Sunday, 27 May 2018 00:00

አንብብ! አንብብ! አንብብ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ - (አተአ)
Rate this item
(1 Vote)


    (የሃሳብን ልህቀት በ1950ዎቹ መፅሐፍ ውስጥ ስንቃኝ … እኛ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሆነን …)
***
አንድ የሆነ ሀሳብ አስባችሁ ስታበቁ፣ “አሃ! … ልክ ነው” ብላችሁ አታውቁምን ?!
ለምሳሌ ‹‹የሆነ ሰው እያየኸው ያለኸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፤ ነገር ግን ያንን ሰው ከዚህ በፊት የሆነ ቦታ አይተኸዋል። በሆነ ሰፈር እያለፍክ ነው፤ ነገር ግን ያንን ሰፈር የሆነ ጊዜ መጥተህበታል፡፡ የሆነ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ እየገባህ ነው፤ ነገር ግን በሆነ አጋጣሚ ቀድሞ እዚህ ነበርክ … ›› አይነት ፡፡
… እኔ ይህ ብዙ ጊዜ ያጋጥመኛል፤ በእውነት ብዙ ጊዜ ለራሴ አጉተምትሜ አውቃለሁ፡፡ እናም እንዲያው ሰዎቹ የሚያስተምሩት እውነት ይሆን እንዴ! ብዬ ተጠራጥሬም አውቃለሁ፡፡ መቼም ሰምታችኋል ደግመህ ደግመህ ወደ ምድር በመምጣት ትወለዳለህ ሲሉ ያስተምራሉ፡፡ እናም ብዙ መፅሐፎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹንም አንብበን ነበር፡፡
የተራራው ስር መንገደኞችና የተራራው ጫፍ መሪዎች!
አንድ ቀን ታዳጊው ራምፓ አንድ ጋዜጣ የሚያነብ ሰው ጠጋ ብሎ ሲያጤን፣ ሰውየው የኮከብ ትንበያ የሚለው አምድ ላይ ተጠምዶ ነበር፡፡ ይህንን ሰው እያሰበ ወደ መምህሩ ሄደ፡፡
ገና እንደተገናኙ እንዲህ አለ … ‹‹… ሰዎች የየዕለቱን ወይም የሳምንቱን የኮከባቸውን ዜና ከየጋዜጣው ላይ ማጥናት አለባቸው እንዴ መምህር ?! … ››  
መምህሩም እንዲህ ሲሉ ይመልሳሉ፤ ‹‹ … ሎብሳንግ ራምፓ! በፍጹም እንዲያ ማድረግ አይገባም፡፡ ጋዜጦቹ ለሁሉም ሰው ምናልባትም በሺ እና በሚሊየን ለሚቆጠር አንባቢያቸው በጅምላ የሚያዘጋጁት ትንበያ ልክ ሊሆን እንደማይችል ማንም ዱልዱም ሊያውቅ ይችላል (ይገባልም!)፤ ዝም ብሎ የገበያ ጉዳይ ነው፣ ምን ያድርጉ ስራቸው ነው፡፡ ያው ማጭበርበር ነገር ነው…››
‹‹…የኮከብ ትንበያ የሚባል ነገር የለም ማለት ነዋ?!…››
‹‹…በርግጥ አለ’ንጂ ሎብሳንግ! … ትንበያውና ቆጠራው ግን መደረግ ያለበት ለተለየ ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ መንገዳቸውን ለተቸገሩና በህመም ለሚሰቃዩ ሰዎች ብቻ በአዋቂዎች መደረግ ያለበት ነው፡፡ ምን መሰለህ ህዝቡ (የቆጠራ እውቀት የሌላቸው ብዙዎቹ ሰዎች) በተራራው ስር ረጅሙን መንገድ እንደሚጓዙ መንገደኞች ናቸው፡፡ በእጃቸውም የሩቅ መመልከቻ መነፅር የላቸውም፡፡ ከፊት ለፊት የሚያጋጥማቸውን ኩርባና መሰናክል አያዩም፤ ነገር ግን ዝም ብለው ይጓዛሉ፡፡ ያው ሁሉንም በጊዜው ይጋፈጡታል፡፡ በተቃራኒው እውቀቱ ያላቸው ጥቂቶቹ ደግሞ፤ በተራራው ጫፍ እንደቆመና በእጁ የሩቅ መመልከቻ መነፅር እንደያዘ ሰው ናቸው፤ ከተራራው አናት ሆነው ከፊት ለፊት የሚመጡትንና ሰዎቹ የሚያጋጥማቸውን ኩርባዎችና መሰናክሎች ያያሉ፤ አንዳንዶቹንም አቅርበውና አጉልተው መመልከት ይችላሉ፤ ስለዚህ ለተወሰነ አገልግሎት ብቻ መንገደኞቹ የሚያጋጥማቸውን መሰናክልና ኩርባ እንዲያዩ ሊረዱና ሊያግዟቸው ይችላሉ፡፡››
ሎብሳንግ በመስማማት ራሱን ይነቀንቃል፡፡
በልዩ መንገድ አገልግሎት መስጠት!
ደግሞ ሌላ ቀን ከመንገዱ ጠርዝ ላይ የሚለምነውን አይነስውር ለማኝ ዜማ እያዳመጠ ይተክዛል፡፡ መንገደኞች ሳንቲሞችን እየወረወሩለት ይሄዱ ነበር፡፡ ለማኙም የሳንቲሞቹን ቅጭልጭልታ እየሰማ፣ ሳንቲሞቹ ሲወድቁ እንደ አዳኝ ድመት ቀብ ያደርጋቸዋል፡፡ ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ የሚያልፉት፡፡ እናማ ራቅ ብለው የወደቁትን ሳንቲሞች ደግሞ ሌሎች ሰዎች አንስተው መልሰው ይሰጡታል፡፡
ጥቂት አፍጥጦበት እንደቆየ ግን አንድ አዲስ ነገር ተረዳ፡፡ ደነገጠ፡፡ ሰውየው አይነስውር አልነበረም። እያስመሰለ ነበር፡፡ በሚገርም ሁኔታ ቤትና ንብረት እንዲሁም ሃብት ያለው ሰው ነበር፡፡
ታዳጊው ራምፓ እየሮጠ ወደ መምህሩ ሄደና አዲሱን ግኝቱን መንገር  ሲጀምር መምህሩ እየሳቁ ያወሩት ጀመር፤ ‹‹ ሎብሳንግ፤ ስለ ሰውየው አወቅህ ማለት ነዋ! … ነገሩንማ እኔም አውቃለሁ፣ ሰውየው እያታለለ ነው..››
‹‹ታዲያ ልናሳስረው ይገባ ነበር’ኮ፤ አታላይ ነው…››
‹‹…ለምን ተብሎ፡፡ ሰውየው’ኮ በጎ ሰው ነው፡፡ እንደማንኛውም ነጋዴ ልታየው ትችላለህ፤ በርግጥም ሰዎች ስባሪ ሳንቲማቸውን እየወረወሩለት ራሳቸውን እንደ ጻድቅ ይቆጥራሉ፣ ጊዜያዊ ደስታና እርካታን ይሠጥሃል ማለት አይደለምን፡፡ መንፈሳዊነትንና ቅድስናህን ይጨምርልሃል። ያንን አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በእርግጥ ጎጂ ሰው አይደለምኮ፣ ለምሳሌ አንዳንድ ታላላቅ የማስታወቂያ ሰዎች የውሸት ማስታወቂያ በመስራት እጅግ በብዙ ጉዳት ይነግዱና ያተርፉብን አይደለምን፡፡ እንዲያውም ጤናን ለዘለቄታ የሚጎዱና የሚመርዙ (በጊዜ ሂደት ገዳይ የሆኑ ጭምር!) ምርቶችን እንድንገዛ ያግባቡናል፡፡ እነርሱን ራሱ እያየን አላወገዝናቸውም፡፡ እናም ይሄ ሰውዬ ባይኖር ሰዎች በመስጠት የሚገኘውን ደስታና ኩራት ከየት ያመጡት ነበር-- ሎብሳንግ (በአካባቢያቸው ሌሎች ብዙ ለማኞች አልነበሩም!)፡፡ ዘራፊዎችስ ባይኖሩ ፖሊሶች ደምወዝ አይከፈላቸውምኮ፣ ስለዚህ ዘራፊዎቹ ለፖሊሶቹ ስራዎች፣ እንዲሁም የገቢና የመኖሪያ ምንጭ ናቸው። ሎብሳንግ አስታውስ! ይህ ምድር የትምህርትና ለመጪው ታላቅ ህይወት የመማሪያ ቦታ ነው፡፡ ››
***
ሎብሰንግ ራምፓ ‹the cave of the ancients!› በሚለው መፅሐፉ ውስጥ ጥቂት አብርሆቶችን ፅፏል። ምናልባት በጣም የሚያዝናና ሌላ እንድናስብ የሚያነሳሳ እሳቤ ነው፡፡ የተፃፈው ሁሉ እውነትና ቅዱስ ነውና ተጠመቁበት የሚለን አይኖርም፣ ነገር ግን እንደዚያም እንደዚህም ነጻ ሆነን ማሰብ እንደምንችል ይጠቁመናል፡፡  
ታዳጊው ራምፓ፤ ከላማ ሚንግያር ስር ስር እያለ ሲማርና ሲበራለት እንታዘባለን (በርግጥ ብሩህ ልጅ ነው)። በጣም ጎበዝና አሳቢ ስለነበር ጥሩ ጥሩ አስተማሪዎች ያስተምሩትና ያለውን (ብሩህ ጭንቅላቱን) ይበልጥ ያሳድግ ዘንድ እንዲረዱት ተመድበውለታል፡፡ መጽሃፉ ውስጥ እዚህም እዚያም ሄደን ስናበቃ፣ ጥቂት ርዕሶችን ብቻ እናንሳና እንይ።(ለመዝናናት ያህል!)
***
ነገሩ ሁሉ የመጠን ነው! - ይላሉ መነኩሴው አስተማሪ!
ታዳጊው ራምፓ አንድ ቀን በሰማዩ ላይ የተነሰነሱትን ከዋክብት እየተመለከተ ባለበት አንድ ምሽት ላማው (መምህሩ) ሰላምታ ከሰጡት በኋላ እንዲህ ይሉታል፤
 ‹‹…የሚያምር ምሽት ነው አይደለም ሎብሳንግ!››
‹‹…በጣም….›› ሲል በለሆሳስ ይመልሳል፤ አይኖቹን ከጽንፍ አልባው ህዋ ላይ ሰክቶ፣ እየተገረመና እየተደነቀ፤
አጠገቡ ቁጭ አሉና ወደ ሰማዩ እየጠቆሙ፤ ‹‹እኛና ነገሮቹ ሁሉ እንደነርሱ መሆናችንን ተገንዝበህ ይሆን?›› ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
ግራ ይገባዋል፡፡ እንዴት ሆኖ ነው እኛ ከዋክብት የምንመስለው፡፡ አትኩሮ ሲመለከታቸው ላማው ራሱ ከነዚህ የሚያምር  ግርማ ሞገሳቸው ጭምር ከዋክብትን ሊመስሉለት አልቻሉም፡፡ ልጁ የሚያስበውን የተረዱት አስተማሪው (ከዚህ በኋላ ላማውን አስተማሪው ወይም መምህሩ እያልን ብናወጋ ይቀለናልና!) እንዲህ ሲሉ ያብራሩለት ጀመር፤
‹‹ሎብሰንግ፤ ለማለት የፈለግሁት ቀጥተኛ ትርጉሙን አይደለም፡፡ ‹የምታያቸውን ነገሮች ሁሉ እንደምታያቸው ብቻ መረዳት የለብህም› ለማለት ነው፤ ለምሳሌ ‹ህዋ!› የሚል ጽሁፍ በወረቀት ላይ ፅፈህ ብትሰጣቸው ሰዎች ያነቡታል፣ አንድ ህንጻ በሚያካክል ፊደል ብትፅፈውም ይታያቸዋልና ያነቡታል፤ ነገር ግን ይህንኑ ፅሁፍ ፊደሎቹን አንድ አገር አሳክለህ ብትፅፈውና ከአንዱ ተራራ ላይ ብታቆመው ሰዎች የሚያነቡት ይመስልሃል! በጭራሽ! … አይታያቸውም (መጨረሻው አይታይም፤ ስለዚህ ትርጉም አልባ ሰፊ ህዋ መሳይ ይሆናል) ስለዚህ አያነቡትም፣ ስለዚህ አይገባቸውም። (ግን ደግሞ በዚያን ያህል ግዝፈት የሉም ማለት አይደለም) እነዚህ ከዋክብትም እንደዚያ ከመሆናቸው የተነሳ አንረዳቸውም…››
ስለ ከዋከብቱ የተነገረው ባይገባውም ስለ መጠን የተወራውን እያሰላሰለ ለመረዳት ግን አልቸገረውም ነበር፡፡ መጠን፡፡
አስተማሪው ቀጠሉ፤ ‹‹ ሎብሰንግ እስኪ ራስህን አስብ። እናም ይህ አካልህን እያኮሰስክ ለማሰብ ሞክር። በጣም እያነስክ፣ እያነስክ አስበው፡፡ ጉንዳን ብታክል፣ ከዚያ እስከ ደቃቅ የአሸዋ ቅንጣት ታህል ብታንስ ምን የሚፈጠር ይመስልሃል፡፡ እንዲያውም ከዚያም በታች ማነስ ይቻልሃል፣ አንሰህ፣ አንሰህ የአሸዋው ቅንጣት ለአንተ የምድርን አካል አክሎ እስኪገዝፍብህ ብትደቅና በዚያ መጠን ላይ ሆነህ እኔን ብትመለከት ምን የሚፈጠር ይመስልሃል…?››
አዕምሮው እንደ ልምሻ ሲሰነካከል ይታወቀው ነበር። ነገሩን ማሰላሰሉ በራሱ ከባድ ነው፡፡ አንሶ፣ አንሶ፣ አንሶ … ቅንጣት አክሎ ፣ እንዲያውም የአሸዋው ደቃቅ ቅንጣት በራሱ የአለምን ያህል እስኪተልቅበት አንሶ … ምን ሊታየው ይችላል፡፡ ከባህር ወጥቶ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸዋ ላይ እንደተጣለ አሳ አፉን ከፍቶ መተንፈስ ጀምሮ ነበር፡፡
‹‹ሎብሳንግ፤ በዚያች ቦታ ሆነህ የምታየው የእኔ አካል የሚታይህ ልክ እንደዚያ ሰማይ ላይ እንደተበታተኑት ከዋክብት የተበታተነና የሚንሳፈፍ፣ ህልቆ መሳፍርት የሆነና ወሰን አልባ ህዋ ሆኖ ነው፡፡ ለምን መሰለህ፤ እንዲያ እስከ ቅንጣት ድቃቂ ካነስክ የምታየው ነገር ሰውነቴ የተገነባበትን ሞለኪውል ይሆናል፡፡ እነዚህ ሞለኪውሎች በህልቆ አልባው ህዋ ገላዬ ሲንሳፈፉ ነው ልታይ የምትችለው፡፡ አካሌን ሙሉውን ልታየው አትችልም፤ ልክ አሁን እኔና አንተ አለም (ሉሏን) እዚህ ቁጭ ብለን እንደማናያት ሁሉ፡፡ አለማት፣ ጋላክሲዎችና ከዋክብት በአለማትና በፀሃያቸው ዙሪያ ሲዞሩና የመሳሰለ ትዕይንት ነው የሚታይህ፤ እዚሁ እኔው ላይ…›› አይኖቹን ጨፍኖ ምስሉን ለማስተዋል ይሞክራል፡፡
‹‹ሎብሳንግ … ከልብህ እየተከተልከኝ እንደሆነ አይኖችህ ይናገራሉ--›› ፈገግ ብለው ቀጠሉ፤ ‹‹…ቆይማ እስኪ ሹራብህን ተመልከት፡፡ ዳስሰውና አጢነው። ለስላሳ የሆነ ልብስ ነው እንደምትል ይገባኛል፡፡ በውስጡም አሳልፈህ ልትመለከት አትችል ይሆናል። አስር ግዜ በሚያጎላ ሌንስ ብትመለከተው ግን ሌላ ነው፡፡ እያንዳንዷን የክር ውቅር አስር ግዜ አጉልተህ ትመለከታለህ፡፡ እናም በመሃሉ ብርሃን ማየትና ማሳለፍ እንደሚቻል ትረዳለህ፡፡ ስለዚህ አሁን እንደምታየው አይደለም ማለት ነው፡፡ በቅንጣት ደረጃ ዘና ብለው ማለፍ የሚችሉ እጅግ ብዙ ነገሮች አሉ ማለት ነው፡፡››
የገባው መሆኑን ጭንቅላቱን በመነቅነቅ ያሳያል …
‹‹…ሚሊየን ግዜ በሚያጎላ ሌንስ ብናየውስ ምን ይከሰት ይመስልሃል? በእርግጠኝነት በክፍተቱ መሃል ፈረስ መጋለብ ያስችላል ብሎ መወራረድ ይቻላል፤ ሎብሳንግ፡፡ እንዲያውም በሚገርም ሁኔታ አንዷ ክር ብቻዋን ጋልበህ የማትወጣት ተራራ መሆኗን ትረዳለህ። እናም ነገሩ ሁሉ እንዲያ ነው፡፡ አንተም አንሰህና ደቀህ እኔን የምትመለከት ቢሆን የምታየው ያንን ነው…››
***
ነገርየው ግራ ይገባል፡፡ ግን ደግሞ ስታሰላስለው ይገባሃል፡፡ ያ ማለት በድቃቂና በቅንጣት ደረጃ የተዋቀርን ስለሆነ ሙሉ መስለን እንታያለን እንጂ የቁርጥራጭ ነገሮች ስሪት ነን፡፡ ሁሉም ነገርም እንዲያ ነው፡፡ ምንም ሙሉ የሆነ ነገር የለም፡፡ ሁሉም የግጥምጥሞሽ ውጤት ነው፡፡ እናም አንሰን የተሰራንበትን ሞለኪውል ማየት ከቻልን፣ ሙሉው ነገር ህዋ እንጂ አንድ ብቻውን የሆነ ነገር አይደለም፡፡
የምናየው አለምና ህዋ ራሱ የአንድ ግዙፍ አካል ክፍሎች ይሆኑ ይሆንን፣ ወይስ ምን፡፡ እኛ እጅግ ደቀን ስላለን ይሆን ይሆናል፡፡ እውነት ግን አንዲት ቁጫጭ እንኳ እግሬ ስር ብትቆም መላው እኔን ታያለች ማለት አይቻልም። እንዲያውም ጫማዬን እያጤነች እንደ ዓለም ሳትቆጥረኝ ይቀራልን?! እናም እኔም ከጋላክሲያችን እግር ስር ቆሜ ነው የማየው ማለት ነው፡፡
በግድግዳው ውስጥ መዝለቅ ትችላለህ!
‹‹አየህ ሎብሳንግ፤ አንተ ራሱ ያንን ያህል ማነስ ብትችል በግድግዳ ውስጥ ቀጥታ ማለፍ ትችላለህ…››
ግራ ሲገባው ይቁለጨለጫል …
‹‹…ከእያንዳንዱ ግድግዳው ከተገነባበት ሞለኪውል ካነስክ ያንን ታደርጋለህ፡፡ ይህ ህያው  መስሎ ከፊትህ የቆመው ግድግዳ የተዋቀረው ከተርገብጋቢ ሞለኪውሎች እንደሆነ አውቀናል፡፡ ሞለኪውሎቹ ደግሞ የተጣበቁ ሳይሆኑ ተለያይተው የሚርገበገቡ ናቸው፡፡ እናም በመካከላቸው ባለው ክፍተት ማለፍ ከቻልክ፣ በግድግዳው ውስጥ ትዘልቃለህ ማለት ነው። ልክ የሙታን መንፈሶች በግድግድዳው ውስጥ ያለ ችግር እንደሚዘልቁ ማለት ነው…››
‹‹…ግን…››
‹‹…ነገሩ እንኳ እንደምታየው ህዋ የጠራ ነው፡፡(በርግጥ የምናየው ህዋ ለአይናችን የጠራ ነውና!) ግና ቀስ እያለ ይበራልሃል አትቸገር፡፡ ትረዳዋለህ ሎብሳንግ። አሁን ቀድሞ የጀመርነውን ሃሳብ እንጨርስ…›› ይሉና ወደ ሌላው ሃሳብ ዘው ይላሉ፡፡ …
***
ነገርየው አሁንም ግራ ነው፡፡ እንደገና ማሰብና መመራመር ይጠይቃል፤ ወይም ደግሞ አይጠይቅም ይሆናል!
***
የምትኖረው በድጋሚ እየመጣህ በመወለድ ነው። ወደዚህ ሲኦል ደጋግመህ የምትመጣውም ለመማር ነው፡፡
ስለ ነፍስና ስለ ሌላ አለም እንዲህ ሲሉ ውይይታቸውን ያደምቁታል … ‹‹…አየህ ሎብሳንግ ራምፓ … ነብስያህ ወደ ምድር የምትመጣው ለሚቀጥለው ህይወት የሚያስፈልጋትን ትምህርት ልትቀስም ነው፤ በመጣችበት ወቅት የቀራትን ትምህርት ተመልሳ ትወስዳለች…››
‹‹…እንዴት…?›› ይላል ታዳጊው ራምፓ፡፡
‹‹…ለምሳሌ በዚህኛው ህይወትህ በጣም ጨካኝ ሆነህ ካሳለፍክ፤ ለሚቀጥለው ስትመጣ ነብስያህ ጎድሏት የነበረውን ነገር የሚሞላ ቤተሰብ ወዳለበት ጎራ ትላለች፤ እናም ከዚያ ካለችው እንስት ማህፀን ሽል ውስጥ ትገባለች፣ አዲስ ሰው ሆነህ ትወለድና የሚገባውን ሌላ ትምህርት ትቀስማለህ፡፡ ሌሎች ደግሞ ያንን እንዲያግዙ ይወለዳሉ፤ … ብዙ ሃይማኖቶች ገሀነም ስለመኖሩ ያስተምራሉ፣ ሆኖም ገሀነም ራሱ እዚህ ነው ያለው፡፡ እውነተኛው ህይወታችን ገና በሌላኛው ስፍራ ነው፡፡ እዚህ ትምህርት ላይ ነን፡፡ አሁን የሚሰቃይ ሰው በባለፈው ህይወቱ በደል የፈፀመ በመሆኑ እየተቀጣና እየተማረ ነው፡፡ ያጠፋውን ጥፋት የማስተካከያ ድጋሚ ዕድል ነው፡፡ በአጠቃላይ የጎደለውን ለመሙላት ነው የሚመላለሰው፡፡ ደጋግሞ ይመላለሳል፡፡…››
አንድ የማይገባው ነገር አለ፡፡ ለትምህርት ደጋግመን የምንፈጠር ከሆነ፣ ህጻናትና የተወለዱ ለምን ይሞታሉ፡፡ ምን ተማሩና ይሞታሉ፡፡ ሲል ያሰላስላል፡፡
መምህሩ ይቀጥላሉ፤ … ‹‹…ሎብሳንግ! እርሱ ደግሞ ምን መሰለህ…›› … ፈገግ ብለው ያሰላስላሉና ‹‹…ለምሳሌ አንድ ሰው 30 ዓመት እንዲኖር ታስቦ (ምን ያህል ልንቆይ እንደሚገባ ቀድሞ የታቀደ ነው!) ወደ ምድር ይመጣል። ነገር ግን ህይወቱ የብስጭትና የተስፋ መቁረጥ ይሆንና ቀድሞ መሄድ ይፈልጋል። በ28 ዓመቱ ራሱን ያጠፋና ይሞታል እንበል፡፡ ልብ በል! ሰውየው 2 ዓመት ሲቀረው በራሱ ፍቃድ ሞቷል (ሄዷል!)፡፡ ስለዚህ በድጋሚ ሲመለስ መጀመሪያ በዚያኛው ጊዜ የቀረውን 2 ዓመት አሟልቶ እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ የ2 ዓመት ልጅ ሆኖ ድጋሚ ያልፋል ማለት ነው…››
‹‹…ግን …›› ይላል ታዳጊው ሎብሳንግ ራምፓ …
‹‹…እ… አዎ! ወላጆቹ! … ልክ ነህ! እነሱ ደግሞ የምትወደውን በማጣት የሚገኘውን ትምህርት እንዲያገኙ የመጡ ናቸው፡፡ በመውለድ ከሚገኘው ደስታ ባሻገር በማጣት የሚመጣውን ሀዘን ይማራሉ! … ልብ በል ሎብሳንግ! ይህኛው አለም ጊዜያዊና የሲኦል ቦታችን ነው፡፡ ሁላችንም የመጣነው ለሌላው ዓለም በቂ ትምህርት እንድናገኝ ብቻ ነው…››
***
እና እላለሁ እኔ ብቻዬን ስቆዝም፤ ምናልባት በበፊት ህይወቴ ስንፍና ያበዛሁ ሰው በመሆኔ አሁን ጥረትና ልፋት እንዳውቅ የተላክሁ ሰው መሆን አለብኝ።
ሁሉንም አንብብ፣ ዝባዝንኬ ሁሉ ግን ጭንቅላትህ ውስጥ አታጭቅ!
ከንጂ የሚባለው ጃፓናዊ መነኩሴ በማንበብ ብዛት ተሳክሮበት አብዷል፡፡ እናም ራምፓ ስለ ሰውየው ማበድ እያሰበ እያለ አስተማሪው ስለምን እያሰበ እንደነበረ ተረዱና ማብራራያውን ይሰጡት ጀመር፡፡ (ሰዎች እርስ በርስ ለመግባባት ንግግር አያስፈልጋቸውም፡፡ የሚያስቡትን ሳይነገራቸው በቴሌፓቲክ ያውቃሉ፡፡ እንደ ዋይርለስ የሆነ ግንኙነት ልንል እንችላለን፡፡ ሰው የብቃት ደረጃው ላይ ሲገሰግስ ይህ ቀላል ነው ይላሉ፡፡)
‹‹ልክ ነህ ሽማግሌው ንክ ስለሆነ አይደለም። ለአመታት ያገኘውን ሁሉ በማንበብ አእምሮውን አጨቀው፡፡ ማንበቡ አይደለም ክፋቱ፣ ክፉቱ ሁሉንም እንደ እውቀት በጭንቅላቱ ማጨቁ ነው፡፡ የሚጠቅመውንም የማይጠቅመውንም ለማጣጣም ታገለ፡፡ በመንፈስ ከፍ እንዳለ ምሁር ራሱን ይቆጥራል፣ እውነቱ ግን ምስኪን ነው፡፡ መንፈሳዊነቱ ከስሯል። ሁሉንም ያውቃል ግን አልተረዳም፡፡ ሁልጊዜ እንደ ወንዝ ንባቡን ብቻ የሚከተል ሰው ጥሩ አይደለም፡፡ በጎ ብቻ ሳይሆን የተፃፈ ሰይጣናዊ ነገር ስላለ፡፡››
‹‹ታዲያ መፅሃፍ ማንበብ የሚጎዳ ከሆነ መፅሃፉ ለምን አስፈለገ…?›› ሲል ይጠይቃል ራምፓ፣ አሁን አገኘኋቸው ብሎ እያሰበ፡፡
ፈገግ ብለው፤ ‹‹…ሎብሳንግ ይህማ ቀላል ጥያቄ ነው፡፡ ህጉ የሚለው አንብብ፣ አንብብ፣ አንብብ ነው። አንብብ ግን ያነበብከው ሁሉ በምርጫህ ውስጥ ዘው እንዲል አትፍቀድ፡፡ መፅሐፍ ሊያስገርምህ፣ ሊያማክርህና ሊያስተምርህ ይችላል። ሆኖም ሁሉ መፅሐፍ በጭለማ የምትከተለው መሪ ኮከብህ አይደለም፡፡ ማንም ሰው ባነበበው መፅሐፍ ሃሳብ ዥው እያለ መወሰድ አይገባውም፡፡ ምናልባት ያነበብከው መፅሐፍም እኮ የአንድ ሰው ስራ ነው፡፡››
ታዲያ መፅሐፍ ስለ ማንበብ ምን ያስጨንቀኛል? እያለ ያስባል ሎብሳንግ ራምፓ …
‹‹…መፅሐፍ…›› ሲሉ ይቀጥላሉ አስተማሪው.. ‹‹መኖር አለበት ሎብሳንግ፡፡ የአለም እውቀት ያለውም እኮ በላይብረሪዎች ነው፡፡ እንደ ማጣቀሻና እንደ ታሪክ ተራኪም ነው የተቀመጡት፡፡ ያለ አግባብ የተረጎምከውና የተከተልከው ገደል ሊከትህ ይችላል። አለምን አስሰህና ጎብኝተህ አትጨርሰውም፡፡ ያንን ሁሉ ማድረግ ከፈለግህ ደግሞ መፅሐፍ ነው አማራጭህ ሎብሳንግ … ››
ለጨጓራህ ምቾት ተጨነቅ!
አንድ ቀን ራምፓ የበላው ምግብ ሽቅብ እየተመለሰበት እያለ ያንን ሽማግሌ ጃፓናዊ ከጎኑ ያየዋል፡፡ (በርግጥ በየዕለቱ የሚመገቡት አንድ አይነት ምግብ ብቻ በመሆኑ ሎብሳንግ ራምፓ እጅግ ይማረር ነበር፡፡ በዕለቱ የቀረበው የገብስ ቆሎ ከማረሩ የተነሳ ሊውጠው ሲሞክር ከሆዱ ያለውን ሁሉ ቀላቅሎ ሽቅብ ተመለሰ …)
‹‹…አንተም እየቀነስክ ነው’ንዴ ልጅ! ምግቡ ይደብራል አይደለም’ንዴ! ልክ ያንተው አይነት ችግር እኔም ደርሶብኝ ነበር ወጣቱ ልጅ!…››
‹‹…ጌታዬ...›› ይላል ራምፓ በሰለለ ድምጽ … ‹‹.እዚህ በእድሜዬ ሁሌ ሻይና ፃምፓ ፣ ፃምፓና  ሻይ፣ ሻይና ፃምፓ … መብላት ታከተኝ፡፡ እርሶ አለምን ዞረዋልና ብዙ አይነት ምግቦች በልተዋል፡፡ ለመሆኑ የሌሎቹ ምግብ ምን አይነት ጣዕም አለው?›› (ሌላ አይነት ምግብ ቀምሶም አያውቅም ታዳጊው ሎብሳንግ)
‹‹…አየህ ወጣቱ ልጅ! … አስር አይነት ምግብ ቀላቅሎ መመገብ እንደማይጠቅም እነግርሃለሁ፡፡ ጨጓራ ቀጥሎ የምትበላውን ምግብ ካወቀ ለምግቡ መፈጨት የሚያገለግል ፈሳሽ ያመነጭና ይዘጋጃል፤ እና ምግብ መፈጨቱን ያግዛል፣ በብቃት ይሰራል፡፡ የተለያየ ከሆነ ግን ጨጓራህ ለመፈጨት ዝግጅቱ ግራ ይገባዋል። እናም ሳይፈጭ የሚያስጨንቅ ምግብ እየተሸከምክ ትውላለህ፡፡ የጨጓራና የሌሎች በሽታዎች ታማሚና ተጠቂ ትሆናለህ፡፡ አየህ ልጅ! የኛን ሽማግሌዎች  ተመልከት እስቲ (ሩቅ ምስራቆችን)፤ በጣም ጠንካራና እጅግ ብዙ ጊዜ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ይህንን ምክሬን ተከተል፤ በጤና ትኖራለህ፡፡ ከዚያኛው ተቀላቀል፣ ያው የሚከተለውንም ሸክም ተሸከም … ›› ሽማግሌው ፈገግ ይላሉ፡፡
መምህሩ የሚመጣው ተማሪው ዝግጁ ሲሆን ነው!
በመጨረሻው አንድ ቀን ሎብሳንግ፣ ከተራራው ላይ ቤቱ በመስኮት በሃዘን ይመለከት ነበር፡፡ እነሆ ሽማግሌው ጃፓናዊ እብድ ወደ መነሻዎቹ ተመልሷል (በስጋ ሞቷል!)፡፡ ሎብሳንግ በሃሳቡ ብዙ ያወጣ ያወርድ ነበር፡፡ ‹ወደ ምድር መቼ ይመለስ ይሆን! ፣ በርግጥ ብዙ እውቀቶች ያሉትና ብዙ ያጠና ሰው ነው፡፡ እናም ምንም የቀረው ምድራዊ ትምህርት ያለ አይመስልም፣ አሁን ይህን ጊዜ ነፍስያው የዘመናት ስራዎቿን እየገመገመችና የጎደላትን እያጠናች ይሆናል፡፡ እናም ምናልባትም ከመቶ አመት በኋላ ይመለስ ይሆን ወይስ…?››
ሎብሳንግ ይህንን እያየ የቀብር አስፈፃሚዎቹ (ቀብር እንኳ የለም)፣ ራግያቦች አጅበውት ወደ ተራራው እየወጡ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ስራቸው እንዲህ ነበር፡፡ የሰውየውን አካል ወደ ተራራው አናት ይዘው ይወጣሉ፣ በዚያም ስል የሆነ መሳሪያዎቻቸውን ተጠቅመው ይቆራርጡትና ለአሞራዎቹ ይሰጧቸዋል፡፡ (ጆፌና ጥንብ አንሳዎቹ ይህንኑ እየጠበቁና እየተመገቡ በዚያ አሉ!)
በርግጥ እንዲያ ነበር የሚሆነው፡፡ አለበለዚያ በዚህ ድንጋያማና ቀዝቃዛ በሆኑት የተራራው ጫፎች መቃብር መቆፈር እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ የድንጋይ ኮረብታ ፈንቅለህ ብትቀብረውም ከቅዝቃዜው የተነሳ ሬሳው አይበሰብስም። ከቀናት በኋላ ድንጋዮቹ ሲፈነቃቀሉ ተመልሶ እንዳለ ይወጣል፡፡
እና የሽማግሌ ጃፓናዊውን መመለሻ ጊዜ ሲያሰላስል በሆነ ወቅት የነገሩትን በአእምሮው ያስታውሳል፤ ‹‹...መምህሩ የሚመጣው ተማሪው ዝግጁ ሲሆን ነው፡፡ እናም መምህሩ ሲመጣ ደግሞ የሚነግርህን አድርግ!… ›
“the master always comes when the student is ready and when you have a master do every thing he says, for only then are you ready …”
**
(ይህንን ፅሁፍ ከዚህ ቀደም የሆነ ቦታ ያነበብኩ ያነበብኩ ይመስለኛል፤ እናም አንዳንዴ ‹እንደ እኔ የሚያስብና አማርኛን እንዲሁ እንደ እኔ አድርጎ የሚፅፍ ነበር ይሆን እንዴ ትላለህ!›
ሃሳቦቹ ሁሉ የተወሰዱት ተራ በሆነ መረዳትና ቀጥተኛ (መስመር በመስመር) ባልሆነ ትርጉም ነው፡፡  
(T. LOBSANG RAMPA, THE CAVE OF THE ANCIENTS, CORGI BOOKS, 1ST PUBLISHED IN 1963.)

Read 2373 times