Sunday, 13 May 2018 00:00

“ይሄን ያህል ጭንቅላት ሥራ አቁሟል እንዴ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)


   “--ከዚህስ ይሰውረን፡፡ እውነት ግን…ጭንቅላት ካልሠራ፣ ምን ዋጋ አለው!…ጭንቅላት ካላሰበ፣ ካልጠየቀ፣ ካላሰላሰለ ምን ዋጋ አለው! ብዙ ችግር ባለባት አገር፣ ብዙ መከራ ባለባት አገር፣ ብዙ የተወሳሰቡ ጥልፍልፎች ባሉባት አገር…አእምሮ በሚገባ ካልሠራ ምን ዋጋ አለው!--”
 
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አኔ የምለው…ብዙዎቻችን ማሰብ፣ ‘ደክሞን’ ወይ ‘ሰልችቶን’ ተውን እንዴ! ዘንድሮ ብዙ ነገሮችን ስናይ… “እውነት እንዲህ አይነት ነገር ታስቦበት የተሠራ ነው!” እያልን  ነው፡፡ መክረን፣ ዘክረን… “ይህን ነገር እንዲህ ብናደርገው ይሻላል፣” “እንደዚህ ማድረጉ ችግር ያስከትላል፣” እየተባባልን አእምሮ ያፈለቃቸው ሀሳቦች መለዋወጥ ተውን እንዴ! ልክ ነዋ…ብዙ ነገሮች ከአእምሮ በፈለቁ ሀሳቦች ሳይሆን በስሜታዊነት የሚሠሩ ይመስላሉ። የምር ግን…አእምሮ ክፍት ስፍራዎች በዙበት እንዴ! በቅጡ የማናስብ ሰዎች በዛን እንዴ!
እናላችሁ… የማናስብ ሰዎች ስንበዛ፣ ወይም ከበዛን ጥሩ ምልክት አይደለም፡፡
“አዲስ የማስታወሻ ደብተር አለኝ፡፡ ከጫማዬ ጋር ይመሳሰላል፡፡”
“ማስታወሻ ደብተርህ ውስጥ ምን አለበት?”
“ምንም የለበት፣ ባዶ ነው፡፡”
“እንግዲያው ክጭንቅላትህ ጋርም ይመሳሰላል ማለት ነዋ!”
ከዚህስ  ይሰውረን፡፡ እውነት ግን…ጭንቅላት ካልሠራ፣ ምን ዋጋ አለው!…ጭንቅላት ካላሰበ፣ ካልጠየቀ፣ ካላሰላሰለ ምን ዋጋ አለው! ብዙ ችግር ባለባት አገር፣ ብዙ መከራ ባለባት አገር፣ ብዙ የተወሳሰቡ ጥልፍልፎች ባሉባት አገር…አእምሮ በሚገባ ካልሠራ ምን ዋጋ አለው!
በነገራችን ላይ…ዘንድሮ ብዙ ነገሮች ስታዩ፤ “እንድናስብ፣ አእምሯችንን እንድንጠቀም አይፈለግም እንዴ!” ያስብላል፡፡ “እንዲህ ሥሩ፣” “እንዲህ አትሥሩ፣” የምንባል፤ በ‘ሪሞት ኮንትሮል’ አይነት ብቻ የምንንቀሳቀስ መሆን አለብን እንዴ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንዱ ስለ ስኬት ‘ፎርሙላ’ ሲያወራ ምን አለ… “ሚሊዮን ብር እስክታገኝ፤ አንተ ለሰዎች መልካም ትሆናለህ፤ ሚሊዮን ብር ስታገኝ ሰዎች ለአንተ መልካም ይሆናሉ፡” የዘንድሮ ሂሳብ እንዲህ ነው የሚሠራው። እያየን ነው… እስኪበቃን ድረስ እያየን ነው፡፡ ገና ለገና ሚሊዮን ብር የላቸውም ተብሎ፣ ምን እየሆንን እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ገና ለገና የስልጣን ወንበር የላቸውም ተብሎ ምን እየሆንን እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ገና ለገና አቅም የላቸውም እየተባለ፣ ምን እየሆንን እንደሆነ እያየን ነው፡፡
ስሙኝማ… እግረ መንገዳችን እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ታላቁ መጽሐፍ ላይ ካሉት ትእዛዛት በ‘አሜንድመንት’ ወይም ‘አክላሜሽን’ ምናምን በሚሉት ነገር የተለወጠ ትእዛዝ አለ እንዴ! ግራ ገባን እኮ…እንዴት ነው ነገሩ ሁሉ እንዲህ ትከሻ ከመስበቅ አላልፍ ያለው! ማለትማ “የሰው ሚስት አትመኝ” ምናምን የተባለው ነገር፤ ‘የዘመኑን ተጨባጭ ሁኔታ’ በማየት ‘አፕዴት’ ተደረገ እንዴ!
“ስማ፣ ያ ጓደኛችን ከአንዲት ባለትዳር ጋር እፍ ብሎልህ፣ቤቱን ሊተው ምንም አልቀረውም፡፡”
“እውነት! ምን ታደርገዋለህ…ማታ ቢራ ትገዛለህ”
በቃ ይኸው ነው! ጓደኛ የተባለ ሰው በዚህ ርቀት ‘ቀይ መስመር’ አልፎ ሲሄድ የቅርብ ወዳጆች ምላሽ በቃ እንዲህ ነው!
“ቤተሰቡን እንዳያፈርስ፣ ሰብሰብ ብለን እንምከረው እንጂ!” ብሎ ነገር የለም?
“ባይሆን ለነፍስ አባቱ ነግረን እሳቸው የሚያደርጉትን ያድርጉ እንጂ፣ አለበለዛ ሚስቱና ልጆቹ ጎዳና ነው የሚወጡት” ብሎ ስጋት የለም!
ሰውየው ጓደኛውን አንደ ቀን ጠዋት ሲያገኘው፣ ፊቱ ትንሽ በልዟል፡፡
“ስማ ጉንጭህ አካባቢ በልዟል እኮ! ምን ሆነህ ነው?”
“ያቺ የባንኳ ልጅ፣ ያቺ እንኳን ሲኖ ትሯኳ… ትዝ አለችህ?”
“አዎ፣ ምን ሆነች? ጠፈጠፈችህ እንዴ!”
“ባሏ ፊልድ ሄደ ተብሎ አልነበር…”
“እኮ… ባሏ ፊልድ ስለሄደ ቤቷ ብቅ እላለሁ ያልከኝ፣ ራስህ አይደለህም እንዴ…”
“ለካስ ባሏ ፊልድ አልሄደም ነበር!”  ቂ…ቂ…ቂ….
አላርፍ ሲሉ እንዲህ ነው፡፡ አላርፍ ሲሉ ሄደ አሉ ጋራ ጋራውን…የተባለው ባል፣ በእንትን መሀል በር ይቆረቁራል፡፡ (ልክ… “ጎሽ ሄደልን!” ያልነው፣ እንደ ናቡከደናጾር ሊያደርገው የሚሞክር የመመሪያ ሃላፊ ጭራሽ ‘ሲ.ኢ.ኦ.’ ምናምን ሆኖ ልባችንን ቀጥ እንደሚያደርጋት ማለት ነው፡፡) እኔ የምለው… እሺ፣ “ሄደ” ያሉት አባወራ ድንገት ከች የሚል ከሆነ… አለ አይደል… እሷዬዋስ ብትሆን ‘መስኮት ዘላዩን’ እዛው ጓሮ ማስቀረት ነዋ! ለምንድንው…
አንተ የጓሮ ፍየል ብትስል ብታነጥስ
ዛሬ ባል ነውና ቅጠልም አልበጥስ፣
ያላለችው! ቂ…ቂ…ቂ… (ለነገሩ… አዲስ አበባ ውስጥ ለፍየል የሚሆን ‘ጓሮ’ ቀርቷል እንጂ!) ምንም እንኳን የዘመናችን ሰው፣ አይደለም ቅኔ ሊፈታ፣  በመደበኛውም ቋንቋ መግባባት እያቃተው ቢሆንም “እንዲህ ያንጎራጎረችው የሆነ ችግር ቢኖር ነው” ብሎ በመጣበት እግሩ ይመለስ ነበር፡፡ ለወደፊቱ እንደ ጥቆማ… ፊልድ ይሄዳል የተባለ ባል ካልሄደ…እሷዬዋ
ነድፌ ነድፌ ባልጋ ከምሬያለሁ
የዛሬ ቀን ከብዷል ባለ አለ ብያለሁ፣
ትበል፡፡ አሀ…ምን እናድርግ፣ ባል ፊልድ ሄደም፣ አልሄደ ነገርዬው ‘ኮምፐልሰሪ’ ከመሰለ፣ እኛም እኮ “ጋዜጣ ላይ በተጻፈው ግጥም ስታንጎራጉር፣ ባሏ ቤት መሆኑን አወቅሁ” ምናምን ተብሎ ክሬዲት እናግኛ! (በነገራችን ላይ… “ምን በወጣኝና ነው ነድፌ፣ ነድፌ የምለው! እኔ የምናደፈው የወባ ትንኝ ነኝ እንዴ!” የምትል ልትኖር ትችላለች፡፡)
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…“ብር አምባር ሰበረልዎ!” እኮ የሰርግ የመጨረሻ ማድመቂያ ነበር፡፡ የምር… ማለዳ ላይ በር እየተደበደበ፣ “ብር አምባር ሰበረልዎ፣ ሸጋው ልጅዎ” ሲባል ትልቅ የድል ምስራች ነበር፡፡ ናዚ ጀርመን እንኳን እጇን ስትስጥ፣ ይሄን ያህል መጨፈሩ ያጠያይቃል፡፡
አሁን ግን የእውነትም ሆኖ፣ “ብር አምባር ሰበረልዎ” ቢባል…አለ አይደል…“ቀልዱን ተው፣ አዳሜ ሞዲፊክ እያሠራች…” ምናምን መባሉ አይቀርም፡፡ አሁን ካልጠፋ ‘ሞዲፊክ’ የሚሠራ ነገር  ለእሱ ነገር ‘ሞዲፊክ’ ይሠራሉ! ‘ሂዩመን ሄይር’ እንደሚሉት ‘ሂዩመን እንትን’ ሊባል ማለት ነው! የምር ግን ዘንድሮ ‘ብር አምባር’ ለማግኘት እስከ አርባና ሀምሳ ሺህ ብር የሚከፍሉ አሉ ይባላል፡፡ የምር ግርም የምትል አገር እኮ ነች…ሃምሳ ሺህ ብር እኮ አንድን ቤተሰብ ስምንትና ስንት ጊዜ ይቀልባል፡፡ እና ለሁለት ደቂቃ ተኩል ሀምሳ ሺህ ብር አያበሽቅም! ቂ…ቂ…ቂ…
ሰውየው ንግግር እያደረገ ነበር፡፡ ታዲያ ከተሰብሳቢዎቹ አብዛኞቹ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ደጋግመው ይስላሉ፡፡ ይሄኔ ወደ አስተባባሪው ጆሮ ጠጋ ይልና…
“ሰዉ ሁሉ ይህን ያህል የሚስለው የጉንፋን ወረርሽኝ ገብቶ ነው እንዴ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ምን ብሎ ቢመለስለት ጥሩ ነው…
“ጉንፋን ሳይሆን አንተን ‘በቃህ፣ ውረድልን’ እያሉሀ ነው፣” አለው አሉ፡፡
ሰዋችን እንዲህ ነው፣ ‘በቃህ’ ሲል፣ ‘በቃሽ’ ሲል፣ ‘በቃችሁ’ ሲል የግድ በቃላት አይገልጽም፤ ወይ ዝምታ ያበዛል፣ ወይ ‘ሳል’ ያበዛል፡፡ አዳራሽ ሙሉ ሆነን፣ በሌለ ጉንፋን አብዛኞቻችን ከሳልን፣ ያልተመቹን ነገሮች እንዳሉ ልብ ይባልልንማ!
የምር… ምንም እንኳን ‘ኒዩሮሰርጀን’ ምናምን ባንሆንም፤ ጭንቅላት ክፍት ቦታዎች ሲበዙበት ጥሩ አይደለም፡፡ እሱዬው ኑሮ ያስጠላዋል፡፡ በቃ ይቺን ዓለም እሰናበታለሁ ብሎ ይወስናል፡፡ ጓደኛውንም ያማክራል፡፡
“ራሴን በሽጉጥ ለመግደል ወስኛለሁ፣ ሰውነቴን ምኔ ላይ ልምታው?” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም…
“ደረትህን በለው…” ይለዋል፡፡ አጅሬውም…
“ለምን ደረቴን መረጥክ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ምክንያቱም ጭንቅላትህ አሁንም በድን ስለሆነ ብትመታውም፣ ባትመታውም ለውጥ አያመጣም፣” ብሎት አረፈ፡፡
እኔ የምለው…ብዙ ነገሮችን ስናይና ስንሰማ፣ “ይሄን ያህል ጭንቅላት ሥራ አቁሟል እንዴ!” እንላለን፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1565 times