Sunday, 06 May 2012 14:40

ተቃዋሚዎች የድንኳን ስብሰባ ይልመዱ! (cost effective) ነው!

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(1 Vote)

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ ተፍ ተፍ ማለት መጀመራቸውን ሳትሰሙ አትቀሩም፡፡ መሃል ላይ ግን ምን ተከሰተ መሰላችሁ? አንድ ቅኝታዊ ጥናት ተሰራና አብዛኛው አሜሪካዊ ከኦባማ ይልቅ ባለቤታቸውን ሚሼልን የበለጠ እንደሚወድ ተረጋገጠ፡፡ ኦባማ በዚህ አልተቀየሙም (ሚስቴ ተወደደች ብለው እንዴት ይቀየማሉ?!) ይልቁንም ይሄንን የባለቤታቸውን ተወዳጅነት ለምርጫ ዘመቻው እንዴት እንደሚጠቀሙበት ሲያስቡ ቆዩና የሚከተለውን የምረጡኝ ቅስቀሳ ፈጠሩ:- “የሚሼልን ባለቤት ምረጡ!” የሚል፡፡ (ደስ የሚል ፖለቲካዊ ፈጠራ አይደል!)

አሁን በቀጥታ የፈጠራ ድርቅ ወደመታው ፖለቲካችን እንግባ፡፡ ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ የፊት ለፊት ገፅ ላይ የወጣ አንድ ዜና “ኢዴፓ የምስራቅ አፍሪካ የሊበራል ፓርቲ ኮንፍረንስ ሊያካሂድ ነው” ይላል፡፡ መቼ መሰላችሁ? ዛሬ! ነገርዬው የሊበራል ፓርቲ በሚል ተሸፋፈነ እንጂ በኮንፍረንሱ የሚሳተፉት እኮ የአፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮች ናቸው፡፡

ይሄን ለማወቅ ግን እንደኔ ሙሉ ዘገባውን ማንበብ ይጠይቃል፡፡ (ርዕሱ ሽፍንፍን ነዋ!) ዜናውን አንብቤ ሳጠናቅቅ “ይኼኔ ኢህአዴግ ምን ብሎ ይሆን?” አልኩ - ለራሴ (ከሰማ ማለቴ ነው!)

እኔ እንደው ዝም ብዬ ይሄን ጥያቄ አነሳሁት እንጂ ነገርዬው ኢህአዴግን የሚያሳስብ አይመስለኝም፡፡ አያችሁ … ኢዴፓ ከአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ጋር ግንባር ወይም ጥምረት ከሚፈጥር ይልቅ ከአፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ጉባኤ ቢሳተፍ (ጠበል ቢጠጣ እንደማለት!) ለኢህአዴግ ተመራጭ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? የኢዴፓ ከአፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ማበር መቼም ቢሆን ለኢህአዴግ ሥልጣን ስጋት አይሆንም (Risk - Free ነው!) በእርግጥ የተቃውሞ ልምዳቸውን ለኢዴፓ ሊያስኮርጁት ይችላሉ (በኩረጃ ግን ሥልጣን አይገኝማ!)

እናላችሁ… ባለፈው ቅዳሜ ይሄንን የሊበራል ፓርቲዎች ጉባኤ ዜና ከኮመኮምኩ በኋላ የኢህአዴግ ቀንደኛ አፍቃሪ የሆነውን የልጅነት ጓደኛዬን መንገድ ላይ አገኘሁት፡፡ ከዛ በጠራራ ፀሃይ ድራፍት ቤት ይዞኝ አይገባ መሰላችሁ! ሁለት ሁለት ጃንቦአችንን እንደቀነደብን የፖለቲካ ወሬ ተነሳ (አቧራው ጨሰ!) አስቡት እንግዲህ … ድራፍት፣ ፖለቲካና ጠራራ ፀሃይ ሲገናኙ ምን እንደሚፈጠር! ጓደኛዬ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ስለኢህአዴግ ልማታዊ ሥራዎች እንደ ጉድ ደሰኮረልኝ - ኢቴቪን የዋጠ እስኪመስለኝ ድረስ፡፡ እኔ ደሞ በተራዬ የኢዴፓን የሊበራል ፓርቲዎች ጉባኤ ደሰኮርኩለት ኢዴፓን የዋጥኩ እስክመስል ድረስ፡፡ ትንሽ ካዳመጠኝ በኋላ ደም ስሮቹ ተገታትረው፡- “እንኳን የአፍሪካ ተቃዋሚዎችን ለምን የአውሮፓና የማርስ ተቃዋሚዎችን አያመጣም … ኢህአዴግ የሚቦካ መስሎት ነው!” ሲል ደነፋብኝ (የሰፈር ድብድብ አስመሰለው እኮ!)

እኔም ጃምቦው ገፋፍቶኝ ነው መሰለኝ ይለይለት ብዬ “ቆይ አንተ … አይቦካም ነው የምትለው?” አልኩት፡፡

“አይቦካም!” አለ ፍርጥም ብሎ፡፡

“እንዴት?” ጠየኩት

“ኢህአዴግ በትግል የተፈተነ ነዋ!”

“ሌላውስ?”

“በየሆቴሉ ከመሰብሰብ ውጭ ምን ያውቃሉ … ዲስኩርና ትግል እኮ ይለያያሉ!”

“ይሁንልህ” አልኩት - በልቤ፡፡ (ፍሬንድ ነዋ!) ከዚያም በዘዴ ወደ ሌላ የወሬ አጀንዳ አስቀየስኩት፡፡ አንድ አንድ ጃንቦ ከጨመርን በኋላ በራሳችን ፈቃድ ወደ የጉዳያችን ተበታተንን፡፡

ጓደኛዬ የአፍሪካ ተዋቃሚ ፓርቲዎች አዲስ አበባ መጡ ስለተባለ ብቻ እንዲያ መንጨርጨሩ ግርም ስላለኝ ስለ ኢህአዴግ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ መነሻዬ ላይ ያነሳሁትን ጥያቄ ደግሜ አወጣ አወርድ ጀመር - “እውነት ኢህአዴግ ምን ብሎ ይሆን?” …የአፍሪካ ተቃዋሚ ሁላ መዲናዋ ላይ ከትሞ ስለተቃውሞ የልምድ ልውውጥ ሲያደርግ!

መቼም ምንም ቢሆን የአፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በአገር ቤቶቹ ዓይን አያያቸውም ብዬ እንጂ… በተለያዩ የስጋት ሃሳቦች ተወጥሬ ነው የሰነበትኩላችሁ! “ኢህአዴግ ምን ብሎ ይሆን?” እያልኩ፡፡

ኢህአዴግ እንግዶቹን ተቃዋሚዎች፤ የአገር ውስጥ ተቃዋሚዎችን በሚያይበት መነፅር ካያቸው እኮ ነገር ዓለሙ ብልሽትሽት ነው የሚለው፡፡ አያድርገውና … “ተቃዋሚ ሲባል አንድ ነው!” በሚል እንደ አገር ቤቶቹ ቢሞልጫቸውስ? ይታያችሁ … “የሻዕቢያ ተላላኪ!” “ሽብርተኞች!”፣ “ሰላም አደፍራሽ!” ወዘተ የሚል ታፔላ ተለጥፎላቸው ወደ አገራቸው ሲላኩ! (የአገር ገፅታ ግንባታ ባፍጢሙ!) የምንታወቅበት የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችንም ያከትምለታል ማለት እኮ ነው!

ልብ አድርጉ! እንግዶች ስለሆኑ ይከበሩ ብዬ እንጂ ተቃዋሚዎቹ በየአገራቸው እንደ አያት የሚያሞላቅቁ ገዢ ፓርቲዎች አሏቸው እያልኩ እኮ አይደለም፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ከኢህአዴግ ባይብሱ ነው፡፡ ምናልባትም እኮ ተቃዋሚዎቹ ለጉባኤ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን እንደ ሱባኤ ቆጥረውት ይሆናል - ከገዢ ፓርቲ ቁንጥጫ፣ ወከባና እስር ተገላገልን ብለው፡፡ እናም ትንሽ ዘና ብለው ቢሄዱ ለአገር ገፅ ግንባታ ይጠቅመናልና በአክብሮት እናስተናግዳቸው፡፡ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለልኝ:- ግን ለምን ቤተመንግስት አይጋበዙም? (ችግር አለው?!) ችግር ካለው ይቅር!!

ሌላው ያሳሰበኝ ደግሞ ምን መሰላችሁ? የአዳራሽ ጉዳይ ነው፡፡ ኢዴፓ በደንብ አስቦበት ይሆን? “መድረክ” ፓርቲ በተደጋጋሚ ያሰማው ቅሬታ ትዝ ብሎኝ እኮ ነው፡፡ “መሰብሰቢያ አዳራሽ አጣን!” ያሉትን ማለቴ ነው፡፡ ለነገሩ በመዲናዋ የአዳራሽ ችግር ኖሮ እኮ አይደለም! አንዳንድ አዳራሽ የሚያከራዩ ተቋማት፤ ተቃዋሚዎች ቤታችሁ ከተሰበሰቡ ቢዝነሳችሁ መቅኖ ያጣል ተብለዋል መሰለኝ (በልማታዊ ኮከብ ቆጣሪ!) የተቀበሉትን ገንዘብ እየመለሱ “ስብሰባ አይካሄድም” ይላሉ አሉ፡፡ “መድረክ” እኮ አንዴ ሳይሆን ሁለት ሦስቴ ገንዘብ ከፍሎ አዳራሽ ከተከራየ በኋላ   “ኑና ገንዘባችሁን ውሰዱ!” ተብሎ ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለመሰረዝ ተገዷል፡፡ ለጠ/ሚኒስትሩ ሳይቀር አቤቱታ ማቅረቡም አይዘነጋም - በፓርላማ ጉባኤ፡፡ እናም ኢዴፓም ተመሳሳይ የአዳራሽ ችግር እንዳይገጥመው ከወዲሁ እንዲያስብበት ብዬ ነው፡፡ እንዴ … አገር አማን ነው ብሎ የአፍሪካ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ይዞ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሲያመራ “ገንዘብህን እነሆ! ስብሰባው እዚህ አይካሄድም!” ቢባልስ …  የማን አለህ ሊል ነው! (ቅሌት ነው!)

የአሁኑን ጉባኤ ኢዴፓ እንደምንም ይወጣው እንጂ ለወደፊት አሪፍ ብልሃት ብልጭ ብሎልኛል፡፡ ምን መሰላችሁ? አሪፍ ድንኳን!! አዳራሽ ያከራዩት ሆቴሎች ወይም ኢንተርፕራይዞች ድንገት ተነስተው “ሃሳባችንን ቀይረናል … ገንዘባችሁን እነሆ” ሲሉ ከመወናበድ … ደህና ግቢ ፈልጐ ድንኳኑ ይተከልና ኮንፈረንሱንም ሆነ ሲምፖዚየሙን ወይም ሌላ ሌላውን ማካሄድ ይችላል፡፡ (ችግር ፈቺ ትውልድ ይሏል ይሄ ነው!!)

እናላችሁ… ከዛሬ በኋላ የትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ (የአፍሪካ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ) የስብሰባ አዳራሽ ሲያጡ ድንኳንን በአማራጭነት መጠቀም እንዲለማመዱ ይመከራሉ! በወጪም በኩል ልዩነቱ የሰማይና የምድር ያህል ነው፡፡ (ድንኳን Cost effective ነዋ!) ተቃዋሚዎቹም  በመከራ ያገኙዋትን ገንዘብ ለሆቴል አዳራሽ ከሚገብሩ ድንኳን መትከል አይሻልም? (ሺ ጊዜ ይሻላል!)

ተቃዋሚዎች ሆይ፡- ገዢው ፓርቲ እኮ አራት ኪሎ ቤተመንግስት ሰተት ብሎ የገባው በየተራራውና በየዛፍ ጥላ ሥር ተሰብስቦ ነው (ዛፉም ሲገኝ ነው!) እናም በዲኮሬሽን ያሸበረቀ አዳራሽ የግድ አይደለም (ዋናው መሰብሰቡ ነው!) የሆቴሉ ስብሰባ ከሥልጣን በኋላ ይደርሳል!!

የፖለቲካ ወጌን በቀልድ እንደጀመርኩ በቀልድ ልቋጨው፡፡

በዓለም ላይ የተከሰተው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ክፉኛ ያሳሰበው የተባበሩት መንግስታት (UN) በመላው ዓለም ቅኝታዊ ጥናት አድርጐ ነበር አሉ - ባለፈው ወር፡፡

ለጥያቄ ለተመረጡት ሰዎች የቀረበው ብቸኛ ጥያቄ ምን መሰላችሁ?

“በቀረው ዓለም ለተከሰተው የምግብ እጥረት መፍትሄ የሚሆን ቅን አስተያየታችሁን እባካችሁ አጋሩን” የሚል ነበር፡፡

ቅኝታዊ ጥናቱ ግን ትልቅ ኪሳራ ነበር ብሏል - UN ምክንያቱም ….

በምስራቅ አውሮፓ “ቅንነት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም

በምዕራብ አውሮፓ “እጥረት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም

በቻይና “አስተያየት” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም

በአፍሪካ “ምግብ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም

በመካከለኛው ምስራቅ “መፍትሄ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም

በደቡብ አሜሪካ “እባካችሁ” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም

በአሜሪካ “የቀረው ዓለም” ማለት ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም

 

 

Read 3448 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 14:49