Monday, 21 May 2018 00:00

ከጎንደር እስከ ሎንደን (‹‹Empire and Revolution››)

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

 ይህን የመጽሐፍ ዳሰሳ የሚያደናቅፉ ሁለት ነገሮች ገጥመውኛል፡፡ አንደኛው ኤልፓ ነው፡፡ ሁለተኛው ካርል ማርክስ ነው፡፡ የመብራቱ ጉዳይ ግልጽ ነው፡፡ ጥያቄ የሚሆነው የካርል ማርክስ ነገር ነው፡፡ ማርክስን ከመቃብር ምን አወጣው? ካላችሁ፤ መልሱ ካርል እንጂ ማርክስ መቃብር አልገባም የሚል ነው፡፡ የምዕራቡን ዓለም (አሜሪካን)  የፋይናንስ ቀውስ ከገጠማቸው ከ2008 ዓ.ም ወዲህ የማርክስ ስም እየተነሳ ነው። በህይወት ሳለ፤ በየዕለቱ በሰላይ እና በፖሊስ ታሳድደው የነበረችው እንግሊዝም ስሙን ታነሳሳለች፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማርክስን በደንብ ማጥናት አለብን እያሉ ነው፡፡ በቅርቡም  የማርክስን ህይወት የሚዘክር ቴአትር በሎንዶን ይታይ ነበር፡፡ ታዋቂ የምዕራቡ ዓለም አቀፍ ጋዜጦች እና ታዋቂ የወልስትሪት ኢኮኖሚስቶች ሥሙን ደጋግመው ያነሱታል፡፡ ሐሳቦቹን መልስው ማመንዠክ ጀምረዋል፡፡
አንዳንዶች ‹‹ምርጥ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ሐኪም›› የሚሉት ካርል ማርክስ፤ ባለፈው ሰሞን ሁለት መቶኛ ዓመት የልደት በዓሉ በትውልድ ከተማው ተከብሯል። የማርክስ የትውልድ ከተማ፤ አንዱ የቱሪስቶች ቀልብ መሳቢያዋ ማርክስ ነው፡፡ ጎዳናዎችዋ የማርክስን ምስል በእንጨት እና በድንጋይ እየቀረጸች ትዋብበታለች፡፡ ህጻን ልጅ ሳይቀር ሊለየው የሚችለው የማርክስ ገጽ፤ በትውልድ ከተማው ጎዳናዎች በተተከሉ የትራፊክ መብራቶች ላይ ጭምር ይታያል፡፡ ምስሉ በየትኛው የትራፊክ መብራት ቀለም ይታያል የሚል ጥያቄ ሊነሳ አይችልም - የማርክስን ምስል የምታዩት ቀዩ መብራት ሲበራ ነው፡፡
በልደት በዓሉ ከፈላስፋው ጋር የተያያዙ የተለያዩ ቁሳቁሶች ለገበያ ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ ቁሳቁሶች መካከል በማርክስ የተሰየመ ወይን አንዱ ነው፡፡ አሁንም አጠራጣሪ ሊሆን አይችልም - በማርክስ የተሰየመው ወይን ቀይ ነው። የትውልድ ከተማው የእርሱ መኖሪያ የነበረውን ቤት በደንብ ጠብቃ ይዛ ለእንግዶች ታስጎበኛለች፡፡ ማርክስ የማሻሻጥን ነገር አይወድም፡፡ ግን የትውልድ ከተማው ንግድ አድርጋው ሰንብታለች።
እኔም ወቅታዊ አጀንዳዎችን ማንሳት በመፈለጌ፤ የማርክስን ሁለት መቶኛ ዓመት ልደት የሚዘክር ጽሑፍ ለመጻፍ አስቤ ነበር፡፡ በመጨረሻ ከማርክስ ይልቅ ወደ ሐገሬ ልጅ አደላሁ፡፡ የምታወራው ስለ የትኛው መጽሐፍ ነው? የማንስ መጽሐፍ ነው? መጽሐፉስ ምን አደረገህ? ካለችሁኝ፤
መጽሐፉ፤ ‹‹Empire and Revolution››
ደራሲው፤ ወርቁ ገበየሁ ላቀው
አታሚ፤ ፋር ኢስት ትሬዲንግ
የህትመት ዘመን፤  ሚያዚያ 2010
ገጽ፤ 344
ዋጋ፤ 142 (ብር)
ወርቁ ገበየሁ እና ካርል ማርክስ ዝምድና አላቸው። ማርክስ የርዕዮተ ዓለም አባቱ ነው፡፡ ስለዚህ ማርክስ በመዘከሩ፤ ‹‹በእርሱ ቤት›› መጥቶ ይህን ያህል ሥፍራ በመያዙ ቅር የሚለው አይመስለኝም፡፡ አስቀድሞም የማርክስን ነገር አያይዤ ለማንሳት የደፈርኩት በዚሁ ስሜት ነው - ዝምድናቸው አደፋፍሮኝ፡፡
በተረፈ መብራቱ ስሜቴን ከማወክ ጅምሮ ወሰነ - ዳሰሳዬንም እንዳጠብ አድርጎኛል፡፡ ትኩረቴን በመግቢያው እና በመጀመሪያዎቹ 60 ገጾች ብቻ ለማድረግ አስገድዶኛል። ሆኖም ስድሳ ገጽ ብዬ የወሰንኩት በቁጥር አይደለም፡፡ በይዘት ነው። የመጽሐፉ የመጀመሪያ ምዕራፎች ወይም ተረኮች በወርቁ ገበየሁ የልጅነት ዘመን ጉዳዮች የሚያተኩሩ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ የአብዮት ዘመን ታሪኮች የሚነበቡባቸው ተረኮች ናቸው፡፡
የመጽሐፉ አደረጃጀት ዳሰሳውን በዚህ መልክ ለመክፈል የሚያስችል ነው፡፡ እንዲያውም ሌላ መክፈያ ያለው አይመስለኝም፡፡ ለምርመራ የተነሳ ሃያሲ በቀላሉ ሊያገኘው የሚችለው የመጽሐፉ ብልት ይኸው ነው። ከመጽሐፉ ርዕስ በመነሳት ‹‹የግዛተ አጼ›› (‹‹Empire) እና የአብዮት (Revolution››) ጉዳዮች ብሎ መክፈል እንደሚቻል የሚያስብ ሰው ይኖራል፡፡ ነገር ግን የመጽሐፉ የይዘት በዚህ ለመክፈል የሚያስችል ነገር የለውም፡፡ ስለዚህ በጠቀስኩት ሁኔታ በልጅነት ታሪክ ላይ አትኩሬ አስተያየቴን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ ስለ ሥራው አጠቃላይ ምስል የሚያስይዝ፣ አጠቃላይ አስተያየት እንደ መግቢያ አንስቼ ወደ ዳሰሳው አመራለሁ፡፡
እንደ መግቢያ
ወርቁ ገበየሁ፤ በመጽሐፉ ስለ ፋሽዝም ሲያትት፤ ‹‹ማህበረሰባዊ ውቅር (social formation) ልክ ህይወት እንዳለው አንድ ፍጡር (organism) ነው። ራሱን የሚያስተዳድር ስርዓት ያለው  እና የብቻ ህልውና ይዞ የሚኖር አንድ ሙሉ አካል ነው›› እንዳለው፤ መጽሐፍም እንዲሁ አንድ ራሱን የቻለ ህያው ፍጡር ነው፡፡ ልብ፣ ሳንባ፣ ኩላሊት ወዘተ ለየብቻ የሚጠቀሱ ሆነው ሳለ በአንድ አካል ስርዓት እንደሚገኙ፤ የመጽሐፍም ነገር እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህ የመጽሐፍ ዳሰሳ፤ የይዘት እና የቅርጽ ስምረት ምርመራ ነው፡፡ ይዘት እና ቅርጽ እንደ ባል እና ምሽት ናቸው። የሁለቱ ጋብቻ ጭብጥን ይወልዳል። ጭብጡም በመልዕክቱ መልኩ ይታወቃል፡፡ የሁለቱ ጋብቻ የሰመረ ሲሆን (እንደ አብርሃም እና ሣራ) የተደራሲ ዓይነ ህሊና እና ስሜት የሚገዛ ልጅ ይወለዳል፡፡ አንባቢን እንደ ጓደኛ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡
ቅርጽ እና ይዘት አንድም ሁለትም ናቸው - ያው እንደ ባል እና ምሽት፡፡ ሁለቱም በአንድ ጭብጥ አልጋ የሚያድሩ፤ አንድ የመልእክት አንሶላ የሚጋፈፉ ናቸው፡፡ ትዳሩ የሰመረ ወይም የተቀደሰ ጋብቻ ከሆነ፤ አንዱ አንዱን እየረዳ፤ የረቀቀውን የሚያጎላ የራቀውን የሚያቀርብ ባህርይ ይዘው አንባቢን ያስደስታሉ፡፡ ስለዚህ ሁለቱን ለያይተን የምናየው፤ በምርመራ እንጂ በኩነት ተለያይተው አይገኙም፡፡ ይዘት ነፍስ፤ ቅርጽ ሥጋ ናቸው፡፡ ከሥጋ የተለየ ነፍስ ጣዕረ መንፈስ ነው፡፡ ከነፍስ የተለየም ሥጋ ሬሳ ነው፡፡   
ቅርጽ፤ የቋንቋ አጠቃቀሙን፣ መዋቅሩን፣ የምዕራፍ አደረጃጀቱን፣ የትረካ አንጻሩን፣ ስታይሉን፣ የሽፋን መልኩን፣ የፊደል መልክ ምርጫውን፣ ሌይአውቱን፣ የህትመት ጥራቱን ሁሉ ይመለከታል፡፡ ይዘት፤ የርዕሰ ነገር ምርጫውን፣ ጭብጡን እና መልዕክቱን የሚጠቅስ ነው፡፡  እኒህ ሁለቱ በአንድ ሆነው ድርሰቱን ይሰጡናል። አንድነታቸው መልዕክቱን በሰመረ መንገድ ለተደራሲ ማድረስ ከቻለ ጥሩ ሥራ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ችግር ሲኖር ይኮላሻል፡፡ ከንቱ ድካም የሚያሰኝ ነገር ይፈጠራል። ‹‹ከተጻፈበት ወረቀት ዋጋ የሚያልፍ ዋጋ የሌለው›› የሚያሰኘውም እንዲህ ያለ ሁኔታ ነው፡፡
አሁን የምንነጋገረው ስለ ‹‹Empire and Revolution›› ነው፡፡ በቅርጽ እና በይዘት ሊነሱ የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ እዚህ ማንሳት አንችልም፡፡ ሆኖም ስለ መጽሐፉ አጠቃላይ ስእል እንዲኖረን ያህል አጠቃላይ ባህርይ በማንሳት በተመረጡ ጉዳዮች ላይ ብቻ አትኩረን እንመረምራለን። በቅርጽ ረገድ የትረካ አንጻሩን፣ የትረካ መዋቅሩን፣ የቋንቋ አጠቃቀሙን፣ ህትመቱን እናያለን። በይዘት ረገድ፤ በመጽሐፉ የተካተቱትን አንድ ሁለት ተረኮች እንመዝናለን፡፡
‹‹Empire and Revolution›› በእኔ ባይ ተራኪ የሚነገር ታሪክ ያለው፤ በግለሰባዊ የምልከታ አንጻር የኢትዮጵያን አብዮት አነሳስ፣ ሂደት እና ፍጻሜ የሚተርክ መጽሐፍ ነው፡፡ እኔ ባይ ተራኪው በሚተርከው የኢትዮጵያ አብዮት ሂደት፣ እንደ ታሪክ ነጋሪ የዳር ተመልካች ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ በሰላ የትግል ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እና ዋና ተዋናይ ነው። የአንድ ፓርቲ አባል ነው - ኢህአፓ። አባል ብቻ አይደለም፡፡ የአመራር ድርሻ የነበረው ነው፡፡ ደራሲው ራሱ ‹‹እኔ የአብዮቱ የታሪክ ፀሐፊ እና ቀጥተኛ የድርጊቱ ተሳታፊ ነኝ›› (መግቢያ፣ ገጽ 12) ይላል፡፡
በመሆኑም፤ በአንድ በኩል የአብዮቱ ሂደት ተሳታፊ በመሆኑ በዓይን ምስክርነት የሚናገር ተራኪ ነው፡፡ ይህም ለሥራው ትልቅ ግምት እንድንሰጠው የሚያደርግ ነው። በሌላ በኩል፤ ፊና ለይቶ በአንድ ጎራ የተሰለፈ ተራኪ በመሆኑ፤ በአንዳንድ ቦታዎች የሚሰጠውን ዳኝነት በጥርጣሬ ለማየት የሚገፋፋ ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህ ረገድ የሚኖረውን ጎዶሎ በመጠኑም ሊያግዘው የሚችለው የሚተረከው ታሪክ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት አለመሆኑ ነው፡፡ የፖለቲካ ወላፈኑ በርዷል፡፡ ስለዚህ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችል ምቹ ቅዝቃዜ አለ፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የታሪክም ሽሚያ ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ‹‹Empire and Revolution›› በመርህ ደረጃ ጨርሶ ነጻ ትረካ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል አይሆንም፡፡ ስለዚህ ደራሲው አንባቢን ከዚህ ዓይነት ስሜት እንዲወጣ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በመግቢያውም ሊነሳ የሚገባው አንድ ነገር ይህ ነው፡፡ ነገር ግን ትረካው በደራሲው የግል ህይወት ማዳወሪያነት የቀረበ በመሆኑ እና በአጠቃላይ የትረካው ድምጸት ጭምር የወገናዊነት ክስ ሊነሳበት የሚችልበትን በር ጠበብ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡    
ደራሲ ወርቁ ገበየሁ የአብዮቱን ታሪክ ከራሱ ህይወት ጋር አያይዞ መተረኩ እና ግለሰባዊ ሁነቶችን በመጠቀም የሚተርክ መሆኑ፤ ከወገናዊነት ክስ የጠበቀው ብቻ ሳይሆን፤ ትረካውም ለዛ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ግለሰባዊነቱ፤ የፖለቲካ ቡድኖች የሰላ ትግል ያደርጉበት የነበረ ጉዳይ የሚተርክ መሆኑን ጭምር እንድንዘነጋ ለማድረግ አግዞታል፡፡ ደራሲው ከአከራካሪ ነገሮችን ሆን ብሎ የሚርቅ ይመስላል። በገለጻው የከሳሽነት ድምጸት አይታይበትም፡፡ የሰከነ ስሜት ይዞ የሚጽፍ መሆኑ ይጎላል። ስለዚህ በወገናዊነት ያለውን መሰናክል ተሻግሮታል፡፡
ትረካው የእሳት ዳር ጨዋታ ይመስላል፡፡ የልጅነት ዘመን ህይወቱን ከማህበረሰባዊ ህይወት ጋር አጋምዶ ያወራል፡፡ በአንድ ሰው የህይወት ታሪክ ሰሐን የቀረበ የማህበረሰብ ህይወት ታሪክ ሆኗል፡፡ ይህ የትረካ ዘዴው ጠንካራ ጎኑ ነው፡፡ ወርቁ ገበየሁ፤ የራሱን የግል ህይወት የተመለከተውን ነገር፤ በእንግሊዝ ለተወለዱት ልጆቹ የመኝታ ታሪክ አድርጎ ያጫውታቸው ነበር፡፡ ልጆቹም የሚወዱት ትረካ የመጽሐፉ አካል እንዲሆን ቃል እንዳስገቡት ነግሮናል (ገጽ 12)፡፡ በመሆኑም መጽሐፉ አሁን የያዘውን ቅርጽ እንዲይዝ ልጆቹ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡
ይህም ትረካውን በማዋዛት እና ደረቁን ነገር በማለዘብ ለመተረክ አግዞታል፡፡ እንዲሁም የልጅነት ታሪኩ መግባቱ፤ ወደ ኋላ የሚገልጸው የፖለቲካ ዝንባሌው ከምን ማህጸን እንደ ተወለደ ለመጠቆም አስችሎታል፡፡ በዚህ የተነሳ የወርቁ ገበየሁ መጽሐፍ በሱ በራሱ ቃል፤ ‹‹በከፊል የእሳት ዳር ጨዋታ፤ በከፊል አድቬንቸር፤ በከፊል በእንተ - እኔ (authobiography)፤ በከፊል ታሪክ፤ በከፊል የፖለቲካ ሐቲት ሲሆን፤ በከፊል ደግሞ ምናብ እና የተውጠነጠኑ የሐሳቦች ገበታ ነው›› (ዝከ፣ 13)፡፡
የእሣት ዳር ጨዋታ አካሄድ የተከተለ አቀራረብ መምረጡ፤ አንዳንድ አውዶችን፣ ባለ ታሪኮችን እና ሁነቶችን ህይወት ሰጥቶ ለማቅረብ የሚያስችል ኪነ ጥበባዊ ሊቸንሳ እንደፈጠረለት የሚገልጸው ወርቁ፤ ይህን ሲያደርግ የእውነተኛ ታሪኩን መስመር በመልቀቅ አለመሆኑን ጠቅሷል፡፡ የትረካ ለዛ ያለው የአጻጻፍ ስልት መምረጡ፤ አልፎ አልፎ አውዱን ሳይለቁ የተያዘውን ርዕሰ ጉዳይ ለአፍታ ተወት አድርጎ፤ በተለያዩ ጉዳዮች የእርሱን አመለካከት ለመግለጽ እና ለአንባቢ ማካፈል የሚፈልጋቸውንም አንዳንድ ሐሳቦችም የመሰንዘር ዕድል ፈጥሮለታል (ዝከ፣ 15)፡፡
ወርቁ አንዳንዶች ‹‹እስካሁን ዘገየህ›› የሚል ጥያቄ እንደሚያነሱበት እና ‹‹ጨርሶ ከመቅረት ዘግይቶ መምጣቱ ይሻላል›› በሚል ስሜት የሚያውቀውን ነገር ይዞ ወደ መቃብር ላለመውረድ አርፍዶም ለመጻፍ መወሰኑን በመግቢያው ጠቅሷል፡፡ ደራሲው ታሪኩን በዚህ መልክ አደራጅቶ በማቅረብ፤ ታሪክን ለትውልድ ማስተላለፍ መቻሉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ጽፎ ከጨረሰ በኋላም ‹‹ያልተተረከ ህይወት፤ ሊኖሩት የሚገባ አይደለም›› (An unnarrated life is not worth living) የሚል ስሜት እንዲይዝ እንደሚያደርገው አልጠራጠርም፡፡
ወርቁ ገበየሁ በአብዮት ጎዳና የተመላለሰ ሰው ነው። አብዮት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት ብዙ ደም የፈሰሰበት እና የከረረ ባህርይ ያለው ነው፡፡ አንድ ትውልድን ጨርሶ የበላ አብዮት ነው፡፡ ብዙዎችን ለስደት የዳረገ አብዮት ነው፡፡ ወርቁ ገበየሁ ብዙ ነገሮች በጥድፊያ በተጓዙበት፤ በርካታ ሥር ነቀል ክንውኖች ተደራርበው በተከሰቱበት፤ የሰላ ትግል በተሄካደበት የአብዮት ጎዳና አልፎ፤ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ ሜዳ ወጥቶ፤ ሁኔታዎች ያልተጠበቀ አቅጣጫ ሲይዙ በስደት ወደ ምዕራቡ ዓለም የሄደ ሰው በመሆኑ፤ ራስን መለስ ብሎ ለማየት የሚያስችል ዕድል ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ራሱን በደንብ ለማወቅ የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ መንገድ መጻፍ ነው፡፡ ስለዚህ ወርቁ ገበየሁ ታሪኩን መጻፉ፤ በግል ‹‹ካታርኪክ›› ይሆንለታል፡፡ እንደ ማህበረሰብም ይጠቅመናል፡፡ በእውነት ‹‹ያልተተረከ ህይወት፤ ሊኖሩት የሚገባ አይደለም፡፡››
ወርቁ በአጻጻፍ ስልቱ ግልጽ ለመሆን ሞክሯል። ዣን ጃኮቢስ ሩሶ በኮንፌሽን እንዳለው፤ ‹‹ሁሉንም ሐጢያቴን በዚህ መጽሐፍ ስላሰፈርኩለት፤ ክርስቶስ ሲመጣ የእኔን ነገር በማጣራት ጊዜ አያባክንም›› ማለት ይችላል፡፡ በትረካው ህይወቱን ወለል አድርጎ አሳይቶናል፡፡ የጥጥ ፍሬ ጁስ እየጠጣ፣ ረሃብን አሸንፎ የወጣ ጀግና መሆኑን አይተናል፡፡ አንዳንዱ የህይወት ገጽ ትረካውም የሩሲያ ልቦለድ መምሰል የሚቃጣው አስደሳች ዜማ አለው፡፡
ወርቁ ገበየሁ የተወለደው ደብረ ታቦር ነው። የአራት ዓመት ልጅ ሳለ፤ አባቱ በሸፍጥ ለእስር ተዳርገው ወደ ጎንደር ሄዱ፡፡ በህጻንነቱ ከአባቱ በመለየቱ ተቸገረ። በእርሱ ግፊት፤ ጠላ ጠምቀው እና አረቄ አውጥተው እርሱን እና ሁለት ታላላቅ እህቶቹን የማሳደግ ሸክም የወደቀባቸው እናቱ ወደ ጎንደር ሄዱ፡፡ የወርቁን ለቅሶ ምክንያት አድርገው ወደ ጎንደር ለመሄድ ቢወስኑም፤ 60 ኪሜ ርቀው ለሚገኙት ባለቤታቸው ስንቅ ለማቀበል ወደዚያው ጠጋ ማለቱ እንደሚሻል ማሰባቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ጎንደር እንኮዬ መስክ ገቡ፡፡
ወርቁ እንኮዬ መስክን ውብ አድርጎ ይገልጻታል። እርሱ እና ቤተሰቦቹ አቧራ በበዛባት፤ ጋሪ በሚመላለስባት፤ እህል በሚሰጣባት፤ ባለቤት የለሽ ውሻ እና ድመት በሚርመሰመስባት፤ ለህጻናት የመጸዳጃ ሜዳ ሆና በምታገለግል አንዲት ጠባብ መንገድ፣ በግራ እና ቀኝ ተሰልፈው ከቆሙት ጠላ ቤቶች በአንዱ እየኖሩ ህይወትን ተጋፈጧት፡፡ ወርቁም ችግር እና መከራን፤ በፈገግታ እና በጽናት ማሸነፍ የሚችሉ እናቱን የፍቅር ፀሐይ እየሞቀ፣ በህይወት ጎዳና ጎዞ ቀጠለ፡፡  
የእንኮዬ መስክን ትዕይንት ገልጾ፤ አካባቢው ምን ያህል ጽዳት እንደጎደለው ተርኮ፤ ከየበሩ ፊት በሚዘረጋ የሰሌን ምንጣፍ ስለሚሰጣው ብቅል እና ጌሾ ዘርዝሮ፤ ወደ ገበያ የሚሄደው ፈረስ፣ በቅሎ፣ በሬ፣ አህያ እና በግ ሁሉ በየበራፉ ከስጦው እህል እየቀመሰ እንደሚያልፍ ያጫውተናል፡፡ በመደምደሚያው ለየት ያለ አስተያየት ያመጣል፡፡ የእንኮዬ መስክ ኑሮ፤ ለተለያዩ ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶች የሚያጋልጥ ቢሆንም፤ ትልልቆቹ ሰዎች በቀላሉ ለበሽታ የሚጋለጡ ያልሆኑት፤ ሰውነታቸው ለበሽታ አምጪ ሁኔታዎች በመጋለጥ በሽታ የመከላለል ስርዓቱን ስለሚያጠናክር መሆኑን ይገልጻል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች የድርሰቱ ጌጥ ሆነው የመጡ ብቻ አይደሉም። በግለሰብ ህይወት የማህበረሰብ ታሪክን ለማቅረብ የሚያስችለውን ሁኔታም የፈጠሩለት የትረካ ዘዴዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ገለጻዎች እና ወጣ ያሉ አስተያየቶች የትረካው ፈርጦች ናቸው፡፡
አንባቢ የወርቁን የመጻፍ ክህሎት ለመመስከር በንባቡ ብዙ መግፋት አያስፈልገውም፡፡ የወርቁ የትረካ ብቃት እና የገለጻውን ውበት ለማየት የመጀመሪያ ሁለት ተረኮቹን ማንበብ በቂው ነው፡፡ የወርቁ የመጻፍ ችሎታ፤ የአባቱን የክስ ደብዳቤ በመጻፍ መሠረት የያዘ ነው፡፡ አባቱ በክስ፣ በንግድ፣ በእስር ምክንያት ብዙ ከአጠገቡ አይኖሩም፡፡ ስለዚህ በትረካው በብዙ የምናገኛቸው እናቱን ነው፡፡ እናቱ የህይወትን መከራ እና ሸክም ሳያጉረመርሙ የሚቀበሉ፤ በችግር እና በኑሮ የጭካኔ ይዞታ የፍቅር፣ የፈገግታ፣ የደግነት፣ የሞራል ከፍታ ሐብታቸውን የማያስነጥቁ እናት መሆናቸውን አሳይቶናል፡፡ አጉራህ ጠናኝ ሳይሉ በህይወት ጎዳና በብርታት መራመድ የሚችሉ እናት መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡  
በሌላ በኩል፤ ከደብረ ታቦር ከተማ ትንሽ ወጣ ብላ ከምትገኝ እና ግራሪያ ከተባለች አንዲት የገጠር ቀበሌ የተወለዱት አባቱ፤ ከገበሬ ቤተሰብ የወጡ ቢሆንም ለግብርና ሥራ የተፈጠሩ አይደሉም፡፡ ንግድም አልሆነላቸውም፡፡ ቤተሰብ ተሰብስቦ በመሀላ በሰጣቸው ወረት ዕቃ ገዝተው ለመነገድ ቢሞክሩም፤ የቸገረው ሰው ሲገጥማቸው በዓይነት ወይም በገንዘብ ለችግረኛ እየሰጡ በተደጋጋሚ የሚከስሩ ሰው ናቸው፡፡
ወርቁ እንዲህ ያሉ ታሪኮችን ሲተርክ፤ በመሐል ስለ ማይጨው ጦርነት፤ ስለ ቼኩ ጋዜጠኛ፤ ስለ ባንዳዎች እና አርበኞች ሁኔታ፤ ህዝቡ ስለ ባላምባራስነት ሹመት ያለውን አመለካከት፤ ስለ ሙግት፤ ከሳሽ እና ተከሳሽን አቆራኝቶ አስሮ ለፍርድ ስለማቅረብ ልማድ፤ ጣሊያን ሲወጣ እዚሁ ስለቀረ አንድ ሐኪም እያነሳ ያጫውተናል፡፡
ወርቁ ከመክፈቻ ትረካው በመቀጠል የሚያነሳው ተረክ፣ የገለጻ ብቃቱ ከምን ደረጃ እንዳለ የሚመሰክር ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቃቱም ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው ምዕራፍ ሊገለጹ የማይችሉ ሁነቶችን በልዩ ብቃት ሲገልጽ የምንመለከትበት ምዕራፍ ነው። የከተማውን እና የእነርሱን ሰፈር ሁኔታ፤ የከተማውን አስተዳደር መልክ እና የአኗኗር ዘይቤውን ያሳየናል፡፡ በ1950ዎቹ 40 ሺህ ነዋሪዎችን የያዘችው እና በ1630ዎቹ የተቆረቆረችው፤ በአንድ ወቅት የሐገሪቱ መዲና በመሆን ከመቶ ዓመታት በላይ አገልግሎት የሰጠችው ጎንደር፤ የከተማ እና የገጠር የአኗኗር ዘይቤን አቀላቅላ የያዘች ከተማ መሆኗን የሚገልጸው ወርቁ ገበየሁ፤ ወደ 70 አካባቢ የሚደርሱ ቤተሰቦች የሚገኙባት የእነሱ ሰፈር እንኮዬ መስክ፤ ከገጠር ወደ ከተማ መጥተው የሚኖሩ የመጀመሪያ ትውልድ ከተሜዎች የሚኖሩባት ሰፈር መሆኗን ይነግረናል፡፡ ከመንገድ ግራ እና ቀኝ ተደርድረው ከሚታዩት ቤቶች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ጠላ እና አረቄ የሚሸጥባቸው ናቸው፡፡
በመሐል ሱቅ ወይም መኖሪያ ቤት ጣልቃ እየገባ፣ ከተደረደሩት ጠላ ቤቶች በር ፊት ለፊት የበርሚል ጉማጆች ይቀመጣሉ፡፡ ለክብቶች አተላ ማቅረቢያ ናቸው፡፡ ይህች ቀኑን ከተማ መስላ የቆየችው የእነ ወርቁ መንደር አመሻሹን ከብቶች ወደ ቤት ሲመለሱ ወደ ገጠር መንደርነት ትቀየራለች፡፡ ልጆች ይጫወቱበት የነበረው አደባባይም በበሬ፣ በላም በበግ እና በአህያ ይጥለቀለቃል፡፡
ወርቁ ከብቶቹን በደንብ ያውቃቸዋል፡፡ ከእነሱ ቤት ትይዩ ከመንገድ ማዶ ከሚገኝ አንድ ሱቅ አጠገብ ያሉትን የዕድሜ እኩዮቹን እና በሌላ ጊዜ መልኩንም ሆነ ስሙን እንኳን የማያስታውሱት ወይም በዓይናቸው ሊያዩት የማይፈቅዱት፤ በዚህ ምድር መኖሩንም ጭምር የሚዘነጉትን ጎረምሶች ትኩረት የሚያገኝበት ዕድል የፈጠረው ከብቶች ወደ ቤት በሚመጡበት ሰዓት ነው፡፡ ሰዎች ምርጥ ጠላ ፈልገው ቤት አማርጠው እንደሚመጡ ሁሉ፤ ከብቶችም ምርጥ አተላ የቱ መሆኑን በሽታ እና በቅምሻ መለየት እንደሚችሉ የሚገልጸው ወርቁ፤ ከብቶችን የማያስቡ ፍጡራን አድርጎ አያስባቸውም፡፡
ስለዚህ ሰዎች የእናቱን ምርጥ ጠላ ለመጠጣት እንደሚጋፉ፤ ከብቶቹም ከምርጥ ጠላ የሚገኘውን ምርጥ አተላ ለማግኘት ወደ እነሱ ቤት ይራኮታሉ። ኃይለኛ ተዋጊ ከብቶች የእነሱን አተላ እንዲጠጡ፤ እንዲሰክሩ እና እንዲፋለሙ በማድረግ የጓደኞቹን ትኩረት መሳብ የሚፈልገው ወርቁ፤ አተላውን ከሌሎች ከብቶች ተከላክሎ፤ ለኃይለኞቹ እንዲቀር ያደርጋል። አተላውን እንዲጠጡ፣ እንዲሰክሩ እና እንዲቆጡ በማድረግ ከብቶቹ ለፍልሚያ ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያደርግበት ጥበብ የሮኬት ሳይንስ እስኪመስላችሁ ድረስ ውስብስብ ነው፡፡
ወርቁ ይህን ትዕይንት ሲገልጽ ጊዜ ቀጥ እንዲል አድርጎ ነው፡፡ በቅጽበት የሚከናወኑ ነገሮችን በምትሐት ዕድሜአቸውን አርዝሞ፤ በአንዲት ቅጽበት ውስጥ የታጨቁ ድርጊቶችን በቅደም ተከተል እየሰደረ ያሳያችኋል፡፡ በእኔ ግምት ከእርሱ በቀር ሌላ ሰው ሊገልጸው የማይችለው ትዕይንት ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን በጓደኞቹ አድናቆት ታጅቦ፤ ይህን የከብት ፍልሚያ ለማዘጋጀት ጥረት ሲያደርግ በአንዲት ቦታ በፈጸማት ትንሽ ስህተት፤ የሰላ ቀንድ ያለው በሬ በቀንዱ ወደ ሰማይ አንስቶ አየር ወለድ አደረገው፡፡ ወርቁ ሰማይ ወጥቶ ወደ መሬት እስኪመለስ የሚሆነው ነገር መጽሐፉን በማንበብ የምታዩት እንጂ የሚነገር ነገር አይደለም፡፡
የወርቁ መጽሐፍ ሊነበብ የሚገባው መጽሐፍ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ነገር ግን ከፎንት ጀምሮ የሚታዩ አንዳንድ ጉድለቶች የመጽሐፉን ኃይል እና ውበት የሚጎዱ መሆናቸውን መናገር ይኖርብኛል። ንባቡ በተዝናኖት እንዲሄድ የሚያደርግ የህትመት (ሌይ አውት) መሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ችግሩ ከማውጫው ጀምሮ የሚታይ ነው፡፡ ማውጫው በርካታ የህትመት ሥራ ግድፈት አለበት፡፡ ርዕሶቹ ዐ. ነገራዊ ሆነው መርዘማቸው እንከን ነው፡፡
አጫጭር ርዕሶች ቢሆኑ ለዓይን እና ለጥቅስ ምቹ ያደርጋቸዋል፡፡ በሦስት ገጽ የተዘረዘሩት ርዕሦች በአሃዝ (1 2 3 ….በሚል) የተዘረዘሩ ናቸው፡፡ ሥራው ወጥነት ያለው አይደለም፡፡ በተዘበራረቀ ሁኔታ በርዕሶቹ ሥር የተቀመጠ መስመር አለ፡፡ አንዳንዴም መስመሩ ነጠብጣብ ይሆናል፡፡ ከቁጥሮቹ አጠገብ አንድ ነጥብ (1.) ሲጠቀም እናያለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሁለት ነጥብ (1፡) ሆኖ እናያለን፡፡ ይህ ለዓይን ዕረፍት የማይሰጥ የህትመት ችግር ብቻ በመሆኑ የሚነወር አይደለም። የግዴለሽነት ስሜትን የሚያመለከት እና በታሪኩ ሂደት የሚነሱ ነገሮችን ደራሲው በጥንቃቄ የሚነግረን አይደለም ብለን እንድናስብ የሚያደርግ በመሆኑም ይጎዳል፡፡ ይህ ኃላፊነት የደራሲው የሚሆነው ወደ ህትመት እንዲገባ በመፍቀዱ እንጂ ሥራው የእርሱ አይደለም፡፡ የአርትዖት ሥራ አለመካሄዱንም ይጠቁመናል፡፡ ደራሲው ሥራውን ለቅርብ ጓደኞቹ ወይም ለአርታዒ ማሳየት ነበረበት፡፡ በመግቢያው እንደ ተጠቀሰው በሁለተኛ እትም እንዲህ ያሉ ነገሮች ሊታረሙ ይገባል፡፡ ይበቃል፡፡   

Read 1356 times