Monday, 21 May 2018 00:00

በ21ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

• 736 ተጨዋቾች ይሳተፋሉ 1120 በመጀመርያ እጩ የቡድን ስብስብ በፊፋ ተመዝግበዋል፡፡
• 32 ቡድኖች በ10.43 ቢሊዮን ዩሮ የሚተመን የተጨዋቾች ስብስብ የሚገነቡ ይሆናሉ
• በዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን ሊዮኔል ሜሲ ከአርጀንቲና 180 ሚሊዮን ዩሮ፤ ኪላን ማብፔ ከፈረንሳይ 120
ሚሊዮን ዩሮ ፤ ክርስትያኖ ሮናልዶ ከፖርቱጋል 120 ሚሊዮን ዩሮ
• ውድና ምርጥ 11 ተጨዋቾች ቡድን ከ900 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ያወጣሉ
• በተጨዋቾች ስብስብ ውዱ ቡድን ፈረንሳይ በ999.50 ሚሊዮን ዩሮ


    በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት 32 ብሄራዊ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 35 ተጨዋቾች ያሉባቸውን የመጀመርያ እጩ የቡድን ስብስባቸውን ሰሞኑን ለፊፋ አስታውቀዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኖቹ በዓለም ዋንጫ የሚያሰልፏቸውን 23 ተጨዋቾች ያሉባቸውን የመጨረሻ የተጨዋቾች ስብስብ ውድድሩ ከመጀመሩ ከ10 ቀናት ቀደም ብሎ ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በትራንስፈር ማርከት ድረገፅ መሰረት በዓለም ዋንጫ በሚሳተፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች በመጨረሻ የተጨዋቾች ስብስብ የሚመዘገቡ 736 ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው አጠቃላይ የዋጋ ተመናቸው እስከ 10.43 ቢሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ በምትገባው ጀርመን ወሳኝ ይሆናል የተባለው ቶኒ ክሮስ፤ በአጥቂ መስመር ድንቅ ብቃቱን በማሳየት ለእንግሊዝ ብዙ ያገባል ተብሎ የሚጠበቀው ሃሪ ኬን፤ በቅርቡ ከገጠመው ጉዳት ካገገመ ብራዚልን በአምበልነት በመምራት ለ6ኛው የዓለም ዋንጫ ድል ያበቃታል ተብሎ የተወሳለት ኔይማር፤ በዓለም ዋንጫ ድል ስኬታማ በመሆን አርጀንቲናን ይክሳል የሚባለው ሊዮኔል ሜሲ፤ ከ2017 እኤአ ጀምሮ የዓለም ኮከብ ተጨዋች ሆኖ የሚገኘው ክርስትያኖ ሮናልዶ፤ ሊውስ ስዋሬዝ ከኡራጋይና በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እና በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛ አግቢነት የተሳካለት መሃመድ ሳላህ በኮከብ ተጨዋችነት እና በኮከብ ግብ አግቢነት እንደሚፎካከሩ እየተገመተ ነው፡፡ ሊሮስ ሳኔ ከጀርመን፤ ግራኔት ዣካ ከስዊዘርላንድ፤ ኬሌቺ ኢሄናንቾ ከናይጄርያ ፤ ማቲያ ቬሲኖ ከኡራጋይ፤ ማከስ ራሽፈርድ ከእንግሊዝ እንዲሁም ሮበርቶ ፈርሚሆ ከብራዚል በወጣት ኮከብ ተጨዋችነት የሚጠበቁ ሆነዋል፡፡ በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው ባለመመረጣቸው፤ በጉዳት ምክንያት፤ በጡረታ በመሰናበታቸው እና ብሄራዊ ቡድኖቻቸው ባለመሳተፋቸው ደግሞ ዓለም ዋንጫው የሚያመልጣቸው ምርጥ ተጨዋቾች ጥቂት አይደሉም፡፡  ካሪም ቤንዜማና ሎረን ኮሰልኒ ከፈረንሳይ፤ አሌክስ ኦክስሌይ ቼምበርለይን፤ ጃክ ዊልሸርና ጆ ሃርት ከእንግሊዝ፤ ዳኒ አልቬስ ከብራዚል፤ማርዮ ጎትዜ ከጀርመን በመጀመርያው ተጨዋቾች ስብስብ  በብሄራዊ ቡድኖቻቸው ካልተጠሩት መካከል ይገኙበታል፡፡ ዝላታን ኢብራሞቪች ከስዊድን ዣቪ አርናንዴዝ ከስፔን በጡረታ ዓለም ዋንጫውን ከማይሳተፉ ተጨዋቾች የሚጠቀሱ ሲሆን እነ ሮሲ ከጣሊያን፤_እነ ሩበን ከሆላንድ ብሄራዊ ቡድኖቻቸው ለዓለም ዋንጫ ባለማለፋቸው ታላቁ የስፖርት መድረክ ያመለጣቸው ናቸው፡፡
ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸው ተጨዋቾች
ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ ጋር በተያያዘ በዝውውር ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸው ተጨዋቾች ከ1 እስከ10 ባለው ደረጃ በቅደም ተከተል ሲቀመጡ እንደሚከተለው ነው፡፡ ሊዮኔል ሜሲ ከአርጀንቲና 180 ሚሊዮን ዩሮ፤ ኪላን ማብፔ ከፈረንሳይ 120 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ክርስትያኖ ሮናልዶ ከፖርቱጋል 120 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ኬቨን ዴብርዋኒ ከቤልጅዬም 100 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ኤዲን ሃዛርድ ከቤልጅዬም 100 ሚሊዮን ዩሮ ፤ አንቶኒዮ ግሬዝማን ከፈረንሳይ 100 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ፊሊፕ ኩቲንሆ ከብራዚል 90 ሚሊዮን ዩሮ  ፤ ፖል ፖግባ ከፈረንሳይ 90 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ሉዊስ ስዋሬዝ ከኡራጋይ 85 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም ሮሜሉ ሉካኩ ከቤልጅዬም በ85 ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡
በ80 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው ዴል አሊ ከእንግሊዝ፤ ሮበርት ሎውንዶውስኪ ከፖላንድ፤ቶኒ ክሮስ ከጀርመን፤ ኡስማን ዴምቤሌ ከፈረንሳይ፤ መሃመድ ሳላህ ከግብፅ እንዲሁም ራሂም ስተርሊንግ ከእንግሊዝ ይጠቀሳሉ፡፡ በ75 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው ደግሞ ሊሮይ ሳኔ ከጀርመን፤ ሰርጂዮ አግዌሮ ከአርጀንቲና እንዲሁም ኢስኮ ከስፔን  ሲሆኑ በ70 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን ደግሞ ሳል ኑጎዌዝ ከስፔን፤ ኮኬ ከስፔን ፤ ገብሬል ጂሰስ ከብራዚል፤ ክሪስትያን ኤርክሰን ከስዊዘርላንድ እንዲሁም ጎንዛሎ ሄግዌን ከአርጀንቲና ይገኙበታል፡፡
ከዚህ በታች የቀረበው ደግሞ በዓለም ዋንጫ ከሚሰለፉ 736 ተጨዋቾች  መካከል በክለብ ደረጃ በሚያገኙት ሳምንታዊ ደሞዝ ከ1 እስከ 10ኛ የሚኖራቸው ደረጃ ነው፡፡
ኔይማር (ብራዚል) 509.26 ሺ ዩሮ በሳምንት
ክርስትያኖ ሮናልዶ (ፖርቱጋል) 421.6ሺ ዩሮ  
ሊዮኔል ሜሲ (አርጀንቲና)421.6ሺ ዩሮ  
ሜሱት ኦዚል (ጀርመን) 403.75 ሺ ዩሮ  
ኪላይን ሚባፔ (ፈረንሳይ) 357ሺ  ዩሮ  
ሊውስ ስዋሬዝ (ኡራጋይ) 331.5 ሺ ዩሮ  
ፖል ፖግባ (ፈረንሳይ)  331.5 ሺ ዩሮ  
ሰርጅዮ አግዌሮ (አርጀንቲና) 254.15 ሺ ዩሮ  
ቶኑ ክሮስ (ጀርመን) 229.5 ሺ ዩሮ  
ሰርጂዮ ራሞስ (ስፔን ) 229.5 ሺ ዩሮ  
ባለ ከፍተኛ ዋጋና  ምርጥ 11
የ21ኛው ዓለም ዋንጫ ባለ ከፍተኛ ዋጋና  ምርጥ 11 ተጨዋቾች ቡድን ከ900 ሚሊዮን ዩሮ በላይ እንደሚያወጣ በድረገፁ ያሰፈረው www.transfermarkt.co.uk ነው፡፡ ትራንስፈርማርከት  የዓለም እግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ ታሪክ፤ተመንና የዋጋ ውጣውረድ በማስላት የሚሰራ ታዋቂ ድረገፅ ነው፡፡ የዓለም ዋንጫ ባለ ከፍተኛ ዋጋና ምርጥ 11 ተጨዋቾች  ድረገፁ የመረጠው በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የሚሳተፉት 32 ብሄራዊ ቡድኖች ከሚያሰልፏቸው 736 ተጨዋቾች ነው፡፡ ይህ ቡድን አሰላለፉ 4-3-3 ወይምን 4-3-2-1 እንደሚሆን ድረገፁ ቢያመለክትም ዋና አሰልጣኙ ማን እንደሆነ ግን አልጠቆመም፡፡  
ከዚህ በታች ከ900 ሚሊዮን ዩሮ በላይ የሚያወጣው ቡድን አባላት የቀረበ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ የዓለም ዋንጫውን ከፍተኛ የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን  በሚሊዮን ዩሮ ያስመዘገቡ  ተጨዋቾችን ያገኛሉ፡፡
ግብ ጠባቂ
ዴቪድ ዴ ጊያ (ስፔን)    50,00 Mill. €
ተከላካዮች
ማርኩዊኖስ (ብራዚል) 55,00 Mill. €
ራፋኤል ቫርኔ (ፈረንሳይ)     40,00 Mill. €
ማርሴሎ  (ብራዚል)    40,00 Mill. €
ዳንኤል ካርቫሃል (ስፔን)    45,00 Mill. €
አማካዮች
ፖል ፖግባ (ፈረንሳይ)90,00 Mill. €
ቶኒ ክሮስ (ጀርመን) 80,00 Mill. €
ኬቨን ዴብርዋኒ (ቤልጅዬም) 110,00 Mill. €
አጥቂዎች
ክርስትያኖ ሮናልዶ (ፖርቱጋል) 120,00 Mill. €
ሊዮኔል ሜሲ (አርጀንቲና) 180,00 Mill. €
አንቶኒዮ ግሪዝማን (ፈረንሳይ) 100,00 Mill. €

Read 4948 times