Sunday, 27 May 2018 00:00

ቤታቸው የፈረሰባቸው አስር ሺህ አባወራዎች ለጠ/ሚሩ አቤቱታ አቀረቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ህገ ወጥ ግንባታ ነው በሚል ከሁለት አመት በፊት በአዲስ አበባ ቤታቸው የፈረሠባቸው አስር ሺህ ያህል አባ ወራዎች፤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አቤቱታቸውን በደብዳቤ አቀረቡ፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ገቢ በተደረገው የአቤቱታ ደብዳቤ ላይ፤ አባወራዎቹ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ፣ ማንጎ ጨፌ ግራር በተባለ አከባቢ በተለያየ አግባብ መኖሪያ ቤት ሠርተው መኖር መጀመራቸው ተገልጿል፡፡
በወቅቱ ነዋሪዎቹ ያለ ማስጠንቀቂያ በቡልዶዘር ቤታቸው በጅምላ እንዲፈርስ ተደርጎ ጎዳና ላይ መበተናቸውን የሚጠቅሰው ደብዳቤው፤ በኋላም በአካባቢው በነበረው የቤቶቻቸው ፍርስራሽ ላይ በላስቲክና በሸራ ድንኳን ወጥረው መኖር እንደጀመሩ ደብዳቤው ይጠቁማል፡፡
ይሁን እንጂ ሠሞኑን (ከግንቦት 1 እስከ ግንቦት 3) ወደ ፕላስቲክ መኖሪያ ቤቶቻቸው እንዳይገቡ ተከልክለው ሜዳ ላይ መውደቃቸውን፤ ልጆቻችውም ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸውን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡
ህብረተሠቡ መብቱን ሲጠይቅ በዱላ እየተደበደበ ይታሠራል የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ የውጭ ሃገር ስደተኞችን ተቀብላ በክብር የምታኖር ሃገራችን፣ እንዴት ለኛ ለዜጎቿ ቦታ ታጣለች ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
በ2005 ዓ.ም ገንዘብ አዋጥተን፣ መንገድ፣ መብራትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በክፍለ ከተማ አስተዳደሩ እውቅና አከናውነናል የሚሉት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ በኋላ ላይ ያለ ማስጠንቀቂያ በ10 ኤክስ ካቬተሮችና ዶዘሮች ቤታችን በላያችን ላይ ሊወድምብን ችሏል- ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስር ሺህ ያህሉ አባወራዎች ከነ መላ ቤተሰባቸው ያሉበትን ችግር ተረድተው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጧቸው የተማፀኑት ነዋሪዎቹ፤ ህፃናት በዚህ ሁኔታ ውስጥ በእጅጉ እየተጎዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

Read 6624 times