Sunday, 27 May 2018 00:00

የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር፤ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ እሰራለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ሰሞኑን ወደ ሃገር ውስጥ የተመለሰው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) አመራሮች ከመንግስት ጋር በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና ከመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
የኦዴግ አመራሮች እና ጠ/ሚኒስትሩ ውይይት ባደረጉበት ወቅትም ድርጅቱ ከእንግዲህ መቀመጫውን በኢትዮጵያ በማድረግ፣ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመንቀሳቀስ መስማማቱ ተገልጿል፡፡
በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርአትን ለማጎልበትና በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ ከገዥው ፓርቲ ጋር በጋራ ለመስራትም ስምምነት መደረሱም ታውቋል፡፡
የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የድርጅቱ ሊቀመንበሩ አቶ ሌንጮ ለታ አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ፣ በሀገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል ማድረግ የሚቻልባቸው እድሎች አሉ በሚል እምነት፣ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑንም ሊቀ መንበሩ አስረድተዋል፡፡
“የትጥቅ ትግል ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲን አያመጣም” ያሉት አቶ ሌንጮ ለታ፤ “በሀገሪቱ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ሁሉ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚሰሩበት እድል ሊመቻች ይገባል” ብለዋል፡፡
ድርጅታቸው ራሱን ችሎ አሊያም መሰል የፖለቲካ አላማ ካላቸው ድርጅቶች ጋር ተዋህዶ እንደሚንቀሳቀስ አቶ ሌንጮ አክለው ገልፀዋል፡፡
የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ፣ ምክትላቸው ዶ/ር ዲማ ነጋኦ፣ ከፍተኛ አመራሮቹ ዶ/ር በያን አሶባ፣ ዶ/ር ሃሰን ሁሴን እና የውጪና የህዝብ ግንኙነቱ አቶ ሌንጮ ባቲ ባለፈው ረቡዕ ግንቦት 15 ቀን 2010 ማለዳ ላይ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
አቶ ሌንጮ ለታ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው የኦነግ መስራችና  ሊቀ መንበር የነበሩ ሲሆኑ በ1983 በነበረው የመንግስት ለውጥም ዋነኛ ተሳታፊ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

Read 7173 times