Monday, 21 May 2018 00:00

ጠባቂዎቹን ማን ይጠብቃቸዋል? (Who guards the guards?)

Written by 
Rate this item
(9 votes)

ጥንት ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ዐረብ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ የከሰሱት ሶስት ሴቶች ናቸው፡፡ ያለአግባብ ፈቶናል፣ በድሎናል፣ ብለው ነው አቤቱታ ያቀረቡት፡፡
ዐረቡ ቀርቦ እያንዳንዳቸውን፤ “ለምን እንዳባረርካቸው አስረዳ?” ተባለ፡፡
ዐረቡም፤
“የመጀመሪያዋ ሚስቴ ጠዋት ማታ ጭቅጭቅ አበዛችብኝ!” አለ፡፡
“ምን ብላ ጨቀጨቀችህ?” አሉ ዳኛው፡፡
“ነገ ትፈታኛለህ፤ አላምንህም ትላለች፡፡ ሲሰለቸኝ እንደውም ‹ዛሬ ነው የምፈታሽ› ብዬ አስወጣኋት!”
“መልካም፡፡ ሁለተኛዋንስ?”
“ሁለተኛዋ ደግሞ የትላንትናዋን ሚስትህን እንዴት ፈታሃት? እያለች ነጋ - ጠባ ትነተርከኛለች፡፡ ‹አንቺ ስለትላንት ምን አገባሽ? የዛሬን በሰላም ኑሪ› ብላት አሻፈረኝ አለች፤ አባረርኳት!”
“ሶስተኛዋስ?”
“እሷ ደግሞ ‹ለነገ አታስብም› ትለኛለች፡፡ ‹የዛሬን መደሰት ብቻ ነው ፍላጎትህ፡፡ ነገም እኮ መኖር አለብን› ትላለች፡፡ ‹ዝም ብለሽ የዛሬን ተደሰች› ብላት እምቢ አለች - አባረርኳት!”
ዳኛው የሚስቶቹንም ቃል ከሰሙ በኋላ፣ “ፍርድ ቤቱ ሁኔታውን ካየና ግራ ቀኙን አመሳክሮ ከመረመረ በኋላና በተለይም ለማንኛዋም ባለቤትህ ምንም ንብረት አለማካፈልህን በማመንህ፣ አሁን ለሁሉም ካሳ ክፈል ብትባል ስለሚከብድህ፤ ሶስቱንም አግብተሃቸው እንድትኖር ተወስኗል!”
ዐረቡም፤
“ክቡር ፍርድ ቤቱ ትላንትን፣ ዛሬና ነገን አግብተህ ኑር ነው የሚለኝ?”
“አዎን፡፡ ውሳኔው እንደዚያ ነው፡፡”
“ባይስማሙልኝስ?”
“እሱን ስንደርስ እናየዋለን!”
“ነገም አላችሁ ማለት ነው?”
“ፍርድ ቤቱን አትዳፈር! የታዘዝከውን ፈፅም” አሉ ዳኛው በቁጣ፡፡
*   *   *
ፍትህና የፍትህ አካላት ነገር ሁሌም እንዳሳሰበን አለ፡፡ የተከማቹ ፋይሎች ጉዳይ፣ የቀጠሮዎች መራዘም ልማድ፤ እንደጤናማ ሂደት መቆጠር ከጀመረ ዘመናት አልፈዋል፡፡ “የፍርድ ቤት ሙግት አለብኝ” ይሉ የነበሩት አያት ቅድመ - አያቶቻችን ህይወት ዛሬ ይታያል ማለት ጊዜና ሁኔታን ያላገናዘበ ትዝብት ሆኖ ይሰማናል - anachronistic እንዲሉ፡፡ ያም ሆኖ ወደ ትላንት ተመልሰን እየኖርን ነው ባንልም፣ የትላንት ድባብ ስር እንድንጠለል የሆንን ይመስላል፡፡ የጥንት ፍርድ ቤቶች ዋና ሥራ የመሬት ሙግት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዳኞች ‹በጓሮ በር ሙክት ያስጎትታሉ›፤ ጉቦና እጅ መንሻ ምስሳቸው ነው ይባላል፡፡
“ተወኝ ዳኛ አዳኜ፣ የበግ መግዣም የለኝ እጅ እጄን የሚያዩ ብዙ ልጆች አሉኝ” ተብሎ የተገጠመው ቢቸግር ነው፡፡ ዛሬ ስሙ ሙስና የተባለው ጉቦ፤ የቤት ስሙ “ቢዝነስ”፣ “ኮሚሽን”፣ “የሥራ ማንቀሳቀሻ - ጉዳይ ማስፈፀሚያ” መሆኑ አይገርምም፡፡ “ጠበቃ ማንን ያዝክ?” እገሌን። “በጣም ጥሩ ሰው ይዘሃል፡፡ እሱ ዳኞቹን አሳምሮ ያውቃል!” ሙስና ፈርጁ ብዙ ነው፡፡ የፖሊስ ጣቢያ እስረኛ ስልኩ ተወስዶበት፤ በፖሊሱ ሞባይል ወደዘመዶቹ ለመደወል ብዙ ብር የሚከፈልበት አገር ፍትሕ እንዴት እንደሚገኝ ግራ ይገባል፡፡ ይህ ማለት ግን ሀቀኛና ጠንካራ አካላት የሉም ማለት አይደለም -ይዋጣሉ ነው ችግሩ! የሚገርመው በየመስሪያ ቤቱ ሲዘርፍ የከረመው ሁሉ አንደኛ የፍትህ ተቆርቋሪ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ ዙሪያ - ገባው፣ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ “ሌባ! ሌባ!” እያለ እየጮኸ ሳር - ቅጠሉን የሚግጥ ነው! ከቤተ - ሰባዊ የኮንትሮባንድ ንግድ ጀምሮ እስከ ኩባንያዊ ሽቀላ ድረስ አገሩን ያምሳል፡፡ ዛሬ ለበላይ አካል የሚያስፈልገው ጥያቄ የት ቦታ ሙስና አለ? ሳይሆን፤ የት ቦታ ሙስና የለም? የሚለው ነው፡፡ የመፍትሄው ቁልፍ ጥያቄ፤ የበላይ አካልን እገሌ ከእገሌ ሳይሉ መፈተሽ ነው፡፡ ሀቀኛ ጥናት ማካሄድ ነው። በሽርክና የተገባባቸው ንግዶችን፣ የኮንስትራክሽን እንቅስቃሴዎችን፣ በልማት ስም የሚሰሩ ደባዎችን ደፍሮ ማጣራትና ማጥራት ነው! አንድ ፀሐፊ እንደጠየቀው፤ “ይሄ የበላይ አካል ማለት የብዕር ስም ነው እንዴ?” ተብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ የበላይ አካል ምስጢር መሆን የለበትም፡፡ በተማሪው ለመተማመን፣ አስተማሪውን መመርመር ነው፡፡ የፍትህ የበላይ አካላት፣ የኢኮኖሚ የበላይ አካላት፣ የፖለቲካ የበላይ አካላት፣ የትምህርት የበላይ አካላት … ሁሉም የበላይ ጠባቂ አላቸው፡፡ ሥረ - ነገራችን እንግሊዞች እንደሚያቀርቡት ጥያቄ “Who guards the guards?” ዓይነት ነው፡፡ “ጠባቂዎቹን ማን ይጠብቃቸዋል?” እንበልና ላዕላይ ጠባቂውንም በጥበብ እንመርምር፡፡

Read 5637 times