Sunday, 06 May 2012 14:34

ሽልማት

Written by  አንድነት ግርማ
Rate this item
(1 Vote)

ሁል ጊዜም አንዳንድ ውሳኔዎችን እወስናለሁ፡፡ እኔ የምወስናቸው ውሳኔዎች በአቅሜ ልክ ስለሆኑ ላስፈጽማቸው አልቸገርም፡፡ አቅሜን ማወቄ ግን ሌላም ጥቅም ያገኘሁበት ይመስለኛል፡፡ ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡ ምክንያቱም ድንበሩን አውቆ የሚኖር ሰው ስጋት የለበትም፤ ጣርም የለበትም፡፡ እናንተ ምናልባት ድንበር የውዝግብ ምክንያት እንደሆነ ሊሆን ይችላል የምታውቁት፡፡ ድንበሩን ለተቀበሉት ግን የእረፍት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለማንኛውም ደስታዬን ለሌሎች ለማጋራት እንደምጥር ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡

ዛሬ የወሰንኩት ውሳኔ ይህ ነው፡፡ በእጄ ላይ ወርቃማ ሰአት አለ፡፡ ይህንን ሰአት በእጄ ላይ ካሳለፈው ጥቂት ወራት በላይ ማንጠልጠል እንደሌለብኝ ተረድቼያለሁ፡፡ ይህን እጅግ በጣም የምወደውን የወርቅ ቅብ ሰአት ለማከብረው ሰው ልሸልም አስቤያለሁ፡፡ በዚህም ለመልካም ነገር መጐልበት የራሴን አስተዋጽኦ አበረክታለሁ፡፡ ለራሴም የመንፈስ እርካታ አገኛለሁ፡፡ የሰአቱ ይዞታ ገና አዲስ ነው፤ እንዳልኳችሁም የወርቅ ቅብ ነው፡፡ ለማን ልስጥ? ለማን ልሸልም?...ይህ ሰአት የሚገባው ሰው በየመንገዱ ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡

በአትሌቲክስ ውጤታማ ለመሆን በየማለዳው ተነስተው የሚሮጡትን አገኘሁ፡፡ ብሸልማቸው በምን ያህል ሰአት ምን ያህል እንደሚሮጡ ለማወቅ ይረዳቸዋል፡፡ ከዲስኮ ሰአት ይልቅ የበለጠ ሊያምኑት ይችላሉ፡፡ ማበረታቻም ሊሆናቸው ይችላል፡፡ በማለዳ ተነስተው ወደ ትምህርት ቤት፣ ወደ ንግድ እና ወደተለያየ ጉዳይ የሚቸኩሉትን አየሁ፡፡ ለነሱም ቢሆን የእጄን ሰአት የአድናቆቴ መግለጫ አድርጌ ብሰጣቸው ልባቸው እንደሚፈካ ተረዳሁ፡፡

በመጨረሻም ከሊስትሮነት ተነስቶ ግዙፍ የገበያ አዳራሽ ከፈተ ተብሎ የሚወራለትን ጐልማሳ ለማግኘት አቅጣጫዬን አስተካከልኩ፡፡ በዚህ መንገዴ ላይ ሳዘግም በረንዳ ላይ አድሮ ድሪቶውን የሚሰበስብ ሌላ ጐልማሳ ሰው አገኘሁ፡፡ ይህ ሰው ምናልባት እኔ ቀልቤ ያረፈበትን ሰው ያውቀው ይሆናል፡፡ ምናልባትም አንድ በረንዳ ላይ አድረው፣ በአንድ ብርድ ተበርደው በአንድ ጀብ ተባረው ያውቁ ይሆናል፡፡

አሁን መኝታቸው ተለያይቷል፡፡ ይህኛው አሁንም ይበርደዋል፡፡ የኔን እጩ ግን በስሱ የሚነፍስ ንፋስ ካልሆነ በቀር ብርድ አያገኘውም፡፡ ታዲያ ሰው ማለት ይህ አይደል? እናም የሰማዩን ባላውቅም በምድር ግን ሊሸለም ይገባል፡፡ ይህም የበረንዳ አዳሪ ሊረዳኝ ይችላል፡፡ ምናልባትም የቀድሞ ወዳጁ ቢሆንስ? ይህ ከሆነ ደግሞ ልሰጠው ስላሰብኩት ሰው አነሳስ በመንገር ሽልማቱ በእርግጥም የሚገባው መሆኑን ሊያፀናልኝ ይችላል፡፡

“ይህንን በእጄ ላይ የምትመለከተውን ሰዓት የምሸልመውን ሰው እያፈላለግሁ ነው” አልኩት፡፡

“መስፈርቱ ምንድን ነው?” ጠየቀኝ

“ጉብዝና” አልኩት

“በጉብዝናማ ጌታዬ በዚህ ከተማ እግርዎት እስኪቀጥን ቢፈልጉ እንደኔ አያገኙም”፡፡

“ጉብዝናህ ምንድን ነው?” የመናገር መብቱን ለማክበር ሳይሆን እራሱ ላይ እንዲቀልድ እድል ልስጠው፡፡

“ጉብዝናዬ ያለመታከት ስንፍናን መሸከም ነው” የሚናገረው ቀልድ ሳይሆን የምሩን ነው፡፡

“ይህ ታዲያ እንዴት ነው ሽልማት የሚያስገኘው? አማኑኤል ሆስፒታል በተዘጋጀ የሽልማት ፕሮግራም ላይ ስራህን ብታስተዋውቅ አይሻልም?” ቆጣ አልኩ፡፡

“ሽልማት ያስገኛል ጌታዬ፡፡ ምን መሰልዎት ጉብዝና ካለዎት የሚሰሩት አለም ሁሉ እያጨበጨበልዎ ነው፡፡ ሰው ሁሉ ያበረታታዎታል፡፡ ሰነፍ ከሆኑ ግን ሰው ሁሉ ፊቱን ወደርሶ የሚመልሰው ለቁጣ፣ ለተግሳጽና ከአጠገባቸው እንዲርቁ ለማስጠንቀቅ ነው፡፡ ቀለብዎት ተግሳፅና ቁጣ እንዲሁም ውርደት ነው፡፡ ውጤታማ ሲሆኑ ሳር ቅጠሉ ከርሶ ጋር ነው፤ ውጤት ከራቆት ግን እናቴ የሚሉዋትም ከእርሶ ጋር አትሆንም፡፡ ታዲያ ሽልማት የሚገባው ጉብዝናን የተሸከመ ነው ወይስ ስንፍናን?...የቱ ነው ብርቱ?...ተመልካች የሌለበትን ማራቶን ውድድሩ ካለቀ ከሳምንታት ልዩነት በኋላ መጨረስ አይገርምም…እኔና መሰሎቼ ማለት እንደዛ ነን፤ ተመልካች የለንም ግን እንሮጣለን”

“ግን እናንተ ረዋጮች ናችሁ እንዴ?”

“እንዴታ! እንደሌላው መኖራችንና መሞታችን እስካልቀረ እኛም የህይወት ሩጫ ሩዋጮች ነን፡፡ ግን የምንሮጠው በራሳችን እንጂ በጐበዞች ትራክ አይደለም፡፡ የኛ ትራኩ እራሱ ለየት ይላል፡፡ በመሆኑም ሁኔታዎች እየታዩ ልንሸለም ይገባል”

“ይህን ቡትቶ ያለበሰህ ማን ነው?”

“ስንፍና”

“እግርህን ባዶውን ያለጫማ ያስቀረው ማን ነው?”

“ስንፍና”

“ለምን ያህል ጊዜ ስንፍናን ተሸከምክ?”

“ይኸው መለመን ከጀመርኩ፣ ስንፍና ከጀመርኩ፣ ሰው የሚወደውን ስራ ከተውኩ…ድፍን አርባ አመት”

“ምን አተረፍክ?”

“ስድብና ውርደት”

“ስድቡና ውርደቱን እንዴት ቻልከው?”

“የማይቻል የለም፡፡ ያው በጉብዝና ነው ጌታዬ”

“በዚህን ጊዜ ያበረታታህ የለም?”

“ማንም ሳያበረታታኝ ድፍን አርባ አመት፡፡ የማይቻል የለም የሚል መፈክር አለኝ” ቀጠለ፡፡

“ጉብዝናን የምትሸከሙት ሁላችሁም በፍላጐታችሁ ነው፡፡ ስንፍናን የተሸከምኩት ግን ሳልወድ በግድ ነው፡፡ ሆኖም በጽናት ተሸክሜዋለሁ፡፡ ማን ደስ ብሎት ደሃ ሚሆን አለ?...ጐበዝ በልቶ እና አጊጦ ይውላል፡፡ ሰነፍ የሚበላው የለው፤ የሚዞረው በድሪቶ ነው፡፡

ሊሸለም የሚገባው በልቶ የዋለው ነው ጦሙን የዋለው? የሚከብደው የቱ ነው? መደነቅ የሚገባው የቱ ነው?”

“እንዴት ቻልከው ግን ረሃብን?” የሚናገረው ከልቡ በመሆኑ እኔም ስሜቱን መረዳት ጀመርኩ፡፡

“ረሃብ ሳንጃውን መዞብኝ ይመጣል፡፡ ምን የማደርግ ይመስሃል?...ሆድቃዬን አመቻችቼ አሳየዋለሁ፡፡ እሱ ምን የሚያደርግ ይመስልሃል? ምህረት የሚባል ነገር አያውቅም፡፡ የቻለውን ያህል ይወጋኝና ይሄዳል፡፡

በጀርባዬ ተኝቼ አቃስታለሁ፡፡ ሲብስብኝ ረሃብን የማባርርበት ፍርፋሪ ፍለጋ ሄዳለሁ፡፡ ከዛም እንደምንም ብዬ በትራኩ ላይ ሩጫዬን እቀጥላለሁ፡፡”

“ብርታትህ ሊገባኝ አልቻለም” አልኩት መንገዴን ለመቀጠል እየተዘጋጀሁ፡፡

በመጨረሻ ሃይሉ መናገር ጀመረ “ስንፍናን መሸከም ማለት የሰዎችን ስድብ፣ ቁጣ ትእቢት ተሸክሞ መኖር ማለት ነው፡፡

የሰነፍ ቀለቡ ረሃብና እርዛት ብቻ አይደለም፡፡ ስድብ ቀለቡ ነው፣ ፍርፋሪ ቀለቡ ነው፡፡ በተለይ የጐበዞችን ቁጣ እና ትእቢት መሸከም አለበት፡፡

የቆሻሻ ቅርጫት ሆኜ አገልግዬአለሁ፡፡ ታዲያ ይህ እንዴት አያሸልምም?” አለኝ፡

አሁንም ጨክኜ ልሄድ እግሬን አነሳሁ - በማለዳ በገጠመኝ ነገር እየተገረምኩ፡፡

“ከእነርሱ አንዱ ሳይሆኑ አይቀርም” አለኝ ወደ ስንፍናው እየተመለሰ፡፡ “በርታበት” አልኩ፤ በሆዴ እጩ ወዳጄን ለማግኘት እየቸኮልኩ፡፡

 

 

Read 3399 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:48