Sunday, 03 June 2018 00:00

በሃገሪቱ 1.5 ሚሊዮን ዜጎች ለጎርፍና ተያያዥ አደጋዎች ተጋልጠዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የመሬት መንሸራተት አስጊ ሆኗል

    በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች እየጣለ ባለው መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ በሆነ ዝናብ ምክንያት በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት 39 ሰዎች መሞታቸው የታወቀ ሲሆን በቀጣዩ ክረምት 1.5 ሚሊዮን ዜጎች ለጎርፍ አደጋ ተጋልጠዋል ተባለ፡፡
ከሠሞኑ በደቡብ ክልል በስልጤ ዞን፣ ከባድና ተከታታይ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ በተፈጠረ የመሬት መንሸራተት 7 ሰዎች፣ በደቡብ ክልል ጋሞ ጎፋ በተመሣሣይ አደጋ ዘጠኝ ሰዎች እንዲሁም በደቡብ ክልል በሲዳማና በአርሲ ዞን አዋሳኝ አካባቢ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉን፣ ከፌደራል የአደጋ መከላከልና ስጋት አመራር ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ይህ ሁኔታ በቀጣይ ምን መልክ ይኖረዋል በሚለው ጉዳይ ለአዲስ አድማስ መረጃ የሰጡት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሣ፤ በሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት የመሬት መንሸራተት አንዱ የአደጋ ዘርፍ እየሆነ ነው ብለዋል፡፡ ችግሩም አሣሣቢ ደረጃ መድረሡን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ የሰዎች ህይወትም እየቀጠፈ ነው ብለዋል፡፡
ለመሬት መንሸራተት አስጊ እየሆነ መምጣት በአካባቢ ጥበቃ ጉድለት ደን መራቆት መከሠቱ፣ ሠዎች ተዳፋታማ አካባቢዎች መስፈር መጀመራቸው እንዲሁም የአፈር አይነት ምክንያት መሆናቸውን አቶ ምትኩ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡  ይህ ችግር በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ሊያጋጥም የሚችልበት እድል መኖሩን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ በተለይ በደቡብ እና በኦሮሚያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፣ የክረምቱ ዝናብም መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት አደጋ ሊያጋጥምባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን በካርታ ለይቶ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባር እየከወነ መሆኑን የጠቀሡት አቶ ምትኩ ሰዎችን ከተዳፋታማ አካባቢዎች ማንሣት ዋነኛው መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
ህብረተሠቡም የሚሠጡ የአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን በአተኩሮት መከታተል እና ትዕዛዞችን መተግበር እንዳለበት የጠቆሙት ኮሚሽነሩ በመጪው ክረምት በጎርፍ እና ተያያዥ አደጋዎች 1.5 ሚሊዮን ዜጎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ በሚል ሠፊ ዝግጀት መደረጉን አውስተዋል፡፡

Read 3252 times