Sunday, 13 May 2018 00:00

“ለኢትዮጵያ ቀይ ባህር የደህንነት ቀጠና ነው”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

• የብሔር ፖለቲካ ባለበት፣ ሊበራል አስተሳሰብ በድንገት ቢመጣ ጥሩ አይሆንም
  • ከኤርትራ ጋር መደራደር ስለተፈለገ ብቻ መደራደር ይቻላል ወይ?
  • የጠ/ሚኒስትሩ የጎረቤት አገራት ጉብኝት አንደምታው ብዙ ነው

    ታዋቂው የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ፕ/ር መድህኔ ታደሰ በዶ/ር አብይ ሰሞንኛ እንቅስቃሴዎች ፣ በኤርትራ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት፣ በቀይ ባህር ጉዳይ... ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡
      ፕ/ር መድህኔ ታደሰ (የፖለቲካ ተንታኝ)


    የጠ/ሚኒስትሩን የሥራ እንቅስቃሴ እንዴት አገኙት? በተለይ በክልሎች እየተዘዋወሩ፣ ከህዝብ ጋር የሚያደርጓቸው ንግግሮችና ውይይቶች? ----
የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ከፖለቲካዊ ማዕቀፍ አንፃር ነው መታየት ያለበት። የእሳቸው ቅቡልነት ከኢህአዴግ ውጪ ባሉትም ያመዘነበት፣ የህዝብን ስሜት የያዙበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በየአካባቢውና በየክልሉ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸው፣ ቅቡልነታቸውንና ተፈላጊነታቸውን የሚያሳድጉበት አንድ መንገድ ነው። በሌላ በኩል ከነበረው የጨለምተኝነትና የስጋት ስሜት፣ ህዝቡንና ሀገሪቱን ተስፋ ወደሚፈነጥቅበት ምዕራፍ ለማሸጋገር የተጠቀሙበት አካሄድ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ መንግስት ከአሁን በኋላ ህዝቡን እያዳመጠ፣ የተለያዩ ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ወዘተ-- ማድረግ አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ከህዝቡ ጋር እንዲህ ባለው መንገድ ቀጥታ ተገኝቶ መወያየት ጠቃሚ ነው፡፡ ከህዝቡ የሚያገኙት ግብአት፣ ፖሊሲያቸውን ለመቀመር ያስችላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድርጅታቸው የተሟላ ድጋፍ ባያገኙም በመጪው ነሐሴ ጉባኤ ማካሄዱ አይቀርም። እስከዚያው ድረስ ከህዝቡ ጋር ተነጋግረው፣ የድርጅታቸውን የወደፊት አቅጣጫና ትክክለኛ ማንነት በሚያስረግጥ መልኩ ስራዎች ለመስራት ከተፈለገ፣ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች ማድረግ ተገቢ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ነገር እያደረጉ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከዚህ በላይ  ማድረግ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡
ጠ/ሚኒስትሩና የሚመሩት ድርጅታቸው ኢህአዴግ ምንና ምን ናቸው ?
ግንባሩ በድርጅት የማንነት ቀውስ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የእሳቸው ወደ ስልጣን አመጣጥ አንደኛው ምክንያት፣ የፖለቲካ ውጤት ብቻ ሳይሆን አንድ የተቀየረ ነገር እንዳለ አመላካች ነው፡፡ ኢህአዴግ ድሮ የሚመራበትና ራሱን አጥሮ የሚያስርበት ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ የተዳከመበት ደረጃ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ እሳቸው የተለየ፣ ወደ ሊበራል የሚያደላ፣ ለዘብ ያለ የፖለቲካ መስመር የመያዝ አዝማሚያ ነው የሚታይባቸው፡፡ ሊበራል አመለካከት ሲባል እንግዲህ ኒዮሊበራል ነው ወይስ--? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በሂደት መውጣቱ አይቀርም፡፡ በፓርቲው ውስጥ የሚደረገውን ውስጠ ትግል፣ከህዝብ ተፈላጊነትና ቅቡልነት አንፃር ለማካሄድ የፈለጉ ይመስለኛል፡፡  አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው፤ፖለቲካዊ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንቅስቃሴያቸው በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን የኃይል ሚዛን ጭምር ታሳቢ ያደረገ ነው የሚመስለው፡፡ የመጡበት መንገድ ሲታይ፣ የሚሄዱበትም መንገድ፣ የፖለቲካ ውድድርና ፉክክር የሚታይበት ስለሆነ፣ ለዚያ ውድድርና ፉክክር፣ የተወሰነ እምቅ አቅም ለማግኘት ያሰቡ ይመስላል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ፤ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች መፍታት ከፈለጉ፣ በቅድሚያ ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ድርድር ማድረግ አለባቸው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ  ምን ይላሉ?
ምን ይዘው ነው በቅድሚያ ከፓርቲዎች ጋር ይደራደሩ የሚባለው? ለመደራደር ፍኖተ ቀመር ያስፈልጋቸዋል፡፡ እኚህ ሰው ወደ ስልጣኑ የመጡት በፓርቲው የውስጥ ዲሲፕሊንና አሰራር ተደግፈው አይደለም፡፡ በአለመስማማት መሃል ነው የመጡት። የተለያዩ የኃይል እና የስልጣን ማዕከላት፣ የተለያዩ የተቃዋሚ ኃይሎች---ባሉበት ሀገር፣ በመጀመሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተነጋግረው፣ የህዝቡን ፍላጎት እንዲታይ አድርገው፣ ፓርቲያቸውን ማስተካከልና መለወጥ አለባቸው፡፡ ይሄን መልክ ሳያስይዙ፣ በምን መልክ? በምን ሰነድ? በምን ፍኖተ ካርታ? ነው ሊደራደሩ የሚችሉት? በሌላ በኩል ጠ/ሚኒስትሩ ይዘውት የመጡት አስተሳሰብ አለ። ሙሉ ለሙሉ ከኢህአዴግ ባይለይ እንኳ በተወሰነ አቅጣጫው ሊለይ ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ባለው የሃሳብ የበላይነት ተፈትሾ ነው ተግባር ላይ የሚውለው። እሳቸው አዲስ አቅጣጫቸውን መሬት ባላወረዱበት ሁኔታ እንዴት አድርገው ነው ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደራደሩት? ተቃዋሚዎችስ ምን ያህል ለድርድር ተዘጋጅተዋል? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ይሄ አሁን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ ሃሳባቸውን ለህዝቡም ለፓርቲያቸውም ይፋ እያደረጉ፣በሀሳባቸው ዙሪያ ኃይል የሚያሰባስቡበት ነው የሚሆነው፡፡  
ለወደፊት ስትራቴጂ ቀርፆ ለመደራደርና የፖሊሲ ለውጥ ለማምጣት ይሄ አካሄዳቸው ጠቃሚ ነው። ወደ ሊበራል አቅጣጫ ለመሄድም ብዙ ጥናት የሚጠይቅ ነገር አለ፡፡ ዝም ብለው ቸኩለው ከገቡበት ለራሳቸውም ለፓርቲያቸውም ለሃገርም አይበጅም። የብሔር ፖለቲካ ባለበት ሃገር፤ ሊበራል አስተሳሰብ በድንገት ቢመጣ ጥሩ አይሆንም፡፡ በሂደት ነው ነገሮች መታየት ያለባቸው፡፡ ለምሳሌ አንዳንዱ፣ ለምን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አልተነሳም ይላል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለፖለቲካ ውድድር በሚያመች መልኩ መቀመር አለበት፤ በተለይ የፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ፡፡ እሳቸው የሚያመቻቸውን የአካባቢያዊና አጠቃላይ ሀገራዊ የደህንነት ሁኔታ መፍጠር አለባቸው፡፡ ይሄ ደሞ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ የሚለው ጥያቄ፤ አሁን ያለውን ሽኩቻና ችግር በጥልቀት ካለመረዳት የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡
በጎረቤት አገራት ያደረጓቸው ጉብኝቶች---እንዴት ይገመገማሉ?
እነዚህ ጉብኝቶች በሶስት አቅጣጫ ነው መተንተን ያለባቸው፡፡ አንዱ የተለመደው የጉርብትና እና የዝምድና አቅጣጫ ነው፡፡ ይሄ ኢኮኖሚውንም፣ ፀጥታውም ይነካል፡፡ አላማውም እነዚህን ነገሮች ማጠናከር ነው፡፡ ሁለተኛው አካባቢያዊ አንድምታው ነው፡፡ አካባቢያዊ አንድምታው ሲባል የኤርትራ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያና የቀይ ባህር አካባቢ ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ሶስተኛው የውስጥ የፖለቲካ አንደምታ ነው። ወደ ሱዳን ሲኬድ፣ ወደ ኬንያ ሲኬድ፣ ወደ ጅቡቲ ሲኬድ ብዙ የሚያገናኙን ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ወደ ጅቡቲ ሲኬድ፣ የአፋርና የኢሳ ጉዳይ አለ፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ ያለውን አንዳንድ ያልተገባ ሁኔታ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ ይሄ ከጅቡቲ ሱማሌዎች ጋር በምን ይገናኛል? የአፋር ጉዳይም አለ፡፡ ስለዚህ በሦስተኛ ደረጃ መታየት ያለበት፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ፣ በውስጥ በራሳቸው ስልጣን የማጠናከር ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ካላደረጉ የአካባቢ ህልው አደጋ ላይ ይወድቃል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ መለስ ከመሞታቸው በፊት በፃፉት ደብዳቤ፤ “ከኦብነግ ኃይል ጋር አስታርቁን” ብለው ኬንያን ጠይቀው ነበር፡፡ እዚያ ኬንያ ውስጥ በኦጋዴን ጉዳይ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎች አሉ። እሱ ላይም ለመነጋገር ጉብኝታቸው አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ነገሮች ስላሉት ለየት ሊል ይችላል። በኤርትራ በኩል ደግሞ የመታረቁ ነገር ከአሜሪካኖቹ ግፊት የመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ ከኤርትራ ጋር ለመታረቅ ኢትዮጵያ ብቻዋን ዘው ብላ መግባት አለባት? ወይስ ከወዳጆቿ ጅቡቲና ሱዳን ጋር ማቀናበር አለባት? ይሄ አንዱ ወሳኝ ሁኔታ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ የግድቡ ጉዳይ አለ፡፡ ይሄም ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ ሱዳንና ኢትዮጵያ፤ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ስምምነት አላቸው፡፡ ይሄን ጉዳይ ተነጋግረው፣ የሃገሪቱን ሉአላዊነት ከማስከበር አንፃር መልክ ማስያዝ አለባቸው፡፡ ሌላው የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ነው፡፡ ከሱዳንና ከኬንያ ጋር አንድ አቋም መያዝ ሊያስፈልጋቸው ይችላል፤ለዚህም መነጋገር አለባቸው። ጉብኝታቸው አካባቢያዊ፣ ሁለትዮሻዊ እና የውስጥ ፖለቲካ አንድምታ አለው፡፡
ሃገሮች የተጠናከረ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ካላቸው፣ በፀጥታና በፖለቲካ ጉዳይ ለከባድ ችግር አይጋለጡም። ከዚህ አንፃር በተለየ ሁኔታ በኢኮኖሚ መተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ወደብ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የውሃ አቅርቦት፣ የባቡር መስመር ዝርጋታ የመሳሰሉ ይገኙበታል፡፡  እነዚህ በሀገራቱ መካከል የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር አጋዥ ናቸው፡፡ የጋራ ጥቅም ካለ ፖለቲካው አይጎዳም። እርስ በእርስ መጠባበቁ ይኖራል፡፡
በውጭ የሚያደርጉት ጉዞ ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ በውስጥ ያለውን ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት የሚደረገው ጥረት አካል ሆኖ ነው መታየት ያለበት። ለመጀመሪያ ጊዜ በህዝብ ጫና ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ የኦሮሞ ተወላጅ፣ በኬንያ ኦሮሞዎች ላይ ተፅዕኖ የለውም ማለት ይከብዳል፡፡  ከዚህ አንፃር ከኦነግ ጋር ወደ ሰላም ድርድር ሊገባ ይችል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የውጭ ሃገሩ ጉብኝታቸው አንድምታው ብዙ ነው፡፡
በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል ሰላም መፍጠር ይቻላል ብለው ያስባሉ?
ፍላጎቱ በኢትዮጵያውያንም፣ በኤርትራውያንም፣ በውጭ መንግስታትም አለ፤ በአካባቢው መንግስታትም እንዲሁ፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ሁለቱ ሀገራት የሚደራደሩበትን መነሻ ሐሳብ ማዘገጀትና ማጠናቀር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት አቋም ልክ ጦርነቱ እንደተጀመረበት ወቅት ነው ያለው። የሁለቱ ሃገራት ሁኔታ ያኔ በጦርነቱ ጊዜ እንደነበረው ነው፡፡  
የፀቡ መነሻ የሆነ መሬት ለኤርትራ ተወሰነ፤ የኤርትራ መንግስት ደግሞ ያንን መሬት ለድርድር እንደ ቅድመ ሁኔታ፣ይዞት ቀጠለ፡፡ የኤርትራ መንግስት አንገብጋቢ የሆነበት የባድመ መሬት ቢሰጠው እንኳ በበጎ አይን ይደራደራል ተብሎ አይጠበቅም። ምክንያቱም መነሻው ባድመ አይደለም፡፡ ሁለተኛ የሰላም ዋስትና ባድመ አይደለም፡፡ የኤርትራ መንግስት ባህሪ፤ ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት ያለው መሆኑን በምን ልናረጋግጥ እንችላለን? ይሄን ማረጋገጫ ማንም ሊሰጥ አይችልም፡፡ ኤርትራን ወደ ሰላም እናምጣ የሚሉ የአሜሪካ ፖለቲከኞችም ይሄን ሊያረጋግጡ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ከኤርትራ ጋር ድርድር ማድረጉ ለምን ውጤት ነው?
የኤርትራ ፖለቲካል - ኢኮኖሚ መርህ እስካልተቀየረ ድረስ የሰላም ሂደቱ በቀላሉ የሚከናወንና የሚፈፀም አይደለም፡፡ ከኤርትራ ጋር መደራደር ስለተፈለገ ብቻ መደራደር ይቻላል ወይ? ይሄም ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ ሌላው በአካባቢው የቻይና መምጣት፣ ከየመን ሁኔታ ጋር፣ ከአሜሪካ የቀይ ባህር የጦር ኃይል ጋር፣ ቀይ ባህር ደግሞ ለኤርትራም ሆነ ለኛ ስትራቴጂካዊ ቦታ ነው ከሚል መነሻ ነው ውጤት መምጣት ያለበት። የሚፈለገው ምንድን ነው? የሁለቱ ሀገራት ሰላም መሆን ነው? ወይስ ቀይ ባህር ላይ ያላቸውን ጥቅም ከማስከበር አኳያ ነው? የሚለው ግልፅ አልወጣም። ይሄ ግልፅ ባልወጣበት ሁኔታ፣ የመሬት ልውውጥ ጉዳይ ብቻ ከሆነ ዋጋ የለውም። የሰላም ሂደቱ መጀመር ያለበት ቀጠናውን ባገናዘበ መልኩ ነው፡፡ ባድመ የሰላማዊ ግንኙነቱ መነሻ ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁን ግን ባድመን ለብቻዋ ነጥሎ የመውሰድ ሁኔታ ነው፣ በኤርትራ በኩል ያለው፡፡ ያ ከሆነ ምንም ውጤት የለውም፡፡
ዶ/ር አብይ፤ የቀንዱ አካባቢ ጎረቤት ሃገራትን መጎብኘታቸው፣ የኢትዮጵያን ተፅዕኖና ሚና በማስጠበቅ ረገድ  ከዶ/ር አብይ በቀጠናው ጉዳይ ምን ይጠበቃል?
ቀጠናው ላይ የኢትዮጵያ ሚናን ለማጠናከር ወሳኙ የውስጥ ሰላምን ማጠናከር ነው፡፡ በመጀመሪያ እሳቸው የሀገሪቱን የውስጥ ሰላም ማጠናከር አለባቸው፡፡ የውስጡን ሁኔታ እንዳይጎዳም የጎረቤት ሃገራትን ግንኙነት ማጠናከሩም ጠቃሚ ነው፡፡ አሁን እንደሚያደርጉት ማለት ነው፡፡ በወሳኝ መልኩ ኢትዮጵያ በአካባቢው የሰላም እና የማረጋጋት ሚናዋን ልታጠናክር የምትችለው ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ እና በንግግር ላይ የተመሰረተ ሲቪላዊ የፖለቲካ ሂደት ሲፈጠር ነው፡፡ የውስጧ ሰላም የተረጋገጠ ሃገር፤ የአካባቢው የኃይል ሚዛን ወደሷ ያደላል፡፡ አሁን የህዝብ ቁጥር የበላይነት አላት፤ ወታደራዊ የበላይነት አላት፣ ጥንታዊ የመንግስት አወቃቀርና ስርአት ያላት ሃገር ነች፣ ኢኮኖሚዋ እያደገ የመጣ ሃገር ነች፤ መሃል ላይ ነው ያለችው፡፡ ከዚህ አንፃር መሬት ላይ ያላት ኃይል ጠቃሚ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄን ኃይሏን ተጠቅማ በቀይ ባህር አካባቢ ያላትን ሚናዋን እንዳትወጣ፣ አስሮ የያዛት የውስጥ የፖለቲካ ቀውስ ነው፡፡
 ዶ/ር አብይ፤ ይሄን የውስጥ ቀውስ በመፍታት፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማምጣት፣ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች በማጠናከር --- የሃገር ውስጥ የፖለቲካ ሂደቱን ማስተካከል ለኢትዮጵያ አካባቢያዊ የበላይነት ወሳኝ መሆኑን የተረዱ ይመስላል፡፡ ከዚህ አንፃር እዚህ ላይ ማተኮራቸው አይቀርም፡፡ እስከዚው ድረስ የውጪ ኃይሎች የሚያበላሹት ነገር ይኖራል፡፡ ለምሳሌ የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና የእነ ኳታር በሶማሊያ ጉዳይ የሚያደርጉት ነገር አለ፡፡ ይሄን ከኬንያ፣ ከኢጋድ ጋርም ተነጋግሮ ወደ አፍሪካ ህብረት በአጀንዳነት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ የቀይ ባህር ጉይ ለቀንዱ ሃገራት በሙሉ የደህንነት ጉዳይ ነው፡፡ የወደብ እና የኮንቴነር ጉዳይ አይደለም ቀይ ባህር የደህንነት ቀጠና ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ቀይ ባህር የደህንነት ቀጣና ነው። ይሄ የደህንነት ጉዳይ ኢጋድን የአፍሪካ ህብረትን ይመለከታል፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ሃገሮች ጋር መነጋገር ይሄን አጀንዳ ወደ ላይ ከፍ የማድረግ ሙከራዎች ዶ/ር አብይ እያደረጉ ያለ ነው የሚመስለኝ በጉብኝታቸው። ማድረግ ያለባቸውም ይሄንኑ ነው፡፡ ዋናው ግን የኢትዮጵያን የውስጥ የፖለቲካ ሃዲድ ማስተካል ለኢትዮጵያ ቀጠናዊ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱም የሚመጣው ከዚህ በመነጨ ነው፡፡  

Read 5750 times