Monday, 21 May 2018 00:00

88 በመቶ ኢትዮጵያውያን ዶ/ር ዐቢይ ለውጥ እንደሚያመጡ ያምናሉ ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(13 votes)

ዶ/ር አብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመመረጣቸው 84 በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያውያን ደስተኞች መሆናቸውን የጠቆመው አንድ ጥናት፤ 88 በመቶው ዶ/ር አብይ ለውጥ ያመጣሉ ብለው እንደሚያምኑ አመልክቷል፡፡
ጥናቱን ያካሄደው በማናጅመንትና የማህበራዊ ጥናትና ምርምሮች አማካሪነት የሚሠራው “ዋስ ኢንተርናሽናል” ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዶ/ር አብይ አህመድ መመረጥ ደስተኛ መሆኑንና ለውጥ ያመጣሉ ብሎ እንደሚያምን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ጥናቱ በአዳማ፣ አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ ድሬደዋ፣ ሃዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ነቀምትና ደብረ ብርሃን ከተሞች ላይ የተካሄደ ሲሆን በጥናቱ ላይ በአጠቃላይ 1505 ሠዎች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡
ዶ/ር አብይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመመረጣቸው 94 በመቶ የአዳማ ነዋሪዎች ደስተኛ መሆናቸውን ሲገልፁ፤ ከባህርዳርና ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች 84 በመቶ ያህሉ ደስተኞች መሆናቸውን ተናግረዋል ይላል - ጥናቱ፡፡ 91 በመቶ የሚሆኑት የመቀሌ፣ 82 በመቶ የነቀምት፣ 89 በመቶ የጅማ፣ 84 በመቶ የጅግጅጋ፣ 88 በመቶ የሃዋሳ 76 በመቶ የጎንደር እንዲሁም 70 በመቶ የድሬደዋ ነዋሪዎች በዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ ደስታ እንደተሠማቸው ጥናቱ ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ 88 በመቶ ያህሉ ኢትዮጵያውያን ጠ/ሚኒስትሩ ለውጥ ያመጣሉ ብለው እንደሚያምኑ ተጠቁሟል፡፡ 97 በመቶ የአዳማ፣ 87 በመቶ የአዲስ አበባ፣ 88 በመቶ የባህር ዳር፣ 88 በመቶ የደሴ፣ 90 በመቶ የደብረብርሃን፣ 85 በመቶ የጎንደር፣ 96 በመቶ የጅግጅጋ፣ 90 በመቶ የሃዋሳ፣ 92 በመቶ የጅማ፣ 94 በመቶ የመቀሌ እንዲሁም 91 በመቶ የነቀምት ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአመራር ጊዜያቸው ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ ብለው የሚያምኑ ሲሆን ከድሬደዋ ነዋሪዎች 71 በመቶ ያህሉ ለውጥ እንደሚያመጡ ያምናሉ ብሏል- “የዋስ ኢንተርናሽናል” ጥናት፡፡
ከወንዶች ይልቅ ሴቶች በ4 እጅ በዶ/ር አብይ የለውጥ ተስፋ የሰነቁ ሲሆን በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በጠ/ሚኒስትሩ በእጅጉ ተስፋ አድርገዋል ይላል- የጥናት ሪፖርቱ።

Read 8282 times