Sunday, 27 May 2018 00:00

“የዜጎች መፈናቀል የማይቆም ከሆነ አገር አቀፍ ሠላማዊ ሠልፍ እጠራለሁ” - ሠማያዊ ፓርቲ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

መንግስት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን የዜጎች መፈናቀል በአስቸኳይ የማያስቆም ከሆነ፣ አገር አቀፍ የተቃውሞ ሠላማዊ ሠልፍ ለመጥራት እንደሚገደድ ሠማያዊ ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ፓርቲው በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ ክልል ባጋጠመው የአማራ ክልል ተወላጆች መፈናቀል ጉዳይ ላይ ሰሞኑን በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ መንግስት አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወስድ ይገባል ብሏል፡፡
ባለፉት ዓመታት የሠፈነው ብሄር ተኮር ሥርአት፣ የሃገሪቱን ህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት ይሸረሽራል ያለው ፓርቲው፤ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በዚህ ችግር መፈናቀላቸውንና አሁንም፤ መፈናቀሉ መቀጠሉን ገልጿል፡፡ ዜጎችን ከቤኒሻንጉልና ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያፈናቀሉ ባለስልጣናት ላይ እስካሁን የተወሠደ እርምጃ አለመኖሩን የጠቆመው ሰማያዊ ፓርቲ፤ መፈናቀልን የሚያስቆም ተጨባጭ እርምጃ የማይወሠድ ከሆነ፣ አገር አቀፍ የተቃውሞ ሠላማዊ ሠልፍ እንደሚጠራ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ ተፈናቃዮች በባህርዳር፣ 920 ከኦሮሚያ ቡኖ በደሌ የተፈናቀሉ ዜጎችን በወልዲያ ተጠልለው እንደሚገኙና ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውሮ መመልከቱን የጠቀሰው ፓርቲው፤ ዜጎች በከፋ ሁኔታ እርዳታ አጥተው እየተንገላቱ መሆኑን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
“በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚያጋጥመው የዜጎች መፈናቀል ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ያመጣው ችግር ነው” ያለው ፓርቲው፤ በዚህ በኩል ሥርአቱ ራሱን ሊፈትሽ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡


Read 7144 times