Sunday, 13 May 2018 00:00

“ማይንድ ሴት የትልልቅ ሃሳቦች ኮንቬንሽን” በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የሚሰራው “ማይንድ ሴት ኮንሰልት” መስራች በሆኑት በዶ/ር ምህረት ደበበ የሚዘጋጀው “ማይንድ ሴት የትልልቅ ሃሳቦች ኮንቬንሽን” (Mindset all grand ideas convention) (MAGIC) የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡ ኮንቬንሽኑ፤ “አዲስ አገር - አዲስ እይታ”፣ “አዲስ አገር - አዲስ ትውልድ” እና “አዲስ አገር - አዲስ አስተሳሰብ” በሚሉ ዋና ዋና ርዕሶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የጠቆሙት ዶ/ር ምህረት፤ በዚህ አነቃቂና የትልልቅ ሃሳቦች ኮንቬንሽን ላይ ከ7 እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ላለፉት አራት ወራት “ማይንድ ሴት ኮንሰልት”፤ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በየሳምንቱ በሰብዕና ልቀትና የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ አነቃቂ ሃሳቦችን በማስተማር በርካታ ስራዎችን ሲሰራ እንደነበር የገለፁት ዶ/ር ምህረት፤ በሚሊኒየም አዳራሽ ሰዎች ያለ ክፍያ መጥተው በትልልቅ ሃሳቦች ዙሪያ ትምህርት እንዲቀስሙና ሃሳብ እንዲያንሸራሽሩ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የማይንድ ሴት ምዕራፍ አንድ መጠናቀቅን ተከትሎ፣ ለማህበረሰቡ የተዘጋጀው ይህ መድረክ “ለአዲስ አገር - አዲስ አስተሳሰብ” በሚል መሪ ቃል የተሰናዳ ሲሆን የአንድ ሰው የግል አስተሳሰብ፤ በአንድ አገር ላይ የሚያመጣውን በጎ ተፅዕኖ ለማጉላትና “እኔ ነኝ አዲሷ ኢትዮጵያ” የሚል ሀሳብ በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረፅ መታሰቡን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመታደም ሁለት ዓይነት ምዘገባ ይካሄዳል ተብሏል፡፡ አንደኛው በ8845 ላይ ሙሉ መረጃ በመላክ በሚደርሳቸው ቁጥር መሰረት በዕለቱ መታደም የሚችሉበት ሲሆን ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በ www.registration.mindsetconsult.com ላይ በመመዝገብ መታደም የሚቻልበት ነው፡፡ ታዳሚዎች በእለቱ መታወቂያ መያዝ እንዳይረሱ ተብሏል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ በስብዕና ልቀትና በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ከዶ/ር ምህረት በተጨማሪ አራት ተናጋሪዎች ሃሳባቸውን የሚያጋሩ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የ“ማማ በሰማይ” (Tower in the sky) ደራሲዋ ህይወት ተፈራና የታሪክ ባለሙያው ኢብራሂም ሙሉሸዋ እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡ ይህ ፕሮግራም ለመላው ህዝብ ተደራሽ እንዲሆን በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮና በማህበራዊ ሚዲያ በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ ሲሆን ከቀኑ 9፡00-12፡00፣ ለሶስት ሰዓት የሚካሄድ መድረክ ነው፡፡ የማይንድ ሴት ኮንሰልት ምዕራፍ ሁለት ከአንድ ወር በኋላ ለተከታታይ አራት ወራት በብሔራዊ ቴአትር እንደሚጀመር ጨምረው ገልፀዋል - ዶ/ር ምህረት፡፡

Read 4218 times