Sunday, 13 May 2018 00:00

የረዳት ኢንስፔክተሯ የእስር ዘመን እውነታዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)


• “ለነጻነት መስዋዕትነት ቢከፈልም ጭቆናው ግን አልቀረም “
• “ደርግ ከወደቀ በኋላ የሰው ልጅ ስቃይ ያበቃ መስሎኝ ነበር”
• “ጠ/ሚኒስትሩ ማረሚያ ቤቶችን መጎብኘት አለባቸው”
• “በፖሊስነቴ ማሰር እንጂ መታሰርን አላውቅም ነበር”

     በትግራይ ክልል ዛላምበሣ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ረዳት ኢንስፔክተር አለም ተክላይ፤ በ1983 ዓ.ም በ15 ዓመት ዕድሜዋ ከእህቷ ጋር ህውሓትን ተቀላቅላ መታገሏን ትናገራለች፡፡ የደርግ ውድቀትን ተከትሎ ከኢህአዴግ ሠራዊት ከተቀነሱት ታጋዮች አንዷ መሆኗን ትገልጻለች፡፡ እህቷ ግን በትግል ላይ እንደተሰዋች ጠቁማለች፡፡ በ1986 የትግራይ ክልል ፖሊስ ባልደረባ የሆነችው አለም፤ የዛሬ አራት ዓመት በሽብር ተጠርጥራ እስክትያዝ ድረስ ማገልገሏን ትገልፃለች፡፡
“በሽብር ተከሶ መታሰር ስቃይ ያለው አይመስለኝም ነበር” የምትለው ረዳት ኢንስፔክተሯ፤ በሽብር ተጠርጥራ ማዕከላዊ እስር ቤት በቆየችባቸው ጊዜያት ከማታውቃቸው አስደንጋጭ እውነቶች ጋር ተዋውቃለች፡፡ ምን ይሆኑ? በመጨረሻም በአሸባሪነት ተፈርዶባት ለ7 ዓመት እስር ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የገባችው አለም፤ ለ4 ዓመት ያህል ከታሰረች በኋላ ከሰሞኑ በይቅርታ መፈታቷን ተናግራለች፡፡
ረዳት ኢንስፔክተሯ አለም ተክላይ፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፣ የእስር ዘመን እውነታዎቿን አውግተዋለች፡፡ የታሰረችበትን አጋጣሚ በመተረክ ትጀምራለች- ረዳት ኢንስፔክተሯ፡፡

   ለአንድ አመት የሚቆይ የከፍተኛ መኮንኖች ስልጠና ገብቼ በነበረበት ወቅት ነው ድንገት የታሰርኩት፡፡ ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም መቀሌ- ኪሃ ከሚገኘው ማሠልጠኛ ተቋም፣ የእለቱን ስልጠናዬን ጨርሼ 10 ሰዓት አካባቢ ስወጣ፣ “ሰው ይፈልግሻል” ተባልኩ፡፡ ይፈልግሻል የተባልኩት ሰው፣ በቅርብ የማውቃቸው ነበሩ፡፡ ለምን ይሆን የፈለጉኝ ብዬ፣ ወደተባልኩት ሰው ቢሮ ሄድኩኝ፡፡ ቢሮአቸው እንደገባሁ፣ “ኤርትራ ውስጥ ከማን ጋር ነው ግንኙነት ያለሽ?” በሚል ጥያቄ አጣደፉኝ፡፡ “እህቴ ኤርትራ አለች” አልኳቸው፡፡ “እህትሽ እዚያ እንዳለች እናውቃለን፤ እሱን ተይውና ከሌላ ሰው ጋር ግንኙነት አለሽ?” ጠየቁኝ፡፡ “ሌላ ከማንም ጋር ግንኙነት የለኝም” አልኳቸው፡፡ ወዲያው ሞባይሌን ተቀበሉኝ፡፡ ከዚያም የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽነር (አለቃችን) ጋር ወሠዱኝ። እሡም ተመሣሣይ ጥያቄ ነበር ያቀረበልኝ፡፡ የኔም መልስ፤ “የማውቀው ነገር የለኝም” የሚል ነበር፡፡ እየመሸ ሲሄድ፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሠዱኝ፡፡ የለበስኩት ቀለል ያለ ልብስ ነበር፤ ብርድ አለ፡፡ እኔ ማሠር እንጂ መታሠርን አላውቅም ነበር፡፡ ተጠርጣሪ በማስርበት ጊዜ እንኳ “ከቤተሰብ ልብስ አስመጡ” እላቸው ነበር እንጂ ከልክዬ አላውቅም፡፡ እነሡ ግን ያለሁበትን ሁኔታ ለቤተሰቤ እንኳ እንዳሣውቅ እድል አልሠጡኝም፡፡ እስር ቤቱን ከዚያ በፊት አላውቀውም። እስር ቤት መሆኑም አያስታውቅም፡፡ እኔ የሻይ ክበብ እንደነበር ነው የማውቀው፡፡ በርከት ያሉ ኤርትራውያን ታስረውበት ነበረ፡፡


     ከዚያስ ፍርድ ቤት ቀረብሽ?
በበነጋው ጠዋት እዚያው አካባቢ ያለ ፍ/ቤት አቀረቡኝ፡፡ የ14 ቀናት ቀጠሮም ጠየቁብኝ፡፡ “የተጠረጠረችበት ወንጀል ምንድነው?” ሲባሉ፤ “እኛ አይደለንም የምንፈልጋት፤ ፌደራል መንግስት ነው” የሚል ምላሽ ነበር የሠጡት፡፡ በዚያን ሰዓት ቤተሰቤም ጓደኞቼም የት እንዳለሁ አያውቁም ነበር፡፡ በታሠርኩ በ3ኛው ቀን ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመርን፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቤተሰቤ አያውቅም፡፡ አዲስ አበባ ስንደርስ፣ ማዕከላዊ አስገቡን፡፡ እኔ ማዕከላዊን በስም እንጂ አላውቀውም ነበር፡፡ ማዕከላዊ መሆኑንም የነገሩኝ እዚያው ታስረው የነበሩ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ገና ማዕከላዊ ስደርስ፣ አንድ መርማሪ የተቀበለኝ በስድብ ነበር - “አንቺ ውሻ” በማለት፡፡ እኔም ህግ ያለ መስሎኝ “ውሻማ አትበለኝ፤ እኔን የመስደብ መብት የለህም” አልኩት፡፡ መልሶ በትግርኛ “ውሻ ነሽ” አለኝ፡፡ በጣም ነበር የሚሳደበው፡፡ ማዕከላዊ ሁለት ቀን ከቆየሁ በኋላ ምርመራ ጀመሩ፡፡ በምርመራ ወቅት ከፍተኛ ድብደባ ይፈፅሙብኝ ነበር፡፡ “ለማን የኤርትራ ደህንነት ነው መረጃ የሠጠሽው?” እያሉ ነበር የሚደበድቡኝ፡፡ እኔም “የማውቀው የኤርትራ ደህንነት የለም፤ እናንተ የምታውቁ ከሆነ ስሙን ንገሩኝ” እላቸው ነበር፡፡ በቃ በየቀኑ  ምርመራ ተብሎ የሚቀርብልኝ ጥያቄ፤ “ለማን ነው መረጃ የሠጠሽው?” የሚል ነበር፡፡ በእውነት ይሄ ያሣዝናል፡፡ አንድን ንፁህ ሠው ካሠሩ በኋላ፤ “ለማን ነው መረጃ ትሠጭ የነበረው?” እያሉ መደብደብ ግፍ ነው፡፡
ለምርመራ በተጣራሁ ቁጥር ስለሚደበድቡኝ ከውስጥ ቱታና ታይት እየደራረብኩ ነበር የምለብሠው። ሁለት ካልሲ ነበር አድርጌ የምሄደው፡፡ አራት ወር ሙሉ ተመሳሳይ ጥያቄ እየጠየቁኝ ነበር የሚደበድቡኝ። ምንም ሲያጡ፣ ለ20 ቀናት ያህል ብቻዬን አንድ ክፍል ውስጥ ዘጉብኝ፡፡ ለሽንት የምወጣው እንኳ ሌሊት 11 ሰዓት፣ ሰው በሌለበት ወቅት ነበር፡፡ ይሄን የሚያደርጉት፤ ሆን ብለው እኔን ጭንቀት ውስጥ ለመክተት ነበር፡፡ ቤተሠቤ ደግሞ የት እንዳለሁም አያውቅም፡፡ በምርመራ ወቅት  ከ5 ሠዓታት በላይ እጄን ወደ ላይ አድርጌ፣ ቁጭ ብድግ ያሰሩኝ ነበር፡፡ በሴትነቴ የሚሰነዝሩብኝ ስድብና አስነዋሪ ቃላት ደግሞ ለመግለፅም ይከብዳል፡፡
በማዕከላዊ ተፈፀመብኝ ያልሽውን የስቃይ ምርመራ አልጠበቅሽውም ነበር?
በጭራሽ! እኔ እንዲህ አይመስለኝም ነበር። እንደውም ሠዎች ታስረው ሲፈቱ “ተደብድበን፣ ተሠድበን” ሲሉ፤ “ውሸታሞች” እላቸው ነበር፡፡ እኔ ከምርመራ ጋር የተያያዘ ስራ እሠራ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ባለሁበት አካባቢ እንዲህ ያለ ነገር ስለማይደረግ፣ እንግዳ ነው የሆነብኝ፡፡ እንዲያውም “ውሻ” ብለው ሲሠድቡኝ፣ “ለምን ትሰድቡኛላችሁ” ብዬ እጮህ ነበር፡፡ በኋላ ግን ከስድብም የባሰ ድብደባ ገጠመኝ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ስለ መብት መናገር ቅንጦት ነው፡፡ አሁንም ማዕከላዊ ይፈፀም የነበረውን ግፍ  የሚያምነው፣ እንደኔ የደረሰበት ሰው ብቻ ነው፡፡ ጉዳት ያልደረሠበትን ሰው ቢነግሩት የግፉን መጠን ይረዳዋል ብዬ አላምንም፡፡ እስካሁን የተደበደብኩበት፣ በቅዝቃዜ ውስጥ ለረጅም ሰዓታት የቆምኩበት እግሬ በጣም ያመኛል፡፡ በጤንነት ገብቼ፣ በሽተኛ ሆኜ ነው የወጣሁት፡፡ ጆሮዬን ተመትቼ ለረጅም ጊዜ ያመኝ ነበር፡፡ አይኔን  እስካሁንም ድረስ ያመኛል፡፡ ብቻ ብዙ ነገር ነው የደረሠብኝ፡፡ “ልብስ አውልቁ” እንባል ነበር። ይሄ የኢትዮጵያውያን ባህል አይደለም፡፡ የማዕከላዊ መርማሪዎች ግን እንደ ባህል ነበር የሚቆጥሩት፡፡
በቅርቡ ማዕከላዊ ተዘጋ ሲባል ምን ተሰማሽ?
እኔ ደርግ ሰው ያስር እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ደርግ ኢ-ሠብአዊ ድርጊት በእስረኞች ላይ እንደሚፈፅም እየተነገረኝ ነው ያደግሁት፡፡ በራሴ ላይ በማዕከላዊ ደርሶ ያየሁት ግን ከዚያ የሚተካከል እንጂ የሚተናነስ አይደለም፡፡ ደርግ የጀመረውን የጨረሱት ኢህአዴጎች ናቸው፡፡ በኔ ላይ ብዙ ስቃይ ያደረሰው የማላውቀው ደርግ ሣይሆን የማውቀው ኢህአዴግ ነው፡፡ ማዕከላዊን ለመዝጋት በምክንያትነት የተጠቀሰው የስቃይ ምርመራ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መዘጋቱ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን መስተካከል ያለበት የሰዎቹ አመለካከት ነው፡፡
 እንዴት ነበር ህውሓትን የተቀላቀልሽው?
የ5ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ በ1983 ምን እንደተፈጠረ አላውቅም፣ ታጋዮች ወጣቶችን በስፋት ይመለምሉ ነበር፡፡ እኛ ቤት ደግሞ የተወሰኑ ታጋዮች ይመጡ ነበር፡፡ ምግብ እኛ ነበር  የምናቀርብላቸው። በኋላ “ወደ ትግል ውጡ” የሚል ግዴታ መጣ፡፡ ወጣቶችን እየሰበሰቡ፤ “ወስኑና ወደ ትግል ግቡ” ይሉን ነበር፡፡ እኔም ሆንኩ ታላላቆቼ ወደ ትግሉ ለመውጣት ፍላጎት ስላልነበረን፣ መወሰን አልቻልንም ነበር፡፡ ከዚያም፤ “እናንተ የማትወስኑ ከሆነ…” አሉና አባታችንን ለ1 ወር አሰሩት፡፡ በተለይ “አንቺ ካልገባሽ”… ብለውኝ ነበር፡፡ አባቴ ከእስር እንዲፈታ ብዬ ተቀላቀልኳቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤተሠብ መለየቴ ስለነበር፣ አለቅስ ነበር፤ በኋላ ግን እየለመድኩ ስመጣ፣ እኔም በቆራጥነት በትግሉ መሳተፍ ቀጠልኩ፡፡
ወደ ትግሉ ስገባ እናቴን እንኳ በአግባቡ አልተሠናበትኳትም፡፡ እኔና እህቴ ለትግል ወጣን፡፡ እህቴ በትግሉ ተሰዋች፡፡ እኔ ግን እስከ ግንቦት 1983 በትግል ቆየሁ፡፡ በኋላ ብሄር ብሄረሠቦችን በሠራዊቱ ውስጥ ለማመጣጠን በሚል ተቀንሰን፣ ወደ ትምህርት ቤት እንድንገባ ተደረግን፡፡ በወቅቱ የቀረበው አማራጭ፤ ሁመራ-ዳንሻ ሄዶ፣ ቤት ተሠጥቶት መኖር፤ ይሄ አይሆንም ያለ ደግሞ ወደ ትውልድ ቀዬው እንዲሄድ ትራንስፖርት ተመቻችቶ ነበር፡፡ እኔ ቤተሰቤ ጋ መሄድን መረጥኩ፡፡ እዚያው ትምህርቴን ካቋረጥኩበት ቀጥዬ፣ 6ኛ እና 7ኛ ክፍልን ተማርኩ፡፡ በ1986 ዓ.ም የፖሊስ ምልመላ ቅጥር ሲመጣ፣ ራሣቸው መልምለው አስገቡኝ፡፡ የፖሊስነት ስራ ጀመርኩ፡፡ አዲግራት ተመደብኩ፡፡ እስከ መጨረሻውም አዲግራት ነበር የቆየሁት፡፡ የታሠርኩትም የአዲግራት ምድብተኛ ፖሊስ ሣለሁ ነው፡፡ በቡድን መሪነት ደረጃም እሰራ ነበር፡፡
ለተመሰረተብሽ ክስ ያቀረቧቸው ማስረጃዎች አሉ?
አንደኛ ስልኬ ነው፡፡ ስልኬ ትንሿ የድሮዋ ኖኪያ ነበረች፡፡ ከመደወል ውጪ ኢንተርኔትም ሆነ ሌላ ነገር አትሠራም፡፡ ሌላው ፍላሽ ነው፡፡ ፍላሹን ሲመለከቱት፤ውስጡ ዘፈን ብቻ ነው ያለው፡፡ በቃ ዝም ብለው “ከኤርትራ ደህንነቶች ጋር ትገናኛለሽ፤ ከእነማን ጋር ነው የምትገናኚው?” የሚል ጥያቄ ነበር የሚጠይቁኝ፡፡ “ትገናኛለሽ” ብለው ይወነጀሉኛል፤ ግን ከማን ጋር እንደምገናኝ አይነግሩኝም፤ እኔ እንድነግራቸው ነው የሚፈልጉት፡፡ ለፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ ላይ “ትገናኛለች” የተባለው ሰው ስም አልተጠቀሠም፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው አሸባሪ ተብዬ፣ የ7 ዓመት እስር የተፈረደብኝ፡፡ የስራ ባልደረቦቼን በመከላከያ ምስክርነት አቅርቤ ነበር፡፡ ግን ያው ያቀረብኩት ማስረጃ ውድቅ ሆኖ ተፈረደብኝና፣ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወረድኩ፡፡
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቆይታሽ እንዴት ነበር?
ከእነ ርዕዮት አለሙ ጋር ነበር የታሠርኩት። በቆይታችን ያው እንደ አደገኛ አሸባሪ እንጂ እንደ ታራሚ አንታይም ነበር፡፡ ቤተሠብ እንደፈለገ አይጎበኘንም፣ ከትግራይ ድረስ መጥተው ሳያገኙኝ የሚመለሡ ዘመዶች ነበሩ፡፡ በሽብር የተከሠሠ ሰው፣ እንደ ልዩ ፍጥረት ነው ክትትል የሚደረግበት፡፡ ይህ ሁኔታ ግን ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ እየቀነሠ መጥቷል። እንደውም መፈቻችን ሲቃረብ፣ እንክብካቤ ሁሉ ያደርጉልን ነበር። ሠላምታቸውና የሚሠጡን አክብሮት ተሻሽሏል፡፡ በዚሁ ከዘለቀ ጥሩ ነው። እኔ ሳላሸብር አሸባሪ ተብዬ በመከሰሴ ያሣደረብኝ የስነ ልቦና ጫና እንዲህ በቀላል የሚነገር አይደለም፡፡ ህዝብ ግን እውነቱን ያውቃል፡፡ ህዝብ ከጎኔ እንደሆነ አውቃለሁ። የኔ ቀላል ነው፡፡ በደረሠባቸው ድብደባና ስቃይ መውለድ የማይችሉ በርካታ ናቸው፡፡ ጥፍራቸው የተነቀለ አሉ፡፡ ይሄ ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የተፈፀመ አሳዛኝ ድርጊት፡፡
በዚህ መልኩ  እፈታለሁ ብለሽ ጠብቀሽ ነበር?
በሽብር ወንጀል የተከሠሡ አብዛኞቹ ሴቶች ሲፈቱ፣ በማረሚያ ቤቱ ቀርተን የነበርነው፣ እኔ እና በኦነግ ምክንያት ተከሣ፣ እድሜ ልክ ፍርደኛ የነበረችው ኢፍቱ ወይም ሃሊማ አሊ ብቻ ነበርን፡፡ እኔና እሷ ተነጥለን በማረሚያ ቤት ስንቀር፣ በጣም አዝኜ ነበር። ያዘንኩት ለኔ ሳይሆን ለኢፍቱ ነው፡፡ እኔ እንኳን አመከሮ ከታሰበልኝ፣ በመደበኛ ሂደት ከ5 ወር በኋላ እፈታ ነበር፡፡ ይፍቱ ግን የእድሜ ልክ ፍረደኛ ነች፡፡ ስለዚህ ብቻዋን መቅረቷ በጣም አስጨንቆኝ ነበር፡፡ የማረሚያ ቤቱም ሃላፊዎች፤ ፀባያቸው ሁሉ መልካም ሆኖልን፣ ያፅናኑን ነበር፡፡ “አይዟችሁ የእናንተንም ጉዳይ እየጠየቅን ነው” ይሉን ነበር፡፡ በኋላ ሳናስበው ድንገት እንድንፈታ ተደረገ፡፡ በመፈታቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለኔ አሁንም ይበልጥ የሚያስደስተኝ ግን የእድሜ ልክ ፍርደኛ የነበረችው ኢፍቱ በመፈታቷ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየቦታው ጉብኝት እንደሚያደርጉ፣ ማረሚያ ቤቶችን መጎብኘት አለባቸው። ማረሚያ ቤቶች አንድ ክፍለ ከተማ  ማለት ናቸው፡፡ በዚያ ያለው ሰቆቃ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም፡፡ እኔ ደርግ ከወደቀ በኋላ፣ የሰው ልጅ ስቃይ፣ በኢትዮጵያ ምድር፣ ያበቃ ይመስለኝ ነበር፡፡ ግን ሁሉም እንዳለ ነው ያለው፡፡ በድብደባ ብዛት እንዳይወልዱ የተደረጉ አሉ፡፡ ብዙዎች በዚህ በፀረ ሽብር ህጉ ምክንያት ኑሯቸው ተረብሷል፤ ቤተሠቦቻቸው ተበትነዋል፡፡ ልጆቻቸው ጎዳና ወጥተዋል፡፡
አንቺስ  እስሩ የኑሮ ቀውስ አድርሶብኛል ትያለሽ?
አካላዊ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ እግሬ ህመምተኛ ሆኗል፡፡ ከስራዬ ተፈናቅያለሁ፡፡ እናቴን ጨምሮ 5 ቤተሰቤን ነበር የማስተዳድረው፡፡ እኔ ከታሠርኩ በኋላ ቤተሠቤ የከፋ ችግር ላይ ወድቋል፡፡ የስነልቦና ቀውስ ደርሶብናል፡፡ በእንቅልፍ መድሃኒት ነበር እኮ ማረሚያ ቤት የምንተኛው፡፡ አሁን በ14 አመት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ አለኝ፡፡ ልጄ እስካሁን የሚያውቀው ስልጠና ቦታ መሄዴን እንጂ እስር ቤት መግባቴን አይደለም። የሠውን ልጅ ስቃይ በምድሪቱ ለማስቆም በርካቶች ተሰውተዋል፡፡ ነገር ግን በስህተት ውስጥ ስንጓዝ ከርመናል፡፡ ብዙዎች “የትግራይ ህዝብ ከዚህ ስርአት ተጠቅሟል” ሲሉ እሠማለሁ፡፡ ይሄ ሃቁን አለማወቅ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በደል እየደረሠበት ነው፡፡ ይሄው እኛንም አስረው፣ ደብድበው፣ ጉዳተኛ አድርገውናል፡፡ ብዙ የትግራይ ልጆች፣ የኔ እጣ ፋንታ ደርሷቸዋል፡፡ መንግስት ስህተቱን አምኖ እታረማለሁ ብሏል፡፡ ከታረሙ፣ ታረሙ፣ ያለበለዚያ ግን ከዚህ በኋላ የትግራይ ህዝብ ዝም ብሎ የሚመለከታቸው አይሆንም፡፡ እንደ ድሮ በመሣርያ ባይሆንም በሃሳብ ይታገላቸዋል፡፡
አሁንም በማረሚያ ቤት የቀሩ ሊፈቱ የሚገባቸው ሰዎች አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን መፈተሽ አለባቸው፡፡ እኛን ብቻ መፍታቱ ትርጉም የለውም። በፖለቲካ የታሠሩትን መፍታት ለመንግስት ትርፍ እንጂ ኪሣራ አይሆንም፡፡
በመጨረሻ ምን ዓይነት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ትመኛለሽ?
በቋንቋና በዘር ሳንከፋፈል የምንኖርባት ኢትዮጵያን ነው የምመኘው፡፡ ቤተሰቤ ያስተማረኝ፤ አንድነትንና ፍቅርን ነው፡፡፡ ሁላችንም ከቤተሰባችን እንደተማርነው፣ በፍቅር መኖር አለብን፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ነች፡፡ በሰው ሃይል ሳይሆን በፈጣሪ ሃይል፣ አንድነቷ እንደሚጠናከርም እምነት አለኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለ4 አመት ከትግራይ ተመላልሳ ለጠየቀችኝ እናቴና ለመላው ቤተሰቤ እንዲሁም ፍቅር ለሠጠኝ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

Read 10058 times