፤ “ፕሮፌሰሩ ባለ ልዩ ተሰጥኦና ባለ ብሩህ አዕምሮ ተመራማሪ ነበሩ” ይላሉ፡፡
“ለኢትዮጵያ ሚዲያ ልዕልና የታገሉ ምሁር ናቸው” ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ “እስከ መጨረሻው የነበራቸው እምነትም የሃገሪቱ ሚዲያዎች አራተኛ የመንግስት አካልነታቸውን ሚና ጠንክረው መወጣት አለባቸው” የሚል ነበር ይላሉ፡፡ ለሃገሪቱ የሚዲያ ምህዳር መሻሻልም ቀናኢ የሆኑ ሙግቶችን የሚያቀርቡ የሚዲያው ጠበቃ ነበሩ ይላሉ - ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡፡ 

Read 7521 times