Saturday, 26 May 2018 00:00

የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዳይሬክተርን ጨምሮ በርካታ ባለሥልጣናትና ባለሃብት ከእስር ይፈታሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)


             የግል ኩባንያዎች የሙስና ክስም ተቋርጧል

    ከአምስት አመት በፊት በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ፣ ምክትላቸው አቶ ገብረዋህድ ገ/ጊዮርጊስና ባለቤታቸው ኮ/ል ሃይማኖት ተስፋዬን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች ክሳቸው ተቋረጠ፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክሱን ያቋረጠው የግንቦት 20ን በአል ምክንያት በማድረግ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ክሣቸው ከተቋረጠላቸውም መካከልም አቶ መላኩ ፋንታ፣ አቶ ገብረዋህድ ገ/ጊዮርጊስ እንዲሁም አብረዋቸው ታስረው የነበሩት የነፃ ትሬዲንግ ባለቤት አቶ ነጋ ገ/እግዚአብሄር፣ የኬኬ ኩባንያ ባለቤት አቶ ከተማ ከበደ፣ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ እንዲሁም ባለሃብቱ አቶ ጌቱ ገለቴና፣ አቶ ገብረስላሴ ገብሬ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በቅርቡ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት የኢሊሊ ሆቴል ባለቤት አቶ ገምሹ በየነም ክሳቸው ተቋርጧል፡፡
ከባለስልጣናትም የኢንዱስትሪ ሚ/ር ዴኤታ የነበሩ አቶ አለማየሁ ጉጆ፣ አቶ ዋሲሁን አባተ፣ አቶ አክሎክ ደምሴ፣ አቶ ዛይድ ወ/ገብርኤል (የቀድሞ የመንገዶች ባለስልጣን ዳይሬክተር)፣ አቶ መስፍን  ወርቅነህ፣ ወ/ሮ ሰኙን ጎበና፣ አቶ ጌታቸው ነገሪ፣ አቶ ነጋ መንግስቱና አቶ ሙሣ መሃመድ ክሳቸው ተቋርጧል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ጂኤች ሲ ሄክስ ኩባንያ፣ ጌታስ ኩባንያ፣ ኮሜት ኩባንያ፣ ነፃ ትሬዲንግና ፍፁም ገብረመድህን የግል ኩባንያዎች ላይ ተመስርቶ የነበረው የሙስና ክስም ተቋርጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቅርቡ በቤተ መንግስት ባዘጋጁት የእራት ግብዣ ላይ በሙስና የተከሠሡ ባለሃብቶችን እንደሚፈቱ ፍንጭ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡

Read 9547 times Last modified on Saturday, 26 May 2018 16:07