Saturday, 26 May 2018 00:00

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር ይፈታሉ ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

 በሽብር የሞት ፍርደኛ የሆኑት የ“ግንቦት 7” አመራሩ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር እንደሚፈቱ የተገለፀ ሲሆን በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀናትም ሊለቀቁ እንደሚችሉ ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በሰኔ ወር 2006 ዓ.ም ከየመን አውሮፕላን ማረፊያ ተይዘው በሀገር ቤት የታሰሩት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲለቀቁ፣ የእንግሊዝ መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋማትና ኢትዮጵያውያን ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2010 ዓ.ም ለትግራይ ተወላጅ ባለሀብቶችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በቤተ መንግስት በተዘጋጀ የእራት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “መንግስት አቶ አንዳርጋቸውን በማሰር ያተረፈው ነገር ቢኖር ጥላቻና ከእንግሊዝ መንግስት ያገኘው የነበረውን የ11 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ማጣት ነው” ማለታቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በአቶ አንዳርጋቸው መፈታት ጉዳይ በባለስልጣኖቻቸው መካከል ውዝግብ መፈጠሩን የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “እኔ እንዲፈታ ነው የምፈልገው፤ ይፈታል፤ “እሱን በማሰር የተገኘ ትርፍ የለም” ማለታቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ከአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በተጨማሪ በሙስና ሰበብ ከታሰሩ ባለሀብቶች መካከልም የሚፈቱ እንዳሉ ጠ/ሚኒስትሩ ፍንጭ መስጠታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 7218 times Last modified on Saturday, 26 May 2018 15:04