Monday, 21 May 2018 00:00

ቁጥር 2 የአገር ህልውና አደጋ እና የ290 ሚሊዮን ብር ብክነት!

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(4 votes)

• ኢንቨስትመንትን በጠላትነት የመፈረጅና የማጥቃት ዘመቻ! ከህግ በላይ የመሆን “ልዩ መብት”!
• ስንዴና ዳቦ በተቸገረ አገር፣ የእርሻ መሬት እንዳይስፋፋ ዘመቻ የሚያካሂድ ሚኒስቴር አለን።
• ከሩብ ቢሊዮን ብር በላይ ብክነት! የ290 ሚሊዮን ብር ኪሳራ - መንግስት አለቦታው አለስራው።
^ በ675 ብር ሂሳብ፣ ስንዴ ለማቅረብ በጨረታ ያሸነፈ ኩባንያ፣ ውጤቱ በመንግስት ተሰረዘበት። ባይሰረዝ ኖሮ፣ መንግስት፣ ሁለት ሚ ኩንታል ስንዴ፣ በ1,350,000,000 ብር መግዛት ይችል ነበር።
^ በ820 ብር ሂሳብ፣ ያለጨረታ ስንዴ እንዲያቀርብ በመንግስት ተለምኖ ኩባንያው እሺ ብሏል። አሁን፣… ሁለት ሚ ኩንታል ስንዴ ለመግዛት፣ መንግስት 1,640,000,000 ብር ለመክፈል ወስኗል።


    በተንዛዛ የመንግስት መስሪያ ቤት ዝርክርክነት ሳቢያ፣ የስንዴ ጨረታዎች በተደጋጋሚ እየተሰረዙ… ኪሳራው እጥፍ ድርብ ሆኗል። አንደኛ፣ የስንዴና የዳቦ እጥረት ተባብሷል። በመንግስት ቁጥጥርና ድጎማ ለዓመታት ጤና ማጣቱ ሳያንስ ማለት ነው። ሁለተኛ፣ በ290 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ፣ የድሃ አገር ሃብት እንደዘበት በከንቱ ቀልጧል። ይሄ ግን፣ የብክነቱ ግማሽ ነው። በተመሳሳይ ዝርክርክነት ሳቢያ፣ ተጨማሪ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ለመግዛት፣ ኪሳራው ወደ 580 ሚሊዮን ብር ሲደርስ ይታያችሁ - ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ።
 
መንግስት አለቦታው አለስራው ሲገባ፣ ሁሌም ብክነት አለ። ግን ኪሳራው የማን ነው?
እንደወትሮው፣… ኪሳራው፣ በአምራች ታክስ ከፋይ ዜጎች ላይ ነው! ከዜጎች የተሰበሰበውን ታክስ ነው መንግስት የሚያባክነው - “ድጎማ” እያለ። መንግስት ወደ ቢዝነስ ሲገባ፣ በተፈጥሮው አባካኝ ነው።
በዚህ ከንቱ ብክነት ሳቢያ፣ ከኪሱ አንዲት ሳንቲም የምትጎድልበት ባለስልጣንና ቢሮክራት ይኖራል? አይኖርም። ከኪሱ ምንም አይጎድልበትም፤ ለኪሱ ምንም አይጨመርለትም (ብክነት ፈጠረ አልፈጠረ)።
መንግስት አለቦታው አለስራው፣ የስንዴ ቢዝነስ ውስጥ ሲገባ፣ የዋጋ ተመን አወጣለሁ፣ ኮታ እሰፍራለሁ እያለ አላስፈላጊና ጎጂ ቁጥጥሮችን ሲፈለፍል፣… መዝረክረኩና መንዛዛቱ፣ በዓመቱ ድጎማ እየመደበ ማባከኑና መክሰሩ አይቀሬ ነው። … ጉዳቱ፣… የስንዴና የዳቦ እጥረትን ማባባሱ፣ ዝርክርክነትን ብክነትን ማስፋፋቱ ብቻ አይደለም። የስንዴ ምርትንም ያዳክማል። አብዛኞቹ ዱቄት ፋብሪካዎችና ዳቦ ቤቶች፣ በገበያ ዋጋ ከገበሬ ስንዴ መግዛት አይችሉም - ከመንግስት ብቻ ነው። በገበያ ዋጋ፣ ዱቄትና ዳቦ መሸጥ አይችሉም - መንግስት ተመን ብቻ። የስንዴ ገበያና ምርትን፣ አሳስሮ ቆላልፎታል። መንግስት ራሱም፣ ያለ ብክነት በቂ ስንዴ ማቅረብ አይችልም። ስንዴ አምራቾች በገበያ እንዳይተማመኑ አድርጓቸዋል።
የዛሬ ችግሮች ድንገት የበቀሉ አይደሉም፤ በትናንት ቀሽም “መፍትሄዎች” ሳቢያ እየተባባሱ የመጡ መዘዞች ናቸው። ዛሬ ለ ነገስ? የዛሬ “መፍትሄዎች”፣… ቀሽም ከሆኑም፣… ነገን ያቃውሳሉ። የነገ ከባድ እዳ ይሆናሉ። ችግርን በማባባስ ለነገ የመዘዞች ናዳ ያስከትላሉ።
እና የዛሬ “መፍትሄዎቻችስ” ምንድናቸው? ቀሽም፣ የማይፈይዱና የማይዘልቁ ናቸው? ሁነኛ፣ የሚያዋጡና የሚያዛልቁ ናቸው?
አሳዛኙ ነገር፣… ብዙም ተስፋ አይታይም።
መፍትሄው፣ ምርትን ማስፋፋት ነው ይላል - የግብርና ሚኒስቴር። የስንዴ እጥረትንና የውጭ ምንዛሬ ችግርን ለማቃለል ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ የሚቻለው፣ የእርሻ ምርትን በማስፋፋትና በማሳደግ ነው ብለዋል - የሚኒስቴሩ የስራ ሃላፊ - ሰሞኑን ከየክልሉ የመንግስት ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በተደረገው ውይይት።
ለእርሻ ሊውል የሚችል ከ70 ሚሊዮን ሄክታር ቢኖርም፣ እስካሁን ለእርሻ ስራ የዋለው 13 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ እንደሆነ ገልፀዋል ሃላፊው። የእርሻ መሬት መስፋፋት አለበት፤ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚሻሻል ዘመናዊ የመስኖና የእርሻ ስራ፣ ዋነኛ የእርሻ ትኩረታችን መሆን ይኖርበታል ብለዋል - የስራ ሃላፊው። ዘመናዊ እርሻ ውጤታማ እንደሆነ በአፋር ክልል በ700 ሄክታር ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል፤ በሄክታር 35 ኩንታል ስንዴ ተመርቷል ሲሉም ገልፀዋል።
አሃ!... የተንዳሆ እርሻ ማለታቸው ነው! ዘመናዊና ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎችን የሚስፋፉት፣… በተንዳሆ እንደተሞከረው፣ በመንግስት እንዲሆን ነው የታሰበው? የመንግስት ቢዝነስ መጨረሻው እንደማያምር አሁንም አልገባቸውም? ውድቀቱ ስንት ጊዜ ሲደጋገም ነው እውነታውን ለመገንዘብ ፈቃደኛ የሚሆኑት? ብክነቱ ለስንት ዓመት፣ በስንት ቢሊዮን ብር፣ በስንት መቶ ቢሊዮን ብር ሲቆለል ነው፣ ኪሳራውንና መዘዙን በግልፅ ለማየት የሚፈቅዱት? እስከ መቼ ነው፣ እውነታውን ላለማየትና ላለመገንዘብ አይናቸውን በመጨፈን ለማምለጥ የሚሞክሩት?
እሺ! “ዘመናዊና ሰፋፊ የመስኖ እርሻዎች፣ በመንግስት ብቻ የተያዙ ይሆናሉ” አልተባለም። የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ የግል ኢንቨስትመንትም በዘመናዊ እርሻ ላይ አይሳተፉም አልተባለም። ጥሩ። ግን፣ የግል ኢንቨስትመንት በዘመናዊ እርሻ ላይ እንዲስፋፋ፣ እንቅፋቶችን ለማስወገድ በትኩረት እንሰራለን ተብሎም በግልፅ አልተነገረም።
ቢያንስ ቢያንስ፣ የስንዴ እጥረትን ለማስወገድም በአጠቃላይ ኢኮኖሚን እንዲያድግና የዜጎች ኑሮ እንዲሻሻል፣ የእርሻ መሬት መስፋፋት እንዳለበት መናገር አንድ ቁምነገር ነው።
ግን የባሰ አለ።

የእርሻ መሬት እንዳይስፋፋ ዘመቻ የሚያካሂድ ሚኒስቴራችን
ረሃብና ድህነት በከፋበት አገር፣… የስንዴና የዳቦ እጦት በተባባሰበት አገር ውስጥ፣ የእርሻ መሬት እንዳይስፋፋ፣ በይፋና በአደባባይ እቅድ አውጥቶ፣ በጀት ተመድቦለት፣ ነጋ ጠባ ስብሰባና ግብዣ እየደገሰ፣ የእርሻ መሬት እንዳይስፋፋ ዘመቻ እያካሄደ፣ በዚህም ስኬታማ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነ የሚያውጅ ሚኒስቴር አለላችሁ። ሰሞኑንም እንደ ጀብድ መግለጫ ሲሰጥ ሰንብቷል።
ድሮ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ይባል የነበረ፣… ዛሬ ማዕረግና ሹመት ተጨምሮለት፣ የምናምንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ተብሏል። የቅዠት አለም ውስጥ፣ አልያም በማያባራ ስካር የሚሾር ምናባዊ ዓለም ውስጥ የሚፈነጭ ተቋም ነው የሚመስለው። የመቶ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የኑሮ ችግር፣ የምግብ እጦት፣ የረሃብ፣ የስራ አጥነት ችግር… ምናምን የሌለበት የቅዠት ወይም የስካር ዓለም በምናብ እንማሰብ ነው።
እናማ፣ የሚኒስቴሩ ዋና አላማ፣… ከመቶ ዓመት በኋላ የሚኖር የአለም ሙቀትን ለመቆጣጠር፣ የሰሜን ዋልታ የበረዶ ግግር እንዲጨምር፣… የኢትዮጵያ የከብት ቁጥርን መቀነስ፣ የእርሻ መሬት እንዳፈይስፋፋ መግታት ነው።  የሆንኮንግ የመንገድ ዳር መብራት ከልክ በላይ መድመቅ፣ እና ቁጥር ስፍር የሌላቸው ከኢትዮጵያውያን ኑሮ ጋር ቅንጣት ተጨባጭ ትስስር የሌላቸው ወገኛ ፈሊጦች ናቸው።
200 ከሚደርሱ አገራት መካከል፣ በኢንዱስትሪ ወደኋላ የቀሩ፣ ነዳጅ የመጠቀም አቅማቸው የደከመና የካርቦን ልቀት የሌላቸው 10 አገራት ውስጥ የምትመደብ ድሃ አገር ውስጥ ነን ያለነው። ሚኒስቴራችን ግን፣ የዓለም የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ፣ የኢትዮጵያ እንጭጭ ፋብሪካዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና እርምጃ በመውሰድ ከነጭራሹ እንዲሞቱ ማድረግ፣… የእርሻ መሬት እንዳይስፋፋ መግታት የሚል አላማ ሲይዝ፣ ሌላ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል? እንዲህ አይነቱ አሳፋሪና የተሳከረበት ፀረ እድገትና ፀረ ዜጎች ሃሳቦች የበረከቱበት ተቋም፣… ከዜጎች በተሰበሰበ ታክስ አማካኝነት፣ በጀት ይመደብለታል። ይሄ ሚኒስቴር እንዲፈርስ ለመወሰን፣ ለአንድ ደቂቃም ቢሆን የሚያመነቱበት አይነት አይደለም።
በውጭ ኤንጂኦዎችና ተቋማት የፈንድና የፐርዳይም ክፍያ ዙሪያ በሚጎነጎኑ እልፍ አእላፍ ፀረ እድገት ዘመቻዎች፣ የእርሻ መሬት እንዳይስፋፋ አንድ ሚኒስቴር እያሰናከለ፣ በሌላ ሚኒስቴር ደግሞ፣ የዜጎች ኑሮ እንዲሻሻል የእርሻ መሬት መስፋፋት አለበት እያሉ መደስኮር፣… ከቀውስና ከአደጋ አያድንም።
በተግባር የምናየውም፣ የእርሻ መሬትና ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ አይደለም። በጅምላ፣ የመሬት ወረራ እየተባለ ሲወገዝ፣ የግል ኢንቨስትመንት እንደጠላት የጥቃት ኢላማ ሲሆን እያየን አይደለም?
ኢንቨስትመንትን በጠላትነት መፈረጅ፣… ከህግ በላይ የመሆን “ልዩ መብት”
ታዝባችሁ ከሆነ፣ ከ2002 ዓ.ም ወዲህ፣ “የግል ኢንቨስትመንት”፣ “ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት” የሚሉ አገላለፆች እየጠፉና እየቀሩ፣ ቀስ በቀስ ተመናምነዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን፣ የግል ኢንቨስትመንትን እንደ ጠላት የመፈረጅ ጥንታዊ ነባር በሽታ እንደ አዲስ ፈሊጥ እየተዘወተረ፣ የግል ንብረትን የጥቃት ኢላማ የማድረግ ዘመቻ እየተበራከተ መጥቷል። እንዲያውም፣ ኢንቨስትመንትን በጠላትነት መፈረጅ፣… በአንዳች ተዓምር፣ “የሰውን ህይወትና ንብረትን የማጥቃት፣ ከህግ በላይ የመሆን ልዩ መብት” እንደማግኘት እየተቆጠረ ነው። ይሄ፣… ያለጥርጥር፣ የጥፋት ቁልቁለት ነው - ወደ ገደል የሚያስገባ። ለምን? ኢኮኖሚን ይበልጥ ስለሚያቃውስ፣ የሚሊዮኖችን ኑሮ ይባስ ስለሚያናጋ ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ፣ ህግ አክባሪና ጨዋ የሆነውን አብዛኛውን ዜጋ ለጉዳት የሚዳርጉ በርካታ መዘዞችንም ያስከትላል። ህግ የበላይነት ይልቅ፣ ከህግ በላይ የመሆን ስርዓት አልበኝነትን፣ በሰላም ፋንታ ስጋትን፣ በነፃነት ምትክ ፍርሃትን ያስፋፋል። እንዲህ አይነት ቀውሶችና የጥፋት መንገዶች፣… በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት፣… በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦዘው በምን ያህል ፍጥነት ከቁጥጥር ውጭ ወደለየለት ትርምስ ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ፣… ባለፉት ሦስት ዓመታት ታዝበናል።
በአጭሩ፣ የግል ኢንቨስትመንትን እንደጠላት፣ የግል ንብረትን እንደ ኢላማ መፈረጅ፣… ክፉ የጥፋት ቁልቁለት ነው። ነገር ግን፣ ከዚህ የጥፋት ቁልቁለት ለመዳን፣ ያን ያህልም ጥረት ሲደረግ አይታይም።   
እንዲያውም፣ ከነአካቴው፣ በእርሻም ሆነ በኢንዱስትሪ፣ “ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት”፣… የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ተዘንግቷል ማለት ይቻላል። ምን ይሄ ብቻ! በተቃራኒው፣… በአንድ በኩል የመንግስት ቢዝነስ እንደ ዋና ነቀርሳ እየገነነና ብክነቱ እያበጠ፣… በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ኢንቨስትመንት” የሚለው ቃል እየተጠላ፣ በጠላትነት ተፈርጆም የጥቃት ኢላማ እየሆነ፣ የግል ቢዝነስ በመንግስት ጫናዎች እየተደፈጠጠ መጥቷል። ይሄ፣ እየጦዘ የመጣ የቅይጥ ኢኮኖሚ ጉራንጉር፣… በጣም አደገኛ ነው። ቁጥር 2 የአገር ህልውና አደጋ! ይህንን ለመገንዘብ ምን ያህል ጥፋት ማየት፣ ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ ያስፈልግ ይሆን?
ዘረኝነትን የሚያስፋፋ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ፣ የአገራችን ቁጥር 1 አደጋ እንደሆነ ለመገንዘብ ስንት አመት ፈጀባቸው? ከብዙ አመታት አደገኛ ጉዞ በኋላ፣ በጥፋት ቁልቁለት የገደል አፋፍ ላይ ከደረስን በኋላ ነው ኢህአዴግ  አደጋውን ለማየት ፈቃደኛ የሆነው። የአደጋውን መጠንና መፍትሄውን በአግባቡ ተገንዝቦታል ወይ የሚለው ጥያቄ እስካሁን እርግጠኛ ምላሽ ባያገኝም።
ቁጥር 2 የአገር ህልውና አደጋውን ለመገንዘብስ፣ ምን ያህል ጥፋት ማየት፣ ምን ያህል ጊዜ መጠበቅ ያስፈልግ ይሆን?


Read 4870 times