Sunday, 13 May 2018 00:00

በሱዳንና በኬንያ 3 ሺ ያህል ኢትዮጵያውያን እስረኞች ተለቀቁ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

በሱዳን የተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው የነበሩ 1400 ያህል ኢትዮጵያውያን ከእስር የተለቀቁ ሲሆን በኪንያ እስር ቤቶች የሚገኙ 1600 እስረኞችም እንደተፈቱ ታውቋል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ በሱዳንና በኬንያ ባደረጉት ይፋዊ ጉብኝት፣ ከሃገራቱ መሪዎች ጋር በትኩረት ከተወያዩባቸው ጉዳዮች አንዱ በሃገራቱ ታስረው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን የሚመለከት ሲሆን እስረኞቹ እንዲፈቱ መወሰኑም ይታወቃል፡፡
ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 2 የሱዳን መንግስት፣ በሃገሪቱ ኢትዮጵያውያን በብዛት ታስረው የሚገኙበት ጅድ አልሁዳ እስር ቤት ጨምሮ ከተለያዩ ወህኒ ቤቶች 1400 ያህል እስረኞችን ፈትቷል፡፡
በሱዳን በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ብዛት 3 ሺህ እንደሚገመት የጠቆሙት ምንጮች፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በሱዳን እስር ቤቶች ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ግብፃውያንና ኤርትራውያን እስረኞች እንደሚገኙ የሚናገሩት ምንጮች፤ ኤርትራውያን ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ብለዋል፡፡ ከእስር የተለቀቁ ኢትዮጵያውያን የሱዳንን ህግና ስርአትን አክብረው በሃገሪቱ መኖርና መስራት እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡ በተመሣሣይ በኬንያ በእስር ላይ የነበሩ 1600 ያህል ኢትዮጵያውያን የተፈቱ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው፣ በሃገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ መጠየቃቸው ተጠቁሟል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለተመሳሳይ አላማዎች በተለያዩ ሃገራት ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅ/ቤት አስታውቋል፡፡
ባለፈው አንድ ወር በሃገር ውስጥ እና በጎረቤት ሃገራት በርካታ ጉብኝቶችን ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከትናንት በስቲያ ለ48 ባለስልጣናት የሚኒስትር ዴኤታነትና ሌሎች ሹመቶችን መስጠታቸው ታውቋል፡፡

Read 6624 times