Monday, 21 May 2018 00:00

“ውሸት ደግ ነበር፣ ጣጣው ባልነበር”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እሱና እሷ የሆነ ግብዣ ተጠርተዋል፡፡ እሷ አንድ ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ መስታወት ፊት አጥፍታለች፡፡ (እኔ የምለው… “በሚቀጥሉት አራት ወራት በምንም አይነት በመስታወት ራስሽን መመልከት አትችይም፣” የሚባል አይነት ማዕቀብ ነገር ቢኖር፤ የ‘ፔይን ኪለር’ ኪኒኖች ገበያ አዲስ ክብረ ወሰን የሚያስመዘግብ አይመስላችሁም! አንዳንዴ እኮ… አለ አይደል …ራስን ማስዋብ ሳይሆን በአጉሊ መነጽር የሆነ የላቦራቶሪ ምርምር የሚካሄድ ነው የሚመስለው!) እና እሷ ለጥረቷ ውጤት---ማረጋገጫ ትፈልጋለች፡፡
“እንዴት ነው?”
“ምኑ?”
“ምኑ ይላል እንዴ! እንዴት ነው… አምሮብኛል ወይ?”
ከባድ ጥያቄ ነው …በጣም ከባድ ጥያቄ፡፡ የሚሰጠው መልስ፣ ከስንት ዘመን ወዳጅ ሊያቆራርጥ የሚችል ከባድ ጥያቄ! አሀ… እሷ ስትዋብ  ያን ሁሉ ‘ክሬዲት አወር’ (ቂ…ቂ…ቂ…) አጥፍታ----ውጤት ትፈልጋለቻ! “ይሄ ልብስ ከአንቺ ጋር አይሄድም…”፣ “ፓውደሩን አበዛሽው--…”፣ “ጉንጭሽ እኮ ወፍጮ ቤት የትርፍ ጊዜ ሥራ የጀመርሽ ነው ያስመሰለሽ!” አይነት ነገሮች መስማት አትፈለግማ! ግን ደግሞ ሰውየው ሲያያት ምንም ነገሯ አልጣመውም፡፡ እናማ…እውነተኛ ስሜትን መነጋገሩ ይሻላል ወይስ ወዳጅነትን ማቆየቱ? “እዚህ ላይ ነው ችግሩ…” የሚባለው ይሄኔ ነው፡፡
እናማ…“ምን ጥያቄ ያስፈልገዋል! አንቺ… ስትለባብሺ እንዴት ነው የማታምሪው!…” ምናምን ይባላል፡፡ በቃ በዚህ ብቻ  አስተያየት ሰጪው፣ የፈለገ የሉሲፈርን ዙፋን መውረስ እየሞከረ ያለ ቢሆንም… “እሱ እኮ እንዴት አይነት ጥሩ ሰው መሰላችሁ!” አይነት ክብር ያገኛል፡፡ እናማ..የመዋሸቱ ነገር ጥቅሙ የጋራ ነው፡፡ አለበለዛ “‘ቀለም ባትቀቡኝ በጋዜጣ እንኳን ሸፋፍኑኝ የሚል አሮጌ ግድግዳ ትመስያለሽ፣” ምናምን ቢላት አባል ለሆነበት እድር ሁሉ የሚበቃ እርግማን ይወርድበታል፡፡
የምር ግን… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምንም ልባችን ባይፈቅድ እንኳን አሪፍ፣ አሪፍ ቅጽሎች እየደረደርን ማወደስ፣ የ‘አብሮ መኖር’ ግዴታ ሆኗል፡፡ ጥያቄዎች የሚጠየቁት የሌላውን እውነተኛ አስተያየት ለመስማት ሳይሆን፣ የሌላውን ውዳሴ ለማግኘት ሆኗል፡፡
“ውሸት ደግ ነበር፣ ጣጣው ባልነበር፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡ አሁን ጣጣ የሚያመጣው እውነት ሆኖ ነው የተቸገርነው፡፡  
ሰው ቤት በሆነ ምክንያት እንጋበዛለን፡፡ ምግብም ይቀርብልናል፡፡ ገና አንዷን ከመጉረሳችን በፊት በጋባዦቻችን ሚጢጢዬ ገለጻ ይደረግልናል። “በፈረንሳይ ዋይንና በስፔይን ኦሊቭ ኦይል የተሠራ ግሩም ጥብስ ነው፤ ብሉ!” ይባላል፡፡ ልጄ… አይደለም በፈረንሳይ ዋይን ተጠብሶ፣ በጎጃም በረንዳ ዳግም አረቄ ቢዘፈዘፍም ዘንድሮ አይደለም ጥብስ…ስጋ የሚሉት ‘አልሚ ምግብ’ ምናምን ተገኝቶ ነው! መብላት እንጀምራለን…ወይም፣ መጉረስ እንጀምራለን፡፡ ገመና የመጀመሪያውን ዙር ወደሚሄድበት ሳንልከው የ‘ህዝብ አስተያየት’ ስብሰባው ይጀመራል፡፡
“እህ ታዲያስ፣ ጥብሱ ከሽ፣ ከሽ ሲል ድምጹ ራሱ ደስ አይልም?”
ከሽ፣ ከሽ! ከሽም የለ፣ ኮሽም የለ ስጋው አፋችሁ ውስጥ ያለው እድሜ እጥፍ በእጥፍ ይረዝማል። እንዴት ይዋጥ! የምር ግን…ምንም ቢሆን እንደዛ ልስልስ የሆነውን የየዋሁን ከብት ስጋ፣ እንዲህ ካቦ ብረት ምናምን ነገር ማድረግ ራሱ የተለየ ጥበብ የሚጠይቅ ሳይሆን አይቀርም! “እኔ ትዝ ይለኛል፣ እንደዚህ አፌ ውስጥ ቅቤ የሚሆን ጥብስ የበላሁት---አንድ ጊዜ ሼራተን የሀብታሞች ሰርግ ላይ ነው” እንላለን፡፡ የሚፈለግብን ይሄ ነዋ! የሚጠበቅብን ይኸው ነዋ!
አለበለዛ… “ከብቱ ምንስ ቢሞት ነፍሱ እንኳን አትታዘባችሁም!” ወይንም… “የሆነ ሰው ስጋ እርም ብሎ እንዲተው ከተፈለገ የዚህ አይነት ጥብስ ማብላት ነው” ማለት ግን አስተያየት መስጠት ሳይሆን የሆነ ማካሮቭ ምናምን በራስ ላይ እንደመደገን ነው፡፡
የምር ግን ጥያቄዎቹ እኮ ሲቀርቡ ከእነ መልሳቸው ነው፡፡ “ቆንጆ ምንቸት አብሽ አይደለም?!” ማለት ጥያቄ ሳይሆን “ያልኩትን ድገም!» አይነት ነገር ነው…ያውም ከተጨማሪ ቅጽሎች ጋር፡፡
“ውሸት ደግ ነበር፣ ጣጣው ባልነበር፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡ አሁን ጣጣ የሚያመጣው፣ እውነት ሆኖ ነው የተቸገርነው፡፡
እግረ መንገድ ይቺን ስሙኝማ…
ሦስት ጥንዶች በአንድ ጠረዼዛ ዙሪያ እየተመገቡ ነው፡፡ አሜሪካዊው ለሚስቱ እንዲህ አላት… “የእኔ ማር፣ እስቲ ማሩን አቀብይኝ--” አቀበለችው፡፡
እንግሊዛዊው ለሚስቱ እንዲህ አላት… “የእኔ ስኳር፣ እስቲ ስኳሩን አቀብይኝ” አቀበለችው፡፡
ሦስተኛው ባል ሚስቱን ምን ቢላት ጥሩ ነው፣ “አንቺ ደደብ፣ ጥብሱን አቀብይኝ!” ይሄኛው ሰውዬ፣ ከየትኛው የዓለም ክፍል እንደሆነ ገና እየተጣራ ነው፡፡
“እስካሁን የት ነው ያመሸኸው?”
“ከጓደኞቼ ጋር ነበርኩ”
“እነማን?”
“በቃ ከጓደኞቼ ጋር አንድ ሁለት ቢራ ስል ነበር አልኩሽ፣ የስም ዝርዝር ማቅረብ አለብኝ እንዴ!”
“ምነው ታዲያ ዓይኖችህ እንዲህ የሲኖትራክ ረጅም መብራት መሰሉ! ይሄ ሁሉ በሁለት ቢራ ብቻ ነው!” አሀ…እሷ ዓይኖች እንዲህ ስምንት መቶ ሻማ ምናምን የሚሆኑት፣ ከምን በኋላ እንደሆነ ታውቃለቻ!
የምር ግን… ውሸት መናገር የማያሳፍርበት ደረጃ የደረሰ አይመስላችሁም፡፡ ግለሰባዊ ብቻ ሳይሆን ተቋማዊም እየሆነ ነው እኮ! ከታችኛዋ ጫፍ እስከ ላይኛው ጫፍ እየተካንንበት ነው፡፡ 
“ውሸት ደግ ነበር፣ ጣጣው ባልነበር፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡ አሁን ጣጣ የሚያመጣው እውነት ሆኖ ነው የተቸገርነው፡፡
እግረ መንገድ ይቺን ስሙኝ…ሁለት ሰዎች በየአገሮቻቸው ያሉ ትያትር ቤቶች ምን ያህል ስፋት እንዳላቸው እያወሩ ነው፡፡
“እኛ አገር ትያትር ቤቶች ትልቅ ከመሆናቸው የተነሳ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ልታካሂድባቸው ትችላለህ፡”
“አንተ እንደ እሱ ትላለህ፣ እኛ አገር ትያትር ቤቶች ትልቅ ከመሆናቸው የተነሳ ኋላ መቀመጫ ላይ ሆነህ የወረወርከው እንቁላል፣ መድረክ ሳይደርስ መሀል ላይ ይፍለፈላል” ከዋሹ አይቀር እንዲህ ነው!
ታዲያላችሁ …እየዋሸን እንደሆንን እኮ እንተዋወቃለን…በሆዳችን “ኸረ በእናትህ ቁልቁለት ላይ በአምስተኛ ማርሽ አንደረደርከው!” እያልን…አለ አይደል… ፊት ለፊት ግን  “እውነትህን ነው…” “ልክ ብለሻል” እንባባላለን፡፡
እናማ…ለማህበራዊ ኑሮ ስንል እንሸመጥጣለን፤ “እሱ ሀቀኛ ነው፣ እንዲች ብሎ ውሸት ነገር ከአንደበቱ አይወጣም” ምናምን ብሎ ነገር ጊዜው እያለፈበት ይመስላል፡፡ ሀቀኝነት ምናምን ብሎ ነገር የሞኝነት አይነት እየሆነ ነው፡፡
“አለቃህ ማስጠንቀቂያ ሰጠህ የሚሉት እውነት ነው?”
“አዎ፣ የቃል ማስጠንቀቂያ ሰጠኝ”
“ምን አድርገህ ነው?”
“አርባ አምስት ደቂቃ ያህል ስላረፈድኩ…ተኝቼ ነበር”
“ምን ምክንያት ሰጠኸው?”
“እንቅልፍ ወሰደኝና ሰዓቱን አላየሁትም አልኩት”
“አንተ ያምሀል እንዴ! አውቶብስ ጠፋ፣ ወይ የምሄድበት ሚኒባስ መንገድ ላይ ተበላሸ አትለውም… ምን አይነቱ ሞኝ ነህ!”
አንዳንድ ማስታወቂያዎቻችንን ማመን የተውነው ወደን አይደለም፡፡ አሁን፣ አሁን ከተራና የጎንዮሽ ጣጣ ከሌለው ማጋነን እያለፉ አንዳንድ ነገሮቻቸው ቅልጥ ወዳሉ ውሸቶች ስለሚመስሉን ነው፡፡ በማስታወቂያ የተነገርንን አገለግሎት የማናገኝ ከሆነ፣ “ሀያ አራት ሰዓት አገልገሎት እሰጣለሁ” ያለው ተቋም፤ ሁለት ሰዓት እንኳን ሳይሞላ መብራት አጠፋፍቶ የግቢውን በር የሚከረችም ከሆነ፣ ጣት ያስቆረጥማል የተባልነው ምግብ ጭራሽ ሽቅብ ሊለን የሚሞከር ከሆነ፣ እንዴት ብለን እንመን!
ስሙኝማ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አንዳንድ ጊዜ የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ስትከታተሉ ‘ስታንድአፕ ኮሜዲ’ የምታዩ አይመስላችሁም!? አንዳንዶቹ  ውሸቱን እንደ ጉድ ያንደረድሩት የለ እንዴ! አንዳንድ ፕሬስ መግለጫዎች ላይ እንደ ጉድ ያንደረድሩት የለ እንዴ!
“ውሸት ደግ ነበር፣ ጣጣው ባልነበር፣” የሚሏት ነገር አለች፡፡ አሁን ጣጣ የሚያመጣው እውነት ሆኖ ነው የተቸገርነው፡፡
 ውሸት ‘ጣጣ’ የሚያመጣበት ዘመን ሲመጣ፣ ምናልባት እየበዙ ከሄዱት ሽንቁሮቻቸውን የተወሰኑትን መድፈን እንችል ይሆናል፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 5669 times