Saturday, 12 May 2018 11:35

የ21ኛው የዓለም ዋንጫ አጋሮች፤ ስፖንሰሮች፤ የስፖርት ትጥቅ አቅራቢዎችና ማህበራዊ ሚዲያዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የዓለም ዋንጫ ትርፋማነት ባለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች እየቀነሰ ቢመጣም ስኬታማ ከሆኑ ዓለም አቀፍ የገበያ መድረኮች ተመራጩ እንደሆነ ይታወቃል። የስፖርት ውድድሩን ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ከ6 ቢሊዮን በላይ ድምር ተመልካችና ትኩረት የሚያገኝ ነው፡፡ በ200 አገራት ለቢሊዮኖች በብሮድካስት፤ በህትመት፤ በዲጅታል እና በድረገፅ ይሰራጫል፡፡
ከዓለም ዋንጫ ጋር በስፖንሰርሺፕ እና በንግድ አጋርነት  በመተሳሰር ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ትልልቅ ኩባንያዎች አዳዲስ ደንበኞችን የሚያፈሩበት የገበያ ዘመቻ ይሰሩበታል፡፡ በከፍተኛ ወጭ የሚያሰሯቸውን ማስታወቂያዎች በመጠቀም ምርቶቻቸውን፤ አገልግሎታቸውን፤ የብቃት ደረጃቸውን  ያስተዋውቁበታል፡፡ የንግድ ምልክታቸውን ከስፖርት አፍቃሪው ትኩረት እና ስሜት ጋር ለማዋሃድ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች በሚካሄዱባቸው ከተሞችና ስታድዬሞች ገፅታቸውን የሚገነቡ የማስታወቂያ ቢልቦርዶች ይሰቅላሉ፡፡ በዘመናዊዎቹ ስታድዬሞች ሜዳ ዙርያ  እና ከሜዳ ውጭ ውድድሩን በሚያጅቡ የማስታወቂያ ድባቦች ይሞሉታል፡፡  በተለያዩ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ወቅታዊ ህትመቶችና ዲጅታል የመረጃ ስርጭቶች ለብዙዎች ይደርሳሉ፡፡ በዓለም ዋንጫው ጨዋታዎች መጀመርያ አጋማሽ፤ እና ፍፃሜ በቀጥታ በሚተላለፉ ማስታወቂያዎች፤ የገበያ ማፈላለጊያ ፕሮሞሽኖች፤ በተለያዩ አዳዲስ ምርቶች ትውውቅ፤ ለዓለም የእግር ኳስ የሚያደርጓቸውን ልዩ አስተዋፅኦዎች በሚገልፁ ማስታወቂያዎቻቸው የፊፋ የዓለም ዋንጫ፤ አጋሮች፤ ስፖንሰሮች እና ክልላዊ አጋሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) በራሽያ ለሚካሄደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ በሶስት የስፖንሰርሺፕ  ደረጃዎች  ከ15 ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተዋውሏል፡፡ ከ4 ዓመት በፊት ብራዚል ባዘጋጀችው 20ኛው የዓለም ዋንጫ 20 ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ፊፋ በእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ  ላይ በትብብር በስፖንሰርሺፕ የሚሰሩትን አለም አቀፍ ኩባንያዎች በ3 ደረጃዎች ሲከፍል የመጀመርያዎቹ የፊፋ አጋሮች ፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኙትን የዓለም ዋንጫ ስፖንሰሮች እንዲሁም በ3ኛ ደረጃ ያሉትን ደግሞ ክልላዊ አጋሮች በማለት ይመድባቸዋል፡፡ ለ8 ኩባንያዎች ክፍት በነበረው የፊፋ አጋሮች ምድብ ሰባት ተገኝተዋል። እነሱም ኮካ ኮላ፤ ሃዩንዳይ ኪያ ሞተርስ፤ ቪዛ እና አዲዳስ የነበራቸውን ኮንትራት በማደስ የቀጠሉ የፊፋ ነባር አጋሮች ናቸው፡፡ ዘንድሮ በአዲስ ኮንትራት የፊፋ አጋሮች ሆነው የመጡት ደግሞ በአረቡ ዓለም እና ሩቅ ምስራቅ ግዙፉ አየርመንገድ ኳታር ኤር ዌይስ ከኳታር፤ የነዳጅ ኩባንያው ጋዝ ፕሮም ከራሽያ እና የዓለማችን ግዙፉ የሪልስቴት እና የሃብት ዴቨሎፕር ዋንዳ ግሩፕ ከቻይና  ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች  ከዓለም ዋንጫ ጋር ራሳቸውን በማስተሳሰር የሚሰሩ ሲሆን በመላው ዓለም የውድድሩ ዋና አጋር ሆነው የሚጠቀሱና በስፖንሰርሺፕ ስምምነታቸው በነፍስወከፍ በየዓመቱ 121 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላሉ፡፡
ሁለተኛ ደረጃ የዓለም ዋንጫ ስፖንሰሮች ተብሎ በቀረበው የስፖንሰርሺፕ ምድብ ለ6 ኩባንያዎች ክፍት የነበረው እድል ላይ 5 ተገኝተዋል፡፡ በ20ኛው የዓለም ዋንጫ ብራዚል ላይ  ብዛታቸው ስምንት ነበር። የዓለም ዋንጫ ስፖንሰሮች በነፍስ ወከፍ በየዓመቱ 50 ሚሊዮን ፓውንድ የሚከፍሉ ሲሆን ሎጎዋቸውን በየስታድዬሞቹ የሚለጥፉ  ናቸው፡፡ ቡድዋይዘር እና ማክዶናልድ በሁለተኛ ደረጃ የዓለም ዋንጫ ስፖንሰነታቸው የነበራቸውን ውል በማደስ የገቡ ሲሆን የተቀሩት ሁሉም የቻይና ኩባንያዎች ናቸው።   ከፊፋ ጋር የዓለም ዋንጫ ስፖንሰርሺፕ ውላቸውን ያቋረጡ የዓለም ዋንጫ ስፖንሰሮች የምዕራቡ አለም ኩባንያዎች ሲሆኑ ኮንትኔንታል ጆንሰን ኤንድ ጆንሰንና ካስትሮል ናቸው፡፡  በ2015 እኤአ ላይ እነዚህ የሰሜን አሜሪካ እና የአውሮፓ ኩባንያዎች ውላቸውን ሲያቋርጡ ከ2017 ጀምሮ የተኳቸው የቻይና ኩባንያዎች የመጀመርያው ግዙፉ የቻይና የፅዳት ኩባንያ ሜንጊኒወ ሲሆን በ64 የዓለም ዋንጫ ግጥሚያዎች ምርቱንና ብራንዱን ለማስተዋወቅ የተዋዋለ ነው። ሌሎቹ የቻይና ኩባንያዎች ደግሞ የኤሌክትሮኒክ ኩባንያው ሂሴንሴ እና የስማርት ሞባይል አምራቹ ቪቮ ናቸው። ታላላቆቹን የፊፋ አብይ ስፖንሰሮች በመተካት ወደ ዓለም ዋንጫው የገቡት የቻይና ግዙፍ ኩባንያዎች ናቸው ቻይና ለእግር ኳስ የሰጠችውን ትኩረት የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ቻይና በዓለም እግር ኳስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አድርጋለች፡፡ ዋና እቅዷም በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት እሰከ 2030 እኤአ ዓለም ዋንጫን ለማሸነፍ በመንግስት በተያዘ አቅጣጫ ነው። ፊፋ የቻይና ኩባንያዎች በዓለም ዋንጫ በሰጡት ድጋፍ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በተለያዩ ውድድሮች መስተንግዶ የተለየ ትኩረት እንዲሰጣት ያደርጋል። በመጨረሻም በዓለም ዋንጫው ክልላዊ አጋርነት የስፖንሰርሺፕ ደረጃ በነፍስወከፍ በየዓመቱ ከ8 ሚሊዮን ፓውንድ ጀምሮ የሚከፍሉ ስፖንሰሮች ተገኝተዋል፡፡
ካለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ወዲህ የዓለም ዋንጫን ተዘጋጅቶ እስከሚካሄድባቸው 4 ዓመታት ከውድድሩ ጋር በተያያዘ ገቢው 5.72 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም ወጭው ደግሞ ከ5.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡ በቴሌቭዥን ስርጭት፤ በድረገፅ ማህበራዊ ሚዲያዎች፤ በኦንላይን የቀጥታ ስርጭት እና በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በድምሩ ከ3.6 ቢሊዮን በላይ ህዝብን ቀልብ በሚስበው የዓለም ዋንጫ ኩባንያዎች በስፖንሰርሺፕ እና በማስታወቂያ  ከ5.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ ይከፍላሉ፡፡  በዓለም ዋንጫ 4 ዓመታት በየዓመቱ በቲቪ ለሚቀርቡ ማስታወቂያዎች የሚውለው ወጭ  2.3 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ኮርፖሬሽኖች እና ግዙፍ ኩባንያዎች ከዓለም ዋንጫው ውጭ በሚያደርጉት የገበያ ዘመቻዎች ለቲቪ ማስታወቂያዎች ከ68.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለኦንላይን የገበያ ዘመቻዎች እስከ 56 ቢሊዮን ዶላር ወጭ እንደሚያደርጉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ለ21ኛው ዓለም ዋንጫ በሶስት የስፖንሰርሺፕ ደረጃዎች ፊፋ 34 አጋሮች፤ የዓለም ዋንጫ ስፖንሰሮችና ክልላዊ  አጋሮችን ቢጠብቅም ቢያንስ 25 ያህሉን ባለማግኘቱ አስደንጋጭ እንደሆነበት ነው። ከፊፋ ጋር በዓለም ዋንጫ አጋሮች እና ስፖንሰሮች የነበሩ አንዳንድ ግዙፍ ኩባንያዎች  ኮንትራታቸውን ማቋረጣቸውን ተከትሎ  የተከሰተ ነው፡፡ ከፊፋ ጋር ያላቸውን ኮንትራት ካላደሱት ነባር የዓለም ዋንጫ አጋሮች ሶኒ፤ ኢምሬትስ እና ካስትሮል ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከፊፋ ጋር ለመስራት የምንችለው ዓለም አቀፉ ተቋም ሙሉ ለሙሉ ከሙስና እና ከዘቀጠ አስተዳደር ነፃ በማለት ተቃውሟቸውን ይገልፃሉ፡፡ በስፖንሰርሺፕ ውላቸው በዓመት እስከ 65 ሚሊዮን ዶላር የሚከፍሉ ነበሩ፡፡
የአጋሮችና የስፖንሰሮች መቀነስ  በየዓመቱ ፊፋ እየገጠመው ያለውን ኪሳራም እያባባሰው ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር በሙስና ቅሌት ከታመሰው የአስተዳደር ቀውሱ ጋር በተገናኘ ብዙ ገቢዎች ቀርተውበታል፡፡ በ2016 እኤአ ላይ ከ369 ሚሊዮን ዶላር በላይ፤ በ2017 ደግሞ ከ489 ሚሊዮን ዶላር የከሰረው ከዚሁ የአስተዳደር ቀውስ ጋር በተገናኘ ሲሆን፤ ከ2008 እኤአ ጀምሮ በየዓመቱ እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር የነበረው ተቀማጭ  ወደ 605 ሚሊዮን ዶላር መውረዱም ይገለፃል፡፡ በሌላ በኩል ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር በሚፈልገው ደረጃ ማትረፍ ያልቻለው፤ ለአባል ፌደሬሽኖቹ ለስፖርቱ እድገት የሚሰጠው ድጋፍ መጨመሩ፤ በሙስና ችግሮች ለህግ አገልግሎት የሚያወጣ ክፍያዎች መኖራቸውም ይጠቀሳሉ፡፡ ከ2016 እኤአ ወዲህ ፊፋ ከህግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች በዓመት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ እያደረገ ሲሆን፤ ሌላው በ190 ሚሊዮን ዶላር ወጭ በዙሪክ ያስገነባው ሙዚዬም የተጠበቀውን ገቢ እያስገኘ አለመሆኑም ተወስቷል፡፡ ብራዚል ባስተናገደችው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ከቲቪ መብት 2.43 ቢሊዮን ዶላር፤ ከተለያዩ ንግዶች ዘመቻ 1.58 ቢሊዮን ዶላር፤ ከትኬት ሽያጭ 527 ሚሊዮን ዶላር፤ ከመስተንግዶ 184 ሚሊዮን ዶላር፤ ከባለመብትነት 107 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ 4.83 ቢሊዮን ዶላር ገቢን ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር አግኝቷል፡፡  በኢንተርኔት ድረገፆች እና የማህበረሰብ ሚዲያዎች ከፍተኛ ሽፋን በማግኘት በታሪክ የመጀመርያው የነበረው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ታላላቅ ኩባንያዎች ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርገዋል፡፡
ከ2015 እስከ 2018 እኤአ  በሚቆጠረው የ21ኛው የዓለም ዋንጫ 4 ዓመታት ፊፋ እስከ 5.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚሰበስብ የሚጠበቀው ፊፋ፤ ዋንኛ ገቢዎቹ ከቴሌቭዥ ስርጭት እና ከስፖንሰርሺፕ ናቸው፡፡ ፊፋ ከጠቅላላ ገቢው 30 በመቶውን ከዓለም ዋንጫ በተያያዘ ከስፖንሰርሺፕ፤ ከቲቪ የስርጭት መብት ያገኛል፡፡
ዓለም አቀፉ የገበያ ጥናት አድራጊ ተቋም ግሎባል ዌብ ኢንዴክስ GlobalWebIndex በሰራው ሪፖርት የዓለም ዋንጫን ከሚከታተሉ የዓለም የስፖርት አፍቃሪዎች 54 በመቶው ለውድድሩ ስፖንሰሮች እና አጋሮች ቀልባቸውን የሚያስገዙ ናቸው፡፡ ይህንም ያረጋገጠው ከ34ሺ በላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን በማሳተፍ በሰበሰበው ድምፅ ነው፡፡ ከዓለም ዋንጫ ታዳሚዎች 32 በመቶው ኮካ እንደሚጠጡ፤ 54 በመቶው የማክዶናልድ ምግቦችን እንደሚጠቀሙ ያመለከተው ዌብ ኢንዴክስ ዋንኛው ምክንያት በቲቪ የሚያስተላልፏቸው ማስታወቂያዎች እንደሆነ ጠቅሷል፡፡ በድረገፅ የንግድ ምልክታቸው 35 በመቶ የሚታይላቸው ኩባንያዎች በውድድሩ ስሞን 43 በመቶ የዓለም ዋንጫ ታዳሚዎችን በመማረቅ የንግድ ምልክታቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ በሌላ በኩል የዓለም ዋንጫን ከታደሙ 10 ስፖርት አፍቃሪዎች 4 ያህሉ የአዲዳስን ምርት በ1 እና ሁለት ዓመት ውስጥ መግዛታቸው አይቀርም የሚለው የወብኢንዴክስ ጥናት ከ10 የዓለም ዋንጫ ታዳሚዎች ቢያንስ አንዳቸው የቪዛ ካርድ የሚጠቀሙና ሃዩንዳይ መኪና ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ገምቷል፡፡
የማልያ ስፖንሰሮች
በዓለም ዋንጫው ለሚሰለፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ የስፖርት ትጥቅ በማቅረብ ስምንት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እንደሚሰሩ ታውቋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ በሚያቀርቧቸው ማልያዎች፤ የታኬታዎች፤ ኳስ፤ እና ሌሎች የስፖርት ትጥቆች በሚያገኙት ዓለም አቀፍ የገበያ ትኩረት ከ12.6 እስከ 14.5 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ይጠብቃሉ። የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ደግሞ ሁለቱ ግዙፍ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች አዲዳስ ከጀርመን እንዲሁም ናይኪ ከአሜሪካ ናቸው፡፡ በዓለም ዋንጫው አዲዳስ የ12 ብሄራዊ ቡድኖችን ናይኪ ደግሞ የ11 ብሄራዊ ቡድኖችን ሙሉ የስፖርት ትጥቅ ያቀርባሉ፡፡ ሌሎቹ ፑማ፤ አምብሮ፤ ኒው ባላንስ፤ ኤርያ፤ ሃመል እና ኡሁል ስፖርት የተባሉት ናቸው፡፡
ፑማ ለ4 ብሄራዊ ቡድኖች እንዲሁም ኒውባላንስ ለሁለት ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ የስፖርት ትጥቅ የሚያቀርቡ ሲሆን አምብሮ፤ ሃመል፤ ኢርያ እንዲሁም  ኡሁል ስፖርት በነፍስ ወከፍ አንዳንድ ብሄራዊ ቡድኖች ሙሉ የስፖርት ትጥቅ ለማቅረብ ተዋውለዋል፡፡
ማህበራዊ ሚዲያዎች
ዓለም ዋንጫው በታዋቂዎቹ የኢንተርኔት ማህበረሰብ ድረገፆች ፌስቡክ፤ ትዊተር፤ ዩቲውብ፤ ኢንስታግራም እና ሌሎችም ላይ በሚኖረው ሽፋን ዲጂታል ዓለም ዋንጫ መሆኑ አይቀርም  እየተባለ ነው። በዓለም ዋንጫው ሰሞን 8.8 ቢሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በሚያደርጉት የመረጃ ክትትል የሚፈጠረው መጨናነቅ በሪከርድ ሊመዘገብም ይችላል፡፡ ከዓለም ህዝብ 90 በመቶው ዓለም ዋንጫውን በማህበረሰብ ድረገፆች የሚከታተል ሲሆን በ203 አገራት የስርጭት  ሽፋን ያላቸው ማህበራዊ ሚዲያዎቹ በዓለም ዋንጫው ደንበኞቻቸውን ለማብዛት የተለያዩ የመረጃ አገልግሎት የሚሰጡ ፕሮግራሞችን በማዋቀር እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ከአራት ዓመታት በፊት ትልልቅ ኩባንያዎች ልዩ ልዩ ዲጅታል ማስታወቂያዎች በማህበራዊ ሚዲያው ከ6.9 ሚሊዮን በላይ ግዜ ተጋርተዋል፡፡ ክርስትያኖ ሮናልዶ ለናይኪ የሰራው የዩቲውብ ቪድዮ በቀናት 70 ሚሊዮን ታይቷል፡፡ ፌስቡክ ከ1.28 ቢሊዮን ተጠቃሚዎቹ ከ500 ሚሊዮን በላይ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች እንደሆኑ ሲገልፅ የትዊተር ኩባያ ደግሞ በዓለም ዋንጫው ሰሞን ከውድደሩ ጋር በተያያዘ ከ350ሺ በላይ የትዊተር መልዕክቶች በቀን መሰራጨታቸውን ይጠብቃል፡፡
የማህበረሰብ ድረገፆቹ እና ሚዲያዎቹ ለዓለም ዋንጫው የሚፈጥሩትን ድምቀት በኛው የዓለም ዋንጫ በስፋት የሚያነጋግርም ይሆናል፡፡ የማህበረሰብ ድረገፆችን ከሚጠቀሙ 1.2 ቢሊዮን የዓለም ህዝቦች 40 በመቶው ያህሉ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡

Read 3828 times