Monday, 21 May 2018 00:00

ኤርትራ ኢትዮጵያና ሱዳንን ወነጀለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 የኢትዮጵያና የሱዳን መሪዎች በቅርቡ በካርቱም ባደረጉት ስብሰባ ላይ አሲረውብኛል ሲል የኤርትራ መንግስት የከሰሰ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ክሱን መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ብሎታል፡፡
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያና የሱዳን መንግስታት የኢሳያስ አፈወርቂን መንግስት ከስልጣን ለማስወገድ፣ የፕሬዚዳንቱን ተቃዋሚዎች ለመደገፍ ተስማምተዋል፤ በሀገሪቱ መንግስት ላይ አሲረዋል” ብሏል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በካርቱም ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽር ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ መስማማታቸውን የጠቀሰው የኤርትራ መንግስት፤ በዚህም የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎችን ለመደገፍ ተስማምተዋል ብሏል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በድንበራቸው አካባቢ ነፃ የንግድ ቀጠና ለመመስረት መስማማታቸውም ለዚህ ማሳያ ነው ብሏል የኤርትራ መንግስት መግለጫ፡፡
አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም፤ በበኩላቸው “የኤርትራ መንግስት ክስ መሰረተ ቢስ ውንጀላና አስቂኝ የፈጠራ  ድራማ ነው ብለዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት በአሜሪካ የተጣለበትን ማዕቀብ ለማንሳት የሚያስችል በጎ እርምጃ አለመታየቱን የጠቆሙት የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ፤ የኤርትራ መንግስት የባህሪ ለውጥ ለማምጣት እስካሁን ፍንጭ አለማሳየቱን ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በበአለ ሲመታቸው ወቅት ለኤርትራ መንግስት የእርቅ ጥሪ ማቅረባቸውን በመግለጫው የጠቀሰው የኤርትራ መንግስት፤ “የተለመደ የህዝብ ግንኙነት ስራ ነው፤ ይህን ጥሪ ማቅረባቸው አዲስ ነገርም አስደናቂም አይደለም” ብሏል፡፡

Read 6857 times