Sunday, 27 May 2018 00:00

የኢትዮጵያ ወታደር፤ ኦሎምፒያንና ጀግና ሯጭ ሻምበል ማሞ ወልዴ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 ከ3 ሳምንት በፊት ለዋና አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ እና ለአትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ማስታወሻ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ሆኖባቸው የተሰሩት ሁለት ሃውልቶች በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተተከናወነ ስነስርዓት መመረቃቸው ይታወሳል፡፡ የኢፌዲሪ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመተባበር ሃውልቶቹን አሰርተዋል። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ውስጥ የነበራቸው ጉልህ ድርሻና ታሪክ ለመዘከር እንደሆነም ተወስቷል። ይህን  ተከትሎ ጎተራ አካባቢ በሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር የፈረሰው የሻምበል ማሞ ሐውልት መልሶ እንዲቆም በስፖርት አድማስ በኩል ጥሪ ያቀረበው የበኩር ልጁ ሳሙኤል ማሞ ወልዴ ነው፡፡  የኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ አትሌቶች አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ በቅዱስ ዮሴፍ በሚገኘው መካነ መቃብር ተሰርቶላቸው የነበሩት ሐውልቶች ከ12 ዓመታት በፊት በሚያሳዝን ሁኔታ  ፈራርሰው ነበር፡፡  የሻምበል አበበ ቢቂላ ቤተሰቦች እና ሌሎች ድጋፍ ሰጭዎች ከ4 ዓመት በፊት የታላቁ የማራቶን ጀግና ሐውልት እንደገና ተሰርቶ በስፍራው እንዲተከል አድርገዋል፡፡ ይሁንና  አጠገቡ ለነበረው የሻምበል ማሞ ወልዴ ግን ሃውልት ግን ይህ ማድረግ አልተቻለም፡፡   ክቡር አቤሴሎም ይህደጎ የፈረሰውን ሃውልት ለማሰራት አቅደው የነበረ ቢሆንም  ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ ግን ተመሳሳይ ጥረት ያደረገው የበኩር ልጁ ሳሙኤል ማሞ ወልዴ ነው፡፡
የአባቱን ሃውልት መልሶ ለማቆም በሚያደርገው ጥረት በቦታው ይገባኛል ከአበበ ቢቂላ ቤተሰቦች ጋር ክርክሮች መፈጠራቸው ብዙ ነገሮች ማጓተቱን በቁጭት የሚናገረው ሳሙኤል፤  በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ድጋፍ የሚሰጠው አካል ለማፈላለግ ሞክሯል፡፡
‹‹የተከበሩ አቤሰሎም ይህደጎ በቀስተደመና የስፖንጅ ፋብሪካ የስራ እድል ሰጥተውኝ በወርሃዊ ደሞዝ የምተዳደር ነኝ። ስለዚህም በግሌ ሐውልቱን የማሰራበት አቅም የለኝም። ማሞ የእኔ አባት ሆነ እንጅ ጀግነነቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ክብር ነው፡፡ ስለዚህም ሃውልቱን ተባብረን እንድናሰራ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡ ሃላፊነቱም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ፤ እንዲሁም የስፖርቱ ተቋማት ናቸው፡፡ ፍላጎቱ ካለ በግለሰብ ደረጃም ሊሰራ ይችላል፡፡ ስለዚህም ጀግኖችን ማክበር አለብን፡፡›› በማለት ሳሙኤል ማሞ ወልዴ በስፖርት አድማስ በኩል ጥሪውን አቅርቦ ነበር፡፡
በዚህ የታሪክ ማስታወሻ ላይ የሚታየውን የማሞ ወልዴ ምስልን የሰራው ሰዓሊ እና ዲዛይነር ዳዊት ሙሉነህ ነው፡፡ ሰዓሊ ዳዊት በአይከን ስቱድዮ ይህን ስዕል ለምን ሰርቶ እንደሰቀለው ሲናገር ‹‹ የጀግና መልክ የትውልድ ማሳመሪያና ማነቃቂያ ነው። በሁሉም መስክ ያሉ ጀግኖች ማስታወሻ ያስፈልጋቸዋል። ቤተሰብና አገር የሚገነባው የእነሱን ጀግንነት በማስታወስ እና በማክበር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቶች ደግሞ በዓለም ያስከበሩን ያስጠሩን ናቸው፡፡ እነሱን ስስል ብቻ አይደለም ስማቸውን  ስጠራ እንኳን ከፍተኛ ክብር ይሰማኛል›› ብሏል፡፡ ከ16 ዓመታት በፊት በ69 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን የኢትዮጵያ ወታደር ኦሎምፒያንና ጀግና ሯጭ ሻምበል ማሞ ወልዴ ይህ የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ እንዲህ ይዘክረዋል፡፡
ከትውልድ አገሩ ወደ ውትድርና
ማሞ የተወለደው በ1932 ዓ.ም ላይ ከአዲስ አበባ 60 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ አድአ በተባለች ከተማ በምትገኘው ድሪጂሌ መንደር ነበር፡፡  አባቱ አቶ ወልዴ ደጋጋ እና እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ገነሜ ጎበና የሚባሉ ሲሆን፤ በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ ነበሩ። ገና በልጅነት እድሜው እኚህ ወላጆቹን በመነጠ ማሞን ከቄስ ትምህርት ጀምሮ እያስተማሩ ያሳደጉት የጡት አባቱ ናቸው፡፡ ከትውልድ መንደሩ ተነስቶ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ በውትድርና የመስራት እድል አግኝቶ በክቡር ዘበኛ   በ19 ዓመቱ ተቀጠረ። ለሁለት ዓመታት በውትድርና እየሰለጠነ ጎን ለጎን ትምህርቱን ሲከታተል ቆይቶ 21 ዓመት ሲሞላው የክቡር ዘበኛው 2ኛ ባታሊዮን  በሰላም አስከባሪነት ወደ ኮርያ ሲዘምት አብሮ ዘመተ። በክቡር ዘበኛ ወታደርነት ኮርያ በዘመተው የሰላም አስከባሪ ጦር እና በሌሎች ስራዎች   ለ2 ዓመታት በማገልገል ልዩ ምስጋና ያገኘ ነበር፡፡ በውትድርና ውስጥ ሆኖ ትኩረትን ወደ ስፖርቱ ማድረግ የጀመረው  ከኮርያ መልስ ነው፡፡ በተለያዩ የአገር ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች ለመግባት የውትድርና አቋሙ ያገዘው ሲሆን በየጊዜው በሚደረጉ ብሄራዊ ሻምፒዮናዎች ይሳተፍም ነበር፡፡
የኢትዮጵያና የማሞ የመጀመርያ ኦሎምፒክ
በ1956 እኤአ ላይ በአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ከተማ የተካሄደው 16ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ  ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችበት ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በ8 ወንድ ኦሎምፒያኖች ብቻ የተገነባ ሲሆን በ29 ዓመቱ በእድሜ አንጋፋው የቡድኑ አባል ማሞ ነበር፡፡ ሜልቦርን ላይ ኢትዮጵያ  በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመርያ ግዜ ስትሳተፍ  ሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ጋና፤ ላይቤርያና ደቡብ አፍሪካ ነበሩ፡፡ በዚያን ወቅት ባልተሟላ አደራጃጀት የተመሰረተው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በሜልቦርን ኦሎምፒክ የሚሳተፉ የኢትዮጵያ ፈርቀዳጅ ኦሎምፒያኖችን የመለመለው ከጦር ሃይልና ከተለያዩ የስፖርት ክለቦች ነበር፡፡ አትሌቶቹ በንጉሳዊ ስርዓቱ ልዩ ክትትል ነበራቸው፡፡ ለኢትዮጵያ የመጀመርያ ኦሎምፒክ ተሳትፎ ከተመረጡ በኋላ ዝግጅታቸውን እያከናወኑ በነበረ ወቅት የንጉሱ አስተዳደር ባወጣው መመርያ በኦሎምፒክ የሜዳልያ ክብሮችን መቀዳጀት ከቻሉ  ብሄራዊ ጀግኖች ተብለው ትልቅ የክብር ሽልማት እንደሚያገኙ ቃል ገብቶላቸዋል፡፡  ከመጀመርያዎቹ የኢትዮጵያ ፈርቀዳጅ ኦሎምፒያኖች መካከል በብስክሌት ውድድር ተሳታፊ የነበሩት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የተገኙት ምርጡ ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ እና የማራቶን ሯጩ ባሻዬ ፈለቀ የሚታወሱ ናቸው፡፡  
የክቡር ዘበኛ ወታደርና ስፖርተኛ ሆኖ ማሞ በተለያዩ የአገር ውስጥ ውድድሮች የነበረው ልዩ ብቃትና ውጤታማነት በኢትዮጵያ የመጀመርያ የኦሎምፒክ ቡድን ሲመረጥ  ብዙዎች በማራቶን ውድድር እንደሚሰለፍ ገምተው ነበር፡፡  ይሁንና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ማሞን የመረጠው ደግሞ በ800 ሜትር፤ በ1500 ሜትር እና በ4 X 400  ሜትር እንዲወዳደር ነበር፡፡  የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን አገሪቱ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለመሳተፍ  ከ8 ቀናት አስቸጋሪ የዲሲ አውሮፕላን ጉዞ በኋላ ሜልቦርን ገብቷል፡፡ ማሞ ወልዲ በዚህ የኢትዮጵያ ስፖርት አዲስ ምዕራፍ በመካከለኛ እና በአጭር ርቀት ለመሳተፍ ከበቁ የመጀመርያዎቹ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች አንዱ ለመሆን የቻለ ነበር፡፡ በሜልቦርን ኦሎምፒክ ላይም በመጀመርያው የ800 ሜትር ውድድር ላይ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ላይ ሰባተኛ ነበር የወጣው፡፡ ከዚያም በ1500 ሜትር ለግማሽ ፍፃሜ በመድረስ 11ኛ ደረጃ ነበረው፡፡ በ4 X 400 ሜትር ውድድር የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ደግሞ ከአየነው በየነ፤ ከበየነ ለገሰ እና ከአበበ ሃይሉ ጋር ተሰልፎ በ5ኛ ደረጃ በመጨረሳቸው ፈርቀዳጆቹ የኢትዮጵያውያ ኦሎምፒያኖች ከፍፃሜው ውድድር ውጭ ሆነዋል፡፡ ማሞ በዚህ የኢትዮጵያ የመጀመርያ ኦሎምፒክ ተሳትፎው ለፍፃሜ ውድድሮች ባይበቃም በመካከለኛ ርቀት ፈርቀዳጅ ኦሎምፒያን  መሆኑ የሚጠቀስ ታሪኩ ነው፡፡
ከሮም ኦሎምፒክ ቀርቶ ወደ ኮንጎ ዘመተ
በ1960 እኤአ ላይ የጣሊያኗ ሮም ከተማ 17ኛውን ኦሎምፒያድ ስታዘጋጅ በአገር አቀፍ ደረጃ በሩጫ የተለያዩ የውድድር መደቦች ምርጥ ከሆኑ አትሌቶች አንዱ የነበረው  ማሞ ወልዴ ለሁለተኛ ጊዜ በኦሎምፒክ መድረክ ለመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፡፡ በክቡር ዘበኛ ከአበበ ቢቂላ  ጋር በውትድርናውም በስፖርቱም የነበራቸው ጓደኝነት አነሳስቶት  በኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር መሮጥ ቢፈልግም አልሆነለትም፡፡  ከዚያ የኦሎምፒክ ተሳትፎው ስለቀረበት ምክንያት ያወሱ አንዳንድ የታሪክ ማስታወሻዎች አሉ፡፡ የሮም ኦሎምፒክ ከመድረሱ በፊት በዋዜማው ወራት በአፍሪካዋ አገር ኮንጎ የእርስ በርስ ጦርነት ፈንድቶ እንደነበረ የጠቀሰ አንድ ዘገባ፤ በወቅቱ ንጉሳዊው አስተዳደር በክቡር ዘበኛ የነበረውን  ማሞ ወልዴ ከኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪው ሃይል ጋር ወደ ኮንጎ ሊያሰማራው መወሰኑን ሲያስታውቅ፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ደግሞ  በሮም ኦሎምፒክ ሊያሰልፈው ፈልጎ መሟገታቸውን አውስቷል፡፡ ማሞን  ከኦሎምፒክ ያስቀረው   ያ ሙግት እንዳልነበር ግን ሌላ ዘገባ ሲያመለክት ከኦሎምፒክ ቡድኑ የተቀነሰው በቂ በጀት ባለመኖሩ መሆኑን አውስቷል፡፡ ማሞ በሮም ኦሎምፒክ የሚሳተፍበት እድል ቢበላሽበትም አገሩን በሚያገለግልበት ሃላፊነት መሰማራቱ አልቀረም፡፡ የተባበሩት መንግስታት ኮንጎ ላይ ባሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር አባል ሆኖ ለ1 ዓመት በውትድርናው አገልግሏል፡፡
በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ10ሺ 4ኛ፤ በማራቶን የመጀመርያ  ተሳትፎ
በሮም ኦሎምፒክ የማሞ ወልዴ የቅርብ ጓደኛ፤ አጋር ወታደር እና ስፖርተኛ አበበ ቢቂላ በማራቶን ለአፍሪካ እና ለኢትዮጵያ ፈርቀዳጅ የሆነ ድል ማስመዝገቡ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሮ ነበር። ከአበበ የኦሎምፒክ የማራቶን ታላቅ ገድል በኋላ በ1964 እኤአ ላይ የጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ 18ኛውን ኦሎምፒያድ ስታስተናግድ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በተለያዩ የአትሌቲክስ የውድድር መደቦች በተለይም በማራቶን ከፍተኛ ልምድ ያካበተው ማሞ ወልዴ፤ ለውጤታማነት ከተጠበቁ የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች አንዱ  ነበር፡፡ ሮም ላይ በ10ሺ ሜትርና በማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል እንዲወዳደር ተመርጧል።  ኢትዮጵያ በታሪክ ለ3ኛ ጊዜ በተሳተፈችበት የሮም ኦሎፒክ ማሞ ሁለተኛውን የኦሎምፒክ  ተሳትፎውን በ10ሺ ሜትር አድርጎ አራተኛ ደረጃ በማግኘት የዲፕሎማ ተሸላሚ ለመሆን በቃ። ከፍተኛ ዝግጅት አድርጎ በተሳተፈበት የማራቶን ውድድር ግን አበበ በተከታታይ ኦሎምፒክ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ በፍፁም ብቃት ለመጎናፀፍ ሲበቃ ማሞ ግን ሙሉ ውድድሩን መጨረስ አልቻለም ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ብቸኛው ተስፋ አንተው ነህ….
 በ1968 እኤአ  ላይ  19ኛው ኦሎምፒያድ በሜክሲኮ ሲካሄድ  ከአበበ ቢቂላ በኋላ ለሜዳልያ ውጤት የኢትዮጵያ ብቸኛ ተስፋ  ከፍተኛ ልምድ የነበረው ምርጥ ኦሎምፒያን በወቅቱ የመቶ አለቃ ማዕረግ የነበረው ማሞ ነበር፡፡ እንደ ቶኪዮ ኦሎምፒክ ሁሉ ሜክሲኮ ላይ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የተያዘው  በ10ሺ ሜትር እና በማራቶን እንዲወዳደር ነው፡፡ ውጤታማ እንደሚሆንበት ከታመነው የማራቶን ውድድር አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በመጀመርያ  በ10ሺ ሜትር ተወዳደረ፡፡ ኬንያዊው ናፍታሌ ቴሞ በአጨራረስ ብልጠት አሸንፎ የወርቅ ሜዳልያውን ሲወስድ ማሞ በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የቱኒዚያው መሃመድ ጋሃሚ በሶስተኛ ደረጃ ውድድራቸውን በመጨረስ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎችን ተጎናፅፈዋል፡፡ ማሞ ወልዴ በሶስተኛ የኦሎምፒክ ተሳትፎው የመጀመርያውን የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ለመጎናፀፍ የበቃው በ29፡ 27.75 በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ሲሆን ይህ ውጤት ለኢትዮጵያ የረጅም ርቀት ሩጫ ፈርቀዳጅ ሆኖ መጠቀስ ያለበት ነው፡፡
ማሞ በ10ሺ ሜትር የብር ሜዳልያው ከተጎናፀፈበት ድል በኋላ ግን ከአድካሚው ውድድር እፎይ የሚልበት ጊዜ አልነበረውም፤  ከሳምንት በኋላ በማራቶን ሲወዳደር የአበበን የድል ታሪክ መድገም እንደሚኖርበት የኢትዮጵያን ክብር የማስጠበቅ ኃላፊነት የሱ መሆኑን በወቅቱ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ነገሩት፡፡ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በማራቶን ውድድሩ ላይ በሁለት ተከታታይ ኦሎምፒኮች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን በመጎናፀፍ የተደነቀውን  አበበ ቢቂላን ለመፎካከር ከተሰለፉት የ44 አገራት አትሌቶች ውስጥ አንዱ ማሞ ነው፡፡
ከ34 ዓመታት በኋላ በታዋቂው የአትሌቲክስ መፅሄት ራነርስ ዎርልድ ላይ በዓለም አቀፍ ውድድሮች የቅርብ ተቀናቃኙ የነበረው አሜሪካዊው ኦሎምፒያን ኬኒ ሞር ማሞ ወልዴን በዘከረበት የታሪክ ማስታወሻው በሜክሲኮ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር  ላይ የነበረው የአሯሯጥ ሁኔታ የፃፈው እንዲህ ነበር፡፡
….አበበ ቢቂላ ከግራ ጉልበቱ ከፍ ብሎ በሚገኝ ጡንቻው ላይ ፋሻ አስሮ እየሮጠ ነበር፡፡ 10 ማይሎችን ሮጦ ዞር ብሎ ሌላውን የክቡር ዘበኛ ወታደርን ማሞ ይፈልገው ጀመር፡፡ በማራቶን ውድድሩ መላው ዓለም የአሸናፊነቱን ከፍተኛ ግምት የሰጠው ለሻምበል አበበ ቢቂላ እንጅ ለማሞ ወልዴ አልነበረም፡፡   እንደውም ከማሞ ይልቅ አበበን እሱን እንደሚፎካከሩ የተጠበቁት  የኬንያዎቹ ናፍታሌ ቴሞ፤ ኪፕ ኬኖና አሞስ ቢውት ነበሩ፡፡ … በማለት የኬኒ ሞር የታሪክ ማስታወሻ ይቀጥላል፡፡
እዚህ ጋር ተያይዞ መወሳት ያለበት የአበበ ቢቂላ እና የማሞ ወልዴ አሰልጣኝ የነበሩት ኦኒ ስካነን  ውድድሩን ያስታወሱበት አስተያየት ነው፡፡ ስዊድናዊው አሰልጣኝ ‹‹ማይ አንክል ፍሮም አፍሪካ›› ከሚለው መፅሃፋቸው ባሰፈሩት የታሪክ ማስታወሻ  ‹‹… በማራቶን ውድድሩ ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፉት ሶስቱ አትሌቶች አበበ፤ ማሞ እናመርዓዊ ገብሩ ነበር፡፡ ውድድሩ ከተጀመረ በኋላ በጥሩ ብቃት ላይ የነበረው ማሞ ነው፡፡  3ቱ ኢትዮጵያውያን አጀማመራቸው ጥሩ ነበር፡፡ አበበ ከ5 ኪሜትሮች በኋላ በመሪዎቹ ተርታ ከነበሩት የሌሎች አገራት አትሌቶች ጋር ሲገሰግስ ነበር፡፡ ማሞ እና መርዓዊ ደግሞ በቅርብ ርቀት እየተከተሉ ናቸው፡፡ 10 ኪሜትሮች ሲያልፉ አሁንም አበበ ከመሪዎቹ ጋር መሮጡን ቀጥሏል፡፡ 25ኛ ኪሜትርን ሲያልፉ ግን የኬንያው ናፍታሌ ቴሞ አበበን ቀድሞት አለፈ… አበበም ከነበረበት ጉዳት ጋር ተደማምሮ  ፍጥነቱ እየቀነሰ መጣ….›› በማለት  ትዝታቸውን  አስፍረውታል፡፡
ሜክሲኮ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ የኦሎምፒክ ማራቶንን እንደሚያሸንፍ የተጠበቀው አበበ ቢቂላ በህመም ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ሲገደድ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም የስፖርት አፍቃሪዎች ልብ በሃዘን ተሰበረ፡፡  ጀግና ጀግናን እንደሚተካ የተዘነጋ ይመስላል፡፡  አበበ 20ኛው ኪሎሜትር ላይ ውድድሩን አቋርጦ ከመውጣቱ በፊት ከማሞ ጋር በሩጫ ላይ ያደረጉትን ምክክር  አሜሪካዊው ኦሎምፒያን  ኬኒ ሞር ለራነረስ ዎርልድ በፃፈው መጣጥፍ ላይ መተረኩን እንዲህ ይቀጥላል…
‹‹ሉታነት ማሞ›› ሲል አበበ ተጣራ
‹‹ሻምበል አበበ››
‹‹ውድድሩን የምጨርስ አይመስለኝም፡፡››
‹‹ያሳዝናል ጌታዬ››
‹‹አንተ ግን ውድድሩን ማሸነፍ አለብህ››
‹‹እሽ ጌታዬ››
‹‹አታሳፍረኝም መቼም ›› አለና አበበ ቢቂላ በመጨረሻ ሩጫውን አቋረጠ፡፡
ማሞ ግን ከአበበ ጋር ካደረጉት ምልልስ በኋላ በከፍተኛ ሞራል መሮጡን ቀጠለ፡፡ ዱካውን በመከተል ተፎካካሪ የሆነው የኬንያው ናፍታሊ ቴሞ ነበር፡፡ የመጨረሻዎቹን የማራቶን ርቀቶችን ለመጨረስ ከሜክሲኮው ኦሎምፒክ ስታድዬም አካባቢ ሲደርሱ ማሞ ፍጥነቱን ጨምሮ አፈተለከና የአሸናፊነቱን ሪባን በጠሰ፡፡ በኦሎምፒክ ማራቶን ለኢትዮጵያ ሶስተኛውን ለራሱ ደግሞ የመጀመርያውን የወርቅ ሜዳልያ ለመጎናፀፍ በቃ፡፡ በውድድሩ የመጨረሻ መስመር ላይ ከሁሉም ቀድሞ በመገኘት ድሉን ያደነቀለት አበበ ቢቂላ ሲሆን ከጫነው የአምቡላስ መኪና ወርዶ በድሉ መደሰቱን የገለፀለት  ወታደራዊ ሰላምታ በመስጠት  ነበር ፡፡ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ የ36 ዓመቱ ማሞ ወልዴ ልዩ ብቃት ለማሳየት የበቃው ውድድሩ ከአዲስ አበባ ጋር በሚመሳሰል ከፍተኛ አልቲትዩድ በመደረጉ ነበር፡፡ ማሞ በሜልቦርን ከዚያም በኋላ በቶኪዮ ኦሎምፒክ የነበሩት ልምዶችም ቀላል አልነበሩም። ከሻምበል አበበ ቢቂላ ጋር በልምምድ፤ በውድድር እንዲሁም በውትድርና ሙያቸው በነበራቸው ቅርበትም ብዙ የአሯሯጥ ታክቲኮችና ምክሮችንም እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ ማሞ ወልዴ በአንደኛነት የኦሎምፒክ ማራቶኑን አሸንፎ የወርቅ     ሜዳልያ ሲወስድ ደግሞ ርቀቱን የሸፈነው በ2:20.27 በሆነ ጊዜ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ የተከተለውን ናፍታሌ ቴሞ በ3 ደቂቃ ልዩነት ቀድሞ መግባቱ በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛው የማራቶን አሸናፊ ያስመዘገበው የሰዓት ልዩነት ነበር፡፡
ሜክሲኮ በ1968 እኤአ ላይ ባስተናገደችው 19ኛው ኦሎምፒያድ  ላይ ሻምበል ማሞ ወልዴ በ10ሺ እና በማራቶን በተጎናፀፋቸው 1 የወርቅና በ1 የብር ሜዳልያዎች ኢትዮጵያ ከዓለም 25ኛ ደረጃ እንድታገኝ አስችሏል፡፡ በአበበ ቢቂላ በተከታታይ ሁለት ኦሎምፒክ ድል የተገኘበትን የማራቶን ውድድር ማሞ ወልዴ በድጋሚ አሸንፎ ታሪክ በመስራት ለሶስተኛ ጊዜ በማራቶን የኢትዮጵያን ክብር አስጠበቀ፡፡  ይህ የማሞ ጀግንነት ለኢትዮጵያውን ኩራትንና ደስታን ሲያጎናፅፋቸው በጋዜጠኛ ሰለሞን የተደረሰውን ‹‹ማራቶን ልእልቷ›› ዜማንም አዘምሯቸዋል። ማሞ አትሌቲክሱን ከአበበ ቢቂላ ቀድሞ ቢጀምርም ስኬታማ ሆኖ በጀግንነት የወጣው እሱን ተምሳሌት አድርጎ ነው፡፡ አበበ ሮጦ ውጤታማ መሆን ያስተማረኝ ጀግናዬ ብሎ በአንድ ወቅት አድንቆታል፡፡ አበበ እና ማሞ የክቡር ዘበኛ ወታደሮች ከሆኑ ጀምሮ የቅርብ ጓደኛሞች ናቸው፡፡ አብረው ይሰለጥናሉ፡፡ አብረው ይወዳደራሉ፤ ርስባራሳቸው ይከባበራሉ ይደጋገፋሉ፡፡  ከሌላ ሰው ልናገኛቸው ከምንችላቸው ውለታዎች ሁሉ የላቀ ነው - የጀግና አርአያነት፡፡ ጀግኖች በተግባራቸው ትልቅ ስኬት እውን ማድረግ እንደሚቻል በማሳየት መንፈሳችንን እያበረታቱ ያሳዩናል። የኪነጥበብ ዋነኛ ስራም፤ የጀግኖችን ስኬት አጉልቶ ከውስጣችን ጋር እንዲዋሃድ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን በተግባር ያሳየ ይመስላል - ታዋቂው ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ አትሌት አበበ በቂላንና ማሞ ወልዴን ለማወደስ ባዘጋጀው ዘፈን፡፡ ‹‹ማራቶን ልእልቷ›› የተሰኘው ዘፈን  የህይወትን አቅጣጫ የሚቀይር ሃይል እንደሰጣቸው ነው እሸቱ ቱራ ባንድ ወቅት የገለፁት፡፡ ከእነ አበበ እና ማሞ በኋላ የመጡት የኢትዮጵያ ኦሎምፒያኖች ይህን ደማቅ ታሪክ በየጊዜው እያስታወሱ መንፈሳቸው ከመበረታታቱም በተጨማሪ፤ እንደነ አበበ በቂላ ጀግንነት ለመስራት ጠንክሮ የሚሰሩበትን ፅናትን አጎናፅፏቸዋል፡፡
በጠባብ ጫማ በማራቶን የኦሎምፒክ ነሐስ
በሜክሲኮ በተካሄደው 19ኛ ኦሎምፒያድ ላይ ባገኛቸው የብርና የወርቅ ሜዳልያዎች ማሞ ወልዴ ከንጉሳዊው ስርዓት   የሻምበልነት ማዕረግ ተሰጥቶታል፡፡ በ1972 እኤአ በጀርመን ሙኒክ ከተማ በተካሄደው 20ኛው ኦሎምፒያድ  ለመጨረሻ ጊዜ ኦሎምፒክን በ40 ዓመቱ  ለአራተኛ ጊዜ ለመሳተፍ የበቃም ሻምበል ማሞ ወልዴ ተብሎ እየተጠራ ነበር፡፡ በማራቶን ሶስተኛ በመውጣት የነሃስ ሜዳሊያ ሲያገኝ ነበር፡፡ በሙኒክ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድሩ በ3ኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳልያን 2:15.08 የሆነ ጊዜ አስመዝግቦ መውሰድ ቢችልም የወርቅ ሜዳልያ የማግኘት ብቃት እንደነበረ በማስታወስ ነው በአንድ ወቅት የተናገረው። ማራቶኑን በአግባቡ እንዳይሮጥ ጠባብ የመሮጫ ጫማዎችን ማድረጉን በቁጭት የሚያስታውሰው የሚፈልገውን የመሮጫ ጫማዎች በወቅቱ የነበረው የኦሎምፒክ ኮሚቴ አለማቅረቡን በመውቀስም ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ልዑክ የተዘጋጀሉት የመሮጫ ጫማዎች ጠባቦች ነበሩ፡፡ በሙኒክ ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳልያን ሊወስድ የበቃው አሜሪካዊው ፍራንክ ሹተር ሲሆን ቤልጅማዊው ካሬል ቤስማት ሁለተኛ ነበር፡፡  በሙኒክ ኦሎምፒክ 20ኛው ኦሎምፒያድ ላይ አስቀድሞ በተካሄደ የ10ሺ ሜትር ውድድር ምሩፅ ይፍጠር     በሶስተኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳልያን    27:40.96 በሆነ ጊዜ ሊጎናፀፍ በመብቃቱ ከማሞ ወልዴ የማራቶን የነሐስ ሜዳልያ ጋር   ኢትዮጵያ በ2 የነሐስ ሜዳልያዎች ከዓለም 41ኛ ደረጃ ነበራት፡፡
ከታላቅ ጀግንነት በኋላ የሚያሳዝን መጨረሻው
ከንጉሳዊው ስርዓት በኋላ የደርግ መንግስት ስልጣን ሲይዝ፤ የክቡር ዘበኛ አባል የነበረው ሻምበል ማሞ ወልዴ ከአብዮቱ እርምጃ ህይወቱን ያተረፈው በኦሎምፒክ ባገኛቸው የሜዳልያ ክብሮች ነበር፡፡ የአብዮቱ ወላፈን ግን ሳይነካው ግን አልቀረም። ለረጅም ዓመታት በውትድርና ካገለገለበት የመንግስት ጦር  እንዲሰናበት በማድረግ በቀበሌ ደረጃ ወርዶ እንዲሰራ ተወስኖበታል፡፡ የሩጫ ዘመኑን ካበቃ በኋላም የስፖርት አስተማሪ ሆኖ የሰራ ሲሆን ከዚያም በቀበሌ የልማት ኮሚቴ ገብቶ የጦር ሃይል ደሞዝተኛ ሆኖ ሲያገለግል ነበር፡፡
ከደርግ  በኋላ ኢህአዲግ የመንግስት ስልጣንን ሲረከብ የሻምበል ማሞ ወልዴ የህይወት ውጣውረድ ወደ አሳዛኝ ምዕራፍ ተሸጋገረ፡፡ በቀይ ሽብር ወንጀል ተከስሶ ፍርድ ቤት በመቆሙ ነበር፡፡   የክሱ ሂደት ከ9 ዓመታት  በላይ የፈጀ ሲሆን በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ ሲፈረድበት የ6 ዓመት እስር ተወስኖ በወህኒ እንዲቆይ ነበር፡፡በእስር ቤት ቆይታው ባገኘው አጋጣሚ ከወንጀል ንፁህነቱን በይፋ ሲናገር ቢቆይም የሚጠበቀውን ምህረት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በኢትዮጵያውያን፤ በስፖርት ቤተሰቡና አፍቃሪዎቹ ከኦሎምፒክ ጀግንነቱ በተያያዘም እንዲፈታ ከአየአቅጣጫው ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። የዓለም የኦሎምፒክ ማህበረሰብም በተለያዩ ጊዜያት ከእስር እንዲፈታ ይጠይቁ ነበር፡፡ በወህኒ ስላሳለፈው ፈተናም በርካታ የዓለም ሚዲያዎች ብዙ ዘገባዎችና ሃተታዎችን ሰርተውለታል፡፡ ከእነሱም መካከል የሆነኑሉ ማራቶን እና የራነርስዎርልድ መፅሄት ድረገፆች፤ ዘ ጋድያንና ኒውዮርክ ታይምስ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከፍርዱ በላይ ተጨማሪ  3 ዓመታት በእስር በመቆየቱ  ወዲያኑ እንዲፈታ ተወስኖ  ሻምበል ማሞ ነፃነቱን ያገኘበት ቀን የማርቲን ሉተር ኪንግ መታሰቢያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚከበርበት ቀን ነበር፡፡
ሻምበል ማሞ ወልዴ ከእስር ከተፈታ በኋላ ለ9 ዓመታት በወህኒ በነበረው ቆይታ ላይ መከፋቱን ከመግለፅ ይልቅ የዓለም ኦሎምፒክ ማህበረሰብ ያደረጉለት ማበረታቻን በማመስገን ነበር የሚታወቀው፡፡ በእስር  ቤት ቆይታው ፖሊሶች እና የወህኒው ጠባቂዎች የኦሎምፒክ ሻምፒዮን መሆኑን ያውቁ ስለነበር ያን ያህል አልበደሉትም፡፡ ቢያንስ እጆቹን በካቴና አያስሩትም ነበር።  ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እንዲከራከርለት ያቆመው ጠበቃ ምንም እንኳን በፍርድ ቤት ለነፃነቱ ብዙ ባይሟገትለትም፤ ከቤተሰቦቹና ልጆቹ ጋር እየተገናኘ ድጋፍ ሲያደርግለትና በየሳምንቱ እረፍት ቀናት ወህኒ እየሄደ ሊጠይቀው ችሎ ነበር፡፡
ኤርኪ ቬትኒንያሚ የተባለ ፊንላንዳዊ ጋዜጠኛ በ2002 እኤአ መስከረም ወር ላይ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ሻምበል  ማሞ ከእስር ከተፈታ 3 ወራት ሆኖታል፡፡ በሜዳልያዎች፤ ዲፕሎማዎች፤ የሩጫ ፎቶዎች፤ ሃይማኖታዊ ፖስተሮች ባጌጠው የመኖርያ ቤቱ ሳሎን ውስጥ ተቀምጠው  ቃለምልልሱ አደረጉ፡፡ ፊንላንዳዊው ጋዜጠኛ ይህን ቃለምልልስ ያቀረበው The Life and Trials of Mamo በሚል ርእስ ሲሆን  ብዙ ውጣውረድ ያየበትን ህይወት አስመልከቶ ለቀረበለት ጥያቄ
‹‹ሁሉም ነገር ከእግዚአብሄር ይመጣል፡፡ ብዙ አይቻለሁ፤ ብዙ አሳልፊያለሁ፡፡ ስለዚህ ሁሉን በፀጋ እቀበለዋለሁ፡፡ መጥፎ የህይወት ምዕራፎችም ቢሆኑ፡፡ ምናልባትም ያሳለፍኩት መከራ ለበጎ ነው፡፡ ፍፁም ደስተኛነት መጨረሻው እንባ ሊሆን ይችላል›› ብሎ ምላሽ ሰጥቶታል፡፡
በቀይ ሽብር ወንጀል መከሰሱን አስመልክቶ ሲጠይቀው
‹‹ በቂ ምስክሮች አግኝቼ ለማቅረብ አልቻልኩም፡፡ ፍርድ ቤት ጉዳዩን መመልከት ሲጀምር እኔ ላቀርባቸው የነበሩ ሁሉም ምስክሮች በህይወት አልነበሩም፡፡ የከሳሾቼ ምስክሮች ደግሞ በስማ በለው የወነጀሉኝ ሆኑ…. ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሎ ቢበይንብኝም፤ እኔ ንፁህ ነኝ ብዬ አስብ ነበር በፍርዱ ውሳኔ ላይ ምንም ማለት አልፈልግም›› … ማንም ሰው ፍፁም አይደለም፡፡ ከሰው ስህተት አይጠፋም፡፡ እኔም በህይወት ዘመኔ የሰራኋቸው ስህተቶች ይኖራሉ፡፡›› ማለቱን ነው ፊንላንዳዊው የፃፈው፡፡
የአሜሪካዊው ኦሎምፒያን ኬኒ ሞር የማይዘነጋ ጥረት
አሜሪካዊው ኦሎምፒያን ኬኒ ሞር የሩጫ ዘመኑን ካበቃ በኋላ በሁለት ታዋቂ የአትሌቲክስ መፅሄቶች ስፖርት ኢለስትሬትድና በራነርስ ዎርልድ በአምደኛነት ከ25 ዓመታት በላይ አገልግሏል። በዚህ የስፖርት ፀሃፊነት የአገልግሎት ዘመኑ ከሰራቸው ታሪካዊ ጠቀሜታ ካላቸው ፅሁፎች መካከል በ2004 እኤአ ላይ በራነርስ ዎርልድ መፅሄት ‹‹ቼዚንግ ጀስቲስ›› በሚል ርእስ ስለማሞ ወልዴ ፍትህ የተሟገተበት መጣጥፍ የሚጠቀስ ነው፡፡
ኬኒ ሞር ለማሞ ከፍተኛ ፍቅርና ክብር ነበረው፡፡ በሁለት ኦሎምፒክ ውድድሮች ሁለቴ በማራቶን አብረው ሮጠዋል። በሁለቱም የኦሎምፒክ ማራቶኖች ኬኒ ሞር ማሞ ወልዴን እየተከተለ በመግባት የሜዳልያ ሽልማቶች አምልጠውታል። ኬኒ ሞር ሩጫውን ካቆመ ከረጅም ዓመታት በኋላ ማሞ ወልዴ ከኦሎምፒክ ገድሉና ጀግንነቱ በኋላ የገባበትን የህይወት ውጣውረድ  ባወቀበት ወቅት ደንግጦና እና ተረብሾ ነበር፡፡ ታላቅ የታሪክ ጀብዱ የሰራ ኦሎምፒያን የነበረው ክብርና ዝና በወንጀል ተከስሶ እና ተፈርዶበት ለወህኒ መዳረጉን መቀበል ተስኖት ነው፡፡
ኬኒ ሞር ከሌሎች የአሜሪካ ኦሎምፒያኖች ጋር በመሆን ማሞ ወልዴን ከእስር ነፃ ለማውጣት ያደረጉትን ጥረት፤ ለቤተሰቦቹ ያደረጉትን ድጋፍ የሚተርክ ፅሁፍ ነበር ያቀረበው፡፡ እነዚያ እውቅ ኦሎምፒያኖች ማይክ ቦይት፤ ቢል ቱሚ፤ ማልዊ ታፈልድ  ሲሆኑ ኬንያዊው ኦሎምፒያን ኪፕ ኬኖም አብሯቸው ለማሞ ነፃነት ላይ ታች ብለዋል፡፡ በተለይ በሜክሲኮ ኦሎምፒክ በዴካትሎን ለአሜሪካ የወርቅ ሜዳልያ የተጎናፀፈው ቤል ቱሚ በ1996 እኤአ ላይ አትላንታ ባዘጋጀችው ኦሎምፒያድ የኦሎምፒክ 100ኛ ዓመት መከበሩን ምክንያት በማድረግ በወቅቱ ፕሬዝዳንት ከነበሩት ጁዋን አንቶኒዮ ሳማራንች ባገኘው ልዩ ፍቃድ ማሞን በክብር እንግድነት የሚጋበዝበት እድል ፈጥሮ ነበር፡፡ ከእስር ተፈትቶ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ እንዲካፈል  ለተደረገው ጥረት በቂ ትኩረት ጠፍቶ ሳይፈቀድ ቀረ እንጅ፡፡
የሩጫ ዘመኑ አበይት መረጃዎች
ሻምበል ማሞ ወልዴ በሩጫ ዘመኑ ቁመቱ 170 ሴንቲሜትሮች ክብደቱ 54 ኪሎግራም ነበር፡፡ ዋና አሰልጣኙ ከነበሩት ከስዊድናዊው ኢስካነን በኋላ ለረጅም ጊዜያት አብረውት የሰሩት አሰልጣኝ ንጉሴ ሮባ ናቸው፡፡
በ800 ሜትር፤ በ1500 ሜትር፤ በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር የትራክ ውድድሮች ሯጭነት ከ15 ዓመታ በላይ ያሳለፈ ቢሆንም ከፍተኛውን ስኬት ሊያገኝ የበቃው በማራቶን ነበር፡፡ በሩጫ ዘመኑ ከ15 በላይ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ያሸነፈ ሲሆን በኦሎምፒክ ከተሳተፈባቸው የማራቶን ውድድሮች ባሻገር በሰሜን አሜሪካ የተለያየዩ ከተሞች በሚደረጉ የጎዳና ላይ ሩጫዎችና ግማሽ ማራቶኖች፤ በቦስተን፤ በአቴንስ ማራቶኖች መሮጡንም ከህይወት ታሪኩ ለመረዳት ተችሏል፡፡በመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ፈርቀዳጅ የሆነው ማሞ ወልዴ ኢትዮጵያ በውድድሩ የተሳትፎ ታሪኳ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ እንድታገኝ ማስቻሉ የሚጠቀስ ጉልህ ታሪኩ ሲሆን በ5,000 ሜትር  የነሐስ ሜዳሊያ ሲወስድ ኢትዮጵያን በአትሌቲክስ የደረጃ ሰንጠረዥ 12ኛ፣ ላይ ባጠቃላይ ስፖርት 18ኛ ላይ ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለሻምበል ማሞ ወልዴ የረጅም ጊዜ የአትሌቲክስ አፍቃሪ ክቡር አቤሰሎም ይህደጎ በአዲስ አበባ ስታድዬም በተሰቀለው የኦሎምፒክ ቦርድ መታሰቢያ ላይ ብቻ የሚገኝ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ በሚደነቅበት ስፔን በ2002 እኤአ ላይ ልዩ መታሰቢያ እንደቆመለት መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ በ1963 እኤአ ላይ በስፔኗ ኤልጎባር ከተማ በሚካሄደው የሁዋን ሙጉዌራዛ አገር አቋራጭ የተሳተፈ የመጀመርያው አፍሪካዊ ነበር፡፡ በዚሁ የአገር አቋራጭ ላይ ለአራት ጊዜያት በ1963፤ 1964፤ 1967 እና 1968 እኤአ ላይ ማሸነፍም ችሏል፡፡ ይህን ደማ ታሪኩን በማክበርም በስፔን የባስክ ግዛ በምትገኘው ኤልጎባ የተባለች ከተማ ኢስታላሲኒዮስ ስፖርትስ ማንቴስታ በተባለ ማዕከል በአልሙኒዬም ላይ የተሰራ እና 1.80 ሜትር የሚረዝም ልዩ ሃውልት በ1930ዎቹ ገናና ሯጭ ከነበረው ስፓንያዱ ሁዋን ሙጉዌራዛ ጎን ቆሞለታል፡፡

Read 6259 times