Sunday, 27 May 2018 00:00

የአዲስ አበባ “ሲቲ ሴንተር” በሰንጋ ተራ ዙርያ የባንኮችን ረዣዥም ሕንፃዎች የቻይና ኩባንያዎች እየገነቡ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)


    አሁን፣ የቀድሞ ስሙና ገጽታው ተቀይሮ ፋይናንሻል ዲስትሪክት ተብሏል - በተለምዶ ሰንጋ ተራ ይባል የነበረው አካባቢ፡፡ አዲስ አካባቢያዊ ስም የሰጠው ደግሞ የባንኮች ዋና መ/ቤት ሕንፃዎች በአካባቢው መከተማቸው ነው፡፡
ከዘጠኝ ዓመት በፊት በ2002 ዓ.ም የተመረቁት የአዋሽ ባንክና የአዋሽ ኢንሹራንስ መንታ ሕንፃዎች ግንባታ ለአካባቢው ቀዳሚ ናቸው፡፡ ቀጥሎ፣ ግንባታው በዚህ ዓመት ተጠናቆ የተመረቀው ዳሽን ባንክ ዋና መ/ቤት ሕንፃ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቻይና ሁለት የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች እየተገነቡ ያሉት የሕብረት ባንክ፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክና የዘመን ባንክ ዋና መ/ቤት ሕንፃዎችን ግንባታ እየተፋጠነ ነው፡፡ የንብ ባንክ ህንፃ መዋቅር (ስትራክቸር) በመጪው ሰኔ ወር ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል፡፡
ከእነዚህ የባንክ ዋና መ/ቤት ሕንፃዎች ትንሽ ፈንጠር ብሎ ከጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ጎን በቻይና መንግሥታዊ የኮንስትራክሽን ኩባንያ የሚሠራው፣ በአገራችን ረዥሙ ባለ 53 ፎቅ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መ/ቤት ሕንፃ ሌት ተቀን እየተሠራ ነው፡፡ ከስታዲየም ፊት ለፊት ደግሞ ባለ 23 ፎቁ፣ የወጋገን ባንክ ዋና መ/ቤት ሕንፃ ተገሽሯል፡፡ የኢቢሲኒያ ባንክም ግንባታ አልጀመረም እንጂ እዚያው አካባቢ የዋና መ/ቤት ህንፃ ግንባታ ቦታ መረከቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኦሮሚያ ኅብረት ባንክም ዋና መ/ቤቱን ከአዋሽ ባንክ ጎን ለመሥራት ቦታ አጥሯል፡፡
ለመሆኑ የእነዚህ ተቋማት በአንድ አካባቢ መሰባሰብ ምን ፋይዳ አለው? እንዲህ አይነት አሠራርስ በውጪው ዓለም የተለመደ ነው? የሕብረት ባንክ የዲሬክተሮች የቦርድ ሰብሳቢ  አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በብዙ አገራት የተለመደ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡   
“በብዙ አገሮች ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ወይም በተመሳሳይ ሙያ ላይ የተሰማሩ ተቋማት ወይም ድርጅቶች አንድ ላይ ወይም አንድ አካባቢ የመሰባሰብ ተለምዶ አለ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ “ዎልስሪት”፣ በሎንደን ደግሞ “ሲቲ ሴንተር”፣ የባንክና የኢንሹራንስ (ፋይናንሽያል) ማዕከል ናቸው። የፋይናንስ ተቋማት ለማንኛውም እንቅስቃሴ እንደ እርሾ ስለሚያገለግሉ፣መሃል ከተማ (ሲቲ ሴንተር) ይሰባሰባሉ፡፡ በሌሎች አገሮች እንደዚያ የሚያደርጉት በምርጫቸው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በጣም እያደጉ ሲሄዱ፣ የመኻል ከተማ መቀመጫቸው ወይም አድራሻቸው፣ እዚያው እንዳለ ትተው፣ ወጣ ብለው ከሕዝቡ ጋር ቀጥታ ግንኙነት የማያስፈልገው (ባክ ኦፊስ) ሥራ የሚሠራበት ኮርፖሬት ሄድ ኦፊስ ከመኻሉ ወጣ ብለው ይከፍታሉ፡፡
“ይኼ በምርጫቸው ነው፡፡ እኛ አገር የቦታ ጥያቄ ውድ ነው፡፡ ቦታውን የሚሰጠው አንድ አካል ነው። አጋጣሚ ሆኖ በልደታና በሰንጋ ተራ አካባቢዎች ያረጁና የደከሙ ቤቶችን እያፈራረሰ፣ አዲስ አልሚዎች እንዲገቡ ባደረገ ጊዜ፣ አብዛኞቹ ባንኮች በአንድ ወቅት በአንድ አካባቢ ቦታ ጠይቀው አግኝተዋል። እዚህ ላይ በእኛ አገር ትንሽ ለየት የሚለው ነገር፣ የባንኮች ተቆጣጣሪ (ብሔራዊ ባክ) ራሱም እዚያው አካባቢ ስለሆነና ብዙ ነገር አብረው ስለሚሠሩ ቀረብ ማለታቸው ያንን አካባቢ እንዲመረጥ አደርጎታል፡፡ በዚህ የተነሳ የባንኮች አንድ ላይ መሰባሰብ ከጥቅም በስተቀር የሚያመጣው ጉዳት የለም፡፡ ምክንያቱም ባንኮቹ፣ ተደራሽነታቸው በአብዛኛው በቅርንጫፎቸው ነው፡፡ ስለዚህ ዋና መ/ቤቶቻቸውን አንድ አካባቢ ማድረጋቸው ጉዳት አለው ብዬ አላምንም፡፡”
 በአሁኑ ወቅት ትናንሽ ማይክሮ ፋይናንስ (እንደ ሄሎ ካሽ ያሉ) ተቋማት በየመንደሩ በመግባት፣ የባንክ ቅርንጫፎችን ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት አካሄድ የቴክኖሎጂ ርቅቀት የቅርንጫፎችን አስፈላጊነት አይቀንሰውም ወይ? አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ አይቀንሰውም ይላሉ፡፡
“ከአገራችን ሕዝብ ምን ያህሉ ነው የባንክ ተጠቃሚ ብለን በምንጠይቅበት ጊዜ፣ በጣም አነስተኛ ቁጥር ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ የመሠረተ ልማት ዕድገት አነስተኛ ነው፡፡ ገና ብዙ መሰራት ይጠበቅበታል፡፡ አሁን ባለንበት ሰዓት የቴሌኮሙኒኬሽን ልማት ዕድገት ራሱ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተዘረጉ የቴሌ መስመሮች ተገቢውን አገልግሎት አይሰጡም፡፡ በዚህ የተነሳ ባንኮች በየቦታው ቅርንጫፎች እየከፈቱ ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን የሚከፈቱት ቅርንጫፎች በፍፁም በቂ አይደሉም፡፡ አሁን ያሉን ቅርንጫፎች ቁጥር ሁለትና ሦስት እጥፍም ቢያድጉም  በቂ አይደሉም፡፡ ስለዚህ የባንክ ቅርንጫፎች መብዛት በጣም ጥሩና አስፈላጊ ነው፡፡
“ማይክሮ ፋይናንሶች የራሳቸው ደንበኞች ስላላቸው በቅርንጫፎች ላይ ተፅዕኖ አይፈጥሩም፡፡ ብዙ ሚሊዮኖች ገንዘብ የሚያስፈልጋቸው ድርጅቶች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሺህ ቤት የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስፈልጋቸው ይኖራሉ፡፡ ትልልቆቹ ተቋሞች እጅግ በጣም ትንንሾችን ደንበኞች ማስተናገድ፣ ዋጋውን በጣም ከፍተኛ ያደርግባቸዋል፡፡ ምክንያቱም፣ ቅርንጫፍ አቋቁመው፣ የቤት ኪራይ እየከፈሉ፣ ሠራተኞች ቀጥረው፣ መሳሪያዎች ገዝተው… የ5 እና የ10 ሺህ ብር ብድር ቢሠሩ፣ ዋጋ የለውም፤ በፍፁም አያዋጣቸውም… ለዚህ ዓይነት አገልግሎት ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አሉ፡፡ ሂደቱ በዚህ መልኩ ተደጋጋፊ ወይም ተመጋባቢ ነው፡፡ አንዱ የሌላው ተወዳዳሪ ሆኖ እንደ ባላንጣ የሚተያዩ አይደለም፡፡”
አሁን ደግሞ የባንኮቹን ዋና መ/ቤት ግንባታ የትኛው የኮንስትራክሽን ድርጅት እየሠራው እንደሆነ፣ ሕንፃዎቹ ስንት ፎቅ እንዳላቸው፣ በምን ያህል ጊዜ እንደሚጠናቀቁ፣ የግንባታቸው ወጪ ምን ያህል እንደሆነ እንመልከት፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ቦታው ፡- ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ
የሕንፃው ወለል (ፎቅ)፡- 4 ቤዝመንት+ G+48 ፎቅ  
ኮንትራክተር፡- የቻይና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን
የግንባታ ጊዜ፡- 900 ቀናት ወይም 3 ዓመት ከ6 ወራት
የግንባታው ወጪ፡- 4.7 ቢሊዮን ብር
የሕንፃው አገልግሎቶች፡- ቅርንጫፍ መ/ቤት፣ የንግድ ማዕከል፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ቢሮዎችና ከ1500 በላይ መኪኖች ማቆሚያ
አዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ
ቦታው፡- በተለምዶ ሰንጋ ተራ በሚባለው አካባቢ
የሕንፃው ወለል (ፎቅ)፡- የኢንሹራንሱ ሕንፃ ወለል- 2 ቤዝመንት+ G+ 16
የባንኩ ሕንፃ ወለል - 2 ቤዝመንት+ G+18 ፎቅ
ኮንትራክተር፡- ባርኔሮ
የግንባታው ወጪ፡- 217 ሚሊዮን ብር
ወጋገን ባንክ
ቦታው፡- ስታዲየም ፊት ለፊት
የሕንፃው ወለል (ፎቅ)፡- ከምድር በታች የሚገኙትን ሦስት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ወለሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 33 ወለሎች
ኮንትራክተር፡- የቻይናው ጂያንግዢ ኮርፖሬሽን ፎር ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚክ ኤንድ ቴክኒካል ኮርፖሬሽን
የግንባታው ወጪ፡- 805 ሚሊዮን ብር
ዳሽን ባንክ
ቦታው፡- ከባህልና ቱሪዝም ሚ/ር ፊት ለፊት
የሕንፃው ወለል (ፎቅ)፡- 3 ቤዝመንት ጨምሮ 21 ወለሎች
ኮንትራክተር፡- ሚድሮክ ኮንስትራክሽን
የግንባታው ወጪ፡- 1 ቢሊዮን ብር
የሕንፃው አገልግሎቶች፡- 5 የሰዎችና 1 የዕቃ ማጓጓዥን ጨምሮ 8 አሳንሰሮች፣ በየወለሉ የተለያዩ መጠን ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች፣ ጂምናዚየም፣ ካፊቴሪያ፣ የህፃናት ማቆያ፣ ክሊኒክና በየወለሉ የምግብ ማዘጋጃ ክፍሎች፣ 170 መኪኖች ማቆሚያ  
ሕብረት ባንክ
 ቦታ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ንግድ ሥራ (ኮሜርስ) ፊት ለፊት  
የሕንፃው ወለል (ፎቅ)፡- 3 ቤዝመንት+ ጂ+ 32  
ኮንትራክተር፡- የቻይናው ዳንግሱ ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚና ቴክኒካል ኮርፖሬሽን ግሩፕ
የግንባታው ወጪ፡- 2 ቢሊዮን ብር ገደማ
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ
ቦታ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ንግድ ሥራ (ኮሜርስ) ፊት ለፊት  
የሕንፃው ወለል (ፎቅ)፡- 4 ቤዝመንት + ጂ + 32  
ኮንትራክተር፡- የቻይናው ዳንግሱ ኢንተርናሽናል ኢኮኖሚና ቴክኒካል ኮርፖሬሽን ግሩፕ፣ የመሠረት ሥራውን -  የቻይናው ሬል ዌይ ኩባንያ
የግንባታ ጊዜ፡- 1,460 ቀናት ወይም 48 ወራት
የግንባታው ወጪ፡- 1.6 ቢሊዮን ብር  
ዘመን ባንክ
ቦታው፡- ከንብ ኢንተርናሽናል ባንክ
የሕንፃው ወለል (ፎቅ)፡- 3 ቤዝመንት+ ጂ+32 ወለሎች፣ከ2ኛ ፎቅ እስከ 7ኛ ፎቅ የመኪና ማቆሚያ
ኮንትራክተር፡- ዉ ዪ (Wu yi) የተባለው የቻይና ኩባንያ
የግንባታ ጊዜ፡- 2 ዓመት ከ10 ወር  
የግንባታው ወጪ፡- 1.3 ቢሊዮን ብር

Read 2902 times